ወርኃ ነሐሴ
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሐምሌ ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ነሐሴ የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ላይ “ናሴ” ማለት መጨረሻ የመስከረም ዐሥራ ሁለተኛ በማለት ይፈቱታል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝመበ ቃላት ገጽ ፮፻፴፯)
ከሐምሌ ቅዱስ ቂርቆስ አንሥቶ እስከ ሐምሌ አጋማሽ ያለው ወቅት ነጎድጓድ በብዛት የሚሰማበት፣ መባርቅት የሚጮኹበት ወቅት ነው፤ በዚህ ወቅት በጸሎተ ቅዳሴው ከወንጌል በፊት የሚሰበኩት ምስባካት ጊዜውን የሚያወሱ የፈጣሪን ድንቅ ጥበብ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ለአብነት ብንመለከት ‹‹ያዐርግ ደመናተ እምአጽናፈ ምድር፤ ወገብረ መብረቀ ለጊዜ ዝናም ዘያወጽኦሙ ለነፋሳት እመዛግብቲሆሙ (ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል በዝናም ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል፤›› ደመናትን ከጽንፍ ምድር የፈጠረ እርሱ ነው፤ አንድም እስከ ብሩህ ሰማይ ውኃ ሞልቶ ነበርና ለይትጋባእ ማይ ውስተ ምእላዲሁ ብሎ ከሦስት ከፍሎታል፡፡
ምድርም ደም እንደሠረበው ጉበት ሁና ታየች፤ ዐሥራ ሁለቱን ነፋሳት አውጥጦ አስታት ጸጽ አለች፤ በዚህ ጊዜ ከይቡስ ምድር ይቡስ ጢስ ከርጡብ ባሕር ርጡብ ጢስ ወጥቶ አንድ ደመና ሆኗል፤ ‹‹ወገብረ መብረቀ ለጊዜ ዝናም፤ መብረቅን ለዝናም ምልክት አደረገ፤›› እንዲል፡፡ አንድም ለዝናም ምልክት የሚሆን መብረቅን ፈጠረ፤ የመብረቅ ተፈጥሮ እንደምን ነው ቢሉ ውኃው በደመና ተቋጥሮ በነፋስ ተጭኖ ሲመጣ ደመናና ደመና በተጋጩ ጊዜ ከውኃ ይወጣል፤ ‹‹ዘያወጽኦሙ ለነፋሳት እመዛግብቲሆሙ፤ ነፋሳትን ከየሳጥናቸው የሚያወጣቸው እርሱ ነው፡፡››
ለዐሥራ ሁለቱ ነፋሳተ ዐሥራ ሁለት መሳክው አሏቸው፤ በምሥራቅ ስድስት በምዕራብ ስድስት ከዚህ እየመጠነ የሚያወጣቸው እርሱ ነው፤ አንድ ጊዜ የወጡ እንደሆነ ዓለምን የሚያሳልፉ ናቸውና እየመጠነ ያወጣቸዋል፡፡ (ኢዮ.፴፮፣ ኤር. ፲፣፲፫፣ ዮሐ. ፪፣፰፣ መዝ.፻፴፬ መዝሙረ ዳዊት አንድምታ)
‹‹…ምድርን ጎበኘኻት አጠጣሃትም፤ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ፤ እንዲሁ ታሰናዳለህ፤ ትልሟን ታረካለህ፤ ቦይዋን ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ…›› እንዲል ክቡር ዳዊት (መዝ.፷፬፥፱)፡፡ በወርኃ ነሐሴ ከሰማይ ብቻ ሳይሆን ውኃ እንደ ኖኅ ዘመን ከምድርም የሚፈልቅበት እስኪመስል ድረስ ምድር በውኃ ረስርሳ ከሰማይ የወረደው ጠል ከውስጧ ገብቶ በመሙላት ውኃውን ወደላይ የምትተፋበት በመሆኑ ምንጮቿ እጅግ ይበዛሉ፤ በተለይም በወርኃ ነሐሴ አጋማሽ በኋላ የሚፈሰው ጅረት በሐምሌ ወር ይታይ ከነበረው ድፍርሱ ጠርቶ የሚታይበትም ወር ነው፡፡
ከሰኔ ፳፮ ጀምሮ የገባው ክረምት ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ ከሰማይ የሚወርደው ዝናም የሚቀንሰበት ወቅት ነው፤ አበው በብሒላቸው ‹‹ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት›› የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
በወርኃ ነሐሴ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚዘከሩ በርካታ በዓላት አሉ፤ በተለይ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤና ዕርገት አስመልክቶ ከሕፃናት እስከ አረጋውያን ድረስ ሁሉም በጉጉት የሚጠብቀውና የሚጾመው ጾመ ፍልሰታ በዚህ ወር ነው፤ ምእመናን የሞቀና የተመቻቸ አልጋቸውን፣ የደመቀ ቤታቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን ትተው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅጽረ ግቢ ሰሌን አንጥፈው የክረምቱን ዝናም፣ የቀኑን ቅዝቃዜ የሌሊቱን ቁር ታግሠው እመቤታችንን በሱባኤ ሲማጸኑ የሚያሳልፉበት ወር ነው፡፡ በዚህ ወር በሚጾመው ጾመ ፍልሰታ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አናቅጽ ክፍት ሆነው ሌሊት ለሰዓታት፣ ለማኅሌት ነግህ ለኪዳን፣ ረፋድ ለውዳሴ ማርያም ትርጒም፣ ከሰዓት ለቅዳሴ፣ ሠርክ ለጸሎት ምእመናን ይታደሙበታል፡፡
በወርኃ ነሐሴ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ በዓላት
- ነሐሴ ስድስት (፮) ቀን ጌታዋን በዕለተ ዓርብ እስከ ቀራንዮ የተከተለች፣ ውለታ ፍቅሩ ቀስቅሷት በዕለተ ሰንበት በጎልጎታ የተገኘች ከሁሉ ቀድማ ትንሣኤውን ያየች ቅድስት እናታችን መግደላዊት ማርያም የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው፡፡
- ነሐሴ ሰባት (፯) ቀን በዚህች ዕለት ዳግሚት ሰማይ ምሥራቀ ምሥራቃት የፀሐይ ክርስቶስ መገኛ ድንግል ማርያም ቤዛዊት ዓለም ከቅድስት ሐና እና ከቅዱስ ኢያቄም የተፀነሰችበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡
- ነሐሴ ዐሥራ ሦስት (፲፫) ቀን በዚህች ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት፣ የሊቀ ነቢያት ሙሴ ጌታውን የመመልከት ጸሎቱ ምላሽ አግንቶ በደብረ ታቦር ተራራ ከነቢዩ ኤልያስ ጋር የተገኙበት ዕለት ነው፡፡
- ነሐሴ ዐሥራ ስድስት (፲፮) ቀን በዚህች ዕለት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት መታሰቢያ በዓል ነው፡፡
- ነሐሴ ሃያ አራት (፳፬) በዚህች ቀን የጻድቁ አባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የዕረፍታቸው መታሰቢያ በዓል ነው
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!