«ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው፤» (መዝ.፻፲፭፥፭)
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
«ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው»፤ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ስለሕዝቅያስ በተናገረው በዚህ ኃይለ ቃል ሊያስረዳን የፈለገው የነፍስ ከሥጋ መለየት ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ውጣ ውረድ፣ ድካም ካለበት ዓለም ውጣ ውረድ ድካም ወደሌለበት ዓለም መሄድ ነውና። ስለሆነም እንደ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ በዚህች ዕለት የቅዱሳን ዕረፍት ነው እየተባለ ይነገራል። ድካም ካለበት ድካም ወደሌለበት ስለሆነ ዐረፈ ወይም ዐረፈች እየተባለ ይነገራል። በነሐሴ ፳፬ በዓለ ዕረፍቱን የምናከብረው ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዐረፈ እንጂ ሞተ አይባልም፤ ሞቱ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነውና።
በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያን የቅዱሱን በዓለ ዕረፍት ምክንያት በማድረግ እግዚአብሔርን ከምታመሰግንበት ያሬዳዊ ዜማ እንጥቀስ። «ሞቶሙሰ ለጻድቃን ሕይወቶሙ ውእቱ እስመ ለጻድቅ ይትሌዓል ቀርኑ በክብር ጻድቃን እለ አሥመርዎ ለእግዚኦሙ ምድረ ብርህተ ወጽዕዱተ ይወርሱ፤የጻድቃን ሞታቸው ሕይወታቸው ነው። የጻድቅ ክብሩ ከፍ ከፍ ይላልና። ጌታቸውን ደስ ያሰኙት ጻድቃን ብርህትና ጽዕዱት የሆነች ምድርን ይወርሳሉ» (ቅዱስ ያሬድ)።
እንግዲህ ከላይ በተጠቀሰው ቃለ እግዚአብሔር መሠረት ሞታቸው ሕይወታቸው ነው የተባለ በመጀመሪያ ደረጃ ሞተ ሥጋ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ጻድቃን ሞተ ሥጋን እንጂ ሞተ ነፍስን ሊያዩ አይችሉም። ሞተ ነፍስን የሚያዩ ከሆነ ጥንቱኑ ጻድቃን ሊባሉም አይችሉም። ሞተ ሥጋቸው ግን ወደ ተሻለውና ወደሚበልጠው ዓለም የሚሄዱበት ስለሆነ ሕይወታቸው ነው ተባለ።
ሌላው ደግሞ የጻድቃን ሞት እንጂ የኃጥአን ሞት ሕይወት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ኃጥእን ምንም እንኳ ወደማያልፈው ዓለም የሚሄዱ ቢሆንም መከራ ወደ አለበት፣ ሥቃይ ወደሚበዛበት እንጂ ዕረፍት ወደአለበት መሄድ አይችሉም። መከራና ሥቃይ የሚበዛበት ዓለም መሄድ ደግሞ ሕይወት ሊባል አይችልም። እንዲያውም ነቢዩ ዳዊት «ሞቱ ለኃጥእ ጸዋግ፤የኃጥእ ሰው ሞት ክፉ ነው» (መዝ.፴፫፥፳፩) በማለት አስረድቷል። ጻድቃን ሞተ ሥጋን እንጂ ሞተ ነፍስን አያዩም። ኃጥኣን ግን ሞተ ሥጋም ሞተ ነፍስም ያገኛቸዋል። ስለዚህ ለኃጥእ ሰው ሞተ ሥጋውም ሆነ ሞተ ነፍሱ ክፉ እንጂ መልካም የሚባል አይደለም።
ሞት የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትእዛዝ በመተላለፍ የሰለጠነበት ነው። «በሕይወታችሁ ስሕተት ለሞት አትቅኑ፤በእጃችሁም ሥራ ጥፋትን አታምጡ። እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና፤ የሕያዋንም ጥፋት ደስ አያሰኘውምና። ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረቱን ፈጥሮአልና፣ የዓለም መፈጠርም ለድኅነት ነውና፣ በእነርሱም ዘንድ የጥፋት መርዝ አልነበረምና፣ ለሲኦልም በምድር ላይ ግዛት አልነበረውምና። ጽድቅ አትሞትምና። ክፉዎች ግን በእጃቸውና በቃላቸው ጠሩት ባልንጀራም አስመሰሉት። በእርሱም ጠፉ። የእርሱ ወገን መሆን ይገባቸዋልና ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ» (ጥበ.፩፥፲፪-፲፯) በማለት መፍቀሬ ጥበብ ሰለሞን ነግሮናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ሃይማኖትና ምግባር የማይነጣጠሉ እንደሆኑ በምሳሌ ሲያስተምር የጠቀሰው የነፍስና የሥጋን ህልውና ነው። «ከመ ሥጋ ዘአልቦ መንፈስ ምውት ውእቱ ከማሁ ሃይማኖትኒ እንተ አልባቲ ምግባረ ሠናይ ምውት ይእቲ ለሊሃ፤ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው» (ያዕ.፪፥፳፮) እንዲል፤ ስለዚህ ነፍስ ያለሥጋ ሥጋም ያለ ነፍስ ህልውና አይኖራቸውም። ይህ ማለት በሰውነት ህልውና እንጂ ነፍስና ሥጋ ተለያይተው ነፍስም በገነት ወይም በሲኦል ሥጋም በመቃብር አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም የሥጋ ሞት የሚባለው የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው። ይህ የነፍስ ከሥጋ መለየት የጻድቅ ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው።
ነፍስ በባሕርይዋ የምትሞት አይደለችም፤ ሞተ ነፍስ የሚባለው የማትኖርበት ጊዜ ስላለ ሳይሆን ከምትኖርበት ሁኔታ አንጻር ነው። ይህ ማለት ነፍስ በሃይማኖት ጸንታ በምግባር ቀንታ ባለመኖሯ ወደ ሲኦል በኋላም ገሃነመ እሳት ትወርዳለች። የነፍስ ሞት ማለት ገነት በመግባት ፈንታ ሲኦል፣ መንግሥተ ሰማያት በመግባት ፈንታ ገሃነመ እሳት መግባት ነው። «ድል የነሣው ሁለተኛውን ሞት አያይም» (ራእ.፪፥፲፩) ተብሎ የተጻፈው ነፍስ ከሥጋ መለየትን ሳይሆን ገሃነመ እሳት መውረድን አያይም ለማለት ነው።
ሞት ማለት መለየት ነውና ነፍስ ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር ተለይታ ካልፈጠራት ከዲያብሎስ ጋር መኖር ስትጀምር የነፍስ ሞት ይባላል። ሁለተኛ ሞት የተባለውም ፈጣሪ ያዘጋጀውን መንግሥተ ሰማያት አጥታ በኃጢአቷ ምክንያት ገሃነመ እሳት መውረድ ነውና «ድል የነሣው ሁለተኛውን ሞት አያይም» ማለት ከላይም እንደተገለጸው ገሃነመ እሳት አይገባም ማለት ነው።
በአጠቃላይ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት «የጻድቅ ሰው ሞት ክቡር ነው» ሲል ሞተ ሥጋን አያይም ማለት ሳይሆን ሞተ ነፍስን አያይም ማለት እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ደግሞ ሞተ ሥጋን መቅመስ የግድ ነውና ይህ እንደ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት መንግሥተ ሰማያትን የሚወርስበት ሞት ክቡር ነው፤ሕይወት ነው፣ ዕረፍት ነው እያለ ይገልጸዋል፡፡ እኛም ንስሓ ገብተን ሥጋውን ደሙን በልተን እንደዚህ በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ለተባለው ሞት እንዲያበቃን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የጻድቁ የተክለ ሃይማኖት ረድኤት በረከት አይለየን፤ አሜን።