ክብረ ሰሙነ ሕማማት – ክፍል አንድ
በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና (የሊቃውንት ጉባኤ አባል)
ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ሰሙነ ሕማማት ሰሙነ ስቅለትም ይባላል፡፡ ይኸውም ከሆሣዕና ማግስት (ከሰኞ) ጀምሮ እስከ ዓርብ ስቅለት ያለው ክፍለ ጊዜ ሲኾን ይህም ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ‹‹እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡ ስለ እኛም ታመመ፡፡ እኛም እንደ ታመመ፣ እንደ ተገረፈ ቈጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፡፡ የሰላማችንም ተግሣፅ በእርሱ ላይ ነበረ፡፡ በእርሱም ቊስል እኛ ተፈወስን፤›› በማለት ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ገለጸው (ኢሳ. ፶፫፥፬-፭)፣ ሰሙነ ሕማማት የክብርና የሥልጣን ዅሉ ባለቤት፣ ዅሉን ቻይ፣ ኃያል የኾነው አምላክ እኛን ከመውደዱ የተነሣ የእኛን ዕዳ ለመክፈል በመስቀል እስከ መሞት ድረስ እጅግ ከባድና አሰቃቂ የኾነ መከራ በፈቃዱ የተቀበለበት ሰሙን ከመኾኑም ባሻገር እኛ ፍጹም ድኅነትን ያገኘንበት ጊዜ ነው፡፡
ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ጌቴሴማኒ ይዞ ከሔደ በኋላ ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ ‹‹ሰውነቴ እስከ ሞት ድረስ አዘነች፤›› እያለ ወዙ እንደ ውኃና እንደ ደም እስኪወርድ ድረስ እየወደቀ እየተነሣ በስግደት በኀዘን እንደ መሠረተው ዅሉ፣ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ የኾነ ክርስቲያን በሙሉ በኀዘን፣ በለቅሶ እየሰገደ የፈጣሪውን ውለታ የሚያስብበት፤ ለፈጣሪው ያለውን ፍቅር የሚገልጥበት ወቅት ነው – ሰሙነ ሕማማት (ማቴ. ፳፮፥፴፰፤ ማር. ፲፬፥፴፬፤ ሉቃ. ፳፪፥፵፬)፡፡ ‹‹… ክርስቶስ ተሰቅለ በሥጋሁ በእንቲአነ ወአንትሙኒ ተወልተዉ በይእቲ ሕሊና እስመ ዘሐመ በሥጋሁ ድኅነ እምኃጣውኡ፤ ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋው ከተሰቀለ እናንተም ይህችን አሳብ ጋሻ አድርጋችሁ ኑሩ፡፡ በሥጋው መከራ የተቀበለ ከኃጢአት ድኖአልና፤›› በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ አጥብቆ የመከረን ስለዚህ ነው (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፩)፡፡
የሚገባ ስግደት
ስግደት የአምልኮ ስግደት እና የአክብሮት ስግደት ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ እኛ ኢያሱ ለመልአኩ እንደ ሰገደ ዮሐንስ፤ ወንጌላዊም እንደዚሁ ለመልአኩ መላልሶ እንደ ሰገደ እግዚአብሔር አምላክ ላከበራቸው ቅዱሳን መስገድ ያከበራቸው እግዚአብሔርን ማክበር መኾኑን አውቀን የአክብሮት ስግደት ስንሰግድላቸው ያልገባቸው ሰዎች ከኢያሱና ከዮሐንስ በላይ ለእግዚአብሔር አምልኮት ተቈርቋሪ በመምሰል ይዘብቱብናል፤ ባይገባቸው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎችም እንደዚሁ ‹‹በሰሙነ ሕማማት ሌሎች በዓላት ተደርበው ሲውሉ ስግደት አይገባም፤›› እያሉ ሕዝቡን በየጊዜው ያደናግራሉ፡፡ በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ‹‹በጌታችን በዓል፣ በእመቤታችን በዓል ሥጋ ወደሙ ከተቀበሉ በኋላ ሰጊድ አይገባም፤›› ይልና በጌታ በዓል አድንኖ፤ በእመቤታችን በዓል አስተብርኮ በቅዱሳን በዓል ሰጊድ ይላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሐተታ ለየትኛው ስግደት እንደ ተነገረ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
አንደኛ የሕማማት ዝርዝር ኹኔታ የተጻፈው በአንቀጸ ጾም ነው፤ ይህ ሐተታ ግን የሚገኘው በአንቀጸ ጸሎት ነው፡፡ ከሕማማት ጋር ፈጽሞ ግንኙነት የለውም፡፡ ሁለተኛ ፍትሕ መንፈሳዊ በአንቀጽ ፲፭ ሐተታውን ሲጀምር ‹‹ወዘይጼሊ ቅድመ ይስግድ ወበዘይበጽሕ ዝክረ ሰጊድ ለእግዚአብሔር ልዑል በጊዜ ጸሎት›› በማለት የሚጸልይ ሰው አስቀድሞ (በመጀመሪያ) አንድ ጊዜ ወይም ሦስት ጊዜ ሰጊድን ከሚያነሣ አንቀጽ ላይ ሲደርስ፣ ለአብነትም ‹‹ንሰግድ ለከ ኦ ዘለከ ይሰግድ ኵሉ ብርክ፤ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ፤ ንሰግድ ለከ ክርስቶስ፤ እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐተ ስግደተ፤ እሰግድ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ፤ እሰግድ ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ›› የመሳሰለ ንባብ ሲያጋጥም መስገድ እንደሚገባ ያዛል፡፡
ስለዚህ በግል ጸሎት ጊዜና በንስሓ ወቅት ስለሚሰገደው ስግደት ወይም አንድ ባሕታዊ ፆር እንዳይነሣብኝ ብሎ፤ ምእመናን ክብር ለማግኘት ብለው ስለሚሰግዱት ስግደት የተወሰነውን ሥርዓት ከሕማማት በዓል አከባበር ጋር ያለ ስፍራው ማምጣት ስሕተት ነው፡፡ ምክንያቱም ሰሙነ ሕማማት ዓርብ ስቅለትን ጨምሮ ከጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ በዓሉ ደግሞ የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴ ሳይኾን ባለቤቱ በመሠረተው በኀዘን፣ በጸሎት፣ በልቅሶ፣ በስግደት ነውና፡፡ ስለኾነም ማንኛውም በዓል የዓመትም ይኹን የወር በዓል ከሕማማት ጋር ቢገጥም እንኳ አልፎ ከፋሲካ በኋላ ይከበራል እንጂ በሕማማት ውስጥ አይከበርም፡፡ ስግደትም አይከለከልም፡፡ ታዲያ በዓሉ ቦታውን ለቆ ሒዶ እያለ የሕማማትን ስግደት እንዴት ያስቀራል?
መጽሐፉ በጌታችን በዓል ‹አድንኖ›፤ በእመቤታችን በዓል ‹አስተብርኮ› ብሎ በቅዱሳን በዓል ‹ስግደት› ነው የሚለው፡፡ እንኳን በሰሙነ ሕማማት የቅዱሳን በዓላት በሚውሉባቸው ሌሎች ዕለታትም ስግድት መስገድ አይከለከልም፡፡ እነዚያ በግምት የሚነጉዱ ሰዎች ግን ‹‹የቅዱሳን በዓል በሕማማት ሲውል አይሰገድም፤›› እያሉ ችግር ሲፈጥሩና ‹‹እገሌ በበዓል ጊዜ ይሰግዳል ይላል፡፡ መናፍቅ ነው፤›› እያሉ የእውነተኞችን መምህራን ስም ሲያጠፉ ይስተዋላሉ፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው አካል ተዉ ሲላቸው ካልተመለሱ ጥብቅ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
ጉዳት ያለው ሰላምታ
በመሠረቱ ሰላምታ በቁሙ ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ደኅንነት፣ ተድላ፣ ደስታ፣ ሰላምታ፣ ቡራኬ፣ የምርቃት ቃል፣ ሰው ሲገናኝ ወይም ሲለያይ የሚናገረው የሚፈጽመው ተግባር ነው (መጽሐፈ ሰዋስው ዘኪዳነ ወልድ)፡፡ ስለኾነም ሰላም በየትኛውም ቦታ፣ በማንኛውም ጊዜ ለዅሉ የሚበጅ፤ ከዅሉም በላይ እጅግ ጠቃሚ ተግባር ነው፡፡ ጎጂና በጣም ክፉ ወይም አደገኛ ኾኖ የተገኘው የጥፋት ልጅ የተባለው የይሁዳ ሰላምታ ነው፡፡ ‹‹ይህንንም ሲነግራቸው ሕዝቡ ደረሱ፤ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ይሁዳ ይመራቸው ነበር፡፡ ወደ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ ሳመው፤ የሰጣቸው ምልክት ይህ ነበር፡፡ ‹የምስመው እርሱ ነውና አጽንታችሁ ያዙት፤› አላቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ‹ይሁዳ! የሰውን ልጅ በመሳም ታስይዘዋለህን? ልታስገድለው አይደለምን?› አለው›› (ሉቃ. ፳፪፥፵፯-፵፰፤ ማቴ. ፳፮፥፵፯-፶፮፤ ማር. ፲፬፥፫-፶፤ ዮሐ. ፲፰፥፫-፲፪)፡፡
ጌታችን በዚህ ኹኔታ ከተያዘ በኋላ ነው እስከ ሞት ድረስ ያን ዅሉ መከራ የተቀበለው፡፡ ስለኾነም ከሰሙነ ሕማማት እስከ በዓለ ትንሣኤ (ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን) እስከሚባል ድረስ መስቀል ወይም መጽሐፍ መሳለም እንዳይገባ ‹‹ወኢይትአምኁ በበይናቲሆሙ ዘእንበለ በዕለተ ፋሲካ ወኢየአምኁ መስቀለ ወወንጌለ፤ ያለ ፋሲካ ቀን እርስ በእርሳቸው አይሳሳሙ፤ መስቀልንና ወንጌልንም አይሳለሙ፤›› ተብሎ ተደንግጓል (ፍት.መን. ገጽ ፪፻፳፯)፡፡ ጸዋትወ ዜማም ‹‹ይሁዳ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ ሳመው ወይም በመሳም ስላስያዘው እርስ በርሳቸው አይሳሳሙ፤ ወንጌልንና መስቀልንም አይሳለሙ፡፡ የሞቱትንም ሰዎች አይፍቱ፤›› ይላል (ገጽ. ፺፬-፺፯)፡፡
በግብረ ሕማማት ገጽ ፵፯ እና ፭፻፺፭ ‹‹ወኢይትአምኁ በበይናቲሆሙ ወኢይአምኁ ወንጌለ ወመስቀለ በእንተ ዘአምኆ ይሁዳ ወኢይዝክሩ ሰሞሙ ለእለ ኖሙ ቅዱሳን አበው ወኢይበሉ ሐዳፌ ነፍስ›› ይላል፡፡ ይህ ትእዛዝ በእነዚህ ዅሉ መጻሕፍት እየተደጋገመ መጠቀሱ ለአጽንዖተ ነገር ነው፡፡ በሰሙነ ሕማማት እርስበርስ መሳሳም፣ መስቀል ማሳለምና መሳለም ከይሁዳ ሰላምታ ጋር የተያያዘ ስለኾነና የይሁዳ ተባባሪ ስለሚያሰኝ እስከ ትንሣኤ ድረስ መሳሳምም ኾነ ወንጌልንና መስቀልን መሳለም ተከልክሏል፡፡
ይቆየን