“ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይሰዐር ግብሮ ለጋኔን”

ጥር 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ኃይለ ኢየሱስ ቢያ

“የዲያብሎስን  ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ፡፡” 1ኛ ዮሐን.3፥8

 

ይህንን ኀይለ ቃል የተናገረው  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው፡፡ የተናገረበት ምክንያት፡-

የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የጌታችን መድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ /ሰው ሆኖ የማዳን ሥራውን/ መፈጸሙን ለመግለጥ  የተናገረው /የጻፈው ኀይለ ቃል ነው፡፡

  • መገለጥ ማለት ፡- ረቂቁ አምላክ በተአቅቦ ርቀቱን ሣይለቅ ውሱን ሥጋን ውሱኑም ሥጋ በተአቅቦ ውስንነቱን ሳይለቅ ረቂቅ መለኮትን የሆነበት በአጭር ቃል የቃል ግብር ለሥጋ የሥጋ ግብር ለቃል የሆነበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቀዳማዊ ደኃራዊ የሆነው አምላክ ሞት የሚስማማው ሆነ፤ ዘመን የሚቆጠርለት ሥጋ ዘመን የማይቆጠርለት ሆነ፡፡ ሥጋ በማይመረመር ምስጢር የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ ቢያደርግ “ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ” /ራእ.1፥17/ ማለት የቻለበት ምስጢር ነው፡፡ የረቀቀው ገዝፎ የገዘፈው ረቆ፣ ሰማያዊው ምድራዊ  ምድራዊው ሰማያዊ ሆኖ መታየት ማለት ነው፣  ከዓለም ተሰውሮ የነበረው ምስጢር  ግልጥ ሆኖ መታየት ማለት ነው ይህንንም ምሥጢር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ  መልእክቱ “እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የጠገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ /1ጢሞ 3፥16/ በማለት፡፡ ከልደት እስከ ዓቢይ ጾም መጀመሪያ  ያለው ጊዜ  ዘመነ አስተርእዮ /የመገለጥ ዘመን/ የመታየት ወቅት ይባላል

 

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው መሆኑን /ዓለምን ለማዳን መወለዱን የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡

የእግዚአብሔር መገለጥም በ3 ዘመናት ከፍሎ ማየት ይቻላል

  1. በሕገ ልቡና፡- በቃል፣ በራእይ፣ በተአምር እየተገለጠ በማነጋገር አምላክነቱን አስረድቷል፡፡ ዘፍ.2፥8-18፣ ዘፍ.3፥9፣ ዘፍ.12፥1

  2. በሕገ ኦሪትም፡- በቃል በራእይ በተአምር እና ሕግና ሥርዓት በመስጠት አምላክነቱን አስረድቷል/አስተምሯል፡፡

  3. በሕገ ወንጌል፡- ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኖ በመካከላቸው ተገኝቶ መምህር ሆኖ የአምላክ ልጅ አምላክ መሆኑን በግልጽ አስረድቷል፡፡

 

“መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው፡፡ ብሏል” ዮሐ.1፥18

አስቀድመን የገለጥነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ

  • በሥጋ የተገለጠ

  • በመንፈስ የጸደቀ

  • በመላእክት የታየ

  • በአሕዛብ የተሰበከ

  • በዓለም የታመነ

  • በክብር ያረገ በማለት የገለጠው ፤/1ኛ ጢሞ.3፥16/

 

ጌታ ተወልዶ በመጀመሪያ የሠራው ሥርዓት ምሥጢረ ጥምቀትን ነው፡፡ ለምን ተጠመቀ ቢሉ፤

  • የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም መዝ.113፥3-6

  • አምላክነቱን ለመግለጥ /አንድነትና ሦስትነቱን/ ማቴ.3፥17

  • ለእኛ አብነት ለመሆን ማቴ.11፥28-29

  • የዕዳ ደብዳቤአችንን ለመደምሰስ ቆላ.2፥13-15

  • ውኆችን ለመቀደስ

  • በጥምቀት የሚገኘውን ኀይል /የልጅነት ጸጋ/ ለማስረዳት

እኛስ ለምን እንጠመቃለን ብንል

  • ከኀጢአት ለመንጻት ለመቀደስ ነው 1ኛ ቆሮ.6፥11

  • የሥላሴን ልጅነት ለማግኘት ነው ማቴ.28፥19፣ ዮሐ.1፥12፣ ዮሐ.3፥5

  • ለመዳን እንጠመቃለን ማር.16፥16፣ ኤፌ.1፥3-15

 

የእግዚአብሔር ልጅ ለምን ተገለጠ ቢሉ

1.    የሰይጣንን ሥራ ይሽር ዘንድ ነው፡፡

  • ሰይጣን ማለት፡- መስተጻርር፣ መስተቃርን ባለጋራ፣ ጠላት ማለት ነው 1ኛ ጴጥ.5፥8፣ ማቴ.13፥25

  • ጋኔን ማለት፡- ዕሩቅ፣ ውዱቅ የተጣለ ማለት ነው ራእ.12፥9፣ ራእ.20፥2

  • ዲያብሎስ ማለት፡- ዖፍ፣ ሠራሪ፣ ነድ፣ ውዑይ፣ /የተቃጠለ/ ፈታዌ አምላክነ /አምላክነትን የሚሻ/ ማለት ነው፡፡

 

የሰይጣን ሥራው ምን ነበር ቢሉ

በ3ቱ አርዕስተ ኀጦውዕ /የኀጢአት መሠረቶች/ በመጥለፍ /በማታለል/ የሰውን ልጅ ከክብር ማዋረድ ነው፡፡ በዚህም ሥራው የሰው ልጆችን ለ5500 ዘመን በኀልዮ በነቢብ እና በገቢር  ከመርገም በታች  አድርጎ ገዛ ዮሐ.14፥3

 

“እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፣ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሠሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡” ብሏል ዕብ.2፥14-16

  • ስለዚህ ጌታ በዘር ይተላለፍ የነበረውን ኀጢአት  እንበለ ዘር በመፀነስ

  • የአዳምንን የሔዋን የዲያቢሎስ አገልጋይነት የሚያሳየውን በዮርዳኖስ የቀበረውን  የዕዳ ደብዳቤ በጥምቀቱ

  • በሲኦል ያኖረውን በስቅለቱ እንደሰውነቱ ረግጦ እንደአምላክነቱ አቅልጦ

  • ሞትን በትንሣኤው አጥፍቶ ነጻነትን  ሰብኮልናል 1ኛ ጴጥ.3፥19

 

ሦስቱ አርእስተ ኀጣውዕ የሚባሉትም፡-

  1. ስስት፡- ያልሰጡትን መሻት /መፈለግ ስግብግብነት ማለት ነው፡፡

  2. ፍቅረ ንዋይ፡- በቃኝ አለ ማለት ነው፡፡

  3. ትዕቢት፡- አምላክ እሆናለሁ ብሎ መሻት መፈለግ ነው፡፡

 

ዲያብሎስ ጌታን በእነዚህ በሦስቱ ኀጣውዕ ፈትኖት ድል ተነስቷል፡፡ ማቴ.4፥2-8 እኛም በስስት በፍቅረ ንዋይ እና በትዕቢት እንዳንጠፋ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ኑሮየ ይበቃኛል ማለትን ልንለምድ ይገባናል፡፡ ወደ ዓለም ያመጣነው አንዳች ነገር የለንም፤ ከእርሱም ልንወስደው የምንችል የለምና፡፡ ምግባችንንና ልብሳችንን ካገኘን ይበቃልና፡፡ ባለጸጋ ሊሆኑ የሚወዱ ግን በጥፋትና በመፍረስ፥ ሰዎችን የሚያሰጥምና በሚያሰንፍ፥ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና፥ በወጥመድም ይወድቃሉ፡፡ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ ይህንም በመመኘት ተሳስተው ሃይማኖታቸውን የለወጡ ብዙዎች ናቸውና፥ ለራሳቸውም ብዙ መቅሠፍትን ሽተዋልና፡፡” 1ኛ.ጢሞ.6፥6-11 በማለት መክሮናል፡፡

 

2.    ለሰው ልጅ ነጻነትን ይሰብክ ዘንድ ነው፡፡ /ይዋጀን ዘንድ ነው/

  • ለድኆች የምሥራችን ይነግራቸው ዘንድ፣ ለተማረኩትም ነጻነትን ይሰብክላቸው ዘንድ

  • ያዘኑትንም ደስ ያሰኛቸው ዘንድ፣ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ፣ የተገፉትንም ያድናቸው ዘንድ፣ የታሰሩትንም ይፈታቸው ዘንድ የቈሰሉትንም ይፈውሳቸው ዘንድ

  • የተመረጠችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት ይሰብክ ዘንድ ነው፡፡ሉቃ.4፥18-20፣ ገላ.4፥4

 

3.    እኛ ከእግዚአብሔር እንወለድ ዘንድ ነው፡፡

አምላክ ሰው የሆነው በስሙ አምነን ተጠምቀን የመንግሥተ ሰማያት ዜጋ እንሆን ዘንድ ነው፡፡ ዮሐ.1፥12፣ ማቴ.28፥19፣ ዮሐ.3፥5፣ ማር.10፥16፣ ገላ.3፥26

 

4.    ጽድቅን ያስተምረን ዘንድ ነው፡፡

ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣበት ዋና ዓላማ ሰውን ለማዳን ሲሆን በተጨማሪ፡-

  • ክርቶስ ፍጹም በሆነ መልካም አኗኗሩ፣ ጠፍቶ የነበረውን የእግዚአብሔርን አርዓያና አምሳል /ዘፍ. 1፥26-27/ እንደገና ለመመለስ ለሰዎችም የመልካም ኑሮ አብነት ለመሆን፤

  • እንደመምህርነቱ እውነተኛውን ትምህርትና ዕውቀት ለመስጠት ሐሰት አስተምህሮዎች  አስተሳሰቦችን ለማረምና ለማስተካከል፤

  • እግዚአብሔር ሰውን የሚወድ ሰማያዊ አባት መሆኑን በተግባር ለማሳወቅና ልባችንም በፍቅር እንዲሞላ ለማድረግ፤

  • እንደ መልካም እረኛና ጠባቂ ድሆችንና ችግረኞችን ለመርዳት ነው፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲን ይኼንን ታምናለች፡፡ በመዋዕለ ስብከቱ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ፤ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና፡፡” ብሏል ማቴ.11፥28-29

 

5.    ፍቅርን ያሳየን ዘንድ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ረብ ጥቅም ሳይፈልግ እንዲሁ በከንቱ ወደደን፡፡ ዮሐ.3፥16

  • ፍቅር ሰሐቦ ለወልደ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሆ እስከ ለሞት በማለት ሊቃውንት የተናገሩበት ምክንት ይህ ነው፡፡
  • “እግዚአብሔር ምን ያህል እንደወደደን እነሆ እዩ እኛ ኀጢአተኞች ስንሆን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ እንግዲህ በደሙ  ከጸደቅን ከሚመጣው መከራ በእርሱ እንድናለን፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ጠላቶቹ ስንሆን በልጁ ሞት ይቅር ካለን ከታረቅን በኋላም በልጁ ሕይወት እንድናለን፡፡” ብሏል፡፡ ሮሜ.5፥8-11 ወንድሞቻችን ሆይ እግዚአብሔር ይህን ያህል ከወደደን እኛም እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔርንስ ከቶ ያያሉ ሰው የለም እርስ በርሳችን ከተዋደድን ግን እግዚአብሔር አብሮን ይኖራል፡፡ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል፡፡” ብሏል፡፡ 1ኛ ዮሐ.4፥10-13

 

እንግዲህ በአጠቃላይ እግዚአብሔር ወልድ በሕግም በቃልም በተግባርም ያስተማረን ገብቶን/ ተረድተን በሕይወታችን ዘመን ሁሉ እርሱ ባሳየን ባስተማረን ኖረን የስሙ ቀዳሽ የመንግሥቱ ወራሸ ለመሆን ያብቃን፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱሳን አማላጅነት አይለየን፡፡