ከየማእከላቱ ለተውጣጡ ተጠሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ
ሚያዚያ 9 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዳዊት ደስታ
በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ከየማዕከላቱ ለተውጣጡ 38 የክፍል ተጠሪዎች ከሚያዝያ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. በዋናው ማእከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተካሄደ፡፡
የሥልጠናውን ዓላማ አስመልክቶ የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር ዲ/ን አእምሮ ይሄይስ “የማኅበሩን ስልታዊ ዕቅድ ተጠሪዎቹ ግንዛቤ ኖሮአቸው በቀጣይ በየማእከላቱ የሚሠሩትን ሥራ በተግባር ላይ እንዲያውሉ ለማስቻል ነው” ብለዋል፡፡
አያይዘውም ሥልጠናው በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፣ በቀጣይም በገዳማት ላይ የሚሠራውን የልማት ሥራ በጋለ ሆኖ ከታሰበበት ለማድረስ ያግዛል ሲሉ ሓላፊው ገልጸዋል፡፡
ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የደሴ ማእከል የቅዱስት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ተጠሪ ወ/ት ስንታየው እሸቱ በሥልጠናው የተለያዩ ግንዛቤዎችን አግኝቻለሁ፡፡ በተለይ የአብነት ትምህርት ቤት ላይ የምንሠራቸውን ሥራ እንዴት ማጠናከርና ገቢ ማሰባሰብ እንዳለብን፣ ፕሮጀክት እንደምንቀርጽና እንደምንተገብር ተንዝቤያለሁ፡፡
ሌላው ከአሰበ ተፈሪ ማእከል የመጣው አቶ ብርሃኑ እንዳለ በሀገራችን በሚገኙአብያተ ክርስቲያናት የአገልጋይ እጥረት ይስተዋላል፡፡ ከዚህ አንጻር የአብነት ትምህርት ቤቶች ተተኪ አገልጋይ የሚፈራባቸው በመሆኑ ብዙ ሊሠራ እንደሚገባ የሚያመለክትና ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ለሦስት ቀን በተካሄደው መርሐ ግብር ሉላዊነት እና የቤተ ክርስቲያን የማእከላት ድርሻ ምን መምሰል አለበት፣ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስኮላር ሺፕ ፕሮግራም አፈጻጸም ማእከላት ድርሻቸው ምን መሆን አለበት፣ ቤተ ክርስቲያን ለልማት ያላት ምቹነትና ተግዳሮቶች፣ የሀብት ምንነት የፕሮጀክት ሠነድ ዝግጅት፣ የንግድ ዕቅድ ዝግጅት (ለገዳማት፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ አብነት ት/ቤት ተማሪዎች) በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሥልጠናና ውይይት ተደርጓል፡፡
በመርሐ ግብሩም ላይ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊን ጨምሮ ከሁሉም ማእከላት የተውጣጡ 38 የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ተጠሪዎች ተሳትፈዋል፡፡