ወርኃ ታኅሣሥ
መምህር ሃይማኖት አስከብር
ኅዳር ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ሰፊ አስተምህሮ እና ምሥጢር ካላቸው ወራት አንዱ የታኅሣሥ ወር ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ በባሕረ ሐሳብ ቀመር ቀኑ ዘጠኝ ሌሊቱ ዐሥራ አምስት ይሆናል፤ ከዚህ በኋላ ቀኑ እየጨመረ ሌሊቱ እያነስ ይሄዳል።
ከስሙ ትርጕም ስንጀምር አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ታኅሣሥ የሚለውን ቃል ‹‹መፈለግ፣ ፍለጋ›› የሚል ፍቺ ሲሰጡት ‹‹ኀሠሠ፣ ፈለገ፣ አገኘ›› ከሚለው የግእዝ ቋንቋ እንደተገኘ ሊቃውንትም ይናገራሉ።
“ምንድን ነው የተፈለገው?” ብለን ስንጠይቅ….
፩ኛ በዚህ ወቅት ገበሬው የደከመበትን፣ የድካሙን ዋጋ፣ ፍሬውን ለማግኘት፣ ለመሰብሰብ ማሳውን ፍለጋ የሚሄድበት፣ የሚሰበስብበት ወር ነው፤ ወርኀ ታኅሣሥ የመፈልግ እና የመስብሰቢያ ወር የሚባለውም ለዚህ ነው።
፪ኛ ወርኀ ታኅሣሥ “ጾመ ነቢያት” የሚጾምበት ወቅት ነው፤ ነቢያት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የጠበቁትን አምላክ፣ መድኃኒት ለማግኘት፣ በሱባኤ ደጅ የጠኑበት፣ የፈለጉበት ወር ነው፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ ከታኅሣሥ ፯ እስከ ልደት ድረስ “ዘመነ ስብከት” ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ነቢያት የክርስቶስ ሰው መሆን መወለድ እንደ ደረሰ፣ ለማጠየቅ፣ በብዙ ምሳሌ እና ትንቢት ተገለጾላቸው የአስተማሩበትና የሰበኩበት ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ እንደ ጻፈልን ‹‹በብዙኅ ነገር ወበብዙኅ መክፈልት አይድዐ እግዚአብሔር ለአበዊነ በነቢያቲሁ እምትካት፤ አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን እስኪፈጸም እግዚአብሔር በነቢያት አድሮ ለአባቶቻችን ተናገረ፡፡›› (ዕብ.፩፥፩) ነቢያት የክርስቶስን መምጣት አጥብቀው የፈለጉባትና የሻቱበት ወቅት ዘመነ ስብከት ነው፤ በሦስት ልዩ ሳምንትም ይመደባል።
፪.፩፡- ከታኅሣሥ ፯-፲፫ ድረስ “ስብከት” ይባላል፤ ስብከት ማለት ትምህርት ማለት ነው፤ ከላይ እንዳነሣነው ነቢያት በብዙ ምሳሌና ትንቢት ክርስቶስን መፈለጋቸው (መሻታቸው) የሚታሰብበት ነው፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት ‹‹ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ፤ እነሆ በኤፍራታ ተወልዶ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው›› ብሎ ጊዜው እንደ ደረሰ ለማጠየቅ ተናግሯል፡፡ (መዝ.፻፴፩፥፮) ሌሎችም ነቢያት በተለያየ ምሳሌ መስለውታል፤ ያንን የነቢያት ስብከት ለማሰብ ስብከት ተብሏል።
፪-፪፡- ከታኅሣሥ ፲፬-፳ ድረስ “ብርሃን” ተብሎ ተሰይሟል፤ ይህም የተባለበት ምክንያት ነቢያት ጌታን በብርሃን እየመሰሉ በመስበካቸውና የሞት ጨለማንና የባርነት ጨለማን የሚያስወግድ አማናዊ ብርሃን ክርስቶስ እንደቀረበ ለማጠየቅ ነው፡፡
‹‹እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፥ እጅህንም እይዛለሁ፤ እጠብቅህማለሁ፥ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት፣ በጨለማም የተቀመጡትን ከወኅኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ›› ብሎ ነቢዩ ኢሳይያስ ተናግሯል፤ ሰብኳልም፡፡ (ኢሳ.፵፪፥፮ /፵፱፥፮)
በኋላም ራሱ ብርሃንነቱን ሲያረጋግጥልን ‹‹አነ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም፤ የጨለማው ዓለም ብርሃን እኔ ነኝ›› አለን፡፡ (ዮሐ.፰-፲፪) የማይጠፋና የማይለወጥ፣ ጨለማ የማይለውጠው፣ ደመና የማይጋርደው፣ ጠፈር የማይከለክለው ብርሃን፣ አማናዊ ብርሃን መድረሱን ነቢያት የሰበኩበት ስለሆነ ብርሃን ይባላል። ነቢዩ ኢሳይያስም ‹‹ወአልቦ ጽልመት ውስተ መክፈልታቲሁ እስመ ጸዳለ ብርሃን ውእቱ፤ በአኗኗሩ ጨለማ የለበትም፤ የብርሃን ጸዳል፣ የብርሃን መገኛ እርሱ ነው እንጂ›› ብሏል። (ኢሳ.፱፥፪)
፪-፫፡- ከታኅሣሥ ፳፩ እስከ ታኅሣሥ ፳፰ ኖላዊ ይባላል፡፡
ኖላዊ ማለት ጠባቂ ማለት ነው፤ ኖላዊ የተባለውም ራሱ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ነው፤ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም እንዲህ ብሎ አስቀድሞ ትንቢት ተናግሯል፤ ‹‹ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አጽምዕ እግዚኦ፤ የእስራኤል ጠባቂያቸው አቤቱ ስማ፤ አድምጥ፡፡›› (መዝ.፸፱፥፩) ለጊዜው ለእስራኤል ዘሥጋ ቢሆንም ፍጻሜው ግን ለእስራኤል ዘነፍስ ነው፤ እረኛ ከተኵላ በጎቹን እንዲጠብቅ የሁላችን ጠባቂ ክርስቶስ ነው። ‹‹አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር፤ ወኖላዊሰ ኄር ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግዒሁ፤ ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ ቸር ጠባቂ ስለ በጎች እራሱን አሳልፎ ይሰጣል›› እንዲል። (ዮሐ.፲፥፲፩) የአማናዊ እረኛ ክርስቶስን መምጣት የሚፈልጉ አበው በዚህ መልኩ ስለ ፈለጉት ኖላዊ ተብሏል።
፫ኛ ሰብአ ሰገል ከሩቅ ምሥራቅ ተነሥተው፣ በኮከብ ተመርተው ‹‹አይቴ ሀሎ ዘተወልደ ንጉሠ እስራኤል? የተወለደው የእስራኤል ንጉሥ ወዴት አለ?›› እያሉ ከሩቅ የመጡ ጠቢባን የመጡበት፣ አግኝተው ወርቅ የገበሩበት ነውና ፈልጎ የማግኛ ወር ይባላል፡፡ (ማቴ.፪-፩)
በዚህም መሠረት የሰው ልጅ እና መላእክት በኅብረት ያመሰገኑበት ነው፤ ወርኅ ታኅሣሥ መፈለግ ከተባለበት ምክንያቶች ጥቄቶቹ እነዚህ ናቸው።
ሌላው በዚህ በወርኃ ታኅሣሥ የሚታሰቡ ቅዱሳን በዓላት አሉ፤ በእርግጥ እንደ መጽሐፈ ስንክሳር በሁሉም ዕለት የሚታሰቡ ቅዱሳን ቢኖሩም ከእነዚህ በጣም የሚታወቁትን ብቻ እናነሳሳለን፡፡
፩ኛ፡- ታኅሣሥ አንድ የታላቁ ነቢይ ኤልያስ በዓለ ልደተ ልደት ነው፤ በእሳት ሰፋድል ከእናቱ ማኅፀን የወጣበት ዕለት ይከበራል።
፪ኛ፡- ታኅሣሥ ሦስት የአማናዊት መቅደስ እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ዕለት “በዓታ ለማርያም”፣ ቅድስት ሐና እና ቅዱስ ኢያቄም ስእለታቸውን ወደ ቤተ መቅደስ ይዘው የገቡበት የስጦታ ቀን ነው፡፡ እመቤታች የቤተ መቅደስ ኑሮን የጀመረችበት፣ የመላእክት ዝማሬ በመስማት በቤተ መቅደስ የገባችበት ዕለት ነው፤ በዚህም ዕለት ዕረፍቱ የሚታሰብለት የአቡነ ዜና ማርቆስ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ በዓል ነው፡፡
፫ኛ፡- ታኅሣሥ ፲፪ ዕረፍቱ ለአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ዘእም ትውልደ ጌዴዎን ዘገበዘ አክሱም ነው
፬ኛ፡- ታኅሣሥ ፲፮ ዕረፍቱ ለጌዴዎን መስፍን፤ ጌዴዎን ማለት “ጽንዕ፣ ብርቱ፣ ኃያል” ማለት ነው፡፡
፭ኛ፡- ታኅሣሥ ፲፱ በዓሉ ለቅዱስ ገብርኤል መልአክ ብሥራታዊ አረጋጊው መልአክ ዘአድኀኖሙ ለአናንያ ወአዛርያ ወሚሳኤል እምቶነ እሳት በማለት የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡
፮ኛ፡- ታኅሣሥ ፳፪ በዓለ ብሥራተ ገብርኤል ይከበራል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን እንደምትወልደው ቅዱስ ገብርኤል ያበሠረበት ዕለት የሚታሰብበት ነው፡፡
፯ኛ፡- ታኅሣሥ ፳፫ ዕረፍቱ ለዳዊት ንጉሠ እስራኤል ልበ አምላክ የተባለው እንደ ልቤ የተባለለት ወልደ ዕሤይ ብእሴ ምእመነ ዘከመልብየ የተባለለት የቅዱስ ዳዊት የዕረፍቱ መታሰቢያ ዕለት ነው።
፰ኛ፡- ታኅሣሥ ፳፬ ልደተ ብፁዕ ማር ኢትዮጵያዊ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓለ ልደት ነው፡፡
፱ኛ፡- ታኅሣሥ ፳፰ በዓለ ጌና ነው፡፡
፲ኛ፡- ታኅሣሥ ፳፱ በዓለ ልደተ ክርስቶስ ነው፡፡
የቅዱሳኑ በረከት አይለየን!
ይቆየን!