‹‹ወልድ ተውህበ ለነ›› (ኢሳ.፱፥፮)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ታኅሣሥ ፳፰፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
የሰው ልጅ ሕግ ተላልፎና ትእዛዝ ጥሶ ከገነት ወደ ምድር በተሰደደ ጊዜ ጠላት ዲያቢሎስ በመከራ አስጨንቆ ገዛው፤ ቅዱስ ማቴዎስ በጻፈልን የምሥራች ወንጌል ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባሕር የመጠመቁን ምሥጢር እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምሥጢሩን የገለጠላቸው አበው መተርጉማነ ሲያብራሩልን ‹‹… ዲያብሎስ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ በአዳምና በሔዋን ሥቃይ አጸናባቸው፤ “ስመ ግብርናታችሁን (የባርነታችሁን ስም ጽፋችሁ ብትሰጡኝ ሥቃያችህን ባቀለልሁላችሁ ነበር” አላቸው፤ “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ፤ አዳም የዲያብሎስ ባሪያ ሔዋን የዲያብሎስ ባሪያ” ብለው ጽፈው ሰጡት …አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎታል…፡፡›› (ማቴ.፫፥፲፫ አንድምታ)
አዳምና ሔዋን ሕይወታቸውን ጨለማ ወርሰው በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦልን፣ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን አስፈረደባቸው፤ እነርሱም ልጆቻቸውም በባርነት ቀንበር ተያዙ፤ አዳምም ስለ በደሉ ተጸጽቶ በንስሐ ከተመለሰ በኋላ እግዚአብሔር ‹‹…በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እም ወለተ ወለትከ…›› አምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን) ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው›› የሚልን የተስፋ ቃል ሰጠው፤ ዳግመኛም እርሱንና ዘሮቹን ልጆቹ እንደሚያደርጋቸው ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡ (ማቴ.፲፪፥፵፪ አንድምታ)
አዳም ከነልጆቹ የቀጠሮው ቀን እስኪደርስ በነበረው ዘመን የዲያብሎስ ባሮች የሲኦል ምርኮኞች ሆነው መኖር ጀመሩ፤ ጽድቃቸው ዋጋ አጥቶ፣ የከበባቸው ጨለማ እንዲርቅላቸው በጾም በጸሎት ሁነው ተስፋው እውን እንደሆነ እንደሚፈጸም አምነው “ወልድ ተውህበ ለነ፤ ወልድ ተሰጠን በማለት ተማጸኑ! (ኢሳ.፱፥፮) ሱባኤው ተፈጽሞ፣ ትንቢቱ ደርሶ ምሳሌው እውን የሆነ ጊዜ ከዳግሚት ሰማይ፣ የጽድቅ ፀሐይ መውጫ ከሆነች ከአማናዊት ምሥረቅ ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የኤፍራታ ክፍል በሆነች በቤተ ልሔም ተወልዶ በይቅርታው በቸርነቱ ብዛት ወደ እርሱ አቀረበን፤ ከወደቅንበት አነሣን፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹…ሕፃን ጌታ ተወለደልን…›› በማለት እንደገለጸው በሞቱ ሞታችንን ገድሎ የልጅነት ክብራችንን የሚመልስልን ጌታ ተሰጠን ለዚህም ነው፤ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ‹‹…በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና…›› በማለት የመሠከረው፡፡ (ዮሐ.፫፥፲፮)
የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎሬዎስም በትምህርቱ እንዲህ ይለናል፤ ‹‹…እኛ ግን በፈቃዳችን የጠላታችን የዲያብሎስን ማታለል በመቀበላችን ከሕይወት ሞትን ከተድላ ደስታ ኃሣርን መረጥን፤ ወደን በሠራነው ኃጢአት ፍጻሜ ወደ ሌለው ወደ ዘለዓለም ኩነኔ በሚወስድ በሚጎዳ መካራ ውስጥ ወደቅን፤ እርሱስ ፈጽሞ አልተወንም፤ በከሃሊነቱ ተቀበለን እንጂ፤ በይቅርታው በቸርነቱ ብዛት ወደ እርሱ አቀረበን እንጂ፤ እንግዲህ ወዲህ የእጆቹ ፍጥረቶች ወድቀን እንድንቀር አልወደደም፤ በቸርነቱ በይቅርታው ብዛት የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠረበት አካላዊ ቃሉን ላከልን እንጂ፤ የሚታዩት ያላቸው የሚዳሰሱት ፍጥረቶች ናቸው፤ የማይታዩት ያላቸው ረቂቃን መላእክት ናቸው፤ በከበሩ በነቢያት ቃል አስቀድሞ እንዳናገረ ከተመሰገኑ ከሦስቱ አንዱ አካል ቀዳማዊ ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ተዋሐደ፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎሬዎስ ምዕራፍ ፴፮፥፲፬-፲፯)
ጌታችን በተወለደ ጊዜ ልዑለ ቃል ነቢየ ኢሳይያስ ‹‹ወልድ ተውህበ ለነ›› በማለት እንደተናገረው ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ወልድ ሲወለድልን የጨለማው የሰው ልጆች ሕይወት በራ፤ ቤተ ልሔም አቅራቢያ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ ለነበሩ እረኞች እስካሉበት ቦታ ድረስ ባሕረ የብርሃን ወንዝ (የብርሃን ጎርፍ) ፈሰሰላቸው፤ በአዳምና ሔዋን በደል ምክንያት በሰዎችና በቅዱሳን መላእክት መካከል የነበረው የጠብ ግድግዳ ፈርሶ፣ ሰላም ተመልሶ ፍቅር ነግሦ በአንድ ላይ ሆነው ምሥጋና የባሕርይው ገንዘቡ ለሆነ ፈጣያቸው በተፈጠሩበት ዓላማ መሠረት አዲስ ምሥጋንን አቀረቡ፡፡ ‹‹መላእክት ከኖሎት ኖሎት ከመላእክት ጋር አንድ ሆነው አመስግነዋል፡፡›› (ሉቃ ፪፥፲፬ አንድምታ) ብርሃናውያን መላእክት በጨለማ ላለው አዳምና ልጆቹ ከጨለማ የሚያወጣቸው ወልድ በተሰጣቸው (በተወለደላቸው) ጊዜ ተደስተው ‹‹..ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡›› (ሉቃ.፪፥፲፫)
በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የአዳምና የልጆቹ ታሪክ ተቀይሯል፤ ዓመተ ፍዳ በዓመተ ምሕረት ተተካ፤ አዳም ባርነቱ ቀርቶ ዳግመኛ የልጅነት ሥልጣን ተሰጠው፤ ‹‹…በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው…፡፡›› (ዮሐ.፩፥፲፪)
መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ ከወደቅንበት ተነሣን፤ ዝቅ ካልንበት ከፍ አልን፤ ባርነቱ ቀርቶ ነጻነትን ተጎናጸፍን፤ ‹‹…በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን…፡፡›› (ገላ.፭፥፩) በመወለዱ ከጨለማ ወደ ብርሃን መጣን፤ ‹‹..እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ የንጉሥ ካህናት ቅዱስ ሕዝብ ለርስቱ ተለየ ወገን ናችሁ፤ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን ምሕረት አግኝታችኋል፡፡›› (፩ኛ ጴጥ. ፪፥፱)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ ክብር አጥተን የመርገም ጨርቅ ሆኖብን የነበረው ጽድቃችን ዋጋን አገኘ፤ ‹‹…መልካሙን ገድል ተጋድያለው፤ ሩጫዬን ጨርሻለው፤ ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡ (፪ኛ ጢሞ.፬፥፯) ድካማችን፣ እምነት ምግባራችን ዋጋን አግኝቶ የክብሩ ወራሾች ለመሆን በቃን፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ ኑረንም (ቆመውም) ሙተንም የዲያብሎስ ገንዘቦች፣ የሲኦል ምርኮኞች የነበርን የሰው ልጆች የእግዚአብሔር ሆንን፤ ‹‹…በሕይወታችን ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፡፡›› (ሮሜ ፲፬፥፰) ሞት ሰልጥኖባቸው፣ ሕይወት ርቋቸው የነበሩ የሰው ልጆች በሞት ላይ የሚፎክሩ፣ ከሞት በኋላ ሕይወት፣ ከመቃብር በስተጀርባ ትንሣኤ እንዳለ አምነው፤ ‹‹…ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ…›› በማለት የሚዘምሩ ሆኑ፡፡ (፩ኛ ቆሮ.፲፭፥፶፭)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ የጠላታችን ክፉ መልክ እውን ሆኖልን ልናየው እንናፍቅ፤ የነበረውን ፈጣሪያችንን እግዚአብሔር ወልድ ከድንግል ማርያም ተወልዶ አየነው፤ ዳሰስነው፤ ‹‹..በዓይናችን ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን…›› እንዲል ቅዱስ ቃሉ፡፡ (፩ኛ ዮሐ.፩፥፩) ‹‹ወልድ ተውህበ ለነ›› በተሰጠን (በተወለደልን ወልድ ጥላቻ በፍቅር፣ በደል በይቅርታ፣ ባርነት በልጅነት፣ ጨለማ በብርሃን፣ ውርደት በክብር፣ ዓመተ ፍዳ በዓመተ ምሕረት ተለውጧል (ተተክቷል)፤ በተወለደው ሕፃን ሰውና እግዚአብሔር፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ሰውና መላእክት፣ ነፍስና ሥጋ ታርቀዋል፡፡
‹‹ከሕሊና ሁሉ ለራቀ ለዚህ ድንቅ ምሥጢር አንክሮ ይገባል፤ ምድራዊ ሴት ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃልን ወለደችው፤ ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠረ፤ ከእርሷም እርሱ የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ፡፡ ተዋርዶ በእኛ ባሕርይ ተወለደ፤ እርሱም እኛን ስለ መውደዱ ፈጠረን፤ በእኛ ባሕርይ ወለደችው፤ ፈጣሪም እንደሆነ ታወቀ›› እንዲል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤፍሬም ምዕራፍ ፵፯፥፪-፫)
ውድ ክርስቲያኖች! ይህ የሰው ልጅ ታሪክ የተቀየረበትን ዕለት በደስታ፣ በፍቅር፣ የተጣላን ታርቀን ፣የበደልን ክሰን፣ በኃጢአት ያደፈ ሕይወታችን በንስሐ አንጽተን፣ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ሕይወታችንን አስቀድሰን እናክብረው!
መልካም በዓል!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
አሜን!!!