ዕረፍት ያጣች ነፍስ!
በሕይወት ሳልለው
እግዚአብሔር አምላካችን በአርአያውና በአምሳሉ ሲፈጥረን በክብር ነውና ከአለመኖር ወደ መኖር ያመጣንም በእስትንፋሱ ነበር፡፡ «እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ»፤ (ዘፍ ፪፥፯)፤
አባታችን አዳም ባደረገው ስሕተት ከገነት ተባሮ ወደ ምድር ከወረደ በኋላ ኑሮው የከፋ ነበር፤ ብዙም ተፈትኗል፤ ገነት ሳለ ደስታን እንጂ መከራን አላወቀም፤ ነገር ግን እዚህ ምድር ላይ በፍርሃትና በጭንቀት ይኖር ነበር፡፡ ከልብሰ ብርሃንም ተራቆተ፤ ተበረደ፤ የበለስ ቅጠል ቆርጦም ለበሰ፤ በመከራውም ጊዜ የፈጣሪውን ትእዛዝ በመተላለፉ የሠራውን ኃጢአቱን በማሰብ ያለማቋረጥ ያለቅስ ነበር፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላም በተገባለት ቃልኪዳን መሠረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እስኪያድነው ድረስ በምድር ብዙ ተሠቃይቷል፡፡
ሰው ድኅነትን የሚያገኘው በክርስትና ሕይወቱ ውስጥ ለእምነትና ለሃይማኖቱ መሥዋዕትነት በመክፈል፤ ዘወትር በክርስቲያናዊ ሥርዓት፤ በምስጋናና በሕገ እግዚአብሔር ሲኖር ነው፡፡ ነገር ግን ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ በኃጢአት ማዕበል ውስጥ ተዘፍቃለች፤ መከራ፤ ሥቃይ፤ ችግር፤ እንዲሁም ጦርነት በየሀገሩ በዝቷል፡፡ ትንቢቱም እንደሚገልጸው «ሕዝብ በሕዝብ ላይ፤ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ፤ በየሀገሩም ረኃብ፤ ቸነፈርም፤ የምድር መናወጥም ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡ ያንጊዜም ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ ያን ጊዜም ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ፤ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ» (ማቴ. ፳፬፥፯-፲)፡፡
በዚህች ምድር ላይ ስንኖር ልንፈተን እንችላለን፤ በዕለት ክንዋኔያችን ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድ ሊገጥመን ይችላል፡፡ ከጥንት ጀምሮ አእምሮአችንን ለመቆጣጠርና ትዕግስትን አስጨርሶ ተስፋ ለማስቆረጥ የሚፈታተነን ጠላት ዲያብሎስ የማሳቻ መንገዱ ብዙ ነውና በእምነት ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡ ተስፋ የቆረጠ ሰው ለውድቀትና ለጥፋት የቀረበ ይሆናል፤ ዕረፍትን የሚሻ ሰው ግን በተስፋ ውስጥ ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሔ እንዳለው፤ ለእያንዳንዱ ለተቆለፈ መዝጊያ አንድ ወይም ብዙ ቁልፎች እንዳሉትና ለእያንዳንዱ ውድቀትም መነሻ እንዳለው ይታወቃል::
ሰላምና ፍቅር ከእኛ ሲርቅ ማንነታችንን መጥላት፤ የእኛ ያልሆነውን ባዕድ ጠባይ መቀበል እንጀምራለን፤ ነፍስ ግን ሁሌም ፈጣሪዋን ትፈልጋለች፤ እናም ትጨነቃለች፡፡
ዛሬም ያለው ትውልድ ከነፍሱ ይልቅ ለምድራዊ ሕይወቱ ይለፋል፤ ነገር ግን ከንቱ ልፋት ነው፡፡ «ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ነፋስንም እንደመከተል ነው»መጽሐፈ መክብብ ፩፥፲፬፡፡የሰው ልጅ ኅሊናውን ሳይክድ ለእምነቱ ተገዝቶ ሲኖር ወደ ፈጣሪው መቅረብ ይቻለዋል፤ ሁል ጊዜም አምላኩን ሲያስብ፤ በተስፋም ሲኖር፤ ወደ ክብር ቦታው እንደሚመለስ በማመን በጎ ሥራን አዘውትሮ ይተገብራል፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ሰው ፈጣሪውን ያስባል፤ ይፈራል፤ ያከብራል እንዲሁም በሕጉ ይመራል፤ ከራሱም አልፎ ለሌሎች ጥሩ ማድረግን ይመኛል፤ ያደርጋልም፡፡
እርግጥ ነው ጠባያችን እንደመልካችን ይለያያል፤ እግዚአብሔር አምላካችን በቃሉ «ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሉአት» እንዳለው (ዘፍ. ፩፥፮)፤ በዓለማችን በቢሊዮን የምንቆጠር ሰዎች አለን፡፡ እናም ተከባብሮ የመኖር ውዴታና ግዴታ የእኛ ቢሆንም ኃላፊነትን ከመወጣት ይልቅ ክፋት፤ ተንኮል፤ በደል፤ ጥላቻ፤ ግድያ ከዛም አልፎ ባዕድ አምላኪም በዝቷል፡፡ ፈውስና በረከት ማጣት፤ በምሬትና በሰቆቃ ውስጥ ለመኖር መንስኤው የኃጢአት መብዛት ነው፤ ክፉውም ሆነ ደጉ የሥራችን ውጤት ነው፡፡
በዚህ ምድር ስንኖር ሥጋችንንም ዋጋ በማሳጣት ለነፍሳችን ልንኖርላት እንደሚገባ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል አስተምሮናል፤ «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ፤ ነፍሱንም ቢያጣ፤ ለሰው ምን ይረባዋል? ሰውስ ለነፍሱ ቤዛ ምን በሰጠ ነበር?» (ማቴ. ፲፮፥፳፮)፡፡
ሰላም ፍቅር ማጣት
የባዶነት ስሜት
ማንነትን መጥላት
በምሬት አንደበት
ክፉ ነገር ማውጣት
ርኩሰት በኃጢአት
ነፃነትን መሻት
ነፍስ ስታጣ ዕረፍት
የተጨነቀች ዕለት
«እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ፤» (ማቴ.፲፩፥፳፰) ይለናልና ፈጣሪያችንን አብዝተን እንለምነው፤ እንጸልይ እንጹም፤ ዕረፍት ያጣች ነፍሳችንን እናሳርፋት፡፡