‹‹ከፊት ይልቅ ትጉ›› (፪ ጴጥ. ፩፥፲)

መምህር ምትኩ አበራ
ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ከቀደመ ተግባራችን ይልቅ እንድንተጋ ያስተማረበት ኃይለ ቃል እንዲህ የሚል ነው፤ ‹‹እናንተ ግን በሥራው ሁሉ እየተጋችሁ፥ በእምነት በጎነትን፥ በበጎነትም ዕውቀትን ጨምሩ፤ በዕውቀትም ንጽሕናን፥ በንጽሕናም ትዕግሥትን፥ በትዕግሥትም እግዚአብሔርን ማምለክን፥ እግዚአብሔርም በማምለክ ወንድማማችነትን በወንድማማችነትንም ፍቅርን ጨምሩ፤ እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጓችኋልና፡፡ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብ ያለውን ብቻ ያያል፤ የቀደመውንም የኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል፡፡ ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ፥ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህንም ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም፡፡ እንዲሁ ወደ ዘለዓለም ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በምልአት ይሰጣችኋል፡፡›› (፪ ጴጥ. ፩፥፭-፲፩)

ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ከፊት ይልቅ ትጉ›› ብሎ የተናገረው በጸሎት፣ በጾም፣ በሃይማኖትና በምግባር እየደከሙ፣ ነገር ግን በተለያዩ ችግርና ፈተና ውስጥ ላሉት አገልጋዩች ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አገልግሎታችንን እንደ ልምድ አድርገን በመውሰድ የምንጸልየውን ጸሎትም ከልብ ሳይሆን በአንደበት ብቻ የምንልበት ጊዜ አለ፡፡ አቡነ ዘበሰማያትን አድርሰን እንኳ መጸለይ አለመጸለያችንን የምንጠራጠር እንኖራለን፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በክርስትና ሕይወታቸው ጸንተው ለሚጸልዩ፣ ለሚሰግዱ፣ ለሚመጸውቱ፣ በጽናት ሃይማታቸውንና አገልግሎታቸውን ለሚፈጽሙ ሰዎች ከዚህ ቀደም ከነበረው በይበልጥ እንዲተጉ መክሮአቸዋል፡፡ እኛንም አሁን ያለን እምነትና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የታወቀና የተረዳ ቢሆንም ዛሬም በፊት ከነበረው ትጋታችን ይልቅ የበለጠ እንድንተጋ አስገንዝቦናል፡፡

ለዚህም የመጀመሪያው ትጋት ያለንን ማወቅ ነው፡፡ ሊኖረን ከሚገባው መንፈሳዊነት ማለትም ሃይማኖት፣ በጎነት፣ ዕውቀት፣ ንጽሕናን፣ ትዕግሥትን፣ እግዚአብሔርን ማምለክ፣ እራስን መግዛት፣ መጽናት፣ እግዚአብሔርን መምሰል፣ የወንድማማች መዋደድ፣ ፍቅርን በመጨመር የትኛው እንዳለንና እንደጎደለን መለየት አለብን፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሃይማኖት ሁለት ገጽታዎች አሉት፤ እነርሱም ማመንና መታመን በውስጡ ክርስቲያናዊ ምግባራት በሙሉ በመታመን ውስጥ ይካተታናሉ፡፡ ሃይማኖተኛ ሰው እነዚህን ሁለቱን ሟሟላት እንዳአለበት ሊያውቅ ይገባል፤ የእግዚአብሔርንም ህልውና በማመንና በመታመን ውስጥ መረዳት ይቻለዋል፡፡

ሃይማኖት ኖሮን በጎ ምግባር ከሌለን ዋጋ የለውም፡፡ በጎነታችን ደግሞ በዕውቀት የታገዘ ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ሰዎች ቅንነትና መንፈሳዊ ዕውቀት የጎደላቸው በመሆናቸው በቅንነትና በበጎነት ብቻ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ምክንያት ሆነው ሌት ከቀን ይዳክራሉ፡፡

ሰዎች በጎ ሆነውም ዕውቀት ከሌላቸው ዋጋ የለውም፡፡ ምክንያቱም ዕውቀት የሌለው ሃይማኖት ጅልነት ነው፡፡ ሃይማኖት የሌለው ዕውቀት ደግሞ እብደት ነው፡፡ ከዕውቀት ጋር ደግሞ ራስን መግዛት ያስፈልጋል፤ አንድ ሰው ባካበተው ዕውቀት መታበይ የለበትም፡፡ ልክ ዲያብሎስ በትዕቢቱ የተነሣ ለፈጣሪ ባለመታዘዙ እንደተረገመ እንደ እርሱ ላለመሆን መጠንቀቅ አለብን፤ ዕውቀታችንንም ለሌሎች ልናካፍል ይገባል፤ ሌሎችንም መናቅ የለብንም፡፡

በዕውቀታችን ላይ ራስን በመግዛት መመርመር ማለት ይኸው ነው፤ ራስን በመግዛት ደግሞ መጽናት ይጠብቅብናል፤ በጎነታችንም ሆነ ራሳችንን መግዛታችን እንዲሁም ሌሎች በጎ ምግባሮቻችን ጊዜያዊ ሊሆኑ አይገባም፡፡

ዕውቃታችን በቅድስና ሕይወት እንድንኖር ስለሚያግዘንም የውስጣዊ ንጽሕናን ገንዘብ እንዳርጋለን፤ ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› ብሎ ፈጣሪያችን እንደተናገረው ቅዱስ እንሆን ዘንድ ንጽሐ ልቡናና በጎ ኅሊና ሊኖረን ይገባል፤ ልቡ ንጹሕ የሆነ ሰው ደግሞ በጎውንም ሆነ ክፉን በትዕግሥት ያሳልፋል፤ ሕይወቱ በችግርና በመከራ ውስጥ ሲሆንም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ነገረ ድኅነት በመረዳትና በመተግበር ይኖራል፡፡ (ዘሌ. ፲፱፥፪)

እግዚአብሔርን መምሰል ለሥቃይ ተላልፎ መሰጠት በመሆኑ ለአምላካችን ፍቅር ለሃይማኖታችን ምስክርነት ችግርና መከራ መቀበል፣ መስቀሉን መሸከም ይገባል፡፡ እርሱ የድኅንነታችን መንገድ ነውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ዕዳ ለመክፈል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ መከራ ተቀብሎ መስቀልን ላይ ተሰቅሎ የእርሱን ሕይወት ለእኛ የሰጠን እኛ በክርስቶስ ክርስቲያን እንድናባል እንዲሁም እርሱን መስለን መኖር እንድንችል ነው፡፡ እስከ ህልፈተ ሕይወታችን ድረስ በእምነትና በሃይማኖት ልንጸና ይገባል፤ በዚህም አምላካችንን እግዚአብሔር መምሰል ይቻለናል፡፡ እግዚአብሔርን በመምሰል ለምንኖር ሰዎች ደግሞ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ ሕገ እግዚአብሔርንና አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም የበቃን እንሆናለን፡፡

በመቀጠልም ቅዱስ ጴጥሮስም እንደተናገረው እግዚአብሔርን በመምሰል ላይ የወንድማማችነት መዋደድ በወንድማማች ፍቅርን መጨመር ላይ የባልንጀራነት መዋደድ ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን መጨመር ማለት ነው፡፡ ይህም ደግሞ እግዚአብሔር አምላካችንን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ኃይላችን እንድንወደው ያደርገናል፤ የሕግ ሁሉ ማሠሪያ ፍቅር ነውና፡፡

ለዚህም አንድ ምሳሌ እናንሣ፤ ሦስት የገዳም መነኮሳት የሰው አዝመራ በምንደኝነት አብረው ለማጨድ ተነጋግረው ሲያበቊ ገና በመጀመሪያው ቀን ከመካከላቸው አንዱ ታመመ፤ እርሱም ከወንድሞቹ ጋር ማጨድ ስላልቻለ በዓቱ ቀረ፤ በዚህ ጊዜም አንደኛው ወንድም ለሁለተኛው ‹‹ወንድሜ፥ ወንድማችን እንደታመመ አይተሃል፥ ስለዚህም አንተም እኔም የተቻለንን ሁሉ እናድርግ፤ በጸሎቱ እየታገዝን የወንድማችንንም ድርሻ እንደምንጨርሰው አምናለሁ›› አለው፡፡ ወንድማማቾቹም ሥራቸውን ከጨርሱ በኋላ ዋጋቸውን ሊቀበሉ በሄዱበት ጊዜ የታመመውን ወንደማቸውን ‹‹ና ዋጋህን ውሰድ›› አሉት፤ እርሱ ግን ‹‹ምንም ሥራ ሳልሠራ ምንም ነገር አልወስድም›› አላቸው፡፡ እነርሱም የአንተ ጸሉት ስለረዳን ሥራው ተጠናቋልና ድርሻህን ውሰድ›› አሉት፡፡

የታመመው ወንድማቸውም ‹‹እኔ ምንም አልወስድም ሲል እነዚያ ወንደሞቹ ደግሞ አንተ ካልተቀበልክ እኛም ትተነው እንሄዳለን›› እየተባባሉ ብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ አንድ አረጋዊ ጋር ሄደው የተፈጠረውን ሁሉ ነገሩት፡፡ ‹‹አባ፥ ወደ ሥራ ስንሄድ ገና በመጀመሪያ ቀን ታምሜ ምንም ሳልሠራ ወደ በዓቴ ተመለስኩ፤ እነዚህ ወንድሞቼ ደግሞ ያልሠራሁበትን ና ውሰድ ይሉኛል›› አለ፡፡ ወንድሞቹም ቀጠሉና ‹‹አባ፥ እኛ በእርሱ ጸሎት ባንታገዝ ኖሮ ሦስታችንም አብረን ሥራው ላይ ብንሠማራም ሥራውን ልንጨርሰው ባልቻልንም ነበር፤ ነገር ግን በእርሱ ጸሎት ሥራውን ቶሎ ጨረስን፡፡ ስለዚህም ዋጋህን ውሰድ ብንለው አልቀበልም አለ›› አሉት፡፡ አረጋዊውም ይህን ሰምቶ በመደነቁ በእርሱ ገዳም ያሉትን መነኮሳት ሰብስቦ ‹‹ወንድሞቼ፥ ኑ! ዛሬ ልዩ የሆነ ፍርድን ስሙ›› አላቸው፡፡ አረጋዊው አባትም የተከሠተውን ነገር በሙሉ ከነገራቸው በኋላ መነኩሴው ገንዘቡን እንዲወስድና የፈለገውን ነገር እንዲያደርግበት ፈረደ፤ በዚህ ጊዜ ይህ መነኩሴው አዝኖ እያለቀሰ ሄደ፡፡ (‹ፍኖተ ቅዱሳን› በዲያቆን ያረጋል፤ ገጽ.፷፰-፷፱)

ውድ አንባብያን፤ አያችሁ አይደል! እኛ በምናብና በወሬ ብቻ የምናውቃት ፍቅር በእነዚህ ሦስት አባቶች ምክንያት ገዙፉ በአካል ቆማ ስትታይ? የወንድማማችነት ፍቅር ማለት ይኸው ነው፡፡

በሕይወታችን ውስጥ ፍቅር የሁሉ ነገር ማሠሪያ ነው፡፡ መንፈሳዊ ፍቅርን የበጎ ምግባራችንና ትሩፋታችን ሁሉ ዘውድ አድርገን የክርስትን ጉዞአችንን በማስተዋል ልንጓዝ ይገባል፡፡ የዚህ ዓለም ኑሮ ሁሉ ከንቱ ነው፤ እያንዳንዱ ምግባራችንም በፍቅር ካልታሠራ ዋጋ የለውም፡፡ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ስምንቱን ነጥቦች ሁሉ ገንዘብ በማድረግና በማወቅ እያሟላን በመንፈሳዊ ተግባር ከፊት ይልቅ ልንተጋ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር