‹‹ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ›› ማቴ.፳፮፥፵፩

በወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ቦታ ሄዶ በጸለየበት ጊዜ  ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች እንዲህ አላቸው፤ ‹‹ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ተቀመጡ፤ ከእኔ ጋርም ትጉ፤›› ከዚያም ጥቂት ፈቀቅ አለና በግንባሩ ሰግዶ ጸለየ፤ እንዲህም አለ፤ ‹‹አባቴ ሆይ፥ የሚቻልስ ከሆነ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን ፈቃድህ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይደለም፡፡›› ወደ ደቀ መዛሙርቱ በሄደ ጊዜ ግን ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው ‹‹አንድ ሰዓት እንኳ ከእኔ ጋር መትጋት እንዲህ ተሳናችሁን? ወደ ፈተናም እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ ይሻልና፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፡፡›› ጌታችን ይህን ቃል ለሐዋርያቱ የተናገራቸው እርሱ ከእነርሱ ጋር በማይኖርበት ጊዜም ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም ወደ ፈተና እንዳይገቡ በትጋት መጸለይ እንደሚያስፈልግ ለማሳወቅ ነው፡፡ (ማቴ.፳፮፥፴፮-፵፩)

በክርስትና ሕይወት ውስጥ ጸሎት ተቀዳሚ ተግባር ነው፤ ወደ እግዚአብሔር አምላካችን የምንቀርብበት፣ ከእርሱ ጋር የምንንነጋገርበት እና የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት የምንማጸንበት ክርስቲያናዊ ምግባር ነው፤ እናም ዘወትር ልንጸልይ ይገባል፡፡

ይህች ምድር በችግር፣ መከራና ፈተና የተሞላች በመሆኗ በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖታችንና እምነታችን እየተፈተነ ነው፤ ዓለማችን ወስጥ ስቃይ፣ በሽታና ጦርነት በመብዛቱ  ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ተግተን ልንጸልይ ይገባል፡፡ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ችግርና መከራ ሲያጋጥማቸው የዕለት ጉርሻቸውን ለመሙላትም ማድረግ የሌለባቸውን ነገር ማድረግ ወይንም የእግዚአብሔርን ሕግ መተላለፍ ይጀምራሉ፤ በሐሰት እና በአቋራጭ መንገድም ምድራዊ ሕይወታቸውን ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ዘወተር እግዚአብሔርን በመፍራት ስንኖርና አምላካችን ከእኛ ጋር ሲኖር ከክፋት እንዲሁም ከፈተና ይሰውረናል፡፡ ይህንም ማድረግ የምንችለው ሥርዓቱን ጠብቀን ስንጸልይ ነው፡፡

በተዋሕዶ እምነታችን እኛ ክርስቲያኖችም በ፳፬ ሰዓት ውስጥ ፯ ጊዜ መጸለይ እንዳለብን እንረዳለን፡፡ ይህም እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን በምክንያት ያደረገው በመሆኑ ሁል ጊዜ ወደ እርሱ እንጸልይና እንቀርብ ዘንድ ነው፡፡

የሰባቱ የጸሎት ጊዜያትም ጸሎተ ነግህ (፲፪)፣ ጸሎተ ሠለስት (፫ ሰዓት)፣  ቀትር (፮ ሰዓት)፣ ተሰዓቱ ሰዓት (፱ ሰዓት)፣ ጸሎተ ሰርክ (፲፩ ሰዓት)፣ ጸሎተ ንዋም (የመኝታ ጊዜ ጸሎት) እና መንፈቀ ሌሊት (እኩለ ሌሊት) ናቸው፡፡ (መዝ. ፻፲፰፥፻፷፬)

ጸሎተ ነግህ

ቅዱስ ዳዊት ‹‹አምላኬ አምላኬ በማለዳ ወደ አንተ እገሰግሳለሁ›› እንዳለ ሌሊቱ አልፎ ቀኑ ሲተካ፣ ከመኝታችን ተነስተን የምንጸልየው ጸሎተ ነግህ ነው፡፡ አምላካችን እንደቸርነቱ ሌሊቱን በሰለምም አሳድሮ ለብርሃነ ቀኑ ስላደረሰን በማመስገን፣ ወጥተን እስክንገባ ከክፋት ጠብቆ ወደ ቤታችን በሰላም እንዲመልሰን እና ከፈተና እንዲሰውረን እንጸልያለን።

ነግህ አዳም የተፈጠረበትም ሰዓት በመሆኑም ያንን እያሰብንም እና የሰውን ልጅ በመዓልትና በሌሊት የሚጠብቁን መላእክት የሚገናኙበት ሰዓት በመሆኑ እንጸልያለን፡፡ ሌሊቱን ሲጠብቀን ያደረው መልአክ የቀኑን ሲተካ ስንተገብረው የነበረውን ለቀኑ ያስረክባል፤ እንደዚህ እየተቀባበሉ ይጠብቁናል፡፡ ስለእኛ ምግባር ያውቁ ዘንደ ነውና፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች በደል በጲላጦስ አደባባይ የቆመበት ሰዓት በመሆኑ በነግህ እንጸልያለን።

ጸሎተ ሠለስት

እናታችን ሔዋን የተፈጠረችበት፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቅዱስ ገብርኤልን ብሥራት የሰማችበት፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ሲል በጲላጦስ አደባባይ የተገረፈበት፣ ነቢዩ ዳንኤል ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ መልሶ የቤቱን መስኮት ከፍቶ የጸለየበት፣ ለአባቶቻችን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት /በኢየሩሳሌም ጸንተው በመቆየታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይህንን ታላቅ ጸጋ የተቀበሉበት /ሰዓት በመሆኑ በሦስት ሰዓት እንጸልያለን፡፡

ቀትር

ቀትር ሰይጣን አዳምን ያሳተበት እና በዕፀ በለስ ምክንያት ለስሕተት የተዳረገውን አዳምን ለማዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ መከራና ስቃይ የተቀበለበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ሰዓት የፀሐይ ሙቀት የሚያይልበት፣ የሰው ልጅ ለድካም የሚዳረግበት ስለሆነ አጋንንት ይበረታሉ። ስለዚህ የአዳምን ስሕተት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀልና መሞት፣ እያሰብን፣ በዚያም ሰዓት ሥጋዊ ድካማችንን ሰበብ አድርጎ አጋንንት እንዳይሰለጥንብን እየለመንን እንጸልያለን፡፡ ጴጥሮስም በቀተር ጊዜ ሊጸልይ ወደ ሰገነት ወጣ እንዲል፡፡ (ሐዋ. ፲፥ ፱)

ተሰዓቱ ሰዓት

የተሰዓቱ ጸሎት ዘጠኝ ሰዓት ላይ የምናደርሰው ጸሎት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ነጻ ለማውጣት በፈቃዱ ቅዱስ ሥጋውን ከቅድስት ነፍሱ የለየበት ሰዓት በመሆኑ ነው።
ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን በጎም ሆነ ክፉ ተግባር ወደ ፈጣሪ የሚያሳርጉበት፣
ቆርኖሌዎስ የተባለ መቶ አለቃ በጸሎት ጸንቶ ደጅ ሲጠና ከሰነበተ በኋላ ከፈጣሪው ምላሽ ያገኘበት ስለሆነም ዘጠኝ ሰዓት ላይ እንጸልያለን፡፡ በዚህ ጊዜ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ እና ሞት አያሰብን ቅዱሳት መላእክት ከፈጣሪያቸው እንዲያስታርቁን እየለመንን የቆርኖሌዎስ እድል እንዲገጥመን እየተማጸንን እንጸልያለን፡፡

ጸሎተ ሰርክ

‹‹ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጆቼ የሠርክ መሥዋዕትን አነሡ›› ብሎ ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው በዚህ የጸሎት ሰዓት በቤተ ክርስቲያን ሁላችንም ተሰባስበን ጸሎታችን እናደርሳለን፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ከለየ በኋላ ወደ መቃብር የወረደበት ሰዓት ነውና፡፡ (መዝ. ፻፵፥፪፣ ማቴ. ፳፯፥፶፯)

ጸሎተ ንዋም

ቀኑን እንደ ፍቃዱ ያዋለንን እግዚአብሔር አምላክን እያመሰገንን፤ ሌሊቱንም በሰላም ያሳድረን ዘንድ እንማጸናዋለን፡፡ እርሱ የማይተኛ አምላክ ነውና ሌሊቱን ሁሉ ከክፋት ጠብቆ ያሳድረናል ነው፡፡

በዚህ ጊዜም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት አስተምሯቸዋል፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጸሎት ማስተማሩን እያሰብን እንጸልያለን፡፡

መንፈቀ ሌሊት

መንፈቀ ሌሊት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ዋሻ የተወለደበት፣ ሞትን ድል አድርጎ በታላቅ ኃይልም የተነሳበት እንዲሁም ጌታችን ዳግመኛ ለፍርድ የሚመጣበትም ሰዓት ነው። ቅዱሰ ዳዊት ‹‹መንፈቀ ሌሊት እትነሣእ ከመ እግነይ ለከ በእንተ ኵነኔ ጽድቅከ፤ ስለ ጽድቅህ ፍርድ በእኩለ ሌሊት አመሰግነህ ዘንድ እነሳለሁ›› በማለት ይህ ሰዓት ከእግዚአብሔር ጋራ የሚነጋገርበት እንደሆነ እንደገለጸው ያንን በማሰብ ለፍርድ ሲመጣ በቀኙ ከሚያቆማቸው ወገን እንዲያደርገን እየለመንን በዚህ ሰዓት እንጸልያለን፡፡ (መዝ.፻፲፰-፷፪)

ነገር ግን እነዚህን ሰባቱ የጸሎት ሰዓታት የሚጸልዩባቸው በገዳም ያሉ መነኮሳት በየበረሃው የሚዞሩ ባሕታውያን ብቻ መሆን የለባቸውም፤ ምንም እንኳን በሥራ ምክንያት ሁሉንም  ሰዓታት ጠብቀን መጸለይ ባይቻለን ቢያንስ በነግህ እና በመኝታ ሰዓት መጸለይ አለብን። ይህም በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመንን ችግር መከራ እንድንቋቋም ይረዳናል፤ አምላካችን እግዚአብሔርም ከፈተና ያወጣናል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ከፈተና ይሰውረን ዘንድ ተግተን እንጸልይ!