ወርኃ ጥርና የወጣቶች ሕይወት

ዲ/ን ወልደ ቂርቆስ ደሳለኝ

የወጣትነት ምንነትና ፈተናዎቹ

በዚህ ጽሑፍ የወጣትነት ምንነት፣ መገለጫዎች እና ተግዳሮቶቹ ላይ ትኩረት አድርገን እንመለከታለን፡፡ ወጣትነት ፈጣን፣ አካላዊ፣ ስሜታዊና ማኅበራዊ ለውጦች የሚሰተናገዱበት ከልጅነት ወደ ጎልማሳነት፣ ከጥገኝነት ራስን ወደ መቻል መሸጋገሪያ ድልድይ የሆነ የዕድሜ ክልል ነው፡፡ እነዚህን ለውጦች ተክትሎ በወጣቶች ጠባይ (ባሕርይ) ላይ የሚከሠቱ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፡- ከፍተኛ የሆነ የአቻ ግፊት ተጋላጭነት፣ የሥጋዊ ፍትወት ፍላጎትና ግፊት፣ ከመጠን ያለፈ ግትርነትና ግልፍተኝነት፣ የስሜት መለዋወጥ፣ ቀድሞ ለመረዳት፣ አስቸጋሪ የሆኑ አስተሳሰቦች እና አመለካከቶች፣ ወላዋይነትና ውሳኔ ለመወሰን መቸገር፣ ለፍልስፍና ብሎም ለማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ትልቅ ትኩረት መስጠት፣ ራስን ከሌሎች የዕድሜ አቻዎች ጋር ማወዳደርና ማነጻጸር፣ ከቤተሰብ ብሎም ከሌሎች በዙሪያቸዉ ካሉ ታላላቆች ቊጥጥር ተላቆ ነጻ የመውጣት ፍላጎት፣ ራስን የመቻል ከፍተኛ ፍላጎት ወዘተ ናቸው፡፡
ከላይ በተዘረዘሩት ማለትም ወጣትነት በራሱ ከሚያመጣቸው ፈተናዎች ወይም ተግዳሮቶች ምክንያት የዕድሜ ክልሉን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ነው አበው ወጣትነት ከዐራቱ ባሕርያት መካከል የእሳትነት ባሕርይ የሚያይልበት ነው ብለው የሚያሰተምሩን፡፡ ከዚህ በላቀ ደግሞ የወጣቶች አካባቢያዊና ቤተሰባዊ ተፅዕኖ ችግሮቹን የበለጠ አባብሶ የወጣቶችን ቀጣይ ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል፡፡
ወርኃ ጥር በሀገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን “ለሁሉም ጊዜ አለው፤ ከፀሐይ በታችም ለሆነው ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፡፡” (መክ.፫፥፩) የሚለውን መሠረት አድርጋ ዘመናትን በተለያዩ አዕዋዳት እና አቅማራት ከፋፍላ ከማስቀመጥና ከማሳወቅ ባለፈ የሀገራችንን የተፈጥሮ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ በየክፍለ ዓመቱ (ወቅቶች) ሊከናወን የሚገባውን ተግባር በመዘርዘር በአበው ሊቃውንት አማካይነት በቃልና በጽሑፍ ትመክራለች፤ ታስተምራለችም፡፡ ምእመናንም ይህንን ድንቅ ትምህርት ተከትለው ለመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ማከናወኛ የሚሆኑትን ጊዜያት በወቅት በወቅት ከፍለው ይጠቀሙበታል፡፡
በአብዛኛው የሀገራችን ክፍል በወርኃ ጥር ክብረ በዓላት በደመቀ ሁኔታ የሚከበሩበት (ከበዓለ ልደት ጀምሮ ጥር ፲፩ በዓለ ጥምቀት፣ በበርካታ አድባራትና ገዳማት ዓመታዊ ክብረ በዓላት በተለያዩ ቀናት በአማረና በደመቀ ሁኔታ መከናወኑ)፣ እንዲሁም በርከት ያሉ የማኅበራዊ ጉዳዮች በስፋት የሚከናወኑበት ወራት ነው፡፡
በእነዚህም ምክንያት በወርኃ ጥር ወጣቶች መንፈሳውያን ነን የሚሉትም ሳይቀሩ ለተለያዩ ፈተናዎች ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “አንተ የዕውሮች መሪ በጨለማም ላሉት ብርሃን እንደሆንህ በራስህ የምትተማመን ከሆንህ ሰነፎችን ልባሞች የምታደርግ፣ ሕፃናትን የምታስተምር፣ ጻድቅና የምትከብርበትን የኦሪትን ሕግ የምታውቅ የምትመስል እንግዲህ ሌላውን የምታስተምር ራስህን ለምን አታስተምርም” (ሮሜ፪፥፲፱-፳፩) በማለት እንዳስተማረን አስቀድመን ራሳችንን በፈተና ከመውደቅ ልንጠብቅ ይገባናል፡፡
በዚህ ጽሑፍ መንፈሳውያን ወጣቶች ከሌላው ጊዜ በበለጠ በጥር ወር ከሚከበሩ በዓላት ጋር ተያይዞ ጥንቃቄ ሊያደርጉባቸውና ራሳቸውን በፈተና ተሰናክለው ከመውደቅ ይጠነቀቁ ዘንድ መሠረታዊ ጉዳዮችንና የመፍትሔ ሐሳቦችን ጠቅለል አድርገን እንመለከታለን፡፡
ችግሮቹ
፩. ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማፈንገጥ
ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ለሚከናወን ማንኛውም ተግባር ቅዱስ መጽሐፍን፣ ትምህርተ አበውን እና መንፈሳዊውን ትውፊት አብነት በማድረግ ሕገ ደንብና ሥርዓትን በዝርዝር አስቀምጣለች፡፡ ለዚህም ነው ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያንን ስንዱ እመቤት በማለት የሚጠሯት፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ምሉዕ እና ስንዱ እመቤት ከሚያሰኟት ሀብቶቿ አንዱና ዋነኛው ደግሞ ስለ በዓላት አከባበር ያስቀመጠችው ዝርዝር ሥርዓት ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ወጣቶች በአፍላ ስሜታዊነት እና በሉላዊነት (ዘመናዊነት) ተጽእኖ ምክንያት በታላላቅ መንፈሳውያን በዓላት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ብሎም ከሀገር ባሕልና ወግ ያፈነገጡ መጥፎ ድርጊቶች በዓላትን በማሳመርና በማድመቅ ሰበብ ሲያከናውኑ እንታዘባለን፡፡ በዓላት በቤተ ክርስቲያን የራሳቸው ነገረ ሃይማኖታዊ ትርጓሜና ትውፊታዊ ሥርዓት አላቸው፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወጣቶች ከበዓላቱ ምንነትና ትርጓሜ ይልቅ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወደ ስሕተት እየወሰዱና መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ፈተና ላይ የሚጥሉ ጉዳዮቸ ላይ ትኩረት ሲያደርጉ እንመለከታለን፡፡
ከእነዚህም መጥፎ ልማዶች መካከል፡- ያልተገባና ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ከዚያም አልፎ ከሀገር ባሕል ያፈነገጡ አለባበሶች፣ የበዓላቱን ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጥቅም ከመመልከት ይልቅ ምድራዊና ባሕላዊ ጠቀሜታቸው ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ላይ ያዘነብላሉ፡፡ ለመንፈሳዊ ሱታፌ እና ለሰማያዊ በረከት ከመትጋት ይልቅ በዓይነ ሥጋ ብቻ አይቶ መደሰትን፣ በልቶ፣ ጠጥቶና ጨፍሮ መዝናናትን ዓላማ አድርጎ ወደ ክብረ በዓላቱ መምጣት፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የሚከተሉ ምእመናንን ከመንፈሳዊ ተመስጦ ማስወጣት፣ እንዲሁም ራሳቸውን ወደ ሥጋዊ ሐሳብና ዝሙት የሚመሩ ብሎም ለኃጢአት የሚያነሳሱ ዘፈንና ጭፈራዎች መብዛት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሌላው በወርኃ ጥር በወጣቶች መንፈሳዊ ሕይወት ላይ የምንመለከተዉ ፈታኝ ችግር የአንዳንድ ወጣቶች “የድሮውን ዘመን አስብ፤ የልጅ ልጅንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ ይነግርህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፤ ይተርኩልህማል፡፡” (ዘዳ.፴፪፥፯) እንዲል መጽሐፍ የአበው መምህራንን ምክረ ቃልና ትእዛዝ በማዳመጥ በመንፈሳዊ ብስለትና ቀናዒነት ከማገልገል ይልቅ በስሜት፣ በማን አለብኝነትና በግልፍተኝነት ለማገልገል መነሳት ነው፡፡ ይህም ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ወደ ማፍረስና እና እኔ ብቻ ያልኩት ካልሆነ በሚል አኩራፊነት ስሜት ብዙ ወጣቶችን ከቤተ ክርስቲያን እያሸሸ ይገኛል፡፡ ከዚህ ይልቅ “የሰው ወርቅ አያደምቅ” እንዲሉ አበው የሌላውን ከመናፈቅ ለራስ ሀብትና ሥርዓት ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
፪. ከመጠን ያለፈ ምግብና መጠጥ
ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ደጋግሞ ካነሳችው ምክር አዘል ጉዳዮች አንዱ በመጠን ስለ መኖር ነው፡፡ “ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቧል፤ እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ” (፩ኛ ጴጥ ፬፥፯፤፰፥፭) እንዲል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ነገር ሁሉ በአግባቡና በመጠኑ ይሆን ዘንድ ዘወትር ትመክራለች፤ ታስተምራለች፡፡ እርግጥ ነው የሰው ልጅ ለቁመተ ሥጋ ምግብ ይመገብ ዘንድ ግድ ነው፡፡ ነገር ግን መብላት፣ መጠጣት ከመጠን ባለፈ ጊዜ በመጀመሪያ ድኃ ወገናችንን ያስረሳል፤ ከዚያም ከፍ ሲል ራስን ያስረሳል፤ ከሁሉም በላይ ግን በመጠን አለመኖር የእግዚአብሔርን ሀልዎት ያስዘነጋል፡፡ ሕዝበ እስራኤል ከዚያ ሁሉ ውለታና ስጦታ በኋላ የሊቀ ነቢያት ሙሴን ወደ ደብረ ሲና መውጣት ተከትሎ ከፈርኦን የባርነት ቀንበር ያወጣቸውን፣ ባሕር ከፍሎ ያሻገራቸውን አምላክ ረስተው ጣዖት አስቀርጾ ወደ ማምለክ የወሰዳቸው ከመጠን ያለፈ ምግብና መጠጥ መሆኑን መጽሐፍ መዝግቦልናል፡፡ (ዘፀ. ፴፪፥፩-፮)፡፡
በዘመናችን በተለይም በወርኃ ጥር ለክብረ በዓላት፣ ለጋብቻና ለሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች የሚዘጋጁ ግብዣና ድግሶችን ተከትሎ አንዳንድ ምእመናን በተለይም ወጣቶች በመጠን ኑሩ ያለውን የሐዋርውን ምክረ ቃል በመዘንጋት ራሳቸውን ለዓለም ፈተና አሳልፈዉ ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ እንዲያውም “ዐሥር ጊዜ ካልበሉ፣ ጠጥተውስ ካልሰከሩ የት አለ ዓመት በዓሉ” የሚል ብሂልም ያለማቋረጥ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ይልቅ “እጅግ ለሰበሰበ አልተረፈውም፣ ጥቂትም ለሰበሰበ አልጎደለበትም፡፡” (ዘፀ፲፮፥፲፯) ተብሎ እንደተጻፈ አብዝተን በልተን ከእግዚአብሔር ጋር ከመጣላት ሁሉንም በመጠን ማድረግ አንዱ የክርስትና መገለጫ ነው፡፡
፫.ለባዕድ ልማዶችና ሱሶች ተጋላጭነት
በወርኃ ጥር ለወጣቶች ፈተና ከሚሆኑ ታላላቅ ጉዳዩች መካከል አንዱና ዋነኛው ደግሞ ለባዕድ ልማዶችና ሱሰኝነት መጋለጥ ነው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ወጣቶች መጤ ልማዶችንና ሱሰኝነትን የሚቀላቀሉት ወይም የሚጀምሩት በማኅበራዊ ጉዳዮች ምክንያት የሚዘጋጁ እንደ ሠርግ ያሉ የበዓላት ግብዣና ድግሶች ላይ ነው፡፡ በአቅራቢያችን ያሉ በሱስ የተጠመዱ ወጣቶችን ወደ አልኮል፣ ጫት፣ ሺሻ ወይም ሐሺሽ መጠቀምን እንዴት እንደገቡ ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ ይኸው ነው፡፡
በዘመናችን ከማኅበራዊ ሚድያ ማደግና ከቴክኖሎጂ መዘመን ጋር ተያይዞ የዓለም ሀገራት አንድ መሆንና ልማዶች መወራረስ መጀመራቸውን መመልከት ይቻላል፡፡ ለዚህም ከጋብቻና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚወራረሱ ልማዶች ትልቅ ማሳያ ናቸው፡፡ በሀገራችንም ነባሩ ባሕላዊው፣ መንፈሳዊውና ትውፊታዊው የጋብቻ ሥርዓት (ሠርግ) እየተዘነጋ አልያም እየተበረዘ የጥንት ማንነትና ትርጉሙን እያጣ ይገኛል፡፡ በተለይ ወጣቶች ከመንፈሳዊውና ባሕላዊው ሥርዓት ይልቅ ለምዕራባውያን የሠርግ ሥርዓቶች ትኩረት በመስጠት መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ራሳቸውን ሲከቱ ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት ወጣቶች ለጊዜው ነፃነትና ዘመናዊነት የሚመስሉ፤ ነገር ግን ሙሉ ሕይወታቸውን አሰናክለው፣ ንጽሕናቸውንም አጉድፈው ለከባድ ውድቀት ለሚዳርጉ ጎጂ ሱሶችና ልማዶች ተጠጋላጭ ይሆናሉ፡፡
፬.መጠጥ፣ ጭፈራ፣ ስካርና ዝሙት
ከላይ የተጠቀሱት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያፈነገጡ ልማዶች ባስከተሉት ተጽዕኖ ምክንያት ብዙ ወጣቶች በወርኃ ጥር በሚደረጉ መርሐ ግብሮች ወደ መጠጥ፣ ጭፈራ ብሎም ለስካርና ዝሙት ኃጢያት ይጋለጣሉ፡፡ በሉላዊነት ተፅዕኖ ምክንያት ሠርግን ከመሰሉ ታላላቅ ግብዣዎች አልኮል አለመጠጣት ጠጥቶም አለመስከርና ራስን አለመሳት፣ ከዚያም ከፍ ሲል ዝሙት አለመፈጸም በወጣቶች ዘንድ ያለመዘመንና የኋላ ቀርነት መገለጫ ተደርገው መወሰድ ጀምረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጠንካራ መንፈሳውያን ወጣቶች ሳይቀር ከዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር ለመመሳሰል በሚል ሰበብ ሕይወታቸውን ወዳልተገባ አቅጣጫ ሲመሩና ተሰናከለው ሲወድቁ መመልከት የዘወትር ገጠመኛችን ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
፭.ግጭትና ጠብ
በሌላ በኩል በወርኃ ጥር በሚከናወኑት ተደጋጋሚ የአደባባይ በዓላትና የሠርግ መርሐ ግብሮች መነሻነት ወጣቶችን የሚፈትነው ተግዳሮት ድንገታዊ ግጭት እና ጠብ ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት ባለው የሀገራችን የሰላምና የፖለቲካ አለመረጋጋት ወጣቶች በጭፍን ጥላቻ፣ በአፍላ ስሜታዊነትና በተዛባ መረጃ ተገፋፍተው ወደ ጠብ፣ ግርግር እና ግጭት የመግባት ዕድላቸው ከሌላው ጊዜ እጅግ የሰፋ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳድ ወጣቶች ለበዓለ ጥምቀት በሚወጡበት ጊዜ አስበውና ተዘጋጅተው ስለታም ነገሮችንና ባልንጀራቸውን የሚቀጠቅጡበት በትር (ዱላ) ይዘው ሲወጡ ስናይ በእውነቱ ታቦተ ሕጉን አጅበውና አክብረው በረከተ ሥጋ ወነፍስ ለማግኘት ሳይሆን ጦር ሜዳ ወርደው የሀገርን ዳር ድንበር የደፈረ ጠላትን ለማውደም ቆርጦ የተነሣ የጦር ሠራዊት ይመስላሉ፡፡ ይህ የጠብና ግርግር አጫሪነት ልማድ የሚለበሱ ቲሸርቶች ላይ ከሚያስቀምጡት ኃይለ ቃል ይጀምርና በሚጨፈረው የባህል ጭፈራ ዓይነትና የግጥም ይዘት ይቀጥላል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ሲታዩ ቀላል ቢመስሉም በጽሑፋችን መግቢያ ላይ ያነሳናቸውን የወጣትነት መገለጫዎች ጋር አያይዘን ለመረዳት ከሞከርን ከደረቅ ሣር ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ እሳት ከመልቀቅ ይልቅ የከፋ ነው፡፡
መፍትሔዎች
ሀ/ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በአግባቡ መረዳት
ወጣትነት ከተጠቀምንበት ብዙ ኃይል፣ ትልቅ ተስፋ የአገልግሎት ትጋት ያለበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ለማስገንዘብ “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” (መክ.፲፪፥፩) እያለች ዘወትር ታስተምራለች፡፡ ብዙ ወጣቶች ይህንኑ የጠቢቡን ምክር በመከተል የወጣትነት ዘመናቸውን ለቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በሰ/ት/ቤቶች በጽዋና የጉዞ ማኅበራት በመሰባሰብ ለቤተ ክርስቲያን በጎ ስጦታ ሲያበረክቱ ይስተዋላል፡፡
ነገር ግን በዘመናችን አንዳንድ ወጣቶች በቀናዒነት ተነሣስተው የሚያደርጓቸው ድርጊቶች ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ(ዶግማ) እና ሥርዓት (ቀኖና) የሚጣረሱና አንዳንዴም ከጥቀማቸው ጉዳታቸው የሚያይል ይሆናል፡፡ ይህም የሚመጣው በዋነኛነት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ተምሮና መርምሮ ካለማወቅ ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎታችን “ያላዋቂ ሳሚ …” እንደሚሉት ተረት እንዳይሆንብን ጥረታችንም እግዚአብሔርን የሚያስደስት ቤተ ክርስቲያንንም የሚጠቅምና ራስንም የሚያንጽ እንዲሆን አካሄዳችንን ሁሉ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የተቃኘ ማድረግ ይገባናል፡፡ ወጣቶች ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በልማድና በወሬ ሳይሆን መጻሕፍትን በማንበብና መምህራንን በመጠየቅ ራሳቸውን ከጥፋት መታደግ ይኖርባቸዋል፡፡
ለ/ ከስሜታዊነት ወጥቶ በመንፈሳዊ ብስለት ማገልገል
ወጣትነት ስሜታዊነትና ችኩልነት የሚጨምርበት እርጋታና ማገናዘብ የማይታይበት ወቅት ነው፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ለአገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ ከሚገጥማቸው ትልቅ ፈተና አንዱ ስሜትን ተቈጣጥሮ ራስን ገዝቶ ዝቅ ብሎ በትሕትናና በታዛዥነት ማገልገል አለመቻል ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት ውጤታማ የሚሆነው መንፈሳዊ በሆነ አገልጋይ ሲከናወን ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልጋይ ደግሞ አርምሞን፣ አስተዋይነትንና ታዛዥነትን ገንዘብ ያደረገ እንጂ በአጋጣሚዎች ሁሉ በስሜት ተገፋፍቶ ወደ ግጭትና ግርግር የሚያመራ አይደለም፡፡ ስለዚህ ወጣቶች በተለይ በዚህ በወርኃ ጥር በሚኖራቸው መንፈሳዊ ሱታፌ ቤተ ክርስቲያንን እንጥቀም:: እኛም ለበረከት እንብቃ ካሉ አገልግሎታቸውን በስሜትና በችኮላ ሳይሆን በመንፈሳዊ ብስለት፣ በትሕትናና በታዛዥነት የተዋጀ ሊያደርጉት ይገባል፡፡
ሐ/ ከመጥፎ የአቻ ግፊት መጠበቅ
የወጣትነት የዕድሜ ክልል የአቻ ግፊት የሚያይልበት፣ ከቤተሰብ የነበረን ቅርበትና ቁርኝት እየላላ ለዕድሜ አቻዎቻችን ያለን ቅርበት የሚጨምርበት ነው፡፡ በዚህ የዕድሜ ክልል ስንሆን ምሥጢሮቻችንና ወሳኝ የምንላቸውን ጉዳዮች ለቤተሰብ ከመንገርና ከማማከር ይልቅ ለዕድሜ ጓደኞቻችን ማጋራት ትልቅ ደስታ ይሰጠናል፡፡ ስለሆነም በዚህ ወቅት ወጣቶች በራሳቸው አስበውና አገናዝበው ከሚወስኗቸው ውሳኔዎች ይልቅ በጓደኞቻቸው ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ግፊት(ጫና) ተገፋፈተው የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ በዘመናችን የሀገራችን በርካታ ወጣቶች በዕድሜ እኩያቸው ግፊት ከቤተ ክርስቲያን እየሸሹ፣ ከመንፈሳዊነት እየወጡ ወደ ዝሙትና ሱሰኝነት ሲወሰዱ እንመለከታለን፡፡ በዚህ በወርኃ ጥር ከላይ በዘረዘርናቸው ነገሮች ምክንያት ወጣቶች ከቤተሰብ ተለይተው በጋራ ሆነው የሚዝናኑባቸውና ለኃጢአት የሚጋለጡባቸው አጋጣሚዎች የበዙ ናቸው፡፡
ወጣቶች በቅድሚያ አብረዋቸው የሚውሉ ጓደኞቻቸውን ከመንፈሳዊና ትምህርታዊ ዓላማቸው አንጻር ሊፈትሹና ሊመርጡ ይገባል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ በባልንጀራቸው ምክንያት የተጠቀሙ እንደተገለጹት ሁሉ በመጥፎ ባልንጀራቸው ምክንያት ወደ ክሕደትና ኃጢአት ያመሩ ሰዎች ጉዳይም በስፋት ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ ስለዚህ ወጣቶች ባልንጀራዬ ማነው? ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይገባቸዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጓደኞቻቸውን መምረጥ እንኳን ቢከብዳቸው መጥፎ የአቻ ግፊትን በመከላከል ለፈቃደ እግዚአብሔር እና ለሕይወት ግባቸው ቅድሚያ በመስጠት በንቃትና በቆራጥነት ለመጥፎ ተጽዕኖዎች አይሆንም እምቢ ማለትን ሊለማመዱ ይገባል፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ምስለ ጻድቅ ትጸድቅ ወምስለ ብእሲ ንጹሕ ንጹሐ ትከውን ወምስለ ጠዋይ ትጠዊ፤ ከጻድቅ ሰው ጋር ጻድቅ ትሆናለህ፤ ከቅን ሰው ጋርም ቅን ትሆናለህ፤ ከንጹሕ ሰው ጋር ንጹሕ ትሆናለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ትሆናለህ፡፡” (መዝ፲፯፥፳፬) በማለት እንዳስረዳን ማንኛውም ሰው ውሎውን ካላስተካከለ አወዳደቁ የከፋ ይሆናልና ጓደኞቻችንን መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ በጓደኛ ተጽዕኖ ሕይወታቸው የተበላሸባቸው በርካታ ምሳሌዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከነዚህም መካከል አምኖን ከኢዮናዳብ ጋር፣ ሶምሶን ከደሊላ ጋር ያደረጉት ጓደኝነት ሕይወታቸውን እንደጎዳው ተጠቃሽ ነው፡፡
መ/ ምን አለበት ከሚል አስተሳሰብ መጠንቀቅ
ሌላው ወጣቶች በወርኃ ጥር ፈታኝ የሆኑ ተግዳሮቶችን በድል ለመወጣትና ከውድቀት ለመዳን ሊያደርጉት የሚገባ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ወደ ጥፋት ጎዳና የሚመራቸው የውሳኔ አሰጣጥ ክህሎት ማነስ ወይም መዳከም ነው፡፡ ይህ ክህሎት ከአስተዳደጋችን፣ ከትምህርት ግብዓት ብሎም ከንባብ ሕይወታችን ጋር የተያያዘ ነው ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አስተሳሰባችንና አመለካከታችን በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ በድኅረ-ሥልጣኔ ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ላይ ጎልተው የሚታዩት ”ምን አለበት” ምን “ችግር አለው” እና “ልሞክረው” ዓይነት አመለካከቶች ውሳኔዎችን ከራሳችን ይልቅ ሌሎች ሰዎች በተጽዕኖ እንዲወስኑ ትልቅ መንገድ ከፋች ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አመለካከቶች የአፍላ ወጣትነት ዕድሜም ላይ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ወደ ጥፋትና ውድቀት ሲወስዱ ይስተዋላል፡፡ ስለዚህ ምን አለበት፣ ሞት አለበት ነውና ወጣቶች ራሳቸውን ከዚህ ዓይነት አመለካከት ሊጠብቁ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ ወጣቶች በዚህ በወርኃ ጥር ራሳቸውን ለጽድቅና ለመንፈሳዊ በረከት የሚያበቁባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ቢሆኑም ፈተናዎችም የሚበዙበት ወቅት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ወቅት ወጣቶች በመንፈሳዊ ብስለትና በማስተዋል ከተጓዙ የወጣትነት ዘመናቸውን እንደ ዮሴፍና ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለድል አክሊል ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በስሜትና በትዕቢት እንዲሁም ባለማስተዋል ከተጓዙ ወጣትነታቸው በሕይወታቸውን ለጉዳት አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡ ወጣቶች ከእንደዚህ ዓይነት ጥፋት ይድኑ ዘንድም የቤተ ክርስቲያን አባቶች መምህራን የሰ/ት/ቤት አባላትና አመራሮች እንዲሁም ቤተሰብ ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ ሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት ቁ.9 ጥር 2011 ዓ.ም.