ከጋምቤላ ክልል የመጡ ሠልጣኞች ተመረቁ
በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል አስተባባሪነት ከጋምቤላ ክልል የአኝዋክና የኑዌር ብሔረሰብ ተወላጅ ሠልጣኞች ተመረቁ፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ሓላፊ ዲ/ን አንዱአምላክ ይበልጣል እንደተናገሩት በክልሉ ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ሠልጣኞች መጥተው ሲሠለጥኑ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ሓላፊው የሥልጠናውን ዓላማ ሲያስረዱ በአብዛኛው የጠረፋማ ቦታዎች የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች በቋንቋቸው የሚያስተምራቸው ባለማግኘታቸው ተቸግረው ቆይተዋል፡፡ ይህንን ለማቃለል ከማኅበረሰቡ የተገኙ ወጣቶችን በማስተማር ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ተመልሰው ሕዝቡን እንዲያስተምሩና እንዲያስጠምቁ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ላሬ፣ ኝንኛንግ፣ ፒኝዶ፣ አበቦ፣ ጆር፣ ኢታንግ እና ጋምቤላ ዙሪያ ከሚባሉ ሰባት ወረዳዎች የመጡት ሠልጣኞች በቁጥር ዐሥራ ስድስት ሲሆኑ ሥልጠናው ዐሥራ አምስት ቀን እንደወሰደ ሓላፊው ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናውን ለመሥጠት ከሰላሳ አምስት ሺሕ ብር በላይ ወጪ እንዳስፈለገ የጠቀሱት ሓላፊው ወደፊትም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ በጎ አድራጊዎች ይህንን መሰል መንፈሳዊ አገልግሎት ለማከናወን የእርዳታ እጃቸውን ከዘረጉ በርካታ የጠረፋማ አካባቢ ወገኖችን ለማስተማር እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
በአፍ መፍቻ ቋንቋ ተምሮ ማስተማር ውጤቱ ከፍተኛ በመሆኑም የክርስትናው እምነት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች በቋንቋቸው በማስተማር ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ሠልጣኞቹ ሥነፍጥረት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ነገረ ቅዱሳን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንና የስብከት ዘዴ በሚሉ ርእሶች ትምህርት እንደተሰጣቸው እና ወደ ክልላቸው ሔደው ምን መሥራት እንደሚገባቸው ምክክር እንደተደረገም ለማወቅ ተችሏል፡፡