ወርኃ ጳጉሜን
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ነሐሴ ፴፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ዕለተ ምርያ
ወርኃ ጳጉሜን በዓመቱ መጨረሻ የምትገኝ በአገራችን ኢትዮጵያ እንደ ዐሥራ ሦስተኛው ወር የምትቆጠር ናት፤ ወርኃ ጳጉሜን አምስት ቀናት ያሏት ስትሆን በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ሉቃስ መውጫ በዘመነ ዮሐንስ መግቢያ ያለው ስድስት ቀን ይሆናል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላታቸው ጳጉሜን እንዲህ ይተረጉሟታል፤ ጳጉሜን ማለት ጭማሪ ተውሳክ፣ አምስት ቀን፣ ከሩብ፣ ከዐውደ ወር ተርፎ በዓመቱ መጨረሻ የተጨመረ ስለሆነ ትርፍ ተጨማሪ ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፱፻፭)
በወርኃ ጳጉሜን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተከብረው (ታስበው የሚውሉ በዓላት አሉ፤ በሌላ ስያሜም ዕለተ ምርያ (የመዳን ወር ) ትባላለች፤ ምርያ ማለት ከቀን ወደ ቀን የሚያሻግር፣ አንድም ዕለተ ኅሪት ዕለተ መድኃኒት ማለት ነው፤ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፮፻፰) ምእመናን በዚህች ወቅት ጸበል ይጠበሉባታል (ይጠመቁበታል)፡፡
ሊቀ መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል
ጳጉሜን ሦስት ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ የሊቀ መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል በዓል ነው፤ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል በዚህች ዕለት ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ይከበራል፡፡ በድርሳነ ቅዱስ ሩፋኤል እና በወርኃ ጳጉሜን ሦስት ቀን የሚነበበው ስንክሳርና የተጻፉት ድርሳናት እንዲህ ያስተምሩናል፤ አንዲት ክርስቲያን ሴት በቅዱስ ሩፋኤል ሰም በባሕር መካከል ባለች ደሴት ቤተ ክርስቲያን አሳነጸች፤ ሊቀ ጳጳሱ አባ ቴዎፍሎስ በዚህች ዕለት ቅዳሴ ቤቱን አከበረ፤ ከደሴቲቱ ሥር የነበረ ግዙፍ ዓሣአንበሪም ባሕሩን ባናወጠው ጊዜ በደሴቲቱ የታነጸቸውን ቤተ ክርስቲያኗን ሊያፈርስ ደረሰ፤ በውስጧም ለበዓል ተሰብስበው የነበሩ ምእመናን በጸሎት ወደ ቅዱስ ሩፋኤል ተማጸኑ፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤልም ከእግዚአብሔር ተልኮ መጣ፤ ሕዝቡን ታደገ፤ ከደሴቲቱ ሥር ያለውንም ግዙፍ ዓሣአንበሪው እንዳይንቀሳቀስ በጦር ወጋው፤ ‹‹እግዚአብሔር አዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም!›› አለው፤ ጸጥ ብሎም ቆመ፡፡ ሕዝቡም ከባሕሩ ከመስጠም፣ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኒቱም ከመፍረስ ተረፉ፤ ቅዱስ ሩፋኤል ይህን ድንቅ ተአምር አድርጎ፣ ከፈጣሪው አማልዶ፣ ለጠሩት ፈጥኖ የደረሰበትን ይህን በዓል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓመቱ መጨረሻ ባለችው ወርኃ ጳጉሜን በሦስተኛ ቀን በድምቀት ታከብሯለች፡፡ (ስንክሳር ዘወርኃ ጳጉሜን ሦስት ቀን)
በዚህች ዕለት ከሚከበሩ በዓላት ሌላኛው በመጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፈ ጦቢት እንደተጻፈው ቅዱስ ሩፋኤል በመልካም ምግባሩ፣ በምጽዋት ሥራው ለሚታወቀው ለጦቢት በችግሩ ጊዜ በሰው አምሳል ተገልጦ፣ እንደ ሠራተኛ ተቀጥሮ በማገልገለል ልጁ ጦቢያን ከዓሣአንባሪ ፣ ሣራ የተባለችን ሴት ያሠቃያት ከነበረው ርኩስ መንፈስ፣ ጦቢትን ከዓይን ሕመሙ የፈወሰበት የቅዱስ ሩፋኤል ተራዳኢነት፣ የጦቢት መልካም ምግባር፣ የእግዚአብሔር ቸርነት የተገለጠበት መታሰቢያም በዓል ነው፡፡ (መጽሐፈ ጦቢት አንድምታው መግቢያ) ይህች ዕለት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል የተሾመበት መታሰቢያውም ነው፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ጸሎት ይጠብቀን፤ አሜን!!!
ዕለተ ምጽአት
ወርኃ ጳጉሜን የዕለተ ምጽአት መታሰቢያም ናት፤ እግዚአብሔር ለፍርድ ወደዚህ ምድር የሚመጣበት ወቅት መታሰቢያ ነው፤ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ከፀሐይም መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ምድርን ጠራት፤ ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፤ ዝምም አይልም ….›› በማለት እንደተናገረው ጌታችንም በደብረ ዘይት ተራራ ለደቀ መዛሙርቱ ዳግመኛ ለፍርድ እንደሚመጣ በገለጸው መሠረት ወደዚህ ምድር ለጻድቃን ሊፈርድላቸው፣ በኃጥአን ሊፈርድባቸው ይመጣል፤ (መዝ. ፵፱፥፩-፫) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቼ እንደሚመጣ ዓመቱንና ዕለቲቱን በግልጽ ባይነግረንም ዳግመኛ ግን እንደሚመጣ ነግሮናል፤ ‹‹…ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና፡፡›› (ማቴ.፳፬፥፵፬)
ቅዱስት ቤተ ክርስቲያንም የዕለተ ምጽአቱን መታሰቢያ በዐቢይ ጾም እኩለ ሳምንት ላይና በወርኃ ጳጉሜን ሦስተኛው ቀን ታከብራለች፤ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ጸሎት ላይ ‹‹ለምጽአትከ ከዋላ እስከነ ዘመን ወዕድሜ፣ ለመለኮትከ ዘአልቦ ፍጻሜ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላከ ሱላሜ፤ አመጣጥህ በኋለኛው ዘመን የሆነ ለአገዛዝህ ፍጻሜ የሌለህ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር አምላክ ነህ›› በማለት እንደተናገረው ለዘመኑ ፍጻሜ የሌለው የፍቅር አምላክ ፈጣሪያችን ዳግመኛ ይመጣል፡፡ (ስብሐተ ፍቁር)
ሐዋርው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ‹‹ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋው ቃል አይዘገይም፤ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል›› ብሎናልና፡፡ (፪ኛ ጴጥ.፫፥፱) ጌታ ስለ ተስፋው ቃል አይዘገይምና ሕይወታችንን በንስሐ አንጽተን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን ተዘጋጅተን ልንጠብቀው ይገባል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ‹‹…ኑ እናንተ የአባቴ ቡሩካን…›› ከሚላቸው ወገን ይደምረን! ምስጋና ለእርሱ ይሁን፤ አሜን!!!
ርኆተ ሰማይ
ይህች ዕለት ርኆተ ሰማይ (የሰማይ መስኮቶች የሚከፈቱባት)፣ ሊቃውንቱ የሰማይ ደጆች ተከፍተው የምእመናን ጸሎት የሚያርጉበት በዓመት አራት ጊዜያት እንዳሉ ይገልጻል፤ ታዲያ የመጀመሪያው ዕለት ጳጉሜን ሦስት ቀን በመሆኑ ይህች ዕለት ርኆተ ሰማይ ትባላለች፡፡ የሰማይ መስኮቶች ተከፍተው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል የምእመናንን ጸሎት ለእግዚአብሔር የሚያሳርግበት ዕለትም መታሰቢያ ነው፡፡ የእግዚአብሔር የምሕረት ደጆች የሚከፈቱባት ዕለት መታሰቢያ ናት ርኆተ ሰማይ ! አባቶችና እናቶች በትውፊት በዚህች ዕለት ዝናም ሲዘንብ በእምነት የቤታቸውን ዕቃ (ሌማቱን፣የቡሆዕቃ…) ከሰማይ በሚወርደው ዝናመ ምሕረት እንዲባረክላቸው ከውጭ አውጥተው ያስመቱታል፤ ምእመናን በዚህች ዕለት በሚዘንብ ዝናብ ይጠመቁበታል፤ በርኆተ ሰማይም በጳጉሜን ሦስት ቀን!!!
የኦሪቱ ሊቀ ካህን የመልከጼዴቅ መታሰቢያ
በዚህች ዕለት የጌታችን ምሳሌ የሆነው የኦሪቱ ሊቀ ካህን የመልከጼዴቅ መታሰቢያ ነው፤ መልከ ጼዲቅ ማለት ንጉሠ ጽድቅ ንጉሠ ሰላም ማለት ነው፡፡ ከተማዋም በእርሱ ኢየሩሳሌም/የሰላም ከተማ /ተብላለች፡፡ መልከ ጼዲቅ የእስራኤል እምብርት /ዋና ከተማ/ ኢየሩሳሌምን ያቀና ከካም ወገን የሆኑት የኖኅ የልጅ ልጅ ነው፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለኖኅና ለልጁ ለሴም ከካም ወገን የተለየ የተባረከ ልጅ እንደሚወለድና አጽመ አዳምን ይጠብቅ ዘንድ የተመረጠ መሆኑን ነግሮት ስለነበር ሴም በታዘዘው መሠረት ወደ ማዕከለ ምድር ቀራንዮ ወስዶ አጽመ አዳምን እንዲጠብቅ በእግዚአብሔር የተመረጠ መሆኑን ነግሮት በክህነቱ መፈጸም ስለሚገባው/በኑሮው ስለሚገልጠው/ ሥርዐት ሠርቶለታል፡፡ በክህነቱ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ እንዲያመሰግን የእንስሳት መሥዋዕት እንዳይሠዋ መሥዋዕቱ ንጹሕ ስንዴና ወይን እንዲሆን በእጁም ደም እንዳያፈስ ነግሮታል፡፡
በብሕትውናው ቦታ ፈጽሞ እንዳይለቅ ከመሬት በላይ ቤት ሠርቶ እንዳይኖር፣ ፀጉሩን እንዳይላጭ፣ ጥፍሩንም እንዳይቆረጥ ሚስትም እንዳያገባ ሥርዓት ሠርቶለታል፡፡ በመላከ እግዚአብሔር እየተረዳ ምግቡን መላእክት እየመገቡት እስከ አብርሃም ድረስ በፍጹም ብሕትውና ለማንም ሳይገልጥ ኑሮአል፡፡ አብርሃም የወንድሙ ልጅ ሎጥን ያስጨንቁና ንብረቱን የዘረፉ አምስቱን ነገሥታት ኮሎዶጎሞርን ድል ነሥቶ ሲመለስ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በዘመኑ የሚፈጸም መሆኑንና አለመሆኑን ለማወቅ ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቆ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ምሳሌውን ካህኑ መልከጼዴቅን ከተሰወረበት ቦታ ሄዶ እንዲመለከት ፈቀደለት፡፡ አብርሃምም የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ኅብስተ አኮቴት ጽዋ በረከት ይዞ ወደ ማዕከለ ምድር ቀራንዮ ሄደ፤ መልከጼዴቅም ተገልጦለት ‹‹አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሴት አደረገ፤ አየም ደስም አለው ….›› እንዳለው ጌታችን (መልከጼዴቅ የእግዚአብሔር ወልድ የመድኅን ዓለም ክርስቶስ) ምሳሌ ነበር፡፡ (ዮሐ.፰፥፶፰) ለዚህ ነው ጌታችን ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ አየም ማለቱ) አብርሃም ኅብስት አኮቴት ጽዋ በረከት ለመልከጼዴቅ የሰጠው፤ (ዘፍ.፲፬፥፲፰) ትውልድ ከእርሱ የማይቆጠር ግን አብርሃም ዐሥራትን አውጥቶ ሰጥቶታል፤ የአብርሃምንም መሥዋዕት አስታኮቶለታል፤ አብርሃምንም ባርኮታል፤ የጌታችን ምሳሌ የሆነው የኦሪቱ ሊቀ ካህን መልከጼዴቅን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዕለት ታስበዋለች፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም ሊቀ ካህን የመልከጼዴቅ ጸሎት ይጠብቀን፤ አሜን!!!
ጾመ ዮዲት
በወርኃ ጳጉሜን ምእመናን በፈቃዳቸው ይጾሙባታል፤ መጪው ዘመን እንዲባረክ፣ ስለ ቀደመው ኃጢአት እያዘኑ በጾም በጸሎት ፈጣሪን እየተማጸኑ ያሳልፏታል፤ ይህቺ ወቅት በመጽሐፈ ዮዲት ተመዝግቦ እንደምናነበው ሆሎፎርኒስ የተባለ የናቡከደነጾር ቢትወደድ የእስራኤልን ልጆች ምንጭ ይዞ ሕዝቡን ባስጨነቀ ጊዜ ተስፋ ቆርጠው ለጠላት ምርኮ እንግባ አሉ፤እግዚአብሔርን የምትፈራ በጾም በጸሎት ተወስና የምትኖር ዮዲት የተባለች ደገኛ ሴት ከመሪዎቿ መካከል ተገኝታ ለጠላት እጅ እንዳይሰጡ ከእነርሱ የስንፍናን ንግግር እንዲያርቁ ተማጸነች፡፡ አባቶቻቸውን ከጠላት የታደገ ድንቅ ተአምራት ማድረግ ወደሚቻለው እግዚአብሔር በጾም በጸሎት ለአምስት ቀን እንዲማጸኑ አሳሰበች፤ ከአባቶች ምርቃት ተቀብላ አገልጋይዋን አስከትላ ከጠላት መንደር ተጓዘች፡፡
እግዚአብሔር ግርማ ሞገስ ሆናት፤ ለቀናት በጾም በጸሎት ተወስና አብራ ከሆሎፎርኒስ ጋር ተቀመጠች፤ በአንድ ሌሊት አብዝቶ ጠጥቶ እንቅልፍ ጥሎት ሳለ ወደ ፈጣሪዋ እንዲህ ጸለች፤ ‹‹አቤቱ የመላእክት ፈጣሪ በዚህች ሰዓት ኢየሩሳሌም ከፍ ከፍ ትል ዘንድ መከራችንን አይተህ በእኔ እጅ ይቅርታን አደርግ፤ እስራኤልን ከኃሣር የምታነሣበት ጊዜው ደርሷልና …›› (መጽሐፈ ዮዲት ፲፫፥፬-፭)
ከዚያም የራሱን ሰይፍ አንሥታ ቸብቸቦውን ቆርጣ ወደ ሕዝቦቿ ተመለሰች፤ የናቡከደነጾር ጭፍሮች የመሪያቸው የሆሎፎርኒስን መሞት ሲመለከቱ ሸሹ፤ ዮዲትና ሕዝቧ በእግዚአብሔር ኃይል አስጨናቂ ጠላቶቻቸውን ድል አደረጉ፡፡ ዮዲት በመልካም ምግባሯ፣ በጾም ጸሎቷ ሰው በጠፋበት ዕለት ለወገኖቿ ሰው ሆና ተገኘች፤ በመልካም ጊዜ የጾሙት የጸለዩት ጸሎት በችግር ወቅት የመፍትሔ አካል እንደሚሆን ዮዲት አስተማረች፤ ተስፋ የቆረጠ ሕዝቧን ተስፋ ሰጠች፡፡ የወገኖቿን አስጨናቂ አስወግዳ ለተጨነቀች ነፍሳቸው ሰላም (የዕረፍት) ማግኘት ምክንያት ሆነቻቸው፡፡ ምእመናን በዚህ ይህ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ፣ የዮዲትን የእምነት ጽናት፣ የጾም ጸሎትን ጥቅም ተረድተው ስለ ግል ሕይወታቸው፣ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ አገር ፍቅር ሰላም ብለው በፈቃዳቸው ወርኃ ጳጉሜን በጾም በጸሎት ያሳልፋሉ፤ የሕይወት ኃሣር ይወገድ፣ ጥላቻ ከሕዝብ ይራቅ መጪው አዲስ ዓመት ይባረክ፤ የተዘራው ዘር ለፍሬ እንዲሆን ጠላት ዲያብሎስ ያፍር ዘንድ ይማጸናሉ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!