ዕርገት(ለሕፃናት)
ሰኔ 6 ቀን 2005 ዓ.ም.
በአብርሃም ቸርነት/ዘገዳመ ኢየሱስ/
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን ቅዱሳን ሐዋርያት በጸሎት ይተጉ ወደነበረበት ቤት በመሄድ ደቀመዛሙርቱን ይዟቸው ከቤት በመውጣት መንገድ ጀመረ፡፡ እርሱ ከፊት ከፊት እየመራቸው እነርሱ እየተከተሉት ወደ ረጅሙና በረጃጅም ዛፎች ወደ ተሞወው ደብረ ዘይት ተራራ ይዟቸው ወጣ፡፡
በተራራው ጫፍ /አናት/ ላይ ሲደርሱ፤ በመካከላቸው ቆሞ ሐዋርያትን እንዲህ ብሎ መከራቸው “ከእኔ የተማራችሁትን ትምህርት ጠብቁ በቤተ ክርስቲያንም ጸንታችሁ ኀይልን ከሰማይ እስክልክላችሁ ቆዩ” ብሎ አዘዛቸው፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት እጁን በላያቸው ጭኖ (በአንብሮተ ዕድ) ሾማቸው፡፡
ይህንንም እየነገራቸው ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ፣ ከፍ፣ ከፍ አለ፡፡ ነጭ የሆነችና ለዓይን በጣም የምታምር ብሩህ ደመናም አምላካችንን ተቀበለችው፡፡ ከዓይናቸውም እየራቀ፣ እየራቀ፣ ከእይታቸው ተሰወረባቸው፡፡
ሐዋርያትም ኢየሱስ ክርስቶስን በጣም ይወዱት ስለነበረ ሲለያቸው አዝነው አተኩረው ሰማይ ሰማዩን ለረጅም ሰዓት ተመለከቱ፡፡ ድንገትም ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ቅዱሳን መላእክት በአጠገባቸው ቆመው ታዩአቸው፡፡ መላእክቱም ሐዋርያትን እንዲህ አሏቸው፡፡ “እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን አዝናችሁ ቆማችሁ፡፡ ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ወደ ምድር ይመጣል፡፡” አሏቸው፡፡
ሐዋርያቱም የመላእክቱን ማረጋጊያ ቃል ከሰሙ በኋላ ፈጥነው በኢየሩሳሌም ወደምትገኘው ቤተ መቅደስ በመሄድ እግዚአብሔር ቃል የገባላቸውን ኀይል ከሰማይ እንዲልክላቸው ቀን ከሌሊት በአንድነት ሆነው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንም ከመካከላቸው አድርገው በጸሎት እየተጉ ቆዩ፡፡
ጥቅስ፡- ሉቃ.24፥50-53፣ ሐዋ.1፥9-14