ወርኃ ኅዳር
ኅዳር ፪፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ሦስተኛው ወር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት “ኅዳር” ተብሎ ይታወቃል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ውስጥ የዚህን ወር ቃል ሲተረጉሙ “ማኅደር” ከሚለው ሥርወ ቃል የወጣ እንደሆነና “ማደሪያ” የሚል ፍቺ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
በቤተ ክርስተያናችን የዘመን አከፋፈል መሠረት ከኅዳር ፮ ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፯ ወይም ፲፫ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምሕሮ ይባላል፡፡ ትርጕሙም በሃሌታው ‘ሀ’ (አስተምህሮ) ተብሎ ሲጻፍ የቃለ እግዚአብሔር ማስተማሪያ (የትምህርተ ወንጌል) ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም “መሀረ፤ አስተማረ” የሚለው የግእዝ ግስ ሲሆን፣ ይኸውም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ ርኅራኄ፣ ትዕግሥትና የማዳን ሥራው በቤተ ክርስቲያን በስፋት የሚሰበክበት ጊዜ ነው፡፡ በሐመሩ “ሐ” (አስተምሕሮ ተብሎ) ሲጻፍ ደግሞ የምሕረት፣ የይቅርታ ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም “መሐረ፤ ይቅር አለ” የሚለው የግእዝ ግስ ነው፡፡ ዘመነ አስተምሕሮ ስለ እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ፤ እርሱ በደላችንን ሁሉ ይቅር እንደሚለን፣ ርስ በርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡
በኅዳር ወር ውስጥ በዋነኛነት በቀዳሚነት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልዷ ከጌታችን ከመደኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከቅዱስ ዮሴፍንና ከቅድስት ሰሎሜ ጋር ከተሰደዱበት ምድረ ግብጽና ኢትዮጵያ ወደ ሀገረ እየሩሳሌም መመለስ እንዲሁም በቁስቋም ተራራ ማረፍ የሚታስብበት ወቅት ነው፡፡ ይህም የሆነው በኅዳር ስድስት ቀን ነው፤ መልአኩ ጨካኝ ንጉሥ ሄሮድስ በመሞቱ ከተሰደደቡት ሀገር እንዲመለሱ በነገራቸው መሠረት ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱበትን ዕለት እናስባለን፤ እናከብራለን፡፡
በኅዳር ስምንት ቀንም ሥጋ የሌላቸው የአርባዕቱ እንስሳ በዓላቸው ሆነ። እነርሱም መንበሩን የሚሸከሙ የእግዚአብሔር ሠረገላዎቹ ናቸው። በአምላካችን እግዚአብሔር ዙፋኑ ዙሪያ የሚገኙት አራት አርባዐቱ እንስሶ በፊትም በኋላም ዐይንን የተመሉ ናቸው። የፊተኛው አንበሳ ይመስላል፤ ሁለተኛውም ላም ይመስላል፤ ሦስተኛውም የሰው መልክ ይመስላል፤ አራተኛውም የሚበር አሞራ ይመስላል። የአራቱ እንሰሶች እያንዳንዱ ክንፋቸው ስድስት ስድስት ነው፡፡ ሁለንተናቸውም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው። “የነበረ የሚኖር የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ጽኑዕ ክቡር ልዩ ነው” እያሉ በማመስገን በመዓልትና በሌሊት ዕረፍት የላቸውም። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ በዓላቸውን ታከብራለች፡፡
ዳግመኛም በኅዳር ስምንት ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ አፍኒን የተሾመበት ዓመታዊ በዓሉ ነው፡፡ ይህም ሱራፌልና ከኪሩቤል ጋር የልዑልን የጌትነቱን ዙፋን የሚጠብቅ ነው፡፡ ስለዚህም ክቡር ነቢዩ ሄኖክ እንዲህ አለ፡- “…ያንን ቤት ሱራፌልና አፍኒን ዙሪያውን እየዞሩ ይጠብቁታል፤ እነርሱም የልዑልን የጌትነቱን ዙፋን ሲጠብቁ የማያንቀላፉ ናቸው፡፡”
ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ “በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ሰባት መላእክትን አየሁ” (ራእይ ፰፥፪) እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቁጥር ሰባት ናቸው፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ ፋኑኤልና ኅዳር ስምንት ቀን የተሾመበትን ዓመታዊ በዓሉን የምናከብርለት ቅዱስ አፍኒን ናቸው፡፡
የመላእክት ሁሉ አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም የተሾመው ኅዳር ፲፪ ቀን በመሆኑ የከበረ በዓልን እናደርጋለን፡፡ ይህም “መኑ ከመ አምላክ?፤ ማን እንደ አምላክ” የተባለ መልአክ ቸር ርኅሩኅ የሆነ፣ ለሰው ልጆች ምሕረትን የሚለምንና ይቅርታን የሚያሰጥ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የመልአኩን ዓመታዊ ክብረ በዓል በኅዳር ፲፪ እና በሰኔ ፲፪ ቀን ታከብራለች፡፡
ታቦተ ጽዮን ወደ ሀገራችን የገባችበት ኅዳር ፳፬ ቀን ሌላው በዚህ ወር የሚታሰብ የከበረ በዓል ነው፡፡ በድንቅ ተአምሯ በእግዚአብሔር ቸርነትና ፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው፣ ዐሥርቱ ትእዛዛት የተፈጸመባት ታቦተ ጽዮን መኖሪያ መቀመጫዋ ሀገራችን በመሆኑ ደስታችን እጥፍ ድርብ ነውና የከበረ በዓልን እናደርጋለን፡፡
በዚህ ዕለትም የከበሩ ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ በዓላቸው ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን መላእክት የሥላሴን መንበር የሚያጥኑ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ “ሃያ አራቱ ሊቃናት በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ፦ ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል” እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ” ይላል። (ራእይ ፬፥፲-፲፩) ከዚህ ጋር ተያይዞም የአባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትም ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥሉስ ቅዱስን መንበር ያጠኑበትን በዓል እናከብራለን፡፡
የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት፡ የእመቤታችን እና የቅዱሳን አማላጅነት አይለየን፤ አሜን!