ዕውቀት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ
ቀሲስ ሰሎሞን ዓለሙ
ጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
የዕውቀት ምንነት
ዕውቀት ‹ዖቀ› ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን፤ ትርጓሜውም ‹ዐወቀ› ወይም አንድን ነገር በአግባቡ መረዳትንና መገንዘብን እንዲሁም አንድን ነገር ለመፈጸምና ለማከናወን የሚያስችለንን ችሎታ የሚገልጽ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ዕውቀት አንድን ችግር ለማስወገድ የሚያስችል አቅም ወይም ችሎታ መሆኑ ይታመናል፡፡ በግሪኩ ግኖስ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ዕውቀትን የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌም ያለው ሲሆን ሰው በዕውቀቱ የዘለዓለም ሕይወትን ወይም ድኅነትን እንደሚያገኝ በግኖስቲኮች ዘንድ ይታመናል፡፡ በአንጻሩ ዕውቀት የላቸውም ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች አላዋቂዎች ወይም አግኖስ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን እነዚህ አካት ያልበራላቸው በጨለማ ውስጥ ያሉ እንደሆነ በግሪክና በሮማ ሥልጣኔ ዘመን ይታመን እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፻፸፫፣ መድሎተ ጽድቅ ቅጽ ፩ ገጽ ፶ ፣፪ኛ ቆሮ ፫፥፲፬)
የዕውቀት መንገዶች ወይም መሣሪያዎች
የሰው ልጅ በዋናነት ሦስት የማወቂያ መንገዶች ያሉት ሲሆን ይኸውም የስሜት ሕዋሳቱ፣ ዐዕምሮው እና ልቡናው ናቸው፡፡ ከዚህ የተነሣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሦስቱን ዓይነት የሰውነት ደረጃ የነገረን ሲሆን ይህም ሥጋዊ፣ ተፈጥሮአዊ እና መንፈሳዊ ሰው በማለት ነግሮናል፡፡ ሥጋዊ ሰውም አምስቱን የስሜት ሕዋሳቱን በመጠቀም አንድን ነገር ማወቅና መረዳት የሚችል ሲሆን ይህም በሳይንሱ የስሜት መረዳት በመባል የሚጠራውን የሚገልጽ ሲሆን እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሥጋዊ ሰው ወይም ስሜታዊ ሰው በመባል ይታወቃሉ፡፡ አንድን ነገር የሚያውቁት ሥጋዊ ስሜታቸውን በመከተል ነው፡፡ ለስሜታቸው ደስ የሚላቸውን በመከተል እና ደስ ያላላቸውን ደግሞ ባለመከተል በእንስሳዊና ደመ ነፍሰዊ አካሄድ ሕይወታቸውን የሚመሩ ናቸው፡፡ ተፈጥሯዊ ሰው በተፈጠሮው የሚሰጠውን ዐዕምሮ የሚጠቀም፣ ክፉውንና ደጉን ለይቶ የሚያውቅ እንዲሁም በዚህ ዕውቀቱ የሚመራ ሲሆን ኃጢአትን ወይም ወንጀልን የማይፈጽመው እግዚአብሔርን ፈርቶ እና ዘለዓለማዊ ሕይወትን አጣለሁ ብሎ ላይሆን ይችላል፡፡ ይልቁንም እንዲህ ዓይነቱ ሰው ክፉ ሥራ የማይሠራው ስለሚጎዳው፣ ስለሚያስጠይቀውና በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን አላገኝም ብሎ በማሰብ ይሆናል ፡፡ መንፈሳዊ ሰው በአንጻሩ ተፈጥሯዊ አዕምሮውን ከመጠቀም ባሻገር ልቡናውን የማወቂያ መንገድ አድርጎ የሚጠቀምና በልቡናው እምነት በመመራት የዕውቀቱ ምንጭና መመዘኛ እግዚአብሔር የሆነ ሰው ነው፡፡ መንፈሳዊው ሰው አንድን ነገር ከማድረጉ በፊት እግዚአብሔር ይወደዋል? ይፈቅደዋል ?ብሎ የሚጠይቅና ሁሉን ዐዋቂ በሆነው በእግዚአብሔር ሐሳብ የሚሔድ እንዲሁም ሕይወቱን በዚህ መንገድ የሚመራ ሰው ነው፡፡
የዕውቀት ምንጮች
የዕውቀት ምንጮች የተጻፉና ያልተጻፉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የዕውቀት ሁሉ ዋነኛው ምንጭ እግዚአብሔር አምላክ ሲሆን ይህም በሕገ ልቡና ወይም በሕገ ተፈጥሮ ሰውን በልቡ አዋቂ አድርጎ በመፍጠሩ የተነሣ የዕውቀት ደረጃው ቢለያይም ሰው ሲፀነስ ጀምሮ ማወቅ የሚችል፤ ፍጡር ነው፡፡ አንድ ልጅ ገና እንደ ተወለደ እጁን ወደ አፉ በመስደድ መጥባትንና መመገብን በተፈጥሮው እንደሚያውቅ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የሰው ልጅ ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወቱን ለመመራት የሚያስችለውን ዕውቀት ከፈጣሪው በልቡ በተጻፈለት ሕግ መሠረት የሚፈጽም ሲሆን ከዚህም ባሻገር በሕይወት ተሞክሮና ለዘመናት ባካበተው ልምድ መሠረት ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚደረግ የዕውቀት ሽግግር እየተማረ የመጣ ፍጡር ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ መሠረት የዕውቀት ምንጩ እግዚአብሔር ሲሆን ይህንንም በግልጽ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መሆኑን ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተገልጾ እንመለከተዋለን፡፡ ለሥጋም ሆነ ለነፍሳችን የሚጠቅመንን ዕውቀት የሰጠን እግዚአብሔር ሲሆን የክፉ ዕውቀት ምንጩ ሰይጣን ነው፡፡ አቡሃ ለሐሳት የተባለው ዲያብሎስ አስቀድሞ ውሸትን ከራሱ አመንጭቶ ወደ ዓለም እንዳስገባት ማለት ነው፡፡
የዕውቀት ዓይነቶች
በጥቅሉ ዕውቀት መንፈሳዊና ሥጋዊ ተብሎ ሊከፈል የሚችል ሲሆን ይኸውም የሚታወቀውን ርዕሰ ጉዳይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ስለ ፈጣሪና ከእርሱ ጋር ስለተያያዙ ሁኔታዎች ዕውቀት መንፈሳዊ ሲሆን ይህም ከፈጣሪ በሚሰጥ መገለጥ ሊገኝ የሚችል እንጂ በሥጋዊ ምርመር ሊደረስበት የማይችል ነው፡፡ እንዲሁም ረቂቅ ስለሆነቸው ነፍስ አጠቃላይ ሁኔታ፣ በሰማያት ስላለው ሁኔታ፣ ስለመላእክት እና ከሞት በኋላ ስላለው አነዋወር በሙሉ የሚኖረን መረዳት ዕውቀት መንፈሳዊ ነው፡፡ ይህንንም በእምነት እናስተውላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የሚታየው ከማይታየው እንደሆነ በዚህ አናስተውላለን›› በማለት የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ መንፈሳዊ ዕውቀት በሥጋዊ ምርምር ሊደረስበት የማይችል ነገር ግን በእግዚአብሔር መገለጥ ልንደርስበት የምንችል መሆኑ ሲነግረን ‹‹እኔ ማን ነኝ›› ብሎ ስለእርሱ ያላቸውን ዕውቀትና መረዳት በጠየቃቸው ጊዜ ሌሎች ሰዎች በተሳሳተ መንገድ የተረዱትና ያወቁት መሆኑን ከገለጸላቸው በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስን ግን ‹‹ኦ ስምዖን ወልደ ዮና ኢከሠተ ለከ ዘንተ ሥጋ ወደም አላ አቡየ ዘበሰማያት፤ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ይህንን ሥጋና ደም አልገለጸልህም፤ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ›› በማለት ስለክርስቶስ ወይም ስለ እግዚአብሔር የሚኖረን ዕውቀት በእምነት ከእርሱ የሚሰጥና መንፈሳዊ እንጂ በሥጋዊ ምርምር ሊደረስበት የማይቻል መሆኑን አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን በዕውቀት እርሱን ማወቅ እችላለን በማለት ቀደም ሲል በግኖስቲኮች፣ በኋላም በእነ ዩኖሚየስ፣ በእነ አውግስጢኖስ ሂፖ እንዲሁም በ፲ኛው መ/ክ/ዘ በስኮላስቲሲዝም ዘመን ዕውቀትን ወደ ነገረ መለኮት (ቴዎሎጂ) በማስገባት የምዕራቡ ዓለም የሚመራበትን አምክንዮአዊ ነገረ መለኮትን ፈጥረዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ሁሉንም ነገር ምክንያታዊ እና ተጠየቃዊ ለማድረግ ሲጥሩ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው አስተምህሮ እየወጡ መምጣታቸውን የካቶሊክ እምነት በካሄደው ሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ ላይ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ (የቫቲካን ፪ኛ ምክር ቤት- ፲፱፻፶፭-፲፱፻፶፰)
በሌላ መልኩ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ እግዚአብሔርን በሥራዎቹ እንጂ ባሕርይንና አነዋወሩን ማወቅና መረዳት አይቻልም፤ ስለ እግዚአብሔር ከምናውቀው ይልቅ የማናውቀ ነገር ‹‹እንዲህ ነው፤ ይህንን ያህላል›› ተብሎ ሊገጽ አይችለም፡፡ ከዚህ የተነሣ በጥንት አባቶች በእነ ዲዮናስዮስ ዘአርዮስ ፋጎስ፣ በእነ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስና መሰል አባቶች ሲታመን የነበረውን አሉታዊ እና ምሥጠራዊ ነገረ- መለኮትን በመከተል እውነተኛውን መንገድ መያዛቸውን ሌሎች ሳይቀሩ የሚመሰክሩት ሐቅ ነው፡፡ በዚህ አስተምህሮ የበለጠ በመንፈሳዊ ቅድስና ስናድግና ክርስቶስን እየመሰልን በሄድን ቁጥር ስለ እርሱና ስለማይታየው መንፈሳዊው ዓለም ያለን መረዳት እየጨመረ እንደሚሄድ ይታመናል፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፬፥፲፯፣ ዘፍ. ፪፥፲፬)
ጠቃሚና ጎጂ ዕውቀት
ዕውቀትን በጠቅላላው ጠቃሚና ጎጂ ዕውቀት ብለን ልንከፍለው የሚችል ሲሆን የሰው ልጆችን የሚጎዳው ዕውቀት በዲያብሎስ አማካኝነት የተገኘ ሲሆን ለሰዎች ልጆችም ይህንን ጎጂ ዕውቀት እንዳስተማረንና ይኸውም አሁን ድረስ የሰውን ልጅ ሲጎዳ እንመለከተዋለን፡፡ አዳም መልካሙንንና ክፉውን ያውቅ ዘንድ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ የተባለው ለዚህም ነው፡፡ የሰው ልጅ ሲፈጠር መልካሙን ብቻ የሚያውቅ ሲሆን ከውድቀት በኋላ ግን ክፉውንም ማወቅ እንደቻለ በመጽሐፍ ቅዱስ ተዘግቧል፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁኑ ሰዓት ድረስ ከእግዚአብሔር ፍላጎትና ፈቃድ ውጭ ያለው ዕውቀት ሁሉ ጎጂ እና ምንጩም ዲያብሎስ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ የሰው ልጅ በሥልጣኔ ሰበብ ፈጣሪን የሚያስቀይሙ ድርጊቶች፣ ልምምዶች እና ዕውቀቶች አሉ፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ ሥጋዊ አኗኗሩን ቀላልና ምቹ ለማድረግ የሚያግዘው ሲሆን ይህ ሥጋዊ ዕውቀት አጠቃቀሙን በአግባቡ እስካወቅንበት ድረስ በራሱ መልካም ወይም መጥፎ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የኒውክለር ቦንብን ለኃይል ማመንጨት እና መሰል አገልግሎት በሚውልበት ጊዜ ጠቃሚ ዕውቀት ነው፡፡ ሰዎችን ለማጥፋት በሚውልበት ጊዜ ግን ጎጂ ዕውቀት ይባላል፡፡ ጎጂ የተባለው ቴክኖሎጂው በራሱ ሳይሆን በዲያብሎስ የግብር ልጅ በቃየል የተጀመረው ሰውን የመግደል ጎጂ ዕውቀት የተነሣ አስተሳሰቡና ግንዛቤው ነው ጎጂ ዕውቀት ሊባል የሚችለው፡፡
የሥጋዊ ዕውቀት ደረጃዎች
ሀ. ተለምዷዊ፡– ይህ ዓይነቱ ዕውቀት በዘልማድ አንድን ድርጊት ደጋግሞ በማድረግ የሚገኝ ዕውቀት ሲሆን ከሰው ሰው ሊለያይ የሚችል ነው፡፡ ይህንን መሰል ዕውቀት ፤ ከቤተሰብ በዕድሜ ከፍ ካሉ ሰዎች እና ከራስ የሕይወት ተሞክሮ ይገኛል፡፡
ለ. ፍልስፍናዊ ዕውቀት
ዕውቀት አንድን ነገር ደጋግሞ ለምን እንደዚህ ሊሆን እንደቻለ፣ መቼ እና የት ቦታ፣ በማን አማካኝነት እንደዚያ ሊሆን እንደቻለ፣ ያንን ድርጊት ማን እንደፈጸመውና በምን አግባብ ሊፈጽመው እንደቻለ እና የተለያዩ መሰል ጥያቄዎችን በመጠየቅ ምላሽ የሚፈልግ ሰው የፍልስፍና ዕውቀት አለው ይባላል፡፡
ሐ. ሳይንሳዊ ዕውቀት
ሳይንሳዊ ዕውቀት በጣም የተሻለው ሥጋዊ ዕውቀት ሲሆን በመረጃ እና ማስረጃ ላይ በመመሥረት ስለ አንድ ርእሰ ጉዳይ በሚደረግ ጥናትና ምርምር አማካኝነት የሚገኝ ዕውቀት ነው፡፡ ይህም የተደራጀና የተረጋገጠ ዕውቀትን የሚሰጥ በመሆኑ ሥጋዊ ሕይወትን ለመመራት የሚያስችል እጅግ ተቃሚ የሆነ የዕውቀት ዓይነት ነው፡፡
ዕውቀት ጥበብና ማስተዋል
ከላይ እንደተገለጸው ዕውቀት አንድን ጉዳይ በቅጡ መገንዘብና መረዳትን የሚያመለክት ሲሆን ፣ ጥበብ ደግሞ በአንጻሩ ከዕውቀት ባሻገር አንድ ሰው በሆነ ጉዳይ ላይ አዲስ የፈጠራና ቅጽበታዊ በሆነ አኳኃን ነገሮችን የመረዳትና የማከናወን ልዩ ችሎታንና ተሰጥዎን የሚመለከት ሲሆን ይህም አንድን ጉዳይ ደጋግሞ በመሥራት ከሚገኝ ክህሎት አማካኝነት የሚዳብር ሊሆን ይችላል፡፡ ቤሌላ መልኩ ማስተዋል ግን በራሱ አንድን ዕውቀት ከማወቁ ባሻገር ያወቀውን ዕውቀት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመፈተሸ ጭምር አንጥሮ ድክመቱንና ጥንካሬውን በመለየት ተጨማሪ ዕውቀትን ማስተዋል መቻልንና ከፍ ያለ መረዳትንና በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ አረዳዶችን ማምጣት የሚችልና የተደላለደ ዕውቀት ያለው ሰው ነው፡፡
የመንፈሳዊ ዕውቀት ብልጫ፡–
ሰው ዓለሙን ብቻ አትርፎ ነፍሱን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል እንደሚል ስለዚህ ዓለም ኑሮና ሕይወት ብቻ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ የዚህ ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞኝነት ነው የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ለሥጋ ብቻ እንድናስብ ማለትም ስለምንበላው፣ ስለምንጠጣው፣ ስለምንለብሰው፣ ስለመኖሪያ ቤታችን፣ ስለምንይዘው መኪና፣ ስለሥልጣን መያዝና መሰል ሥጋዊ ጉዳዮች ብቻ የሚያስብና ዕውቀቱ በዚያ ላይ ብቻ ተመሠረተ ሰው ሞኝና አላዋቂ ይባላል፡፡ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ‹‹ጽድቁንና መንግሥቱን ፈልጉ፤ ሌላው ሁሉ ይጨመርላችኋል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ የሚቀድመውን የነፍስ ድኅንነትንና ስለዘለዓለማዊ ሕይወትን ማስቀደም፣ ማሰብና ማወቅ ይገባልና ነው፡፡
መንፈሳዊ ዕውቀት ያለው ሰው ሥጋዊውን ሰው መመርመር ሲችል በሥጋዊ ሰው ግን አይመረመርም፤ አይታወቅምም፡፡ ከዚህ የተነሣ ብዙ ቅዱሳን በዱር በገደል በመዞርና ከዓለማዊ አኗኗር ራሳቸውን ለይተው እግዚአብሔርን ብቻ በመከተላቸው እርሱን መስለው ነቢያቱ፣ ሐዋርያቱ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በየገዳማቱ የሚጋደሉት ቅዱሳን በሙሉ ዓለም በዘመኑ ያልደረሰበት ዕውቀት ከእግዚአብሔር ዘንድ ተገልጾላቸው፣ሳይማሩና ሳይመራመሩ መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መልክ ለመጻፍ በቅተዋል፡፡ ዓለማዊ ዕውቀቱ ያላቸው ሰዎች በጥናት እና ምርመር ሊደረሱበት የቻሉትን ኀልወተ እግዚአብሔር ያራቀውን አቅርበው የረቀቀውን አጉልተው አምልተውና አስፋፍተው ለትውልዱ በጽሑፎቻቸው ሊያስተላልፉ የቻሉት ለዚህ ነው፡፡ ሰዎች በምርምር የሚያገኙት ዕውቀት ጊዜያዊ ሲሆን በሌላ ምርመር ሊሻርና ሊተካ የሚችል ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ዕውቀት ዘላለማዊና ከሆነ ጊዜ በኋላ ሊሻር የማይችል ሁልጊዜ እውነትና ጠቃሚ ዕውቀት ነው፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ ሕይወቱን በሙሉ ከፈጣሪው ባገኘውና በተሰጠው ዕውቀት መምራት ከቻለ ሕይወቱ ወደ ጸጥታ ወደብ የምትሄድና በሥጋም በነፍስም ስኬታማ ሕይወትን ለመምራት የሚያስችል ዓይነተኛ መሣሪያ መንፈሳዊ ዕውቀት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር