ዐሥራ አምስተኛው ዙር ሐዋርያዊ የጉዞ መርሐ ግብር በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡

በደረጀ ትዕዛዙ
ማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ትክክለኛ አስተ ምህሮ ለምእመናን ለማዳረስ ከሚጠቀምባቸው መርሐ ግብሮች አንዱ የሆነውና በደቡብ ኢትዮ ጵያ ቦረና ጉጂ ሊበን ዞኖች ሃገረ ስብከት የተካሔደው  የአሥራ አምስተኛው ዙር ሐዋርያዊ ጉዞ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡ እንዲህ ያለ መርሐ ግብር በተከታታይ ሊካሔድ እንደሚገባ የአካባቢው ምእመናን ቿይቀዋል፡፡
በማኅበሩ ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አዘጋጅነት ከየካቲት 11- 20 2003 ዓ.ም ድረስ የተካሔደው ይኸው መርሐ ግብር ቦረና ጉጂ ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት የሚገኙ አምስት ከተሞችን የሸፈነ መሆኑን የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ዲ/ን ምትኩ አበራ ተናግረዋል፡፡

አራት መምህራንና አሥራ ሰባት ዘማሪያንን እንዲሁም ሌሎች አባላትን ያካተተው ይኸው የልኡካን ቡድን ይዞት ከተነሣው ተልእኮ አንጻር የተሻለ አገልግሎት ሰጥቶ መመለሱን የገለጡት አስተባባሪው በዚህም ምእመናኑ እጅግ ተደስተዋል ብለዋል፡፡

በሐዋርያዊ ጉዞው ትክክለኛውን የቤተክ ርስቲያን ትምህርት እና ዝማሬ ወደ ምእመናኑ ማድረስ ዋና ዓላማው አድርጎ የተንቀሳቀሰው ይኸው የልኡካን ቡድን፤ በሀገረ ስብከቱ በሚገኙ ክብረ መንግሥት፣ ሻኪሶ፣ ዋደራ፣ ቦሬ እና ነገሌ ቦረና ከተሞች በሚገኙ አምስት አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በምእምናን ጥያቄ መሠረት ከዕቅድ በላይ በሁለት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያንም አገልግሎቱን ሰጥቷል ብለዋል፡፡ በዚህም የሐዋርያዊ ጉዞው ቡድን ከሕዝቡ ተቀባይነትን፣ ከበሬታንና ፍቅርን አግኝቶ መመለሱን አስረድተዋል፡፡

ትምህርተ ወንጌሉ በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች መሰጠቱ ምእመናን ቃለ እግዚአብሔርን በአግባቡ እንዲረዱ ያስቻለ ከመሆኑም በተጨማሪ የልኡካን ቡድኑ አባላት የሆኑ ካህናት በቅዳሴ እና በዓመታዊ ክብረ በዓል ወቅት የቤተ መቅደስ አገልግሎት መስጠታቸው አገልግሎቱን ይበልጥ የተሳካ እንዲሆን አግዟል ብለዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ ከቤተክርስቲያኒቱ የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ፈቃድ ይዞ በሕጋዊነት ተንቀሳቅሷል፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ከተሞች በዓላማቸው የተሐድሶ እንቅ ስቃሴውን ለማራመድ በሚጥሩ ግለሰቦች መርሐ ግብሩን የማደናቀፍ አዝማሚያ አጋጥሞት አንደነበር ዲያቆን ምትኩ አበራ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና በቤተክርስቲያኒቷ ሥርዓትና መመሪያ መሠረት የሚካሔድ ሕጋዊ አገልግሎት ስለሆነ የፈቃድ ወረቀቱን ለሕጋዊ አካላት በማሳየት እና ከየደብሩ ሓላፊዎች እና ከምእመናኑ ጋር በመነጋገር መርሐ ግብሩ ሳይስተጓጎል ከተጠበቀው በላይ የተሳካ ሆኖ መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ በተካሔደባቸው አካባቢዎች ከቤተክርስቲያን ሥርዓትና መመሪያ ውጪ የሚንቀሳቀሱ ሰባክያንና ዘማሪያን ስፍራውን ደጋግመው በመጎብኘታቸው ትክክለኛውን የቤተክር ስቲያኒቱን አስተምህሮ ሳያገኙ መቆየታቸውን የአካባቢው ምእመናን ለልኡካን ቡድኑ አባላት ሲገልጡ እንደነበር የተናገሩት ዲ/ን ምትኩ፤ መርሐ ግብሩ በተከታታይ ሊካሔድ እንደሚገባ መጠየቃቸውንም አስረድተዋል፡፡
ማኅበሩ በእነዚህ አካባቢዎች መዋቅሩን በማጠናከር የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሥርዓትና መመሪያ አክብረው ከሚንቀሳቀሱ መምህራነ ወንጌል እና ዘማሪያን ጋር በመተባበር ደጋግሞ ወደ ስፍራው ሐዋርያዊ ጉዞ ማድረግ ይገባል፡፡ በዚህ አካባቢ ትኩረት ሰጥቶ በተከታታይ የተጠናከረ አገልግሎት መስጠትና ትምህርተ ወንጌል የተጠማውን ሕዝብ በማስተማር የቅድስት ቤተክርስቲያንን ተልዕኮዋን ይበልጥ ውጤታማ ለማደረግ መነሣሣት እንደሚያስፈልግ ዲ/ን ምትኩ ተናግረዋል፡፡

 
 /ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ከመጋቢት 1-15 ቀን 2003 ዓ.ም/