ክርስቲያናዊ ሕይወት
ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ መልካም ሥራ ሁልጊዜ ይኖራል፤መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርተ ወንጌል እንዳስተማረን ድኅነትን የምናገኝው በሕገ እግዚአብሔር ጸንተን ስንኖር እንደሆነ ነግሮናል። የሰው ሕይወቱ የጸጋ ነው፤ በፈቃዱ በሁለት ሞት ነፍሱን/ሕይወቱን/ ይነጠቃል፡፡ የመጀመሪያው ሞት የማይቀር ሲሆን የሁለተኛው ሞት ግን በሕገ እግዚአብሔር ለልደተ ነፍሳት የተሰጠ ነው፤ ራዕ. (፪፥፲፩)፤ ሕያው የሆነ ሰው እንጂ ሕይወት የሆነ ሰው የለምና፡፡
ስለሆነም ለዘለዓለም በሕይወት ለመኖር ይቻለን ዘንድ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በቆየበት ጊዜ ያደረገውን ተአምር፤ ያስተማረውን ወንጌልና ለእኛ የገለጸልንን ፍቅር መሠረት አድርገን መመራት ይጠበቅብናል። ይህንንም በተግባር ለመፈጸም የሚከተሉትን ምግባሮች ማከናወን አለብን፡፡
፩.አገልግሎት
ከሁሉም አስቀድሞ የሰው ልጅ ዕለት ዕለት ፈጣሪውን ሊያመሰግን ይገባል፤ ይህም መጸለይ፤መጾም፤ማስቀደስና መዘመር ይገባዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ነዳያንን ማብላትና ማጠጣት በጉልበትና በሙያ አድባራትን ማሰራት ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ሲሆን አሁን አሁን ግን የምንመለከተው እንደዚህ አይደለም፡፡ የዛሬ ፲ ዓመት ሰንበት ተማሪ የነበረው ልጅ ከዓመት በኋላ የመድረክ ዘፋኝ ይሆናል፤ የዛሬ ፭ ዓመት ሰንበት ትምህርት ቤት ድራማ ይሰራ የነበረው ሰው በኋላ ተለውጦ ሌላ ታሪክ ውስጥ ይገባል፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት ሰብሳቢ፤ ጸሓፊና አባል የነበረው፤ ሚስት ሲያገባ ያንን ሁሉ እርግፍ አድርጎ ይተወዋል፤ ትዳር እኮ የአገልግሎት ጡረታ አይደለም፤ አንዴ ካገቡ አይመለሱም፡፡
ሰንበት ተማሪ ሆኖ ቤተክርስቲያንን እያገለገለ እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ዘማሪ፤ ካህን፤ ዲያቆን ወይም ሰባኪ ሆኖ ገዳማትን እያሰራ፤ ነዳያንን እያበላ፤ ጉባኤ እያዘጋጀ፤ ጽዋ ማኅበራትን እየመራና ወዲህ ወዲያ ሳይል፤ ታመምኩ፤ ተቸገርኩ፤ ምስጋና ቢስ ነኝ፤ እጄን በቆረጠው ሳይል የሚኖር ማን ነው? አንዳንዶች ደከምን ብለው አገልግሎትን የሚተው አሉ፡፡ ታማን ብለን የምንተውም አለን፤ ይህቺን ካልታገስን ታዲያ ስለ ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን ለምን እናወራለን? እስከ መጨረሻው የትኛው ሰው ነው የሚጸናው? በክርስቲያናዊ ሕይወት እስከ መጨረሻዋ ዕለት መጽናት ያስፍልጋል፡፡
፪.ጊዜን ማክበር
ጊዜ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ ነው፤ እናም በአግባቡ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡ ጉባኤ ላይ በመገኘት፤ ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ በማገልገል፤ ድሆችን በመጎብኘት፤ ሕመምተኞችን በመጠየቅ፤ ገዳማትንና አድባራትን ለማሰራት በመድከም፤ መምህራኑ ሲያስተምሩና መዘምራኑ ሲዘምሩ በማገልገል ጊዜን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል (፳፭፥፴፬-፴፮) ላይ እንደተገለጸው «እናንተ የአባቴ ቡሩካን፤ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ተጠምቼም አጠጥታችሁኛልና፤ እንግዳም ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፡፡ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፤ ታምሜም ጎብኝታችሁኛልና፤ ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና» ይለናል።
መጠቀም ያለብን ትርፍ ጊዜያችንን አይደለም፤ ያለንን ጊዜ መስጠትና ሙሉ ጊዜን መስጠት ይለያያሉ፤ በወንጌል እንደተጠቀሰው አንድ ሰው ከሞላው ከኪሱ አፈሰና ሰጠ፤ አንዲት ምስኪን መበለት ደግሞ ሁለት ሳንቲም ነበራትና እሱን ሰጠች፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነዚህ ሰዎች ሁሉ ይህቺ ጸደቀች አለ፡፡ በሉቃስ ወንጌል (፳፩፥፫-፬) ላይ እንደተናገረው «እውነት እላችኋለሁ፥ይህቺ ደሃ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብዝታ ለእግዚአብሔር መባ አገባች፡፡ እነዚህ ሁሉ ከተረፋቸው ለእግዚአብሔር መባ አግብተዋና፤ ይህች ግን ከድህነቷ ያላትን ጥሪቷን ሁሉ አገባች»፡፡ካለን እንድንሰጥ ነው እንጂ ሲተርፈን፤ ሥራ ሠርተን፤ በልተን፤ ጠጥተን፤ተዝናንተን ስንጨርስ መጨረሻ ላይ የት ልሂድ ብለን ቤተክርስቲያን የምንሄድ ከሆነ ይህ ለጊዜ ዋጋ መስጠት አይደለም፡፡ በጊዜያችን ተጨማሪ ልንሰራበት የምንችለውንና ገንዘብ የምናገኝበትን፤ ሰው ቤት ሄደን ጥዑም ምግብ ተመግበን የምንጠጣበትን ጊዜ ሰውተን፤ እንደ አስፈላጊነቱ ስንሰጥ ለጊዜ መሥዋዕት አደረግን ይባላል፤ሲተርፍ መስጠት ዋጋው ትንሽ መሆኑን ወንጌልም ነግሮናልና፡፡
፫. በሃይማኖት መጽናት
በዮሐንስ ራእይ ፲፪፥፲፮-፷ እንደተጠቀሰው ዘንዶው በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስ ምስክር ያላቸውን ከዘሯ የቀሩትን ሊወጋ ሄደ ይላል፡፡ ከዘሯ የቀረነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ያለንን ሊዋጋ ከተነሣው ዘንዶ ጋር ታግሎ ሃይማኖትን መጠበቅ ተገቢ ነው፤ በዚህ ዘመን ሃይማኖት ጸንቶ ሃይማኖትን መጠበቅና ከመናፍቃን ጋር መዋጋት የክርስቲያን ኃላፊነት ነው፤ ይሁዳ (፩፥፫) «ለቅዱሳን የተሰጠችውንም ሃይማኖት ትጋደሉላት ዘንድ አማልዳችኋለሁ» ይላል።
ስለ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መጋደል ክርስቲያናዊ ምግባር ነው፤ ብዙዎቹ ዛሬ በገንዘብና ከንቱ በሆነ ነገር ይታለላሉ፤ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው «ለዚህ ዓለም ስሕተት፥ በክርስቶስ ሕግ ያይደለ፥ በሰው ሠራሽ ሥራዐት ለከንቱ የሚያታልሉ ሰዎች በነገር ማራቀቅ እንዳያታልሉአችሁ፥ተጠንቀቁ» (ቈላ. ፪፥፰)፡፡ በሰይጣን በመታለል ሃይማኖታቸውን የሚለውጡ አሉ፤ ጌታችን በማቴ. (፳፬፥፲፫) ላይ «እስከ መጨረሻው የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል» ብሏል፡፡
፬.እራሳችንን ከፍትወት መጠበቅ
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በዚህ ዘመን ራሳችን ከዚህ ዓለም ፍትወት መጠበቅ እንዳለብን አሳስበለዋል፡፡ አሁንኮ እስከ ጋብቻ ድረስ በድንግልና መጽናት ከባድ ሆኖብናል፤ የ «መ» ሕጎች እየተባለ በትምህርት ቤቱ ሁሉ መከራ የሚበላው ይህን ሕግ እየረሳን ነው፡፡ ልክ የዚህን ዓለም ፍትወት መቻል በእሳት ውስጥ ማለፍ እንደሆነ፤ ፍትወት ራሱን የቻለ እሳት ነው፤ እሳት እንኳን የቀረበውን የራቀውን ይጠራል፡፡ አባቶቻችን «እሳት ይጠራል» ይላሉ፤ እኛ የምንኖረው በዓለም ነው፡፡ ስለዚህ ለምን በኅሊናችን የፍትወት ስሜት መጣ? ለምን በዙሪያችን ኃጢአት ኖረ? ማለት አንችልም፤ ግን ወንዙን አቋርጠን ማለፍ እንችላለን፤ ራስን በንጽሕና መጠበቅም አለብን፡፡ ወንድና ሴት ራሳቸውን ከዝሙት ስሜት ጠብቀው ሲኖሩ፤ በቤተክርስቲያን በተክሊል ሲጋቡ አክሊል ይጫንላቸዋል፤ ቤተ ክርስቲያን አክሊል ላደረገችለት ሰው ደግሞ እግዚአብሔር እጥፍ ዋጋን እንደሚከፍል ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተጽፏል፡፡ እነዚህ ሰዎች እድል ወይም ምድራዊ ጥቅም ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም፤ ነገር ግን ምድራዊ ፍላጎታቸውን በመግታት ከራሳቸው፤ ከጓደኞቻቸውና ከአካባቢያቸው ጋር በመታገል ለነፍሳቸው መሥዋዕት ለመክፈል ስለሚሹ ነው፡፡
፭. በትዳር መጽናት
በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ አንድ ወንድ በአንዲት ሴት፤ አንዲት ሴት በአንድ ወንድ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ባልና ሚስት በመቻቻል በሰላም መኖር ከቻሉ፤ ሰው የራሱን፤ የአጋሩንና የልጆቹን ጠባይ ችሎ በትዕግሥት ከኖረ፤ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎም፤ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን የሚያገለግል ከሆነ ክርስቲያን ይባላል፡፡ በምንኩስና ሳይወሰኑ ወይም በትዳር አንድ ሳይሆኑ እንዲሁ የሚኖሩ ሰዎች ክርስቲያናዊ ሕይወትን የማይሹ ሰዎች ናቸው፤ ልክ በዘመነ ሰማዕታት ጊዜ እንደነበሩ ለጊዜው ክደናል እንደሚሉት አይነት ናቸው፡፡ ፶ እና ፷ ዓመት በትዳር እየኖሩ የብር፤ የወርቅ፤ የአልማዝና ኢዩቤልዩ የሚያከብሩ ሰዎች ተመችቷቸው እንዳይመስለን፤ ብዙ የችግር ጊዜን አሳልፈው ሊሆን ይችላል፤ እግሬን በሰበረው፤ ምላሴን በቆረጠው፤ አይኔን በሰወረው፤ ብር ብዬ በጠፋው ያሉበት ጊዜም ይኖራል፤ ግን ያን ሁሉ አልፎ መጽናት ያስፈልጋል፡፡
በትዳር ያላችሁ እስከመጨረሻው እንድትጸኑ፤ንጽሕናችሁን ጠብቃችሁ በመዘምርነት የምታገለግሉ፤ በስብከት፤ ለአድባራትና ገዳማት ያላችሁን እየመጸወታችሁ ከቁርሳችሁ ቀንሳችሁ፤ ሁለት ጫማ ካላችሁ አንድ ጫማ፤ ሁለት ልብስ ካላችሁ አንዱን እየለበሳችሁ፤ እኛ ይቅርብን፤ አባቶቻችን ተርበው ከተማ ለከተማ ሲንከራተቱ አንይ ብላችሁ የምታገለግሉ፤ የምታስታርቁ አባቶች፤ የጠፉትን ፈልጋችሁ የምታመጡ፤ መናፍቃንን ተከራክራችሁ የምታሳምኑ፤ አሕዛብን ወደ ጥምቀት የምታመጡ ሰዎች ሁሉ እስከ መጨረሻው ጸንታችሁ፤ ጸንተን፤ ኑ «የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን ርስት ውረሱ» እንድንባል የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፤አሜን፡፡