ወርኃ ጥር

ጥር ፩፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ቀኑ ዐሥር ሰዓት ሲሆን ከዚህ በኋላ ሌሊቱ እየጨመረ ይሄዳል። ጥር የሚለው ስያሜ “ጠር፣ ጠይሮ፣ ጠየረ፣ ጠሪእ፣ (ጠርአ፣ ይጠርእ፣ ጸርሐ) ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጒሙም “መጥራት፣ መጮኽ፣ አቤት ማለት” ነው፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፭፻፲) ጥር የወር ስም ሆኖ በታኅሣሥ ወር እና በየካቲት ወር መካከል የሚገኝ፣ ከዐሥራ ሦስቱ ኢትዮጵያ የወራት አቆጣጠር ውስጥ አምስተኛው ነው።

በዚህም ወር ዘመነ አስተርእዮ ይታሰባል፤ አስተርእዮ በጥሬ ትርጉሙ “መገለጥ” ነው፤ ይህም ወቅት በዋናነት ስውር የነበረ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት፣ ሰማያዊ አምላክ በኩነተ ሥጋ ለድኅነተ ዓለም ሲል በዚህ ዓለም የተገለጠበት፣ ሰማያዊ ምሥጢርም የታየበት ድንቅና ልዩ ዘመን ነውና እንዲህ ተብሎ ተጠራ።

ዘመነ አስተርእዮ (የመገለጥ ዘመን) የምንለው ከጌታችን ጥምቀት አንሥቶ እስከ ዐቢይ ጾም ቅበላ ድረስ ከጥር ፲፩ ቀን እስከ መጋቢት ፫ ቀን ድረስ ያለውን ጊዜ ነው። በዚህ ዘመን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት መካከል ልደቱና ጥምቀቱ፣ ከንዑሳን በዓላት ደግሞ ግዝረትና ቃና ዘገሊላ ይታሰባሉ። ከእነዚህ በዓላት በተጨማሪ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሰማያት ላሉ ነፍሳት መገለጧም ይታሰባል። በዚህም ወቅት ውስጥ በዋናነት ሦስት አዝማናት ይገኛሉ፤ እነርሱም ዘመነ ልደት፣ ዘመነ ጥምቀት እና ዘመነ መርዓዊ የሚባሉት ናቸው። በእነዚህም በሦስቱ አዝማናት ውስጥ ጎልቶ የሚታየው አንዱ ዐቢይ ጉዳይ ትሕትና ነው።

ዘመነ ልደት
ሰማያዊ አምላክ በቅዱሳን አዳም ወሔዋን በደል ምክንያት የሞት ሞት ፍርድን ከፈረደ በኋላ አበ ኲልነ (የሁላችን አባት) ቅዱስ አዳም እግዚአብሔር አምላኬን በደልሁ አሳዘንሁ ብሎ መላ ዘመኑን በእንባ አሳለፈ። የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትም በትርጓሜያቸው ሲናገሩ ‹‹አልቦቱ ለአዳም ካልዕ ኅሊና ዘእንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢአቱ››፣ ‹‹አዳም ስለ ኃጢአቱ ከማንባት በቀር ምንም ምን ሌላ ሐሳብ አልነበረውም››

አስፋፍተውም ሲነግሩን፣ አዳምን የቤተ ፈት ልማድ አላገኘውም ይሉናል። ቤተ ፈት፣ በዚህ ጊዜ እበላ እጠጣ፤ በዚህ ጊዜ ተድላ ደስታ አደርግ ነበር እያለ ያዝናል፤ አባታችን ቅዱስ አዳም ግን ጌታዬን አሳዘንሁት፤ በደልሁት እያለ እንባው ሲያልቅ እዥ፣ እዥም ሲያልቅ ይቡስ (ደረቅ) እስኪሆን ድረስ አልቅሷል። በዚህም ጽኑዕ እንባው ምክንያት እግዚአብሔር አምላካችን ኹላቸው ቀደምት አበው ተስፋ አድርገው ሲጠብቁት የኖሩትን “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ”፣ ”ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” ብሎ ቃል ኪዳንን ሰጠው። በዚህም ቃል ኪዳኑ መሠረት ከዕለቷ ዕለት ከሰዓቷም ሰዓት ሳያጎድል በወርኃ ታኅሣሥ በቤተልሔም በከብቶች በረት ውስጥ ተወለደ።
ሰው ቀድሞ ከክብሩ የተዋረደበት ምክንያት ትዕቢት እና እኔ አውቃለሁ በማለት መሆኑን አንድ የቤተ ክርስቲያናችን የጥንት መጽሐፍ ይነግረናል። ይኸውም ማለት፣ እግዚአብሔር ቀድሞ ትእዛዝ ሲያዘን አትብሉ፤ ከበላችሁ የሞት ሞትን ትሞታላችሁ ብሎ ነበር። ሰው ግን በምክረ ከይሲ ሲስት ብበላው አልሞትም፤ አምላክ እሆናለሁ እንጂ ብሎ በመታጀር፣ ከእግዚአብሔርም ይልቅ ስለ እኔ የሚጠቅመኝን እኔ አውቃለሁ በማለት ሳተ። በዚህም እግዚአብሔርን እንደነፈገው አድርጎ ቆጠረ። ይህም ከፍጹም ተዋርዶ እና ሞተ ነፍስ አደረሰው። ጌታችንም በቃል ኪዳኑ መሠረት በመታጀር የወደቀውን ለማንሣት ሲል በትሕትና፣ በአውቃለሁ ባይነት የወደቀውን በአላውቅም ባይነት በፍጹም ትሕትና ተወልዶ ፍጹም ካሣን ካሠለት።

ይህ ትሕትና የነገረ ድኅነት መሠረት እንደሆነ የምናስተውልበትን አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ንጽሕት ቅድስት ድንግል እመቤታችንን እናስባታለን። ቀዳሚት ሔዋን በገዛ ልቡናዋ ምክር ተመርታ በደል ብትበድልና ድንግልናዋን በጥንተ ተፈጥሮ የተሰጣትን ንጽሐ ጠባይዕ ብታሳድፍ፣ ዳግሚት ሔዋን እመቤታችን የእርሷን የጥንተ ተፈጥሮ ንጽሐ ጠባይዕ ሳያድፍባት በመገኘት በንጽሕናዋ መዓዛ፣ ኃያል ወልድን ከልዑል ዙፋኑ ሳበችው። ሊያበሥራትም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ሲላክ በትሕትና ተነጋገረችው። “እነሆኝ የጌታ ባሪያ” ብላም በፍጹም ትሕትና የመልአኩን ብሥራት ተቀበለች። ከወለደችውም በኋላ የሚኾነውን ገቢረ ተአምር ኹሉ እያየች የአምላክ እናት ነኝ’ኮ ብላ አልታበየችም።
ይልቁንስ ሁሉንም እያየች በልቧ ትጠብቀው ነበር እንጂ። በስደት ተሰዳ እንዲያ በውኃ ጥም፣ በረኃብ፣ በጭንቅ ስትሠቃይ፣ እርሷ ግን እንኳን የአምላክ እናት ሆኜ ይህ ሁሉ ይደርስብኛል አላለችም። ይልቅስ መከራዋን ሁሉ በጽኑዕ ትዕግሥት ታገሠች እንጂ። በዚህም ቀድሞ በትዕቢት የፈረሰውን ንጽሕና አጽንታ ይዛ ተገኘች።

ይህም ብቻ ሳይሆን በበደል ምክንያት ያስወሰድናትን ልጅነታችንን ለመመለስ ጌታችን ካህኑን ወደ እርሱ አስመጥቶ ሳይሆን ራሱን ዝቅ በማድረግ ወደ ባሪያውና ወደ አገልጋዩ ዮሐንስ በመሄድ በፍጡሩ እጅ ተጠመቀ። በዚህም ፍጹም ትሕትናውን አሳየን። ይህ የተደረገው ታዲያ ክርስትናን በትሕትና መሥርቶ ለእኛ በመስጠት እኛም ሕይወታችንን ከትሕትና ውጪ እንዳንመራ ለማሳሰብ ነው። ሰው ራሱን ዝቅ በማድረግ እና እኔ መች አውቃለሁ በማለት በፍጹም ትሕትና ከልቡ የሚኖር ከሆነ የኃጢአት መግቢያው ትልቁ ደጅ ተዘጋ ማለት ነው። እንኪያስ የቸር ጌታችንን መገለጥ ስናስብ ፍጹም ትሕትናን ገንዘብ አድርገን ለማክበር ልንደክም ይገባል።

ዘመነ ጥምቀት
በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ከምናገኛቸው በዓላት አንዱ ዘመነ ጥምቀት ነው። ይህም በበደል ምክንያት ያስወሰድናትን ልጅነታችንን ለመመለስ ካህኑን ወደ እርሱ አስመጥቶ ሳይሆን ራሱን ዝቅ በማድረግ ወደ ባሪያውና ወደ አገልጋዩ ዮሐንስ በመሄድ በፍጡሩ እጅ ተጠመቀ። በዚህም ፍጹም ትሕትናውን አሳየን። ይህስ ስለምን ሆነ ቢሉ ይህ የተደረገው ክርስትናን በትሕትና መሥርቶ ለእኛ በመስጠት እኛም ሕይወታችንን ከትሕትና ውጪ እንዳንመራ ለማሳሰብ ነው። ሰው ራሱን ዝቅ በማድረግ እና እኔ መች አውቃለሁ በማለት በፍጹም ትሕትና ከልቡ የሚኖር ከሆነ የኃጢአት መግቢያው ትልቁ ደጅ ተዘጋ ማለት ነው። እንኪያስ የቸር ጌታችንን መገለጥ ስናስብ ፍጹም ትሕትናን ገንዘብ አድርገን ለማክበር ልንደክም ይገባል።

ዘመነ መርዓዊ
ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን ይህም ጥር ፲፪ ቀን ይውላል፡፡ በዓሉ መከበር የነበረበት የካቲት ፳፫ ነበር፤ ነገር ግን የካቲት ላይ ጾም ስለሚሆን “የውኃን በዓል ከውኃ ጋር” ሲሉ ሊቃውንት ጥር ፲፪ ቀን አደረጉት፡፡
በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ከምናገኛቸው በዓላት ወይም ወቅቶች ውስጥ አንዱ ዘመነ መርዓዊ ነው። ይህ ወርኅ የሚደንቀው ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ከሠራቸው ገቢረ ተአምራት አንዱ የሆነውን የቃናውን ተአምር የምናስብበት ወቅትም ጭምር ነው። ከዘመነ አስተርእዮ ጋር አንድ አድርገን እንድናከብረው የሚያደርገንም አምላክነቱን በግልጥ ያሳየበት ግሩም ተአምር በመሆኑ ነው። የቃናውን ሠርግ ስናስብ በቃና የተደረገው ተአምር እንደ ቀላል ተናግረን የምናልፈው አይደለም፤ በውስጡ ብዙ ምሥጢር የታየበት ነውና። ከሁሉ ከሁሉ ግን፣ የቃናውን ሠርግ ቤት ታሪክ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈልን መጽሐፍ እንዲጻፍ ምክንያት የሆነው ምን እንደኾነ ስንጠይቅ ‹‹ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ››፣ ‹‹የጌታ ኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች›› የሚለው እንደሆነ እናስተውላለን። ይኸውም ደግሞ በእመቤታችን መኖር ሰው በሕይወቱ የሚያገኘው በቊዔት እንዴት ያለ ታላቅ እንደሆነ ይናገራል።

በዚህም መሠረት ይህ የመገለጥ ወቅት ታላቁን ሥውር የነበረውን ምሥጢረ ሥላሴን ያወቅንበት የተረዳንበት ታላቅ የምሥጢር ወቅት፣ ከቸር ጌታችን እና ከውድ እናቱ የተማርነውን ፍጹም ትሕትና ገንዘብ በማድረግ የምንደክምበት የተጋድሎ ወቅት መሆኑን እና ከዚህም ሲያልፍ በቤተ ዶኪማስ በቃናው ሠርግ ላይ እመቤታችን ከጌታችን እና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የተገኘችበትን እና ያገኙትን ረድኤት በማሰብ እኛም ቸር ጌታችንን፣ ንጽሕት የአምላክ እናት እመቤታችንን እና ቅዱሳኑን ሁሉ ወደ ሕይወታችን በማስገባት የምናገኘውን የነፍስ ድኅነት በቊዔት (ረብሕ) እናስተውልበታለን። እንኪያስ በዓሉን ስናከብር ይህን ትሕትና ገንዘብ በማድረግ ከመጸለይ እና ከመለመን ጋር ቢሆን ብዙ በረከት የምናገኝበት ይኾናልና በዚህ የመከራ ወቅት አምላከ ቅዱሳን ለሁላችን ትሕትናውን ያድለን፤ አሜን።

በጥር የሚታሰቡ በዓላትም አሉ፤ በእርግጥ እንደ መጽሐፈ ስንክሳር በሁሉም ዕለት የሚታሰቡ ቅዱሳን ቢኖሩም ከእነዚህ በጣም የሚታወቁትን ብቻ እናነሳለን፡፡

፩ኛ ጥር አንድ ቀን የቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሚ ሰማዕት (ዕረፍቱ) ነው፡፡

፪ኛ ጥር ሦስት የአባ ሊባኖስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡

፫ኛጥር አራት ቅዱስ ዮሐንስ /ወንጌላዊ/ወልደ ነጎድጓድ የተሰወረበት ቀን ነው፡፡

፬ኛ ጥር ስድስት ኢየሱስ/ግዝረቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ ግዝረት በመግባት የኦሪትን ሕግ ፈጸመ፤ ልሳነ አረፍተ ሐዋርያው ጳውሎስ ጌታ ክርስቶስ በሥጋው ግዝረትን ተቀበለ ለአባቶች የተሰጠውን ቃል ኪዳንም የፈጸመበት ዕለት ነው፤ እንዲሁም ነቢዩ ኤልያስ የተሰወረበት ቀን ነው።

፭ኛ ጥር ሰባት ቅድስት ሥላሴ፡- በዓለ ቅድስት ሥላሴ በጥር ወር የሚከበረው ስለ ሁለት ምክንያቶች ነው:: ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን፣ሁለተኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው::

፮ኛ ጥር ዐሥራ አንድ በዓለ ጥምቀት በዚች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአጥማቂው ዮሐንስ ዘንድ በዮርዳኖስ ወንዝ በውኃ የተጠመቀበት ነው።
በዚህችም ቀን የአቡነ ሐራ ድንግል የዕረፍታቸው በዓል ነወ፡፡

፯ኛ ጥር ዐሥራ ሁለት በዓለ ቅዱስ ሚካኤል /ቃና ዘገሊላ/ የክብር ባለቤት ጌታችን፣ ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ክፍል በሆነች በቃና በሠርግ ቤት የሠራው የተአምራቱ መታሰቢያ የተደረገባት እና የተአምራቱ መጀመሪያ መታሰቢያ እንድትሆን የቤተ ክርስቲያን መምህራን የሠሯት ቀን ናት።

፰ኛ ጥር ዐሥራ አምስት ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት እየሉጣ ዳግመኛ ለከበረ ሕፃን ቂርቆስ ማኅበር የሆኑ ዐሥራ አንድ ሺህ አራት ሰዎች በሰማዕትነት ያረፉበት ቀን ነው።

፱ኛ ጥር ዐሥራ ስምንት “ዝርወተ አጽሙ” ስትል ቤተ ክርስቲያን የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በዓል አዘክራ ትውላለች፤ በስሙ በታነጹለት አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ታቦተ ሕጉ ውጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል።

፲ኛ ጥር ሃያ አንድ ቀን አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለከበረች ድንግል ማርያም የዕረፍቷ በዓለ መታሰቢያ ነው።

፲፩ኛ ጥር ሃያ ሦስት ቀን አሕዛብ ለሚያስተምር ለከበረ ሐዋርያ ጢሞቲዎስ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው።

፲፪ኛ ጥር ሃያ ስምንት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ቅዱስ አማኑኤል) ተአምራትን በማድረግ ሰባት እንጀራና ሁለት ዓሣ አበርክቶ ለአምስት ሺህ ሰዎች ያበላበት ቀን ነው።

ከበዓላቱ በረከት ይክፈለን!