ወርኃ መጋቢት
ክፍል አንድ
መምህር ተስፋ ማርያም ክንዴ
የካቲት ፳፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሰባተኛው ወር ወርኀ መጋቢት ይባላል። መጋቢት በቁሙ “ስመ ወርኅ፣ ሳብዕት እመስከረም፣ የመዓልትና የሌሊት ምግብና ትክክል የሚሆንበት ወርኅ ዕሪና” ማለት ነው። “እስመ ይዔሪ መዓልተ ወሌሊተ አመ እስራ ወኀሙሱ ለወርኀ መጋቢት፤ በመጋቢት ወር ፳፭ ቀን ሌሊቱና መዓልቱ ይስተካከላልና” እንዲል፡፡ (ዲድስቅልያ ፴፣ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፭፻፸፯)
በሌሎች ጸሐፍያን ዘንድ ደግሞ መጋቢት “መገበ፣ ሾመ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ቃል ሲሆን ትርጒሙም “የመመገቢያ ወር” ማለት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህን ትርጒም ያገኘውም በዚህ ወር ገበሬዎች በጎተራ የተሰበሰበውን እህላቸውን እያወጡና እያስፈጩ የሚመገቡበት ወር በመሆኑ ነው ይላሉ። (ኅብረ ኢትዮጵያ፣ ከቴዎድሮስ በየነ አዲስ አበባ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም፣ አንድሮ ሜዳ፣ ገጽ ፫፻፺፭፣ አቡሻክር የጊዜ ቀመር በኢንጅነር አብርሃም አብደላ፣ ገጽ ፵፱)
አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ደግሞ በመዝገበ ቃላቸው ላይ የመጋቢትን ትርጒም እንደዚህ አስቀምጠውታል፦ “የወር ስም፣ ሰባተኛ ወር ይኸውም ጌታ በጸሎተ ሐሙስ ለሐዋርያት ሥጋውንና ደሙን መስጠቱን፣ ዓርብ በሠርክ ዲያብሎስን ሽሮ አዳምን ወደ ቀድሞ ማዕርጉ መመለሱን ያሳያል፡፡” (ደስታ ተክለ ወልድ፤ አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ፲፱፻፷፪ ዓ.ም ገጽ ፯፻፵፮)
በምዕራባውያን አጠራር ደግሞ መጋቢት ወር “አዳር” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህንንም ስም የሰጡት ሮማውያን የጦር አምላክ ብለው ከሚያከብሩት የጣዖት አምልኮ ጋር ተያይዞ ነው። (የብሉይ ኪዳን በዓላትና አጽዋማት አወጣጥ፣ ያልታተመ የእጅ ጽሑፍ) የሮማውያን የዓመታቸው መጀመሪያ ወር መጋቢት ፳፭ እንደነበረ ይታወቃል፤ ይህም ቀን የዐውደ ዓመታቸው መባቻ ነበር። ይህንም ቀን የዐውደ ዓመታቸው መባቻ ያደረጉበት ምክንያት “መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ያበሠረበት፣ ጌታ የተፀነሰበት ነው” በሚል ነው። በኋላ ግን በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አቆጣጠሩ ማስተካከያ ከተደረገበት በኋላ ጥር አንድ ቀን የዓመታቸው መጀመሪያ እንደሚሆን ተወስኖ እስከ አሁን በዚያው ቀጥሏል።
መጋቢት ወር ዓለም የተፈጠረበት ወር ነው። ለዚህ ምስክር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከማምጣታችን በፊት ሰው ቆጥሮ ሊደርስበትና ሊያረጋግጠው የሚችል አቡሻክራዊ ምስክር እናምጣ፤ ለዚህም መነሻ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አንሥተን ወደ ሐሳቡ እንገባለን። ይህም “እስመ ኢየሱስ ክርስቶስ ውእቱ ዘትማልም ወዮም ወክመ ውእቱ እስከ ለዓለም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬም እስከ ዘለዓለም ያው ነው ያለው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ነው።” (ዕብ.፲፫፥፰)
በዚህች መልእክቱ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ “ትማልም” ብሎ የገለጣት እግዚአብሔር ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ መፍጠር የጀመረባት መጋቢት ዕለተ እሑድ ናት። ምክንያቱም በማንኛውም ጊዜ የተነሣ ትውልድ ካለበት ዕለት ተነሥቶ ትማልምን (ትናንት) እየፈለገ ወደ በኋላ ቢሄድ የሚያገኘው ትማልም (ትናንት) የሌላት ትማልምን (ትናንትን) ነው።
ይህችም ዓለም የተፈጠረባት ዕለት መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ማለትም እሑድ የታወቀችው ከላይ እንደገለጽኩት አባቶቻችን እነርሱ የደረሱበትን ዓመተ ዓለም (ዓመተ ፍዳ ሲደመር ዓመተ ምሕረት) እንደገመድ ይዘው ወደኋላ ሲጓዙ የያዙት ዓመተ ዓለም ወይም ቁጥር ሚያዝያ አንድ ቀን አዳም ከተፈጠረበት ከሦስት ቀን በፊት ከምትገኘው ዕለተ ሠሉስ (ማክሰኞ ማግስተ ሰኞ) ያልቃል፡፡ ይህን ዕለትም የቁጥር መጀመሪያ ብለው “ጥንተ ቀመር” ብለውታል፤ ምክንያቱም ለመቁጠር አንድ ብለን የምንነሣበት ዕለት ነውና። ይህችን ዕለት ካገኙ በኋላ ደግሞ ዓለም የተፈጠረው መጋቢት ፳፱ ቀን በዘመነ ዮሐንስ በቀመረ ማርቆስ እሑድ መሆኑን ያውቃሉ፡፡
ከዚህ ላይ “ዘመኑ ዘመነ ዮሐንስ፣ ቀመሩ ቀመረ ማርቆስ መሆኑና እሑድ መሆኑ እንዴት ይታወቃል?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሐተታው ብዙ የሚፈጅ ስለሆነ ለጊዜው ከያዝነው ርእስ ላለመውጣት አቆይተነዋል።
ከዓለም በፊት የሚኖር አምላካችን እግዚአብሔር መጋቢት ፳፱ እሑድ ዓለምን ካለ መኖር ወደ መኖር አምጥቶ ፈጥሯል። ዓለምን ካለ መኖር ለፈጠረ ሁሉን ለሚችል “ቀኝ እጅህ ብዙ ድቦችና ቁጡ አንበሶችን ትልክባቸው ዘንድ አይሣነውምና” እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን (መጽሐፈ ጥበብ ፲፩፥፲፰)፡፡ ዮሐንስም በወንጌሉ መጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ከሆነው ነገር ሁሉ ያለ እርሱ የሆነ የለም ማለቱ ዓለምና በዓለም ያለው ሁሉ በእርሱ እንደተከናወነ ለመግለጽ ነው። ዓለም በ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን በአንድ ዕሪና ተፈጥሮዋል፡፡
ከዚህ ተጀምሮ ሲቆጠር በ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)= አንድ ዕሪና በ፳፰ (ሃያ ስምንት)= ሁለት ዕሪና በ፳፯ (ሃያ ሰባት)= ሦስት ዕሪና በ፳፮ (ሃያ ስድስት)= አራት ዕሪና በ፳፭(ሃያ አምስት)= አምስት ዕሪና በ፳፬ (ሃያ አራት)= ስድስት ዕሪና በ፳፫ (ሃያ ሦስት)= ሰባት ዕሪና ይሆናል፡፡ በዚህ በ፳፫ (ሃያ ሦስት) መዓልት በ፲፬ (ዐሥራ አራት) ሌሊት ረቡዕ ለሐሙስ የፋሲካውን በግ በልተው በበ፲፭ (ዐሥራ አምስት) ሌሊት ሐሙስ ለዓርብ በ፳፬ (ሃያ አራት) መዓልት እስራኤላውያን ከግብጽ ወጥተዋል። (አቡሻክር ትርጓሜ ገጽ ፫፻፶፮)
“ዕሪና” ማለት መተካከል ማለት ሲሆን በዚህ ዐውድ የመዓልትና የሌሊት መተካከል የሚለውን ትርጒም ሲይዝ በ፮፻ (ስድስት መቶ) ዓመትም ጳጉሜን ሰባት በምትሆንበት ጊዜ ያለውን ዓመትም ዕሪና እንደሚለው አቡሻክር ይናገራል፤ ይህን በይበልጥ ለመረዳት መጽሐፈ አቡሻክርን ይመልከቱ።
በዜና እስክንድርና በጊዮርጊስ ወልደ አሚድ ተጽፎ እንደምናገኘው ዓለም በአምስት ክፍል ተከፍላ እናገኛታለን። ከእነዚህም አንደኛው በውስጡ ማንም የማይኖርበት ምድረ በዳ ሲሆን ሁለተኛው ክፍል በምሥራቅ በኩል ሆኖ በውስጡም ዘወትር እሳት የሚነድበት እንሰሳትና አራዊት የማይኖሩበት ነው። ሦስተኛውም እንዲሁ በምዕራብ በኩል ሆኖ በውስጡም ሊሄዱበት የማይቻል ብዙ ቦታ የሚሸፍን ባሕር ያለው ብዙ ደሴቶች ያሉበት ነው።
አራተኛው ክፍል ሁል ጊዜ እንደ በረዶ የረጋ ብርድና ውርጭ የማይለየው ከውርጩም ብዛት የተነሣ እንሰሳትና አራዊት የማይኖሩበት ክፍል ሲሆን የመጨረሻውና አምስተኛው ክፍል የምድር መካከል ነው፤ በእርሱም ክፍል ፍጥረት ሁሉ ይኖሩበታል፤ ይህም ለሰባት ክፍል ተከፍሎ ሰባት አህጉር የምንለው ነው፤ ይህም ክፍል ከአራቱ ክፍል ይልቅ ከፍ ያለ እንደሆነ ይነገራል።
፸፻ (ሰባት ሺህ) ዘመን በሰባቱ ዕለታት ተገኝተዋል፤ “ዓለም ብሂል ፯ቱ ዕለታት ውእቱ” እንዲል፤ “ወተውህቦን እግዚአብሔር ሰቡአ መዋዕለ ለእጓለ እመሕያው ከመ ይንበር በዲበ ምድር፤ በምድር ላይ ይኖር ዘንድ እግዚአብሔር ለአዳም ሰባት ቀኖችን ሰጠው” እንዲል፤ “ወሶበ ፈትሐ ሳብዓየ ማኅተመ አርመመ ኩሉ ፍጥረት ዘበሰማይ ወዘበምድር፤ ሰባተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ በምድርም በሰማይም ያለው ፍጥረት ሁሉ እኩል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ” እንዳለ ዮሐንስ በራእዩ፡፡ (ራእይ ፰፥፩)
ጠቢቡ ሰሎሞን ፲፩ ሲራክ አንድምታ ፵፫ “ወኀተምክዋ ለምድር በሰባቱ ማኅተሚሃ፤ ሰባተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ በምድርም በሰማይም ያለው ፍጥረት ሁሉ እኩል ሰዓት የሚህል ዝምታ በሰማይ ሆነ” እንዳለ፡፡ (ራእይ ፭፥፩)
“በሰባት ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ” እንዳለ ዓለም በሰባት ትከፈላለች፤ እነርሱም ዓለመ እሳት፣ ዓለመ ነፋስ፣ ዓለመ መሬት፣ ዓለመ ውኃ፣ ዓለመ በረድ፣ ዓለመ ግሩማን አራዊት (በድምፅ ብቻ ሰውን የሚገሉ አራዊቶች የሚኖሩበት) እና ዓለመ ብሄሞት ወሌዋታን ናቸው።
ይቆየን!