ወርኃ መስከረም

ዲያቆን ዘካርያስ ነገደ

ጳጉሜን ፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

መስከረም ለሚለው ቃል መነሻ “ከረመ” የሚለው ግስ ነው፤ ትርጓሜውም “ቀዳማይ፣ ለዓለም ሁሉ መጀመሪያ፣ ርእሰ ክራማት፣ መቅድመ አውራኅ” የሚለውን ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል መስከረም የመጀመሪያ ወር ስም፣ ከዘመነ ሥጋዌ በፊትም ለዓለም ሁሉ የመጀመሪያ ወር ማለት ነው፤ “መስ” የሚለው ቃልም መነሻ መስየ የሚለው ግስ ሲሆን “ምሴተ ክረምት (የክረምት ምሽት) በምሥጢር ደግሞ ፀአተ ክረምት (የክረምት መውጫ)፣ የክረምት ጫፍ መካተቻ፣ የመፀው መባቻ” መሆኑን ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላታቸው ይገልጣሉ፤ (ገጽ ፮፻፲፪) እንዲሁም “መቅድመ አውራኅ (የወራት መጀመሪያ) ርእሰ ክራማት” ይሰኛል ይላሉ፡፡

ስለ ቃሉ መገኛም ሲገልጡ መዝከረ ከረም (መዝከረ ዓም) እንደማለት ሆኖ ‘ዝ’ የምትባለው ፊደል በጊዜ ሂደት ተለውጣ “መስከረም” ተብሏል፡፡ የዐውደ ዓመት ማሰቢያ መታሰቢያ ወይም ዐውደ ዓመት ማለት ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡

መስከረም የወራት መጀመሪያ፣ የአዲስ ዓመት መግቢያ

የመስከረም ወር በወርኃ ክረምት (ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭) ውስጥ የሚካተት ቢሆንም የጨለማው ጊዜ አልፎ ብርሃን የሚታይበት፣ ዕፀዋትና አዝርዕት የሚያብቡትና የሚያፈሩበት፣ እንስሳት የጠራ ውኃ እየጠጡ፣ ለምለም ሣር እየነጩ የሚቦርቁበት በመሆኑ ልዩ ወር ነው፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር መግቢያው ላይ እንደተገለጸው ወርኃ መስከረም ለግብፃውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችና ለኢትዮጵያውያን የወራት መጀመሪያ ነው፤ በግብፆች ዘንድ ወሩ ቱት/ቶት/ቲቶ/ ተብሎ ይታወቃል፡፡

እንዲሁም የመስከረም መባቻ የአዲስ ዓመት መግቢያ በመሆኑ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ” በማለት የሰየመው በመሆኑ ዓመቱ በተለዋወጠ ቁጥር ተተኪው ዓመት አዲስ ዘመን እየተባለ ይጠራል፡፡ (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

በቅዱስ ያሬድ ትምህርት መስከረም ፩ ቀን ርእሰ ዐውደ ዓመት ሆኖ የተመረጠበትን ምክንያት እንረዳለን፤ ይኸውም፡- መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ የነቢያት መጨረሻ፣ የሐዋርያት መጀመሪያ ሆኖ “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ ሲያስተምር፣ የንስሐ ጥምቀትን ሲያጠምቅ ቆይቶ በገሊላው ንጉሥ በሄሮድስ እጅ በጳጕሜን ፩ ቀን ተይዞ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት በማረፉ የዕረፍት ቀኑ ከዘመን መለወጫ ዕለት ጋር የሚከበር በመሆኑ ርእሰ ዐውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ መባሉን ልብ ይሏል፡፡ (ማር.፩፥፲፭)

እንዲሁም የባሕረ ሐሳብ ሊቃውንት የበዓላት /የደብረ ዘይት፣ የሆሣዕና፣ የስቅለት፣ የትንሣኤ፣ የዕርገት፣ የጰራቅሊጦስ/ እና የጾም ቀናት /ጾመ ነነዌ፣ ጾመ እግዚእ፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ድኅነት/ ያገኙት በዚህ መግቢያ ወርና ዕለት በመሆኑ በተለይ መስከረም ፩ የበዓላቱና የአጽዋማቱ ዐዋጅ የሚነገርበት በመሆኑ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ” ይለዋል፡፡ (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ) መጥቅዕ የዓመቱ በዓላትና አጽዋማት ማውጫ ሲሆን አበቅቴ ደግሞ የዓመቱን የቀን፣ የሌሊት፣ የፀሓይና የጨረቃ ቁጥር ማውጫ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ቀኖና መሠረት በመስከረም ፩ ቀን የሚፈጸሙ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ይኸውም ሥርዓተ ማኅሌት ይደርሳል፤ ለዓመቱ ሙሉ የሚያገለግል ዐዋጅ (ባሕረ ሐሳብ) በየቤተ ክርስቲያኑ ከበሮ እየተጎሰመ በዚህ ቀን የበዓላትና የአጽዋማት ቀናቸው ይታወጃል፡፡ ይህን ዐዋጅ ማውጣት የሚቻለው መስከረም ፩ ቀንን መሠረት በማድረግ ብቻ ነው፡፡

እንዲሁም በዚሁ ቀን ለመሥዋዕት የሚቀርቡት ስንዴ፣ ዘቢብ፣ ዕጣንና ውኃ ቀርበው ይጸለይባቸዋል፤ ይህም በአዲሱ ዘመን የሚቀርበውን መንፈሳዊ ስጦታና ጸሎት ሁሉ ተቀብለህ በምሕረትህ አስበን፤ ዓመቱን ባርክልን ብለን ፈጣሪያችንን በጸሎት መለመናችንን የሚያመለክት ነው፡፡

መስከረም ፩ ቀን ርእሰ ዐውደ ዓመት ከመባሉም በተጨማሪ ዕንቊጣጣሽ በመባል ይታወቃል፤ ዕንቊጣጣሽ ማለት ገጸ በረከት ማለት ሲሆን ጠቢቡ ሰሎሞን ከንግሥተ ሳባ (ማክዳ) በወለደ ጊዜ ደስ ስላለው “ዕንቊ ለጣትሽ” ሲል ስጦታ ለጣቷ የዕንቊ ቀለበት ስላበረከተላት በዚያ የተሰየመ ነው ሲሉ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡

ዘመነ ዮሐንስ

በቅድስ ያሬድ ስያሜ መሠረት ከመስከረም ፩ እስከ ፯ ያለው ጊዜ ዘመነ ዮሐንስ ይባላል፡፡ ከላይ እንዳየነው ቅዱስ ዮሐንስ በሄሮድስ እጅ ሰማዕትነት የተቀበለው በዚህ ወር በመስከረም ፪ ቀን ነው፡፡

“ከእኔ አስቀድሞ የነበረ ከእኔ በኋላ ይመጣል ያልኳችኋል፤ ይህ ነው” እያለ ስለ ጌታችን ምስክርነት ሲሰጥ የነበረው ዮሐንስ፣  (ዮሐ.፩፥፳፱‐፴) ደግሞም በወንጌላዊው በቅዱስ ዮሐንስ መጽሐፍ “ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ፡- ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ፤ እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀበልን፤ በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና፤ ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ” በማለት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መገለጥ ምስክርነት መስጠቱ የተጻፈለት ዮሐንስ በዚህ ወር ሰማዕትነት በመቀበሉ ከመስከረም ፩ እስከ ፯ ያለው ጊዜ ዘመነ ዮሐንስ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ (ዮሐ.፩፥፲፭-፲፰)

ይቆየን!