ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር

ክፍል ሁለት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሐምሌ ፲፭፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ክረምቱንስ እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? የዚህን ዓመት የትምህርት ጊዜ ጨርሳችሁ ዕረፍት ላይ ናችሁና በዚህ ወቅት ከቤት ስትወጡ፣ ከቦታ ቦታ ስትንቀሳቀሱ በጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡ ከበድ ያለ ዝናብ ሲጥል ድንገት ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ሁሉን በጥንቃቄ ልናደርገው ይገባል፤ ደግሞም ይህንን ወቅት ቴሌቪዥን ብቻ በማየት ወይም በጨዋታ ማሳለፍ የለብንም፤ ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ሊረዱን የሚችሉ መጻሕፍትን ልናነብ ይገባል እንጂ፡፡

ሌላው ደግሞ በአቅራቢያችሁ ባለው ቤተ ክርስቲያን በመሄድ የአብነትና የሥነ ምግባር ትምህርት መማር አለባችሁ፤ ልጆች! ባሳለፍነው የትምህርት ዘመን ጥሩ ውጤት ያላመጣን ካለን በሚቀጥለው በርትቶ በመማርና በማጥናት በመጪው ዓመት የፈተና ወቅት ጥሩ ውጤት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ መልካም!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ባለፈው ስለ መልካም ምግባራት ተምረናል፤ እንዲሁም ከመልካም ምግባራት (ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር) መካከል ስለ ፍቅርና፣ ስለ መታመን ተምረን ነበር፤ ለዛሬ ደግሞ ስለ መታዘዝና ይቅርታ እንማራለን፡፡

መታዘዝ

መታዘዝ “እሺ ማለት፣ የተሰጠን ኃላፊነት መፈጸም” ነው፡፡ በትእዛዝ ውስጥ “አድርጉ” እና “አታድርጉ” የሚሉ መልእክቶች (መመሪያዎች) አሉ፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር እንድንፈጽመው (እንድናደርገው) ያዘዘን እንዳለ ሁሉ እንዳናደርገው ያዘዝን ትእዛዝም አለ፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ “አትስረቅ” የሚል ትእዛዝ እንዳናደርገው (ስርቆትን እንዳንፈጽመው) የተከለከልነው ትእዛዝ ነው፡፡ እንድናደርገው ከታዘዝነው ትእዛዝ ለአብነት (ለምሳሌ) ብንመለከት ‹‹ሰንበትን አክብር ….ባልንጀራህን ውደድ…›› እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የታዘዙትን መፈጸም በረከትን ያሰጣል፤ አለመፈጸም ደግሞ መርገምን (መከራን) ያመጣል፤ ቅዱስ ጳውሎስ ኤፌሶን በምትባል አገር ላሉ ምእመናን ጽፎ በላከላቸው አባታዊ ምክሩ ልጆች ለወላጆቻችን መታዘዝ እንዳለብን መክሮናል፤ ለወላጅ መታዘዝ ምርቃትን ያሰጣል፤ ለወለዱን፣ እኛን ተንከባክበው የሚያስፈልገንን እያሟሉ፣ ለሚያሳድጉን ወላጆቻችንን “እሺ” ብለን መታዘዝ ይገባል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ተጽፎልናል፤ ‹‹የአባት ምርቃት የልጅን ቤት ያጸናልና፤ የእናት እርግማን ግን ሥር መሠረትን ይነቅላል…፡፡›› (መጽሐፈ ሲራክ ፫፥፲) ጠቢቡ ሰሎሞን እናትና አባቱን አክባሪ፣ ትእዛዛቸውን ፈጻሚ ልጅ እንደነበረና ስላገኘው ጥቅም እንዲህ ሲል ይነግረናል (ይመክረናል)፡፡ ‹‹…እኔ አባቴን የምሰማ ልጅ ነበርሁና በእናቴም ዘንድ እወደድ ነበር፤ ያስተምረኝም ነበር፤ እንዲህም ይለኝ ነበር፤ ልብህ ቃሌን ይቀበል፤ ትእዛዜን ጠብቅ፤ በሕይወትም ትኖራለህ…፡፡›› (ምሳሌ ፬፥፫)

በታዛዥነታቸው አብነት ከሚሆኑን ቅዱሳን አንዱን እንመልከት:-

ለታዛዥነት ምሳሌ ከሚሆኑ አባቶቻችን አንዱ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ነው፤ የተወለደው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ነው፤ ቁመቱም በጣም አጭር ጽድቁ ግን ከሰማይ የደረሰ ታላቅ ቅዱስ አበት ነው፡፡ ወላጆቹ መልካም የክርስትና ሕይወትን፣ ሃይማኖትን፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርን እያስተማሩት አደገ፤ ፲፰ (ዐሥራ ስምንት) ዓመት ሲሞላው የታላቁ አባ ባይሞን ደቀ መዝሙር ሆኖ የተጋድሎን ትምህርትን ተማረ፤ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በወቅቱ ከነበሩት ቅዱሳን በትሕትናው፣ በትዕግሥቱና በመታዘዙ ይታወቅ ነበር፡፡

መምህሩ አባ ባይሞን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ ተፈልጦ የደቀቀ ደረቅ እንጨት ሰጠውና ‹‹ትከለውና እንዲያፈራ አድርገው፤ ከዚያም ፍሬውን አምጥተህ አብላኝ!›› አለው፤ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ‹‹እሺ›› ብሎ ወስዶ ተከለው፤ ለሁለት ዓመታትም ከገዳሙ ፲ (ዐሥር) ኪሎ ሜትር ከሚርቅ ቦታ ላቡ ጠብ እስኪል ውኃ እየቀዳ አጠጣው፤ በሦስተኛው ዓመት ለምልሞ አበበ፤ ፍሬም አፈራ፤ ከፈራው ፍሬም ለመምህሩ ለአባ ባይሞን ወስዶ ‹‹አባቴ እንካ ብላ›› ብሎ ሰጠው፡፡ አባ ባይሞን ማመን አልቻለም፤ እጅግ አደነቀ፤ አለቀሰም፡፡ ወዲያው ያንን ፍሬ ታቅፎ ወስዶ ለገዳሙ መነኮሳት ‹‹ውሰዱ፤ ብሉ፤ በረከትም አግኙ፤ ይህ የዛፍ ሳይሆን የመታዘዝ ፍሬ ነው›› በማለት ሰጣቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የታላላቆቻችንን ትእዛዝ ሁል ጊዜ ማክበርና መፈጸም አለብን፤ ያንን መታዘዛችንን ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እግዚአብሔርም ይመለከታል፤ ከሰዎች ምርቃትን ከእግዚአብሔር በረከትን እናገኝበታለን፡፡

ይቅርታ

“ይቅርታ” ማለት “የበደለን ሰው መልሶ አለመበደል” ማለት ነው፤ ለምሳሌ የሰደበን ሰው መልሶ አለመሳደብ፣ ክፉ ያደረገብንን ሰው እኛም እንደ እርሱ ክፉ አለማድርግ፣ በይቅርታ ማለፍ ይህ ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አንዱ ነው፡፡ የበደለን ሰው ይቅር ማለት መታደል ነው፤ ልጆች! በማንኛውም ነገር ሁሉ ይቅር ባይ ከሆንን ሰዎችን በይቅርታ ስናልፍ እግዚአብሔር ይባርከናል፤ እኛንም ይቅር ይለናል፤ “አባታችን ሆይ” እያልን በምንጸልየው ጸሎት ላይ ‹‹…እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል…ይቅር በለን…›› የሚል ኃይለ ቃል አለበት፡፡ (ማቴዎስ ፮፥፲፪)
ልጆች! በዚህ ጸሎት ላይ እንዳለው የይቅርታ ሰዎች መሆን አለብን፤ በቤት ውስጥ ካሉ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን፣ አልያም ሰፈር ውስጥ ካሉ ወይም በትምህርት ቤት ከምናውቃቸው ጓደኞቻን ጋር በአንዳንድ ነገር ልንጣላ (ላንግባባ) የሚያስችሉ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ! ታዲያ እኛ ከሆንን በደለኞች ይቅርታን መጠየቅ አለብን፤ ወይም እኛ ተበድለን (አስቀይመውን) ከሆነ ይቅርታን ማድረግ አለብን፤ ቂም መያዝ አይገባም፤ እነርሱ እንዳደረጉብን መጥፎ ያልነውን ነገር እኛ ደግመን ማድረግ የለብንም፤ በይቅርታ ማለፍ አለብን፡፡

በይቅርባይነታቸው አብነት ከሚሆኑን ቅዱሳን አንዱን እንመልከት

ነቢይ ኤልሳዕ

ኤልሳዕ የሚባል ነቢይ ነበር፤ አንድ ቀን ሦርያ የምትባልን አገር የሚመራው ንጉሥ ይዘውት እንዲመጡ ነቢዩ ኤልሳዕ ወዳበት ሥፍራ ላካቸው፤ ወታደሮቹም ነቢዩ ኤልሳዕ የሚያድረበትን ዋሻ ዙሪያውን ከበው ሊይዙት ሲጠብቁ ተመሪው (ደቀ መዝሙሩ) ግያዝ ጠዋት በሩን ከፍቶ ሲወጣ አያቸውና ደንገጦ ሮጦ ገብቶ ለነቢዩ ኤልሳዕ ነገረው፡፡ ነቢዩም እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ይበልጣሉ፤ አትፍራ” አለውና “እባክህ አምላኬ ለዚህ ብላቴና ዓይነ ልቡናውን አብራለት” ብሎ ተማጸነ፡፡

ቅዱሳን መላእክት ደግሞ ነቢዩ ኤልሳዕና ግያዝን እየጠበቋቸው ነበር፤ በጸሎት እንዳያስተውሎ ካደረጋቸው በኋላ ወደውጭ ወጣና “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ ወታደሮቹም “ኤልሳዕን” አሉት፤ “ኑ ላሳያችሁ” ብሎ ራሱ እየመራቸው ወደ እስራኤሉ ንጉሥ ወሰዳቸው (ማርኮ)፡፡

ንጉሡ ግን ልግደላቸው ብሎ ተነሣ፤ ነቢዩ ኤልሣዕ መልሶ “አይ እንዳትነካቸው፤ እንጀራ አብልተህ፣ ውኃ አተጥጠህ በሰላም ወደ አገራቸው ሸኛቸው” አለው፤ ሊገድሉት (ሊይዙት) የመጡትን ጠላቶቹን ይቅርታ አድርጎ በሰላም ወደ አገራቸው ሸኛቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ክፉውን በክፉ ሰይሆን በመልካም መመለስ አለብን፤ ሁል ጊዜ እኛ መልካም ከሆንን ከማንኛውም ክፉ ነገር እንዲጠብቁን ቅዱሳን መላእክትን አምላካችን እግዚአብሔር ይልክልናል፡፡

‹‹..ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና…›› እንደተባለው ይቅርታ ማድረግ ክብሩ ለራስ ነውና የይቅርታ ሰዎች እንሁን፡፡ (ማቴዎስ ፮፥፲፬) ይቅር ባይ ሆነን ለክብር እንበቃ ዘንድ ማስተዋሉን ይስጠን!

ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በትምህርታችሁ በርትታችሁ ትማሩ ዘንድ ይገባል! ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ! ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!