ወጣትነትና ፈተናዎቹ
የወጣትነትን የዕድሜ ክልል በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምሮ መሠረት ከሃያ እስከ ዓርባ ዓመት ያለው ዕድሜ ነው፡፡
እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ማለትም ከነፋስ፤ ከእሳት፤ ከውሃና፤ ከመሬት ሲሆን አምስተኛ ነፍስን ጨመሮ እነዚህ በአንድ ሰው የሕይወት ዘመን ላይ ሲንጸባረቁ ይኖራሉ፡፡ የሰው ልጅ በሚሞትበት ጊዜ አራቱ ባሕርያት ወደነበሩበት ጥንተ ህላዌ ይመለሳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሥጋ ይበሰብሳል ይፈርሳል፡፡ በትንሣኤ ዘጉባኤ ደግሞ አራቱም ባሕርያት ከነፍስ ጋር እንደገና ተዋሕደው ይነሣሉ፡፡ አራቱን ባሕርያተ ሥጋ ረቂቃን ግዙፋን (ክቡዳን ቀሊላን) ብለን እንጠራቸዋለን፡፡ የሚገርመው ክቡዳኑን ከላይ ቀሊላኑን ከታች አድርጎ ነው ያስቀመጣቸው፡፡ እርስ በእርሳቸው ተጠባብቀው እንዲኖሩ አደረጋቸው ምክንያቱም ክቡዳኑ ከላይ ሆነው እንዲጠብቋቸው ነው ቀሊላኑ ግን ከላይ ቢሆኑ ኖሮ ሽቅብ ይሄዱ ነበር ክቡዳኑም ከታች ቢሆኑ ኖሮ ቁልቁል ሲሔዱ በኖሩ ነበር፡፡ ተሸካክመው የሚኖሩት ምሳሌነቱም አራቱ ባሕርያተ ሥጋ ተቻችለው እንደሚኖሩ እኛም ከኛ በላይ ያሉ እንዳሉ በማወቅ ተቻችለን እንድንኖር ነው፡፡ የመሬት መሠረቷ ጽናቷ ነፋስ ነው፡፡ የእኛም ከላይ ሥጋችን መሬት ነው፡፡ መሬትም በውኃ ላይ ናት ይህም ውሃው ደማችን ነው፡፡ የእኛም ሥጋችን በደማችን ነውና የሚጸናው የውሃዎች ሕይወት ነፋስ ነው ውሃው ንጹሕ አየር ከሌለው ይበከላል፡፡ አበው ከአፋፍ ላይ ነፋስ ከአፍ ላይ እስትንፋስ እንዲሉ የሰው ልጅም ሁሉ በዘመኑ ሲተነፍስ ይኖራልና፡፡ የሰው ልጅ የሰውነት ሙቀት ባሕርየ እሳት ለመኖሩም በቂ ማስረጃ ነው፡፡
ከሃያ እስከ አርባ ያለው የዕድሜ ክልል የእሳት ባሕርይ ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡ ይህም ዘመነ እሳት ወይም ምግበ እሳት ይባላል፡፡ ይህም ሰውን ወጣት የሚያሰኘው ዘመን ነው፡፡
በዚህ የወጣትነት ዘመናችን ጥሩና ታላቅ መሆን ካልቻልን የምናጣው ክብርን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ኃላፊነት ጭምር እናጣለን፡፡ እንደ ኤሳው ስንሆን እንደ ያዕቆብ ያለ ታናሽ ወንድምህ ብኵርናህን ይወስድና አንተ የእሱን እጅ ስታይ ትኖራለህ፡፡ እንዲሁም ታናናሾችህን የመቅጣትና የመገሠጽ መብት አይኖርህም፡፡ አላዋቂ ጎልማሳ ወጣቶችን መገሠጽ እንደማያምርበት ሁሉ አንተ ሕገ ወጥ ወጣት ሆነህ ታናናሾቼን ልቅጣ ልምከር ብትል ማንም አይሰማህም፡፡ ምክንያቱም (ማቴ. ፯፥፭) ላይ አንተ ግብዝ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፡፡ ከዚያ በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ ስለተባልን ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰው ልጅ ከልጅነት ወደ ወጣትነት በሚሸጋገርባቸው ወራትና ዓመታት አካላችን እንደሚደራጅና አእምሮአችን እንደሚዳብር ሁሉ ምኞታችንም በዓይነትና በመጠን እየሰፋና እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይህ የወጣቶች ምኞት በአመዛኙ ከመንፈሳዊነት ጋር የሚቃረን ይሆናል፡፡ እንዲሁም በጎልማሶች ላይ የሚከሰተውን ምኞት አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ (በ፪ኛ ጢሞ. ፪፥፳፪) ላይ ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ ብሎናል፡፡ በእርግጥም በወጣትነት ዘመን የሚገኝ ምኞት እጅግ ክፉ ነው ወጣትነት የሚሠራበት ዘመን እንጂ ክፉ ምኞት የሚመኙበት ዘመን አይደለም፡፡
ወጣቶችና ጾሮቻቸው (ፈተናዎቻቸው)
ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ ፩፥፲፬ ላይ «ሰው ራሱ በገዛ ምኞቱ ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል» በማለት እዳስተማረን፤ በወጣትነት ዘመን የሚገኝ ምኞት ከመጠን በላይ ወደ ጥፋት የሚስብ የሚጎትትና የሚያታልል ነው፡፡ በተለይ ሰው በገዛ ምኞቱ ሲሳብ በወጣትነት ዘመን ምንም አእምሮው የበሰለ ቢሆንም እንኳ ራሱን መግዛት ካልቻለ በብዙ ነገር ይፈተናል በዚህም ወጣቶች ከሚፈተኑባቸው መንገዶች መካከል ዝሙትና ትውዝፍት (የምዝር ጌጥ) መውደድ ነው፡፡ እንዲሁም የወጣቶች ልዩ ልዩ ጾር (ፈተና) ቢኖሩም እነዚህ ዐበይት ጾሮች የኃጢአት መንገድ ጠራጊ ይሆናሉ፡፡
መፍትሔዎች
- ራስን መግዛት
ይህ ማለት ፍቃደ ሥጋን ለፍቃደ ነፍስ ስናስገዛ፤ በዚህም ሕገ እግዚአብሔርን ስንጠብቅ፤ ራሳችንን ሆነን በተማርነው መኖር ስንጀምር፤ ልማድ የሆነብንን ድርጊት አስወግደን በተቀመጠልን ትእዛዝ ስንኖር እና ሁለንተናችንን ለእግዚአብሔር ስናስገዛ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት (በመዝ. ፪፥፩) ላይ በፍርሀት በመንቀጥቀጥ ተገዙ ስላለን በመገዛት ውስጥም የማያቋርጥ ዘለዓለማዊ ደስታ እንዳለ አውቀን ራሳችንን መስለን መኖር እንችላለን፡፡ ስለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ (፩ኛ ጢ. ፫፥፭) ላይ ቤቱን ማስተዳደር የማይችል የእግዚአብሔርን ቤት ሊመራ እንደማይችል ሁሉ ሌሎችን ማስተዳደር የምንችለው ራሳችንን ስንገዛ፤ ስንገራና ስንቆጣጠር እንደሆነ ነግሮናል፡፡ እንዲሁም ኖኅን ስንመለከት (ዘፍ. ፮፥፩) ላይ ከነቤተሰቡ ራሱን ገዝቷል፡፡ ሌሎችን ለመናገርና ለመውቀስ መርከቧን በመሥራት፤ አራዊትን፤ እንስሳትንና አዕዋፍን ሁሉ መግዛት ችሏል፡፡ ራስን መግዛት ማለት ቤተ ክርስቲያን ገብተን እስክንወጣ፤ ትዳር እስክናገኝ፤ ሥራ እስክንይዝና እና የፈለግነው ነገር ሁሉ እስኪሳካልን ድረስ አይደለም፡፡ ነገር ግን ራስን መግዛት ማለት መፍረድ ሲቻል አለመፍረድ፤ ማድረግ ሲቻል አለማድረግ ልክ እንደ ዮሴፍ (ዘፍ. ፴፱፥፩) ጀምሮ ሁሉ ሲቻል መተው እንዲሁም ልክ ይሁን አይሁን በነገሮቻችን ሁሉ ራሳችንን ስንገዛ በአጠቃላይ ከአላስፈላጊ የሥጋ ጠባይዓት ሁሉ መራቅ ስንችል ራሳችንን ገዝተናል ማለት እንችላለን፡፡
- ራስን ማወቅ
ለራሳችን ያለንን አመለካከትና ጠባይ በአጠቃላይ ከሌሎች ሰዎች የሚለየንንና የሚያመሳስለንን ማንነት በመረዳት በዓላማ መኖር ስንችል ራሳችን ማወቅ ቻልን ማለት ነው፡፡ ይህም ሰው ጠንካራና ደካማ ጎኑን ማወቅ ከቻለ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ሕይወት አዎንታዊ አስተዋጽዖ ለማበርከትና ዓላማውን ከግቡ ለማድረስ የሚያስችለውን እውቀት ያገኛል፡፡ ሙሴ (በዘፀ. ፬፥፲) ላይ ጌታ ሆይ እኔ አፌ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የኮነ ሰው ነኝ ብሎ ነው የተናገረው፡፡ ሆኖም ሙሴ በውስጡ ያለውን ጠንካራ ጎን አልተመለከተም፡፡ ራሱን የሚያውቅ ሰው ለራሱ ሕይወት ኃፊነት ይወስዳል ሌላ ሰው እንዲንከባከበው አይጠይቅም፡፡ በጉብዝናው ወራት ገደል አለ ከተባለ ይሰማል፤ ገደሉ እንደሚጎዳው ስለሚያውቅ፤ ሕይወቱን ለአደጋ አያጋልጥም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልዕክቱ (፪ኛ ጴጥ. ፩፥፭-፮) ላይ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፤ በበጎነትም እውቀትን፤በእውቀትም ራስን መግዛት፤ ራስን በመግዛትም መጽናትን በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰልን ነግሮናልና፡፡ ስለዚህ ይህን በማድረግ ለሕይወታችን ኃላፊነትን እንወስዳለን፡፡
ራሱን የሚያውቅ ሰው ሰብእናውን ያከብራል፤ ለምን ዓላማ እንደተፈጠረ በመረዳት ሰብእናውን ጠብቆ በደስታ ይኖራል፤ በራሱም ይተማመናል፡፡ የሚያውቀውን በአግባቡ ይናገራል፤የማያውቀውን ይጠይቃል፤ ድክመቱን ሲነግሩት በአዎንታዊ መንገድ ይቀበላል፤ ማንነቱን በቦታና በጊዜ ራሱን አይለዋውጥም የጸና ግንብ ነው፤ በዐለት ላይ ተመሥርቷልና፡፡ ከሐሜት ይርቃል፤ በግልጽ መወያትን ያዘወትራል፤ ለውድቀቱም ራሱን ተጠያቂ ያደርጋል፤ ሌሎቹን ተጠያቂ አያደርግም፤ ለውድቀት በቀላሉ እጁን አይሰጥም የሚጓዝበትን ያውቃልና፡፡ ካለፈው የወጣትነት ሕይወቱ ልምድ በመውሰድ አሁን ያለበትን ሁኔታ በመረዳት ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወቱ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል አስቀድሞ ይዘጋጃል፡፡ ይህም የዛሬ ማንነቱ ለነገ ዘለዓለማዊ ሕይወቱ መሠረት መሆኑን በመረዳት ጠንክሮ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ይተጋል፡፡ በመጨረሻም ራሱን የሚያውቅ ወጣት ለመንፈሳዊ ሕይወቱ መሳካት አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ይከፍላል፡፡ ራሱን ያላወቀና ያልገዛ ወጣት ዓላማውን ይስታል፤ ለራሱም ለሌሎችም መሆን አይችልም፡፡
ስለዚህ በወጣትነት ዘመናችን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያቀርበንን እንጂ የሚያርቀንን ነገር እንድንሠራ አይጠበቅብንም፡፡ እኛ ራሳችንን አድነን ሌሎችን በማዳን ክርስቲያናዊ ግዴታችንን መወጣት ይጠበቅብናል፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከሰኔ ፩-፲፭ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም