‹‹ወወፅኡ እምዐውድ እንዘ ይትፌሥሑ፤ ከሸንጐው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ›› (የሐዋ. ሥራ ፭፥፵፩)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት “እንበለ መከራ ኢይትረከብ ጸጋ እግዚአብሔር፤ ያለ መከራ የእግዚአብሔር ጸጋ አይገኝም” በማለት ያስረዳሉ። የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ራሷና ሙሽራዋ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ራሱ ታሞ ጤነኛ የሚሆን አካልና ሙሽራዋ መከራ ሲቀበል ያለ መከራ የምትቀመጥ ሙሽሪት አይኖሩም፡፡ ራሷ፥ ጉልላቷ መስቀል ተሸክሞ አካሉም እንደሱ መስቀል ተሸክማ እንድትከተለው አዟታል፡፡ ሙሽሪትን በሞቱ እንድትመስለውና የትንሣኤው ተካፋይ እንድትሆን ጠርቷታል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ  የተባረከ የመስቀል ጉዞ፣ የተቀደሰው ይህ ጥሪና በዚህ ጥሪ መሠረት የመስቀል ጉዞውን የመሳተፍ ጸጋም በአላዋቂዎች ዘንድ ሞኝነት በአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ደግሞ መሸነፍ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ለእኛ ለምናምነው ግን የክርስቶስ የመስቀሉ ጉዞ ሞኝነትም መሸነፍም ሳይሆን የድል አድራጊነትን ምሥጢር የማዳኑን ኃይል ሰውን ከፈጠረበት ይልቅ ያዳነበትን ረቂቅ ጥበብ የምንረዳበት ነው፡፡ ነገረ መስቀሉን እያሰቡ በመከራውና በሞቱ ክርስቶስን የመሰሉት ሁሉ የሚዋጋቸውን ጠላት ድል እንዳደረጉበት ቅዱሳት መጻሕፍት አብነቶቻችን ናቸው፡፡

እንግድህ ወደተነሣንበት ርእሳችን ስንመጣ ቅዱሳን ሐዋርያቱ በክርስቶስ ስም ከሚደርስባቸው መከራ ይልቅ ስለ ስሙ በሚቀበሉት መከራ የሚያገኙት ጸጋ እጅግ የሚበዛ መሆኑን በመረዳ ነውና ሁልጊዜም ከከሳሾቻቸው ፊት ደስ እያላቸው ይወጡ ነበር፡፡ በዚህ መከራቸውም በሞቱ መስለውታል የትንሣኤውም ተካፋዮች ሆነዋል፡፡

እኛስ በሕይወት ዘመናችን በምናደርገው ክርስቲያናዊ ጉዞ ሁሉ ክርስቶስን በሞቱ መስለነው የትንሣኤው ተካፋዮች እንሆን ዘንድ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ስንመለከት ደግሞ እኛ ዛሬ ማድረግ ያለብን፡-

ሀ. መስቀሉን መሸከም

የክርስትና ሃይማኖት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተመሠረተ የመገለጥ ሃይማኖት ነው። እንደሚታወቀው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ የሰቀሉት በሰውነቱ ክፋት፥ በአንደበቱ ሐሰት ሳይገኝበት በቅንዓትና በግፍ ነው ። ይህ በደረሰበት ጊዜ እንዳይደናገጡና እንዴት ሊሆን ቻለ? እንዳይሉ  ስለሚደርስበት መከራ “እነሆ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ተላልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል። ለሕዝቡም አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነርሱም ይዘብቱበታል፤ ይገርፉታል፤ ይሰቅሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።” (ማቴ.፳፥፲፰-፳) በማለት ቀድሞ ተናግሯል። በኋላም ጊዜው ሲደርስ የተፈጸመው ይሄው ነው። ከእርሱ የተወለዱ፣ በስሙም የተጠሩ የክርስቲያኖችም ሕይወት በዚሁ መንገድ እንደሚቀጥል በሚገባ ገልጾልናል። “ከክፉዎች ሰዎች ተጠበቁ፤ ወደ አደባባዮች አሳልፈው ይሰጧችኋልና፤ በምኵራቦቻቸውም ይገርፏችኋልና። ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር ትሆኑ ዘንድ ስለ እኔ ወደ መሳፍንትና ወደ ነገሥታት ይወስዷችኋል።” (ማቴ.፲፥፲፯-፲፱) በሆነ ጊዜ እንዳንደናገጥና እንዳይገርመን አስቀድሞ በዚህ መልክ አስረዳን። ዳግመኛም “መስቀሉን ተሸክሞ ሊከተለኝ የማይመጣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።” (ሉቃ.፲፬፥፳፯) ብሎናል። ጌታችን “መስቀሌን” ሳይል “መስቀሉን” ያለውም እያንዳንዳችን እንድንሸከመው የተሰጠን መስቀል መኖሩን ያመለክተናል። እየደረሰብን ባለው ዘርፈ ብዙ መከራ ውስጥ የሚያጸናን፥ ከሐዘናችንም ፈጥኖ የሚያጽናናን እንዲህ ያለው የጌታችን ድምጽ ነው። መስቀላችንን ስንሸከም የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እናረጋግጣለንና።

ለ. የአባት የሆነው መከራ ሁሉ የልጆችም መሆኑን መረዳት

በቅዱስ መጽሐፍ “ከሸንጐው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤” የተባሉት ቅዱሳን ሐዋርያቱ ናቸው። እንደተገለጸው በመከራ ውስጥ እንደሚያልፉ ተገንዝበዋል። በተጨማሪም “ዓለም ቢጠላችሁ አስቀድሞ እኔን እንደ ጠላ ዕወቁ። እናንተስ ከዓለም ብትሆኑ ዓለም በወደዳችሁ ነበር፤ ዓለም ወገኖቹን ይወዳልና፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ ከዓለም አይደላችሁምና ስለዚህም ዓለም ይጠላችኋል።. . . እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዷችኋል።” (ዮሐ.፲፭፥፲፰-፳፩) “በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኋችሁ፤ በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤ እኔ ዓለሙን ድል ነሥቼዋለሁና።” (ዮሐ.፲፮፥፴፫) በእርሱ የደረሰ መከራ በልጆቹም እንደሚደርስና የባሕርይ ገንዘቦቹም በጸጋ ለልጆቹ እንደሚታደሉ እንደሚታደሉ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ ከጌታችን አንደበት በተነገሩት በእነዚህ የሕይወት ቃሎችም መከራ እንደሚያገኘን ብቻ ሳይሆን መከራችን የብርታት፣ የሰላም፣ የድል አድራጊነትና የደስታ ምንጭ እንደሚሆን አስተምሮናል፡፡ ደስታ ምድራዊና ሰማያዊ ተብሎ በሁለት የሚከፈል ሲሆን አሁን እየተናገርን ያለነው ስለ ሰማያዊው ደስታና ስለ መንፈሳዊው ሐሴት ነው። የዚህ ዓለም ተድላና ኀላፊው ክብር የምድራዊ ደስታ ምንጭ ሲሆን እነዚህን ሁሉ መናቅና በክርስቶስ ስም መከራ መቀበል ደግሞ የእውነተኛውና የሰማያዊው ደስታ ምንጭ ነው።

ሐ.  እንጸና ዘንድ መስቀሉን ተሸክመው የጸኑትን ሐዋርያትን መዘከር(ማሰብ)

በበዓለ ኀምሳ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብለው ክርስቶስ እንዳዘዛቸው በቁርጠኝነት ማገልገል በጀመሩ ጊዜ ሰይጣን በየፊናው ልዩ ልዩ በሆኑ መከራዎች ደቀ መዛሙርትን ማሳደድ ጀመረ። በየዘመናቱ ገብቷቸውም ሆነ ሳይገባቸው የሐሳቡ ሥራ አስፈጻሚ ግብረ አበሮችን ሰይጣን አጥቶ አያውቅም። ጌታችን እንደተናገረው በእርሱ ላይ የደረሱ መከራዎች ሁሉ በሐዋርያት፣ በሰማዕታት፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በጻድቃን፣ አሁን ባለና  እስከ ዕለተ ምጽአት በሚኖሩ ክርስቲያኖች ላይ የደረሱ፣ እየደረሱ ያሉና የሚደርሱ ናቸው። ርእሰ ጉዳይ አድርገን ባነሣነው ኀይለ ቃል ዙሪያ ያለው ታሪክም የሚነግረን ይህንኑ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት በታዘዙት መሠረት ቅዱስ ቃሉን ማስተማራቸውና አስደናቂ ተአምራትን ማድረጋቸው አይሁድን በቅንዓት አሳርሯቸዋል። እነርሱ የሕይወት ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ርቀው መኖራቸው ሳያንስ የሌሎች መዳን ነበር የሚያናድዳቸው። በሐዋርያት ሥራ በምዕራፍ እንደተገለጸው ሊያታልሉ የሞከሩት ሐናንያና ሰጲራ በቅዱስ ጴጥሮስ ሰይፈ ቃል ተቆርጠው መሞታቸው፤ በቅዱስ ጴጥሮስ ጥላ ሕሙማን ሁሉ አምነው መዳናቸው፤ አይሁድን ዕረፍት ነሳቸው። በቅንዓት ተነሣስተውም ሐዋርያትን አስረው በወኅኒ ቤት አገቧቸው፤ የክርስቶስ ገዳዮች ለእነርሱ ሊራሩላቸው አይችሉምና። መልአከ እግዚአብሔርም በሌሊት ወኅኒ ቤቱን ከፍቶ ከአወጣቸው በኋላ “ሂዱ፤ ወደ ቤተ መቅደስም ግቡና ለሕዝብ ይህን የሕይወት ቃል አስተምሯቸው።” (ሐዋ.፭፥፳) በማለት አዘዛቸው።

ሊቃነ ካህናቱም ሐዋርያትን ከወኅኒ አምጡ ብለው የወኅኒ ቤት ጠባቂዎችን ባዘዙ ጊዜ ከወኅኒ ቤቱ እንደሌሉና በመቅደስ እያስተማሩ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ በእጅጉ ተበሳጩ። ምንም እንኳን ደጆቹ እንደተዘጉ በድንቅ ተአምር መውጣታቸውን ቢረዱም ወደ ክርስቶስ ፊታቸውን ከማዞር ይልቅ በክፋታቸው ገፉበት። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ኢየሱስ ክርስቶስንም በማምለክ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች በክፋት ላይ ክፋትን እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ ራሳቸው ይስታሉ፤ ሌላውንም ያስታሉ።” (፪ጢሞ.፫፥፲፪-፲፬) እንዳለው ዛሬም እየሆነ ያለው ይኸው ነው። የሰይጣን ሠራዊትና ግብርአበሮቻቸው ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ተከፍታ አማኙ ክርስቶስን እያመለከ ሲኖር ማየት ዕረፍት ይነሳቸዋል። ክፉዎች በክፋት በባሱ መጠን “በክርስትና ሃይማኖቴ ጸንቼ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን መስዬ በመኖር ያዘጋጀልኝን ዘለዓለማዊ ርስት መውረስ አለብኝ፤” የሚሉ ሁሉ ሐዋርያው እንዳለው መከራ ይቀበሉ ዘንድ ይገደዳሉ። ወደ ቀደመ ታሪካችን እንመለስና ሕዝቡን በመፍራት አባብለው ሐዋርያትን ከሚያስተምሩበት መቅደስ አመጧቸው። በሸንጐው መሐል አቁመው “በኢየሱስ ስም ለማንም እንዳታስተምሩ ከልክለናችሁ አልነበረምን? እነሆ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤” (ሐዋ.፭፥፳፰) በማለት ገሠጿቸው። ሐዋርያትም “ለሰው ከመታዘዝ ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባል።” (ቁ.፳፱) በማለት አይሁድ ሰቅለው የገደሉት ክርስቶስ የሕይወት ራስና አዳኝ አምላክ መሆኑን ዳግም አረጋገጡላቸው። ይህን መስማት በጣም ያበሳጫቸው አይሁድም ሊገድሏቸው ፈለጉ፤ ይሁን እንጂ በእነሱ ዘንድ በከበረው መምህር በገማልያል ምክር ዳግመኛ እንዳያስተምሩ ገርፈውና ገሥጸው ለቀቋቸው። የዚህ ጊዜ የሆነውን ወንጌላዊ ሉቃስ ሲገልጽ “ከሸንጐው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ስለ ስሙ መከራ ይቀበሉ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አድሏቸዋልና። ሁልጊዜም በቤተ መቅደስና በቤት ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አልተዉም።”  (ቁ.፵፩-፵፪) ብሏል።

 

መ. በክርስቶስ ስም የምንቀበለው መከራ የእውነተኛ ደስታ ምንጭ መሆኑን ማመን

እንዴት ነው መከራቸው የደስታቸው ምንጭ ሊሆን የቻለው? ቅዱሳን ሐዋርያት በመከራቸው ውስጥ ደስተኞች የሆኑት፦

፩ኛ. ስለ ሰው ልጅ ፍቅር መከራ የተቀበለውን ክርስቶስን ስለ እሱ ፍቅር መከራ በመቀበል ስለመሰሉት፤

፪ኛ. ስለ ስሙ የሚቀበሉት መከራ ለእውነተኛ ደቀ መዛሙርትነታቸው ሕያው ማረጋገጫ ስለሆናቸው፤

፫ኛ. ክርስቶስ ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ መስቀሉ የተናገረውና ቃል የገባላቸው እውነተኛ መሆኑን ስለሚያረጋግጥላቸው፤

፬ኛ. እግዚአብሔር ከአዘጋጀላቸው ዘላለማዊ ሕይወትና ታላቅ ክብር አንጻር መከራቸው ኢምንት (ቀላል ) ስለሆነ፤ “ነገር ግን የዚህ ዓለም መከራ ለእኛ ሊገለጥ ከአለው (ከተዘጋጀው) ክብር ጋር እንደማይተካከል ዐስቡ።” (ሮሜ ፰፥፲፰) እንዲል።

፭ኛ. መከራ አማኞችን እንደ ኀጢአት የሚያዋርዳቸው ሳይሆን ወደ ክብር ማማ የሚያወጣቸው መሆኑን ስላረጋገጡበት፤ ከመከራዎቻቸው መሐል የማይደበዝዝ ደስታ ይፈልቅ ነበር፤ አሻግረው እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸውን የማይፈጸም ደስታ ያያሉና።

ሰማዕታት አንገታቸውን ለስለት፣ዓይናቸውን ለፍላት፣ እጃቸውን ለሰንሰለት፣ እግራቸውን ለእግር ብረት፣ ሰውነታቸውን ለእሳት አሳልፈው እንዲሰጡና ደስ እያላቸው ወደ ስቃዩ ሥፍራ እንዲገሠግሡ ያደረጋቸው ይኸው ነው። ጻድቃን ፀብአ አጋንንትን፣ ግርማ ሌሊትን፣ ድምጸ አራዊትን ታግሠው፤ ዳዋ ጥሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው በደስታ እንዲጋደሉ የሚያደርጋቸው ይኸው ነው። መከራ በደረሰብን ጊዜ  የደስታችን መፍለቂያ ይህ መሆን እንደሚገባው ነው የሚያስተምረን።ይህንን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስ “ሙሴም በአደገ ጊዜ የፈርኦን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እንቢ አለ፤ ለጊዜው በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት ከግብፅ ሀብት ሁሉ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንደሚሆን ዐውቋልና፥ ዋጋውንም ተመልክቷልና።” (ዕብ.፲፩፥፳፬-፳፯) በማለት የሊቀ ነቢያት ሙሴን ሕይወት አብነት እንድናደርግ አስተምሮናል።

ሠ. ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል ለክብር መመረጥ ወይም መታደል እንደሆነ ማወቅ

ጌታችን በጠጣበት ጽዋ መጠጣት የቻሉ ክርስቲያኖች ምንኛ የታደሉ ናቸው! ጌታችን “አባቴ ሆይ፥ የሚቻልስ ከሆነ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ … አባቴ ሆይ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ከእኔ ልታልፍ የማይቻል ከሆነ ፈቃድህ ይሁን።” (ማቴ.፳፮፥፴፱-፵፫) ብሎ ጌታችን የተናገረው ይህንን ነውና። ጽዋ የሚለው መከራንና ሞትን ሲሆን “ትለፍ” የሚለው ቃል አንዱ ትርጕም ለምእመናን ትድረስ፤ እኔ የጠጣኋትን የመከራና የሞት ጽዋ እነሱም ይጠጧት ማለት ነውና።  በሃይማኖታቸው ምክንያት ልዩ ልዩ መከራ የተቀበሉ፣ እየተቀበሉ ያሉና የሞቱ፣ እየሞቱም ያሉ ክርስቲያኖች ይህንን የክርስቶስን ጽዋ የጠጡና እየጠጡም ያሉ የጌታችን ምስክሮቹ ናቸው። ታዲያ ከዚህ በላይ መታደል ከወዴት ይገኛል? ወንጌላዊው ለዚህ ነው “ከሸንጐው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤” ካለ በኋላ “ስለ ስሙ መከራ ይቀበሉ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አድሏቸዋልና።” ያለው። ስለ ቅዱስ ስሙ መከራ ከመቀበል በላይ የሚወዳደር ምን ክብር ይኖራል?

ሰይጣን በክርስቶስ፣ በደቀ መዛሙርቱና በክርስቲያኖች ሁሉ ላይ ያደረሰውን ስደት፣ መከራና ሞት ዛሬም ባለነው ክርስቲያኖች ሁሉ ላይ ከማድረስ ወደኋላ አይልም። በዘመናችን መንፈስ ቅዱስ እየረዳቸው መከራውን በምስጋና ለመቀበል ያበቃቸው ያረፉትም ያሉትም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ ክርስቶስን በመከራ የመሰሉት ምርጦቹ ለመሆን የታደሉ፥ መንፈስ ቅዱስም ያልተለያቸው ናቸውና። በአጸደ ነፍስ ያሉት በአጸደ ሥጋ ሳሉ ስለክርስቶስ ስም ስለተቀበሉት መከራ  በተሰጣቸው ሰማያዊ ክብር በደስታ ይኖራሉ፡፡ በዚህ ዓለም በመከራ ውስጥ ያሉት ደግሞ ዋጋቸውን እያሰቡ በተስፋ የሚደሰቱ የክብሩ ተካፋዮች ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ “በሞቱ ከመሰልነውም በትንሣኤው እንመስለዋለን።” (ሮሜ ፮፥፭) “ከእርሱ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን።” (፪ጢሞ.፪፥፲፩) በማለት ተስፋ እንዳስደረገን። ከጽዋው ተጎንጭቶ ዘላለማዊ ርካታን ከግኘት በላይ ጸጋ ከወዴት ይገኛል?

ረ. ዛሬም ሆነ ወደፊት ስለክርስቶስ በሚመጣብን መከራ ምን እናድርግ?

ክርስቶስን የምንመስለው በቃሉ ያስተማረንንና በግብር ያሳየንን በሕይወት በመተግበር ነው። እውነተኛ በመሆን፣ በመጸለይ፣ በመጾም፣ ይቅር በማለት፣ እስከ ሞት ድረስ እርሱንና ሰዎችን በመውደድና የመሳሰሉትን በመፈጸም ነው። በፈቃደ ካህንና በንስሐ ሕይወት በመመላለስ፣ ሥጋውን ደሙን በመቀበል፣ መኖር፥ ከክርስቶስ ጋር መኖርና እርሱንም መምሰል ነው። በተለይም በእንደዚህ ያለ አስጨናቂ ዘመን አብዝተን በክርስትና መርሆች ለመኖር መጋደል ይጠበቅብናል። መጪውን የፍልሰታ ለማርያም ጾም ከምንጊዜውም ላቅ ባለ ሁኔታ በጸሎትና በመልካም ምግባራት አጊጠን ለማሳለፍ መዘጋጀት ይኖርብናል።ቅዱሳን ሐዋርያት በክርስቶስ ስም በማመናቸውና በማስተማራቸው ተገርፈውና ዳግም እንዳያስተምሩ ተገሥጸው ተለቀቁ። አባቶቻችን ሐዋርያትም ከወኅኒው በደስታ ከወጡ በኋላ ስለ ክርስቶስ በመቅደስና በቤት ማስተማራቸውንና ማገልገላቸውን ቀጠሉ እንጂ ፈርተው አላፈገፈጉም። ይህም ለክርስቲያኖች ሁሉና በዚህ ዘመን ላለነው ክርስቲያኖች የሕይወት መመሪያ ነው።

የክርስቶስ (ክርስቲያን) በመሆናችን ምክንያት የምንቀበላቸው ማናቸውም መከራዎች መስቀሉን በመሸከም የክርስቶስን ሕማም የምንሳተፍባቸው ቋሚ መንገዶቻችን ናቸው። ከክርስቶስ ሕማም የተሳተፉ ሁሉ የትንሣኤውም ተሳታፊዎች በመሆን የዘለዓለማዊ መንግሥት ወራሾች ይሆናሉ። እንደገለጽነውም ሐዋርያት እየተሠቃዩ ደስ የሚያሰኛቸው ይኸው ነው። እኛም በመከራ ውስጥ ስንወድቅ በነፍስ ልዕልና ከፍ ብለን ሰማያዊውንና ዘለዓለማዊውን ርስት እያሰብን እንጋደል። እንኳን ለዚህ ክብር ይቅርና ለጊዜያዊውና ለምድራዊው ርስትስ መዋጋትና መሞት አለ አይደለምን? በዚሁም ላይ በሰማዕትነት ያረፉት የክብር ባለቤቶች በመሆን አስቡን፣ ጸልዩልን፣ አማልዱን ከሚባሉት ጋር ሲደመሩ ከማየት በላይ ምን ደስታ ይኖራል? መከራን ተቀብለው ለጊዜው ከሞት የተረፉትም በጠላት ማስፈራሪያ ሳይደናገጡና ሳይሸማቀቁ በአገልግሎታቸው ሊገፉበት ይገባል። ተጨማሪ ዕድሜ ሰጥቶ ያሰነበታቸው ለበለጠ አገልግሎትና ምስክርነት መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም። ምስክርነታቸውንም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ በመኖሪያ ቤትና በሥራ ቦታ በትጋት መቀጠል ይኖርባቸዋል። ለጊዜው ጠንካራ መከራ ያልደረሰብንም ብንሆን ለማይቀረው ቀጣይ መከራና ምስክርነት ራሳችንን ከወዲሁ ማዘጋጀት ይጠበቅብናል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ  ማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ የተዘጋጀ

ሐምሌ ፳፻፲፪ ዓ/ም

 አዲስ አበባ