ወርኃ ሐምሌ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሰኔ ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ሐምሌ የወር ስም ሲሆን ሐምል “ሐመልማል” ከሚለው ግስ የተገኘ ነው፤ “ሐምል” ማለት “ቅጠል፣ ቅጠላ ቅጠል፣ ሣር፣ ቋያ፣ ቡቃያ፣ ተክል” ማለት ሲሆን ሐምሌ ማለት ደግሞ ቅጠላም ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፬፻፵፱)

ወሩ ስያሜውን ያገኘው ምድር የሰማይ ጠልን ስታገኝ በእርሷ ላይ ከሚታየው ተፈጥሮአዊ ለውጥ የተነሣ ነው፤ በበጋው ወራት ደርቃና ተሰነጣጥቃ የነበረች ምድር በክረምቱ መግቢያ የሚዘንበው ዝናብ ድርቀቷን አስወግዶ ሲያለሰልሳት ልምላሜ ይታይባታል፡፡ ሣሩ፣ ቅጠሉ በቅሎ በአረንጓዴ ዕፅዋት ተውባ የክረምቱን መግባት የበጋውን ማብቃት ታበሥርበታለች፡፡

ወርኃ ሐምሌ የክረምቱ መባቻ በመሆኑ ገበሬው ዘርን ሊዘራ ባለሰለሳት መሬት የሰማዩ ጠል ሲያርፍበት በአረንጓዴ ዕፅዋት ትዋባለች፤ ቡቃያው፣ ሣሩ፣ ጎመን፣ ሰላጣው፣ ቅጠላ ቅጠሉ ይበቅልባታል፡፡ ወርኃ ሐምሌ ነጎድጓድ የሚሰማበት፣ መባርቅት የሚጮኹበት ከሰማይ ደመና፣ ከምድር ዝናም የማይለይበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወር በበጋው ወራት በጠራው ሰማይ ላይ ከምሥራቅ ወጥታ ለምድር ነዋሪዎች ብርሃኗን፣ ሙቀቷን ለግሳ በምዕራብ ትጠልቅ የነበረችው ፀሐይ የተፈጥሮ ዑደቷን ባታቋርጥም በደመና መጋረጃ ተጋርዳ አልፎ አልፎ ብቅ በማለት ደብዛዛ ብርሃኗን፣ ለስላሳ ሙቀቷን የምትሰጥበት ወር ነው፡፡

ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቅዳሴው ‹‹ከምድር ዳርቻ ደመናውን ያወጣል፤ መብረቅንም በዝናም ጊዜ አደረገ፤ ዝናምንም እንደ መሸረብ ነጠብጣብ ያፈሳል፤ ጉምን እንደ አመድ ይበትነዋል፤ በረድንም እያጠቃቀነ ያወርዳል፤ ለእንሰሳቱም ሣሩን ያለመልማል›› በማለት የፈጣሪን ችሮታ እንደገለጸው እንስሳቱ ለምለም ሣርን የሚያገኙበት ወቅት ነው፡፡ (ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ቁጥር ፴፭)

ክረምቱ ሲገባ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚቀርበው የኪዳኑ ሰላምታም ‹‹ደመና ብሩህ ዘከለላ መልአክ በሰላም ተናገረ …›› ተብሎ ይቀርባል፤ በቅኔ ማኅሌቱ ምስጋና ደመናውን፣ ዝናሙን፣ ነጎድጓዱን፣ መባርቅቱን በተመለከተ የፈጣሪን ድንቅ ጥበብ ችሮታ ‹‹…መኑ ሰፈሮ ለሰማይ በስዝሩ ወለማይኒ በሕፍኑ፤ አኮኑ አንተ እግዚኦ ዘታርኁ ክረምተ በበዓመት…›› (ሰማይን በስንዝሩ የሚለካ፣ ውኃን በእፍኙ የሚይዝ፣ ክረምትን የሚለዋውጥ እንደ አንተ ማነው!) እያሉ ሊቃውንቱ በቅኔ ማኅሌቱ ያመሰግናሉ፡፡

ዝናሙ ዝናመ ምሕረት፣ እክሉ እክለ በረከት እንዲሆን ‹‹…ዝናመ ምሕረት ፈኑ ዲቤነ፤ እመሥገርቱ ለሰይጣን ሠውር ኪያነ… ናሁ ሐረሳውያን ይጸንሑ ፍሬሃ ለምድር እስከ ትሰዊ ሎሙ በብዝኃ ሣህልከ…›› የምሕረት ዝናም በላያችን ላክ…እነሆ የምድርን ገበሬዎች የምድር ፍሬን በቸርነትህ እስክትሰጣቸው ይጠብቃሉ…›› በማለት ፈጣሪን ይማጸናሉ፡፡ ( ዝክረ ቃል መጽሐፍ ገጽ ፪፻፵፩)

ከክረምቱ መባቻ ጀምሮ እስከ ወሩ አጋማሽ ቅዱስ ቂርቆስ (ሐምሌ ፲፭) ድረስ “ወርኃ ዘር” ይባላል፤ እግዚአብሔር ደመናን፣ ዝናምን እንደሰጠና ምድር እንደለመለመች ይነገርበታል፤ ይዘመርበታል፤ ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር ይመሰገንበታል፡፡ መጋቤ አእላፍ ሄኖክ ወልደ ያሬድ በጻፉት “ያሬድና ዜማው” መጽሐፋቸው በወርኃ ክረምቱ በቅኔ ማኅሌቱ ከሚዘመሩት ዝማሬዎች መካከል አንዱን ለአብነት ብንመለከት እግዚአብሔር ክረምትና በጋን እንደሚያፈራርቅ እንዲህ ገልጠውታል፤ ‹‹መኑ ከማከ መሐሪ ሐረገ ነፍስ መታሪ ወልሳነ ኩሉ አሣሪ ክረምተ ወሐጋየ ዘታስተባሪ…፤ እንዳንተ ያለ መሐሪ ማነው የነፍስን ሐረግ የምትቆርጥ ክረምትና በጋንም የምታፈራርቅ፡፡›› (ዝክረ ቃል መጽሐፍ ገጽ ፪፻፵፩)

ከሐምሌ ፳፪ ጀምሮ እስከ ነሐሴ ደብረ ታቦር ያለው “ነጎድጓድ” ይባላል፤ በዚህ ወቅት ከባሕር እየተነነ፣ እየበነነ ወደ ሰማይ በሚወጣ ጉም ምድር ትሸፈናለች፤ በሚዘንበው ዝናም ውኃው ሲበዛባት መሬት ትንቀጠቀጣለች፤ ትርዳለች፤ ገደሉ ይናዳል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹…ደመና ከባሕር ወጣች…›› ተብሎ እንደተጻፈው ሰማይ በደመና ትሸፈናለችና ነጎድጓድ ይሰማባታል፤ መብረቅ ይባርቅባታል፡፡ (፩ኛ ነገ. ፲፰፥፵፬)

ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊትም በወርኃ ክረምት (ሐምሌ) ስለሚከሠተው ተፈጥሮአዊ ድርጊት እንዲህ ገልጧል፤ ‹‹…እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ፤ ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፤ በዝናብ ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል…፤›› (መዝ.፻፴፬፥፯) በረድ ( በረዶ) ይወርድባታል፤ ‹‹…በረድ ዘነበ… ፡፡›› (መዝ.፷፰፥፲፬) ሊቃውንቱ በቅኔ ማኅሌቱ ‹‹…ዑራኤል ለሄኖክ ዘአርአዮ ትእምርተ አምሳልኪ ቤተ ነድ፤ ዘመብረቅ ጠፈራ ወኅብረ በረድ፡፡ በከመ ተነበየኪ ድንግል ጽጌ ነጎድጓድ፤ ያስተበጽዑኪ ኩሉ ትውልድ፤ ወእምኔሆሙ አንሰ ገበርኪ ዋሕድ…፤ ዑራኤል የሚባል መልአክ ለሄኖክ ያሳየው ጣራዋ መብረቅ፣ መልኳ በረድን የሚመስል የእሳት ቤት የምሳሌሽ ምልክት ናት፤ የነጐድጓድ አበባ የሆንሽ ድንግል ሆይ አንቺም ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል ብለሽ እንደተናገርሽ ከእነርሱም አንዱ ነኝና ባሪያሽ አመሰግንሻለሁ›› በማለት ከማኅሌተ ጽጌ አመሥጥረው ነጎድጓድ መባርቅት በሚሰማበት ወቅት ያመሰግናሉ፡፡ (ሄኖ ፬፥፵፭-፶፩፣ ሉቃ.፩.፴፭-፶፣ የሐምሌ ፳፩ ቀን መጽሐፈ ስንክሳር)

በወርኃ ሐምሌ የሚከበሩ ክብረ በዓላት

ሐምሌ አምስት (፭) ቀን በዚህች ቀን ብርሃናተ ዓለም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና እና ቅዱስ ጳውሎስ ዓመታዊ ክብረ በዓላቸው የሚታሰብበት ነው፡፡ የምሥራቹን ወንጌል አስተምረው በጨለማ ይኖር ለነበረው ሕዝብ የወንጌል ብርሃንን በማብራታቸው፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በመመለሳቸው ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም አደባባይ በመስቀል የቁልቁል ሲሰቀል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በሰይፍ ሰማዕተነትን ተቀብለውባታል፡፡ በረከታቸው ይደርብን! (ምንጭ ስንክሳር ወርኃ ሐምሌ)

ሐምሌ ሰባት (፯) ቀን ፈጣሬ ዓለማት ቅድስት ሥላሴ በአበ ብዙኀን አብርሃም ቤት በእንግድነት የገቡበት ዓመታዊ ክብረ በዓል ይከበራል፤ እንግዳን በመቀበል በጎ ምግባርን ያደርግ የነበረን አብርሃምን ሰይጣን በበጎ ምግባሩ ቀንቶ ከቤቱ ሰው እንዳይሄድ ቢያደርግም እንግዳ ቤቱ ባለመምጣቱ ለሦስት ቀን ዓይኖቹ በሰው ረኃብ፣ ሆዱ ምግብ በማጣት የተራበን አብርሃም ቅድስት ሥላሴ በሦስት አረጋውያን ሰዎች አምሳል ተገልጠው በቤቱ በመስተናገድ ልጅ እንደሚወልዱ ያበሠሩበት ዕለት ነው፡፡

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ዳግማዊ ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መታሰቢያው ነው፤ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በርካታ መጻሕፍትን የደረሰ፣ ዐፄ ዳዊት ልጆችን አስተምሮ በምግባር በሃይማኖት አንጾ ዘርዓ ያዕቆብን ለንግሥና ቴዎድሮስ የተባለውን ለቅድስና ሕይወት ያበቃ ታላቅ ሊቅ ነው፡፡ እመቤታችንን እጅግ ይወድ የነበረና አርጋኖን፣ ሰዓታት፣ መዐዛ ቅዳሴ፣ ሕይወተ ማርያም እና ሌሎችንም የምስጋናዋን መጽሐፍ የደረሰ፣ በዘመኑ ለተነሡ መናፍቃን ምላሽ የሰጠ ሊቅ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ በረከቱ ይደርብን! (ምንጭ ስንክሳር ወርኃ ሐምሌ)

ሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ (፲፱) ቀን በዚህች ዕለት የእግዚአብሔር አዳኝነት፣ የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት፣ የቅድስት ኢየሉጣ እና ቅዱስ ቂርቆስ እምነት ጽናት፣ የታየበት የጣዖታት ከንቱነት የተገለጠበት፣ ጠላት ዲያቢሎስ ያፈረበት ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው፡፡ እለእስክንድሮስ የተባለ ጣዖት አምላኪ ንጉሥ ሕዝቡን እያስፈራራ ለጣዖት እንዲሰግዱ ሲያስደርግ ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ለጣዖቱ አንሰግድም በማለት ለቅጣት ወደተዘጋጀው የፈላ ጋን ውስጥ ተጨመሩ፡፡ የሃይማኖት አርበኛ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ መጥቶ የፈላውን ውኃ አቀዘቀዘው እናትና ልጁንም አዳና፡፡ (ድርሰነ ቅዱስ ገብርኤል ወርኃ ሐምሌ)

ሐምሌ ሃያ አንድ (፳፩) ቀን የሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል መታሰቢያ ናት፤ ዑራኤል የስሙ ትርጒም ኦርያሬስ (የፀሐይ ብርሃን) ማለት ሲሆን ዑራኤል የብርሃን መልአክ ማለት ነው፤ ወሀቤ ጥበብ፤ ጥበብን ሰጪ መልአክ ነው፤ በዚህች ቀን የሲመቱ መታሰቢይ ተከብሮ ይውላል፡፡ ረድኤት በረከቱ አይለየን፡፡ (ድርሰነ ቅዱስ ዑራኤል ወርኃ ሐምሌ)

ሐምሌ ሃያ ስድስት (፳፮) ቀን በዚህች ቀን ለእመቤታችን ጠባቂና አገልጋይ ይሆን ዘንድ አደራ የተሰጠው አረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ ዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ ለእመቤታችን ከዘር ሐረግ (ግንድ) ገብቶ ይቆጠር ዘንድ በአደራ ከተቀበላት በኋላ አብሯት በስደት በግብፅ በረሃ ተሰዷል፤ የመከራዋ ተሳታፊ ሆኗል፤ በዚህችም ዕለት ዕረፍቱ ሆነች፡፡ በረከቱን ያድለን፤ አሜን! (ምንጭ ስንክሳር ወርኃ ሐምሌ)

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!