ወርኃ ሚያዝያ

መምህር ተስፋ ማርያም ክንዴ

መጋቢት ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ስምንተኛው ወር  “ወርኃ ሚያዝያ” በመባል ይታወቃል፡፡ ሚያዝያ ማለት “መሐዘ፣  ጎለመሰ” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን “ጎለመሰ፣ ጎበዘ፣ አደገ፣ ሚስት ፈለገ፣ የሚዜዎችና የሙሽሮች ወር” የሚል ትርጒም ይይዛል። ይህን ስያሜም ያገኘው በሀገራችን በአብዛኛው ሰርግ የሚደረገው በዚህ ወር  ስለሆነ ነው።

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ደግሞ በግእዝ መዝገበ ቃላት ትርጒማቸው ላይ ሚያዝያ ማለት በቁሙ “ስመ ወርኃ፣ ሳምንት እመስከረም፣ የሚዛዝርትና የሙሽሮች ወር” ብለው ከፈቱ በኋላ ይህን ስያሜ የያዘበትን ምክንያት ሲገልጹ እንዲህ ይሉታል፤  “በግንቦት ወር ከጥንት ጀምሮ በአገራችን ልማድ ጋብቻና ሠርግ ሳይደረግ ይቆይና በኋላ ሚያዝያ ሲገባ ሰርግ መሠረግ ይጀምራል፡፡ ከዚህም የተነሣ የሚያዝያን ወር የሚዜዎች፣ የሙሽሮች ወር ተብሏል።” (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፭፻፹፯)

በምዕራባውያን በእንግሊዘኛው “April”  ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህንም ስያሜውን ያገኙት የአፍሮዳይት አምላክ ብለው ከሚያመልኩት የጣዖት ስም ጋር በማያያዝ ነው። በሮማውያን ይህ ወር አራተኛ ወራቸው ሲሆን ቀድሞ ከልደተ ክርስቶስ ከ ፵፭/፮ ዓመት በፊት ፳፱ ቀን በማድረግ ሲያከብሩት ከኖሩ በኋላ በአሁኑ ጊዜ ግን ፴ ቀን አድርገው እያከበሩት ይገኛሉ። (የብሉይ ኪዳን በዓላትና አጽዋማት አወጣጥ ያልታተመ የእጅ ጽሑፍ።)

ለእስራኤላውያን ወርኃ ሚያዝያን (ኔሳን) ራሱ እግዚአብሔር የመጀመሪያ ወር አድርገው እንዲያከብሩት ነግሯቸዋል። እግዚአብሔር በግብጽ ሀገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፤ “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ፤ ለእስራኤላውያን ማኅበር ሁሉ ተናገሩ።” (ዘፀ.፲፪፥፪) ይህም ወር የመጀመሪያ የሆነበት ምክንያት እስራኤላውያን ከግብጽ የወጡበት ወር በመሆኑ ነው። አስራኤላውያን በ ፴፻፰፻፵፬ ዓመተ ዓለም ከግብፅ ወጥተዋል። ከግብጽ በወጡ በሃምሳኛው ቀን ሊቀ ነቢያት ሙሴ በደብረ ሲና ጽላቱን ተቀብሏል፡፡

በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ከሕገ ልቡና ወደ ሕገ ኦሪት ተሸጋግረዋል። ወደ ኢትዮጵያውያን ስንመጣ ግን ኢትዮጵያ ከሕገ ልቡና ወደ ሕገ ኦሪት የተሸጋገረችው ሙሴ ጽላቱን ከተቀበለ ከ፭፻፺፫ ዓመት በኋላ ቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ ጽዮንንና የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን እንዲሁም ሌዋውያን ካህናትን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ከመጣ ከክርስቶስ ልደት በፊት ፲፻ ዓመት አካባቢ ነው።

የሚያዝያ ወር ከመስከረም ወር ጋር ተጣማጅ ከመሆኑም ባሻገር የሚብቱበትም ዕለት ተመሳሳይ ነው። በዚህ ሠርቅ መስከረም ይሠርቅ ሚያዝያ እንዲል። ኢትዮጵያውያን መስከረምን የበዓላቸው መጀመሪያ ካደረጉበት ምክንያትም አንዱ ይህ ነው።

ቅዱስ ያሬድ የዓመቱን የኢትዮጵያ ወሮች በአራት ወቅቶች ከፍሎ በእያንዳንዱ ወቅት መድረስ ያለበትን ሥርዓተ ማኅሌት ያስቀመጠልን ሲሆን አከፋፈሉም ከመስከረም ፳፮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን መጸው፣ ከታኅሣሥ ፳፮ እስከ መጋቢት ፳፭ ቀን ዘመነ ሐጋይ (በጋ) ከመጋቢት ፳፮ እስከ  ሰኔ ፳፭ ቀን ዘመነ ጸደይ (በልግ)፣ ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ዘመነ ክረምት (የዝናም ወራት) ተብሏል፡፡ በዚህ መሠረት የሚያዝያ ወር ከመጋቢት ፳፮ እስከ ሰኔ ፳፭ ውስጥ ባለው በዘመነ ጸደይ (በልግ) ውስጥ ይካተታል።

ይህ የኢትዮጵያ የወቅቶች አከፋፈል እጅግ የሚደንቀው ኢትዮጵያ የራሷ የዘመን አከፋፈልና  አቆጣጠር ያሳትና ይዛው የመጣችው፣ የሀገሪቱን የአየር ጠባይ እና የተፈጥሮ መስተጋብር ይዞ የሚከሠት መሆኑ ነው።

ኢትዮጵያውን  ወቅቶቹን ጠብቀው በየዘመናቱ ሥራቸውን ያከናውናሉ፤ ባህላቸውን ይገልጹባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ወቅቱ ሁኔታ ከፋፍላ ሃይማኖታዊ ሥርዓቷን ታከናውናለች፡፡ ወደ ፈጣሪው ምስጋና ታቀርባለች፤ ለምሳሌ፡- ድጓ፣ አቋቋም፣ ቅኔ፣ ስብሐተ ነግህ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ ወዘተ… ሁሉም በወቅት፣ በወር፣ በሳምንት፣ በቀንና በሰዓት የተከፋፈሉ ናቸው።

የሌሎች ግን እንዲህ አይደለም፤ እኛ በጋ ያልነውን እነርሱ ክረምት እኛ ክረምት ያልነውን እነርሱ በጋ ይሉታል። በዚያውም ላይ የብዙዎቹ ሀገራት የወቅታቸው አከፋፈል እንደ ኢትዮጵያውን የአየሩን ጸባይ መሠረት በማድረግ የሚመጣ አይደለም።

በሚያዝያ ወር ፀሐይ በአራተኛው መስኮት ትወጣለች፤ በመሆኑም የካቲት ወር በኢትዮጵያ ዘንድ መዓልቱ እየጨመረ ሌሊቱ እያጠረ የሚሄድ ሲሆን የመዓልቱ ርዝመት ፲፫ ሰዓት የሌሊቱ ርዝመት ደግሞ ፲፩ ሰዓት ይሆናል።

በክፍል በሚቆጥረው በሄኖክ አቆጣጠር ደግሞ መዓልቱ ፲ ክፍል ሌሊቱ ፰ ክፍል ነው።

ፀሐይና ጨረቃ የተፈጠሩት በዚሁ በሚያዝያ ወር በአራተኛው መስኮት ነው። በአራተኛው ወር በሚያዝያ ኆኅት ፀሐይ በምዕራብ ለመግባት ፵፰ ደቂቃ ወይም አራት ኬክሮስ ሲቀራት፣ ጨረቃ ደግሞ በዚሁ ኆኅት በምሥራቅ ፵፰ ደቂቃ ወይም አራት ኬክሮስ ከፍ አድርጎ ፈጥሯቸዋል። (አቡሻክር ሰዒድ ወልደ በጥሪቅ ሊቀ ጳጳሳት ዘሮም ወእስክንድርያ ገጽ ፯፻፸፩)

ፀሐይና ጨረቃ በተፈጠሩበት ጊዜ የነበራቸውን የብርሃን መጠን እና የኬክሮስ ሁኔታ የተለያዩ ሊቃውንት በተለያየ መልክ የገለጡት ሲሆን ለማሳያ ያህል የተወሰኑትን እንመልከት፡፡

፩. ጨረቃ በአራተኛው ኬክሮስ ተፈጥራ ስታበራ አድራ ገብታለች፤ ፀሐይ ደግሞ በምዕራብ ተፈጥራ ወዲያው ታይታ ገብታለች የሚሉ አሉ፡፡

፪. ፀሐይ በአራተኛው ኬክሮስ ተፈጥራ ስታበራ አምሽታ ገብታለች፤ ጨረቃም በሙሉ ብርሃን ተፈጥራ ስታበራ አድራ ገብታለች የሚሉ አሉ፡፡

፫. ጨረቃ በምልዓት ተፈጥራ ስታበራ አድራ ገብታለች፤ ፀሐይም በጧት ተፈጥራ ስታበራ ውላ ጨረቃ በገባችበት ኆኅት ገብታለች የሚሉ አሉ።

አቡሻክር ግን በዐሥራ ሦስተኛው አንቀጽ እንዲህ ይላል፤ “ያጤይቅ ከመ ወርኅ ተፈጥረ በቀዳሚት ሰዓተ ሌሊት በዕለተ ረቡዕ ፍጹመ ብርሃን ምሉዓ በገጸ ምሥራቅ እምቅድመ ፍጥረተ ፀሐይ በ፲ወ፪ቱ ሰዓት (ጨረቃ በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በዕለተ ረቡዕ በምሉዕ ብርሃን ፀሐይ ከመፈጠሯ ከ፲፪ ሰዓት በፊት በምሥራቅ በኩል ተፈጥራለች ይላል። ይህ ከላይ ከተባለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

ፀሐይ ከመፈጠሯ ከ፲፪ ሰዓት በፊት ማለቱ ከላይ እንደተገለጸው ፀሐይ በምዕራብ አራት ኬክሮስ ሲቀራት ተፈጥራ ወዲያው ትገባና በሰሜን በኩል ዙራ በምሥራቅ ወጥታለች፡፡ በዚህ ጊዜ በምሥራቅ የተፈጠረችው ጨረቃ ስታበራ አድራ ሳትገባ ፀሐይ ወጣችባት፤ ይህም ጨረቃ ያልጨረሰችው ትርፍ ሕፀፅ ይባላል። አቡሻክር ከላይ በተገለጸው አንቀጽ እንዲህ ማለቱ ፀሐይ ከመፈጠሯ ከ፲፪ ሰዓት በፊት ያለው ፀሐይ በምሥራቅ የታየችበትን ሲያይ ነው። ለምን ከተባለ ዐሥራ ሁለቱን ሰዓት ብርሃን ካልሰጠች የተፈጠረችውን ፀሐይ እንዳልተፈጠረች አድርጎ ቆጠረ፡፡ እንዲህ ማለትም የመጽሐፍ ልማድ ነው፡፡ በሕይወት ያለውን ኃጢአት ከሠራ ዘንድ እንደሞተ ቆጥሮ  እስመ ዝንቱ ወልድየ ሞተሂ ወሐይወ፤ ይህ ልጀ ሞቶ ነበርና ዳግመኛም ሕያው ሆኗል”  እንዳለ፡። (ሉቃ.፲፭፥፳፬)

ከላይ ያሉት እንዳለ ሁኖ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አፈጣጠር ሲጠቃለል አሁን ባሉት ሊቃውንት ዘንድ የሚታመነውና የሚታወቀው እንዲህ ነው።

ፀሐይና ጨረቃ የተፈጠሩት በዚሁ በሚያዚያ ወር በአራተኛው መስኮት ሆኖ። በአራተኛው ወር በሚያዚያ ሆኅት ፀሐይን በምዕራብ ለመግባት ፵፰ ደቂቃ ወይም አራት ኬክሮስ ሲቀራት ጨረቃን ደግሞ በዚሁ ሆኅት በምሥራቅ ፵፰ ደቂቃ ወይም አራት ኬክሮስ ከፍ አድርጎ ፈጥሯቸዋል። (አቡሻክር ሰዒድ ወልደ በጥሪቅ ሊቀ ጳጳሳት ዘሮም ወእስክንድርያ ገጽ ፯፻፸፩) ይህም ሐሳብ ከላይ አቡሻክር ካለው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ አይተናል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን መሠረት አድርጋ የቅዱሳንን በዓላት በዓመትና በወር የምታዘክር ሲሆን በዚህ ወር ከሚታሰቡት ዋና ዋና በዓላት መካከል የሚከተሉትን እናነሣለን፡፡

፩ኛ ሚያዝያ አንድ ቀን ለሙሴ ወንድም የሆነ የካህኑ አሮን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡

፪ኛ ሚያዝያ አምስት የታላቁ ነቢይ ሕዝቅኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡

የቅዱስ ያሬድ የልደት በዓሉ ነው፡፡

፫ኛ ሚያዝያ ስድስት በበረሃ የኖረችው ግብጻዊት ማርያም ያረፈችበት ቀን ነው፡፡

ዳግመኛም የጥንተ ዳግም ትንሣኤ መታሰቢያ ነው፡፡

የአባታችን ኖኅም የልደት ቀኑ መታሰቢያ ነው፡፡

፬ኛ በሚያዝያ ሰባት ቀን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አባት ጻድቁ ኢያቄም ዐረፈ፡፡

፭ኛ ሚያዝያ ዘጠኝ የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ የዕረፍት መታሰቢያ ነው፡፡

፮ኛ በሚያዝያ ሃያ ሦስት ቀን ፀሐይና የአጥቢያ ኮከብ የተባለ ታላቅና ክቡር የሆነ የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ የምስክርነቱ ፍጻሜ ነው፡፡

፯ኛ ሚያዝያ ሃያ ሰባት የታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር ዓመታዊ የዕረፍት መታሰቢያው ነው፡፡

፰. ሚያዝያ ሠላሳ ቀን ለእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት አለቃ የሆነ ወንጌልን የጻፈ ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡

የቅዱሳኑ ጸሎት፣ አማላጃነትና ተዳኢነት አይለየን፤ አሜን!