‹‹ከእናንተ ብዙ ይጠበቃል›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሰኔ ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በልዩ ልዩ ትምህርት ክፍል ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞች በተገኙበት ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ አስመርቋል፡፡ ተመራቂዎቹም የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን በሚመለከት ያዘጋጁትን የአቋም መግለጫ በተወካያቸው አማካይነት አቅርበዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምዕዳን ‹‹ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ጠብቃ ያቆየችው ትክክለኛ የኾነ አስተምህሮዋ፣ ባህል እና ትውፊቷ ሳይበረዝና ሳይፋለስ ለትውልደ ትውልድ መሸጋገር ይችል ዘንድ ከእናንተ ብዙ ይጠበቃል›› ሲሉ ተመራቂዎቹን አሳስበዋል፡፡
ዕለቱ፣ ተመራቂዎቹ የቤተ ክርስቲያንን አደራ ተቀብለው በየተሠማሩበት የሥራ መስክ ዅሉ እስከ መጨረሻው በታማኝነት ቃል የሚገቡበት ቀን መኾኑን ያስገነዘቡት ቅዱስነታቸው ‹‹የመንግሥተ እግዚአብሔር መልእክተኛ የኾነ ዅሉ መስቀሉን ተሸክሞ ለማገልገል የተመረጠ ስለ ኾነ በሚያጋጥመው የጕዞ ዐቀበት እና ቍልቍለት ሊቸገር አይገባውም፤ በማን እንደ ተመረጠ ያውቃልና ነው›› በማለት ተመራቂዎቹ ብዙ ፈተና እንደሚጠብቃቸው አውቀው ዅሉንም በትዕግሥት በማሸነፍ የሕይወት አክሊል ባለቤቶች ለመኾን ከወዲሁ እንዲዘጋጁ መክረዋል፡፡
ተመራቂዎቹ በሚላኩበት ቦታ ዅሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለትውልድ የሚጠቅም አርአያነት ያለው ሥራ ለመሥራት እንዲችሉ ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ዘወትር እንደምትጸልይም ተናግረዋል፡፡ በቃለ ምዕዳናቸው ማጠቃለያም መንፈሳዊ ኮሌጁ በየጊዜው ተተኪ መምህራንን ለማፍራት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ‹‹ዘመኑ የዕውቀት ነውና የመማር ማስተማር ዘዴው ዘመኑን የዋጀ እንዲኾን ከበፊቱ በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ በቤተ ክርስቲያናችን ስም አደራ እንላለን›› በማለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሸካ ቤንጂ ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ በበኩላቸው ‹‹በቆያችሁበት የትምህርት ዘመን ከመምህሮቻችሁ ያገኛችሁትን መንፈሳዊ ዕውቀት እግዚአብሔር ሒዱ ብሎ ወደሚልካችሁ ዓለም በመሔድ ሕዝባችሁንና ሃይማኖታችሁን ጠብቃችሁ ሳትታክቱ እንድታገለግሉ ስትል ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ መልእክቷን ታስተላልፋለች›› የሚል ቃለ በረከት ለተመራቂዎቹ ሰጥተዋል፡፡
በኮሌጁ ተምረው የሚመረቁ መምህራን በልዩ ልዩ የዕውቀት ዓይነት የበለጸጉ ሊቃውንት መኾናቸውን በማውሳት ‹‹ከአሁን በኋላ ዝናብ ዘንቦ መሬትን እንደሚያርሰው ዅሉ ከሞላው የዕውቀት ባሕራችሁ እየቀዳችሁ የምእመናንን አእምሮ እንደምታረሰርሱት ትጠበቃላችሁ›› ያሉት ደግሞ የኮሌጁ ዋና ዲን ሊቀ ኅሩያን መሐሪ አስረስ ናቸው፡፡
‹‹በኮሌጃችን ተምረው የሚመረቁ መምህራን የአብነቱን ትምህርት ከዘመናዊው ጋር አጣጥመው በዕውቀት ላይ ዕውቀት ጨምረው የሚወጡ መንፈሳውያን ሐኪሞች ናቸው፡፡ ትምህርታቸውም ደዌ ሥጋን ብቻ ሳይኾን ደዌ ነፍስንም ይፈውሳል›› ያሉት መምህር ማሞ ከበደ የመንፈሳዊ ኮሌጁ አስተዳደር ምክትል ዲን እና የኮሌጁ መምህርም ኮሌጁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያፈራ እንደ ቆየ አሁንም በማፍራት ላይ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ዓመትም በብሉይ ኪዳን አንድ፤ በሐዲስ ኪዳን አንድ፤ በቀን አዳሪ ሲሚናር ዐሥራ አንድ፤ በቀን ተመላላሽ ሃያ ሦስት፤ በማታው መርሐ ግብር ሁለት መቶ ዐርባ አምስት በድምሩ ሁለት መቶ ሰማንያ አንድ ደቀ መዛሙርትን ማስመረቁን፤ ከተመራቂዎች መካከልም አካል ጉዳተኞች እና ሴቶች እንደሚገኙ መምህር ማሞ ከበደ አስታውቀዋል፡፡ አራቱን ጉባኤያት ማስተማር፤ በዲግሪ መርሐ ግብር ማስመረቅ እና የርቀት ትምህርት መጀመር ከኮሌጁ የወደፊት ዕቅዶች መካከል የሚጠቀሱ ተግባራት መኾናቸውንም አስረድተዋል፡፡
አጠቃላይ የኮሌጁን የማስተማር ተልእኮ በሚመለከት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ምክትል ዲኑ እንዳብራሩት ኮሌጁ ከኅዳር ወር ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ ሰርጎ ገብ መናፍቃንን የሚከታተል ኰሚቴ አቋቁሞ ከኦርቶዶክሳዊው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያፈነገጠ ባዕድ ትምህርት የሚያስተምሩ ደቀ መዛሙርትን በማጣራት በየጊዜው እንዲወገዙና ከትምህርት እንዲታገዱ ሲያደርግ የቆየ ሲኾን፣ በዘንድሮው ዓመትም እምነቱ ተጣርቶ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ የሃይማኖት ሕጸጽ የተገኘበት አንድ ደቀ መዝሙር እንዳይመረቅ እገዳ ተጥሎበታል፡፡
ከዚሁ ዅሉ ጋርም የካህናትና ሰባክያነ ወንጌል እጥረት ካሉባቸው አህጉረ ስብከት መሥፈርቱን የሚያሟሉ ሰባት ደቀ መዛሙርትን በመምረጥ ማኅበረ ቅዱሳን ሙሉ ወጫቸውን ሸፍኖ በመንፈሳዊ ኮሌጁ እያስተማረ መኾኑን፤ ከእነዚህ መካከልም ከምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት የመጡት ሁለቱ ሰባክያነ ወንጌል ቀሲስ አድማሱ ሰንበታ እና ዲያቆን ዳንኤል ታደሰ ለሦስት ዓመታት ተምረው በዘንድሮው ዓመት መመረቃቸውን ከቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡
ዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ሁለቱ ተመራቂዎችም ማኅበሩ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን በእግዚአብሔር ስም አቅርበዋል፡፡ ለወደፊቱም በየቦታው እየተዘዋወሩ ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ተቋቁመው በክህነት እና በስብከተ ወንጌል ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰጣቻቸውን መንፈሳዊ ሓላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡