ወርኃ ሰኔ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ግንቦት ፳፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ወርኃ ሰኔ በዓመት ውስጥ ከሚገኙ ዐሥራ ሦስት ወራቶች መካከል ዐሥረኛው ወር ነው፤ ስለ ቃሉ ትርጒም መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ጀምረው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ፈጽመውት ደስታ ተክለ ወልድ ባሳተሙት መዝገበ ቃላት መጽሐፍ ላይ “ሰነየ” ከሚለው ግስ የተገኘ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ሰኔ ማለትም “ሰነየ፣ አማረ፣ መሰነይ፣ ሁለት ማድረግ፣ ማጠፍ ፣መደረብ፣ በመልክ በባሕርይ መለወጥ፣ ሌላ መሆን፣ መምሰል” እያለ ይተረጉመዋል፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፰፻፸፭)

ወርኃ ሰኔ የመዐልቱ ሰዓት ፲፭ የሌሊቱ ሰዓት ደግሞ ዘጠኝ ሰዓት ነው ፤ ከወራት በተለየ መልኩ የሚታወቅበት የበጋው ጊዜ አብቅቶ የክረምት ወቅት መድረሱ የሚበሠርበት መሆኑ ነው፡፡ በዓመቱ ውስጥ ካሉት ከዐራቱ ወቅታት በጋው አብቅቶ ክረምቱ የሚገባበት፣ ከሪቅ ከጎተራ የነበረው ያለፈው የሚያልቅበት፣ መጪው የሚጠበቅበት፣ በጠራው ሰማይ ላይ ከምሥራቅ ወጥታ ወደ ምዕራብ የምትጠልቀው ፀሐይ በሰማይ ደመና በከፊል የምትጋረድበት ወቅት፣ ሐጋይ (በጋ) እና ክረምት የሚፈራረቁበት ወር ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹…አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ፤ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ …›› በማለት እንደገለጸው ክረምትና በጋን የሚያፈራርቅ እግዚአብሔርን ድንቅ ሥራውን በእምነት መነጽር ተመልክተን የምናደንቅበት ወቅት ነው፡፡ (መዝ. ፸፫፥፲፯)

ወርኃ ሰኔ “ወርኃ ዘር፣ ወርኃ ማይ፣ ወርኃ ደመና” ይባላል፤ አርሶና ዘርቶ፣ አርሞና ኮትኩቶ፣ አጭዶ በጎተራው ለመክተት የሚያልመው ገበሬው ተስፋው የሚገለጥበት፣ ምድር የምትዋብበት፣ በወርኃ ግንቦት፣ በፀሐይ ደርቃ የነበረች ምድር በዝናብ ረጥባ ለዘር የምትመችበት ወር ነው፡፡

ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹…ምድርን ጎበኘኻት አጠጣኻትም፤ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ…›› በማለት ገልጽኦል፤ (መዝ.፷፭፥፱) ቅዱስ ኤጲፋንዮስም በትምህርቱ ‹‹ጠል በመስኩ ላይ ከወረደ፣ መስክም ጠልን የሚቀበለው፣ ሥሩንም የሚያሳድገው ከሆነ፣ ገበሬዎች ተስፋ የሚያደርጉት እርሻም ዝናምን የምትቀበል ከሆነ፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝም በተቀበለው ጊዜ ዘሩን የሚያሳድገው ከሆነ፣ ፍሬንም የሚሰጥ ከሆነ፣ ዝናም ለእርሻ ጠል በመስጠቱ ፍጹም ትምህርት ይገኛል›› እንዳለ፣ ለምድር የሰማይ ጠልን ሰጥቶ እህልን የሚያሳድገውን ፈጣሪ፣ ምድር የሰማይ ጠልን አግኝታ ታፈራ ዘንድ የሰው ልጅ በዚህ ወቅት ምድርን አርሶ፣ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ በምድር ላይ ለዘራው ዘር ፈጣሪ ዝናመ ምሕረቱን ይልክለት ዘንድ መማጸን የሚጀምርበት ወቅት ነው፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ ምዕራፍ ፶፮፥፳፬)

ወርኃ ሰኔ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጸሎት መጻሕፍትና ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ጾመ ሐዋርያት በሌላኛው ስም ይጠራበታል፤ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤዛዊት ዓለም በልጇ በመድኃኔዓለም መቃብር የጸለየችውን ጸሎት የጻፈልን መጽሐፍ መጠሪያ ስሙ ‹‹ሰኔ ጎልጎታ›› ነው፡፡ በዓለ ትንሣኤ ከተከበረ ከኀምሳኛው ቀን በኋላ የሚጾመው ጾመ ሐዋርያት አብዛኞውን ቀን የሚጾመው (ጾሙ የሚውልበት ወቅት) ወር ሰኔ በመሆኑ የሰኔ ጾም በመባልም ይታወቃል፡፡

ወርኃ ሰኔ ተማሪው ዓመቱን ሙሉ ከመምህራን ሲሰጠው የነበረውን በልቡ ማሳ ላይ የተዘራው ጥበብ፣ ዕውቀት ምን ያህሉ እንዳፈራ የሚታይበት፣ የልፋቱ (የድካሙ) ውጤት ፍሬን የሚለቅምበት (ሲቀስመው የነበረውን ዕውቀት (ጥበብ) ምን ያህሉን እንዳወቀ በማስተዋል ሚዛን ተቀምጦ ዋጋውን የሚቀበልበትም ወር ነው፡፡

ስለ ወርኃ ሰኔ አበው በብሒላቸው ብዙ ብለውለታል፤ ለአብነት ያህል ጥቂቱን እንመልከት፤ ወርኃ ሰኔ ከላይ በመጠኑ እንደገለጽነው ገበሬው ለቀጣይ ቀለቡ የሚሆነውን እህል ለማምረት ተግቶ የሚሠራበት ወቅት ነው፤ ነገን በማለም ዛሬ ላይ ሆኖ ደፋ ቀና ይላል፤ በደስታ ሊያጭድ በደስታ ይዘራል፡፡ ታዲያ በሰኔ ወር ይህን የማያደርግ ዘርቶ መቃም አይቻለውም፤ በዚህ ወር ለሥራ ተግቶ የማይገኝ እንዲህ ይተረትበታል፤ ‹‹ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል››፤ ‹‹ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ፤›› በወርኃ ሰኔ ምድር ከሰማይ ጠል ካላገኘች የዘሩባትን ማብቀል እንዳማትችል ይህም ደግሞ የአንድ የሴኔ ወር ችግር ለዓመት ሙሉ መከራን መዛዥ መሆኑን ሰኔን ተግቶ የሠራ ለዓመት እንደሚጠቀምም እንዲህ በማለት በድንቅ አባባላቸው ይገልጡታል፤ ‹‹አንድ ሰኔ የተከለው ካመት አተረፈው፡፡››

  • በወርኃ ሰኔ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዕለቱ የሚታሰቡ (የሚዘከሩ) ብዙ በዓለት ቢኖሩም ከሚከበሩት ዐበይት በዓላትን በመጠኑ እንመልክት፡-
    ሰኔ ስምንት ቀን እመቤታቸን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ታቅፋ ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር ወደ ግብፅ ከተሰደዱበት ሲመለሱ ጌታችን በተአምራት ውኃ ያፈለቀበት ነው፡፡
  • ሰኔ ዐሥራ ሁለት ቅዱስ ሚካኤል ባሕራን የተባለ ወጣት እንዲገደል የተጻፈበትን የሞቱን ደብዳቤ ወደ ሕይወት የለወጠበትና ከመከራ የታደገበት፣ ቅድስት አፎምያን ከዲያብለስ (ከሰይጣን) ተንኮል የታደገተበት ነው፡፡
  •  ሰኔ ዐሥራ ሰባት በቀደመ ስሙ ይስሐቅ በኋላ አባ ገሪማ በመባል የተሰየሙ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ የሆኑ ቃል ኪዳን የተቀበሉበትና ወደ ብሔረ ሕያዋን በብርሃን ሠረገላ የተነጠቁበት መታሰቢያ ነው፡፡
  •  ሰኔ ሃያ በዚህች ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም የመጀመሪያዋን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በፊልጵስዩስ ከተማ ከሦስት ደንጋዮች ያነጸበት ነው፡፡
  • ሰኔ ሃያ አንድ በእመቤታችን ስም በታነጸችው ቤተ ክርስቲያን ጌታችን ሥርዓተ ቅዳሴን አድርሶ ቅዱሳን ሐዋርያትን ያቆረበበት መታሰቢያ ነው
  • ሰኔ ሃያ ሦስት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ያነጸ፣ መጸሕፍትን የጻፈ፣ የጠቢቡ ሰሎሞን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡
  • ሰኔ ሃያ አራት ከቀድሞ የበደል ሕይወቱ ተመልሶ በአስቄጥስ ገዳም በተጋድሎ የኖረ አባ ሙሴ ጸሊም በሰማዕትነት ያረፈበት መታሰቢያ (ክብረ በዓል ) ነው፡፡
  • ሰኔ ሃያ አምስት ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የዮሴፍ ልጅ ይሁዳ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
  • ሰኔ ሃያ ስድስት በሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ስም ኔቅሎን በሚባል ቦታ ቤተ ክርስቲያን የታነጸበት ዕለት ነው፡፡
  • ሰኔ ሃያ ሰባት ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ቅዱስ ሐናንያ በሰማዕትነት ዐረፈ፤ ይቅር ባይ ጌታችን ቅዱስ ጳውሎስን በቸርነቱ ከአሳዳጅነቱ በጠራው (በመለሰው) ጊዜ ያጠመቀው አባት ነው፡፡
  • ሰኔ ሠላሳ ነቢይ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕት የሆነ በእናቱ ማኅፀን ሳለ ለእግዚአብሔር የሰገደ፣ መድኅን ዓለም ክርስቶስን ያጠመቀ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተወለደ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአማናዊ ቃሉ ‹‹…ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፤ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም …›› እንዳለው (ማቴ.፲፥፵፪) አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ቃል ኪዳን ረድኤት በረከትን ያሳትፈን፤ አሜን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!