ከጥምቀት በኋላ ክርስትና
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ጥር ፳፭፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? የጥምቀት በዓል እንዴት አለፈ? እናንተስ የጥምቀትን በዓል እንዴት አከበራችሁት? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አብነት ለመሆን እንዲሁም ደግሞ የዕዳ ደብዳቤያችንን ሊደመስስልን መጠመቁን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ በደስታ በምስጋና በዓሉን እናከብራለን፡፡ መቼም ልጆች! ከወላጆች አልያም ከጓደኞቻችን ጋር በመሆን አክብራችኋል፤ መልካም!
ሌላው ደግሞ ወቅቱ ለእናንተ ለተማሪዎች የዓመቱ አጋማሽ የምዘና ፈተና ነበር! ፈተናስ እንዴት ነበር? እንግዲህ የዓመቱ አጋማሽ የትምህርት ወቅት አልቆ ፈተናም ተፈትናችሁ ውጤት የተሰጣችሁ እንዲሁም ውጤት በመጠባበቅ ላይ ያላችሁ ትኖራላች፡፡ ከባለፈው ውጤታችሁ በመነሣት በቀጣዩ የትምህርት ጊዜ በርትታችሁ ለመማር እንደ ምታቅዱ ተስፋችን እሙን ነው፡፡ ደግሞ በዕረፍት ጊዜያችሁ መልካምን ነገር በማድረግ አሳለፉ፡፡ በርቱ! ለዛሬ የምንነግራችሁ ከጥምቀት በኋላ ክርስትና ምን ይመስላል የሚለውን እንመለከታለን፤ መልካም ቆይታ!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን የተጠመቀው ለእኛ አርአያ ለመሆን ነው፤ እኛ መጠመቅና የልጅነት ጸጋ ማግኘት እንደ ሚገባን ሲነግረን ተጠምቆ አሳየን፡፡ እርሱ መጠመቁ ለእኛ ነው፤ እኛ በተወለድን ፵ እና ፹ ቀን ስንጠመቅ የእግዚአብሔርን ልጅነት እናገኛለን፤ ያዘጋጀልንን መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለው የአይሁድ መምህር እንዲህ ብሎ አስተምሮታል፤ ‹‹..ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም…›› (ዮሐ.፫፥፭) ስለዚህ ልጅነትን ለማግኘት በወላጆቻችን እቅፍ ሆነን ቤተ እግዚአብሔር በመምጣት ጥምቀት እንጠመቃለን፤ ቅዱስ ቁርባን እንቀበላለን፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን፡፡
ክርስቲያን የሚለውን ታላቁን ስም እንጠራበታለን፡፡ እናም ታዲያ ከተጠመቅን በኋላ ጥሩ ምግባርን ልንሠራ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ተጠምቆ ክርስትና ከተነሣ በኋላ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት መልካም ምግባር መሥራት አለበት፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ ‹‹…ሰው በእምነቱ ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ…›› በማለት እንደ መከረን ለሰዎች በጎ ነገርን በማድረግ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ክርስቲያን መሆን ይገባናል፡፡ (ያዕ.፪፥፳፬)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ እኛ በተወለድን በ፵ እና በ ፹ ቀናችን ተጠምቀናል፡፡ ታዲያ የእግዚአብሔር ልጆች ከተባለን ክርስቲያን የሚለውን ስም የምንጠራበት ሁሉ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አብነት ሆኖ እንደ ተጠመቀ እና ጾምን መጾም እንዳለብን ሲያስረዳን በገዳመ ቆሮንቶስ ጾሞ እንድንጾም እንዳሳየን፤ ጸሎትን ጸልዮ እንድንጸልይ እንዳደረገን እኛም እድሚያችን ከሰባት ዓመት በላይ የሆንን ሁሉ እንደ አቅማችን መጾም እና መጸለይ አለብን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ታዛዦችና አስተዋዮች ልንሆንም ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹…ልጆች ሆይ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ ይህ የሚገባ ነውና፡፡ መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር …›› በማለት እንደ መከረን በቤተሰብ፣ በሠፈር፣ በትምህርት ቤት ቅኖችና ታዛዦች መሆን አለብን፡፡ (ኤፌ.፮፥፩) ተጠምቀን የእግዚአብሔር ልጆች ተብለናል የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን መልካም ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ሰዎችን የምንወድ ልጆች መሆን ይገባናል፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹…እርስ በእርሳችን እንዋደድ፤ ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና›› ተብለናልና ሰዎችን መውደድ አለብን፡፡ (፩ኛዮሐ.፬፥፯)
ውድ የእግዚአብሔር ልችች! …..በክርስትና እምነት ስንኖር ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ያደረገልንን ውለታ እያሰብን እኛም ለሰዎች ሁሉ መልካም ነገርን በማድረግ ክርስትናችንን መግለጥ አለብን፡፡ በሠፈር ውስጥና በትምህርት ቤት ለሚመለከቱን ሁሉ የመልካም ምግባር አርአያ (ምሳሌ) መሆን ይገባናል፡፡ በዓላትን ማክበራችን ከበዓሉ በረከትን በማግኘት የተሰጠንን ሰላም በማሰብ የሰላም ሰዎች መሆን፣ የተከፈለልንን መሥዋዕትነት በማሰብ፣ ሰዎችን መውደድ፣ ለሰዎች መልካምን ማድረግ አለብን፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ማስተዋሉን፣ በረከቱንና ረድኤቱን ያድለን፤ አሜን!!! ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!