ወርኃ መጋቢት

ክፍል ሁለት

መምህር ተስፋ ማርያም ክንዴ

መጋቢት ፩፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ጠቢቡ ሰሎሞን ፲፩ ሲራክ አንድምታ ፵፫ “ወኀተምክዋ ለምድር በሰባቱ ማኅተሚሃ፤ ሰባተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ በምድርም በሰማይም ያለው ፍጥረት ሁሉ እኩል ሰዓት የሚህል ዝምታ በሰማይ ሆነ” እንዳለ፡፡ (ራእይ ፭፥፩)

“በሰባት ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ” እንዳለ ዓለም በሰባት ትከፈላለች፤ እነርሱም ዓለመ እሳት፣ ዓለመ ነፋስ፣ ዓለመ መሬት፣ ዓለመ ውኃ፣ ዓለመ በረድ፣ ዓለመ ግሩማን አራዊት (በድምፅ ብቻ ሰውን የሚገሉ አራዊቶች የሚኖሩበት) እና ዓለመ ብሄሞት ወሌዋታን ናቸው።

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ደግሞ የሚያሳምን ማስረጃ ባያቀርቡም “ዓለም የተፈጠረው በጥቅምት ነው። በፀሐይ ቁጥር ግን የመስከረም ጫፍ ይሆናል። ይኸውም “ንግሮሙ ለደቂቀ እስራኤል ወበሎሙ በሳብዕ ወርኅ አመ ርእሰ ሠርቀ ወርኅ ዕረፍተ ይኩንክሙ ተዝካረ ዘመጥቅዕ ቅድስት ስማ ለእግዚአብሔር፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት በመለከት ድምፅ መታሰቢያ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ” ባለው ይታወቃል ብለው መጽሐፈ ዘሌዌውያን (፳፫፥፳፬) ይጠቅሱና የግእዝና የቅብጥም ዐውደ ዓመት በመስከረም ራስ መሆኑ መጥቅዕን መሠረት ይዞ ነው” ይላሉ። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፪፻፵፱)

በአቡሻክር ትምህርት ፀሐይ የምትወጣባቸውን የምትገባባቸው በምሥራቅ ስድስት በምዕራብ ስድስት መስኮቶች እንዳሉ ነቢዩ ሄኖክ ተናግሯል፡፡ “ፀሐይ የሚወጣባቸው ስድስት መስኮቶችን አየሁ፤ ፀሐይ የሚገባባቸውን ስድስት መስኮቶችንም አየሁ፤ ጨረቃም በእነዚህ መስኮቶች ይወጣል፤ ይገባል” እንዲል፡፡ (ሄኖክ ፳፩፥፮) አንዱ መስኮት ፴ ከንትሮስ ስላለው ፀሐይ አንዱን ወር ሙሉ በአንዱ መስኮት ትወጣና በቀጣይ ወር ደግሞ ወደ ቀጣዩ መስኮት ትሸጋገራለች።

የመጀመሪያው መስኮት በአዜብ (ደቡብ ምሥራቅ) በኩሌ ሆኖ ወደ ምሥራቅ እየተቆጠረ ስድሰተኛው መስኮት በሰኔ ይጨርሳል። መስኮቱ በአዜብ (ደቡብ ምሥራቅ) ለመጀመሩም ምስክሩ ፀሐይና ጨረቃ በአራተኛው መስኮት በወርኃ ሚያዚያ በመፈጠራቸው ይታወቃል። (አቡሻክር ሰዒድ ወልደ በጥሪቅ ገጽ ፯፻፸፩)

የፀሐይ መስኮት በደቡብ በኩል ሆኖ ፀሐይ ጥርና ታኅሣሥ በደቡብ በኩል ባለው በመጀመሪያው መስኮት የካቲትና ኅዳር በሁለተኛው መስኮት መጋቢትና ጥቅምት በሦስተኛው መስኮት ሚያዝያና መስከረም በአራተኛው መስኮት ግንቦትና ነሐሴ በአምስተኛው መስኮት ሰኔና ሐምሌ በስድስተኛው መስኮት ትወጣና ትገባለች፤ ከዚህ በኋላ እንደገና ወደ ደቡብ ትመለሳለች። በዚህ አረዳድ መሠረት  በመጋቢት ወር ፀሐይ በሦስተኛው መስኮት ትወጣለች፤ ይህን ሁሉ መዘርዘራችን መጋቢትን ወር ለማምጣት ነው።

በመሆኑም በመጋቢት ወር በኢትዮጵያ ዘንድ መዓልቱ እየጨመረ ሌሊቱ እያጠረ የሚሄድ ሲሆን የመዓልቱ ርዝመት ፲፪ ሰዓት የሌሊቱም ፲፪ ሰዓት ይሆናል። በክፍል በሚቆጥረው በሄኖክ አቆጣጠር ደግሞ የመጋቢት ወር መዓልቱ ዘጠኝ ክፍል ሌሊቱም ዘጠኝ  ክፍል እኩል ነው። ይህ የሚሆነው ግን ከፍ ብለን በሰዓት ስለምንለካው ነው እንጂ ዝቅ ብለን ከሰዓት በአነሰው በከንትሮስ ብንለካውስ ቀንና ሌሊት እኩል ዕሪና የሚሆኑት መጋቢት ፳፭ እና መስከረም ፳፭ ቀን ብቻ እንደሆነ እንረዳለን፤ ይህም እንዲህ ነው። በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር መጋቢት ፳፭ ቀንና ሌሊቱ እኩል ይሆናል። ከመጋቢት ፳፭ ቀጥሎ ከሚመጣው ከመጋቢት ፳፮ ቀን ጀምሮ ግን ቀኑ ሌሊቱን በአንድ ከንትሮስ መብለጥ ይጀምራል። በስሌት ፴ ከንትሮስ አንድ ሰዓት ነው። እስከ ሰኔ ፳፭ ቀን ፺ ከንትሮስ ወይም ሦስት ሰዓት ቀኑ ሌሊቱን ይበልጣል፤ በዚህ ጊዜ ቀኑ ፲፭ ሰዓት ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ይሆናል።

በዚህ ጊዜ ፀሐይ የጉዞ አቅጣጫዋ ከደቡብ ወደ ሰሜን ነው። ከሰኔ ፳፮ ቀን ጀምሮ ደግሞ ሌሊቱ በተራው የተበለጠውን ኬንትሮስ እያስመለሰ ይሄድና እስከ መስከረም ፳፭  ቀን ድረስ ዘጠናውን ከንትሮስ ወይም ሦስት ሰዓቱን በሙሉ አስመልሶ መስከረም ፳፭ ቀን ቀንና ሌሊቱ እኩል ፲፪ ሰዓት ፲፪ ሰዓት ይሆናል። የፀሐይ ጉዞ በዚህ ጊዜ ከሰሜን ወደ ደቡብ ወይም ከመጨረሻው መስኮት ወደ መጀመሪያው መስኮት እንደሆነ አስተውል። ከመስከረም ፳፮ ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ሌሊቱ በተራው ቀኑን በአንድ ከንትሮስ እየበለጠ ይሄድና፤ ሌሊቱ ቀኑን ፺ ከንትሮስ ወይም ሦስት ሰዓት ይበልጣል።

በዚህ ጊዜ ሌሊቱ በተራው ፲፭ ሰዓት ሲሆን ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይሆናል። የፀሐይ ጉዞ በዚህ ጊዜ ከመጨረሻው ወደ መጀመሪያው ወደ ደቡብ ተጉዞ የመጀመሪያውን የታኅሣሡን ኆኅት ያገኛል፤ ታኅሣሥ አንድ ስንክሳር ይመልከቱ፤ ከዚህ ላይ ግን ያመለክታል እንጂ እንደማይገልጸው አስተውል።

ከታኅሣሥ ፳፮ ቀን ጀምሮ እስከ መጋቢት ፳፭ ቀን ድረስ ቀኑ ከሌሊቱ ላይ አንድ ከንትሮስ እያስመለሰ ሄዶ መጋቢት ፳፭ ላይ ሁሉን ዘጠናውን ከንትሮስ ወይም ሦስቱን ሰዓት አስመልሶ መጋቢት ፳፭ ላይ ሌሊቱ ፲፪ ሰዓት ቀኑ ፲፮ ሰዓት ይሆናል፤ ይህ መነሻችን ነው እንዲህ እያለ እስከ ምጽአት ድረስ ይኖራል።

ጨረቃ ወራቱን ተከትላ በየቀኑ በስድስቱ የፀሐይ መስኮቶች የምትፈራረቅ እንደሆነ ከላይ ገልጸናል፤ በመሆኑም በመጋቢት ወር ጨረቃ ከፀሐይ ጋር የምታድርባቸው ቀናት የሚከተሉት ናቸው። በሦስተኛው መስኮት ሁለት ቀን፤ በአራተኛው መስኮት ሁለት ቀናት፣ በአምስተኛው መስኮት ሁለት ቀን፣ በስድስተኛው መስኮት ስምንት ቀን፣ በአምስተኛው መስኮት አንድ ቀን፣ በአራተኛው መስኮት አንድ ቀን፣ በሦስተኛው መስኮት ሁለት ቀን፣ በሁለተኛው መስኮት አንድ ቀን፣ በመጀመሪያው መስኮት ስምንት ቀን፣ በሁለተኛው መስኮት ሁለት ቀን፣ በሦስተኛው መስኮት አንድ  ቀን ከፀሐይ ጋር ታድራለች፡፡ መጋቢት ፳፱ ቀን ተፈጸመ፡፡ (መጽሐፈ አቡሻክር ያልታተመ የእጅ ጽሑፍ፣ ብርሃነ አእምሮ ገጽ ፶፱)

በኢትዮጵያ የወቅቶች አከፋፈል መሠረት ከታኅሣሥ ፳፮ እስከ መጋቢት ፳፭ ዘመነ ሀጋይ፣ በጋ ስለሚባል የመጋቢት ወር ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሚካተተው በበጋ ወራት ሲሆን የኮከብ ምግብናውም ናርኤል  ነው። (ባሕረ ሐሳብ አለቃ ያሬድ ፈንታ)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን መሠረት አድርጋ የቅዱሳንን በዓላት በዓመትና በወር ትዘክራለች፡፡ በየቀኑ የሚታሰቡትን የወርና የዓመት የቅዱሳንን በዓላት ቢኖሩም ለዚህ ጽሑፍ ግን ቦታ ስለሚገድበን የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡ (የሌሎች ቅዱሳንን ታሪክ ለማግኘት የመጋቢትን ስንክሳር ይመልከቱ።)

፩ኛ መጋቢት አንድ የሄኖክ ልጅ የማቱሳላ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡

፪ኛ መጋቢት አምስት የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡

፫ኛ መጋቢት ስምንት የሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ የዕረፍት በዓል ነው፡፡

፬ኛ መጋቢት ዐሥር ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የተሰቀለበት የከበረ መስቀል የተገለጠበትና የተገኘበት ነው፡፡

፭ኛ መጋቢት ዐሥራ አራት የቅዱስ ቄርሎስ ዕረፍት በዓል ነው፡፡

፮ኛ መጋቢት ዐሥር አምስት ቀን ጌታችን የሚወደው እና በአራተኛው ቀን ከሞት ያስነሣው የከበረ ጻድቅ አልዓዛር ያረፈበት ነው፡፡

፯ኛ መጋቢት  ሃያ ሁለት ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ገብቶ ቤተ መቅደስን በአህያ ግልገል ተቀምጦ በመዞር “ሆሣዕና በአርያም” እያሉ እንዲያመሰግኑት አድርጓል፡፡

፰ኛ መጋቢት ሃያ ሦስት ታላቁ ነቢይ ነቢዩ ዳንኤል ያረፈበት ነው፡፡

፱ኛ መጋቢት  ሃያ አራት ቀን አይሁድ በጌታችን ላይ አጽንተው መከሩ፡፡

፲ኛ መጋቢት ሃያ ስድስት ቀን ጌታችን የደቀ መዛሙርትን እግር ያጠበበት ነው፡፡

፲፩ መጋቢት ሃያ ዘጠኝ ቀን ለክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፅንሰት በዓል መታሰቢያ ነው፡፡ ይህም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምሥራች እንደነገራት አካላዊ ቃል በማኅፀኗ አድሯል፡፡

ዳግመኛም በዚህች ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረችና ልዩ በሆነች ትንሣኤው የዓለም ድኅነት ሆነ!

ስብሐት ለእግዚአብሔር!