ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ፣ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲኾን በፍትሕ መንፈሳዊ በተደነገገው መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የዘንድሮውን መደበኛ የረክበ ካህናት ስብሰባ ከበዓሉ ዋዜማ ከግንቦት ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ ለ፲፬ ቀናት ያህል ሲወያይ ሰንብቷል፡፡
በምልዓተ ጉባኤው የተደረገውን የመክፈቻ ንግግር በተመለከተ፡-
- በቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ዘርፍ ዙሪያ እየተሠሩ ያሉትን ማኅበራውያን ተግባራት የዳሰሰ፤
- በአገራችን አንዳንድ አካባቢ በዝናም እጥረት ምክንያት ድርቅ ባስከተለው ችግር ለተጎዱ ወገኖች ሊደረግ የሚገባውን ሰብአዊ አገልግሎት ያገናዘበ፤
- በአገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን ዅለንተናዊ ዕድገት የሚበጀውን በማመቻቸት በዅሉም አቅጣጫ ያለው ኅብረተሰብ የሥራ ተነሳሽነቱን በበለጠ አጐልብቶ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል መልእክት መኾኑን ምልዓተ ጉባኤው ተመልክቶ ለተላለፈው አጠቃላይ መመሪያ ትኵረት ሰጥቶ በቀረበው አጀንዳ ከተወያየ በኋላ በርከት ያሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሳኔዎቹም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፤
፩. ከፍ ብሎ እንደ ተገለጸው ዅሉ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በአንዳንድ አካባቢ በተከሠተው ድርቅ ለረኃብ የተጋለጡ ወገኖቻችንን ለመታደግ መንግሥት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት በመገንዘብ፣ ቤተ ክርስቲያናችንም የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሓላፊነቱን ወስዶ ከርዳታ ሰጪዎች ጋር በመነጋገርና በማስተባበር የሚገኘውን ርዳታ ድርቁ የተከሠተባቸው የክልል መሪዎች በሚሰጡት አቅጣጫ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
፪. ከቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓት ውጭ በመደራጀት የኑፋቄ ትምህርት ሲያካሒድ የበረው ‹አሰግድ ሣህሉ› የተባለ ግለሰብ ለበርካታ ዓመታት የኑፋቄ ትምህርት ሲያሠራጭ መኖሩ በመረጃ የተደረሰበትና የተረጋገጠበት በመኾኑ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እንዳያስተምር፣ ምእመናንም እንዳይከተሉት ምልዓተ ጉባኤው ከግንቦት ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ ቃለ ውግዘት አስተላልፏል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ውጭ ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳያገኙ በተመሳሳይ ኹኔታ አዳራሽ ተከራይተው በቤተ ክርስቲያናችን ስም ‹‹ወንጌል እናስተምራለን፤ ዝማሬ እናሰማለን›› የሚሉ ሕገ ወጦች ከእንዲህ ዓይነት ድርጊታቸው እንዲታረሙ፤ ምእመናንንም በተለይ ወጣቱ ትውልድ እንዲህ ዓይነት ሕገ ወጦችን ከመከተልና ሃይማኖታችሁን ከሚበርዙ ኃይሎች እንድትጠበቁ ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል፡፡
፫. የቤተ ክርስቱያኒቱ መገናኛ ብዙኃን ጉዳይን በተመለከተ የሚዲያ ድርጅቱ በሰው ኃይል እንዲጠናከር፤ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶችም ጥራት እንዲኖራቸው ማድረግ በሚቻልበት ኹኔታ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተነጋግሮ፣ ለ፳፻፲ በጀት ዓመት ብር 12,000,000.00 (ዐሥራ ሁለት ሚሊዮን ብር) ተፈቅዶለት በበጀት ተጠናክሮ ሥራውን እንዲቀጥል ተስማምቷል፡፡
፬. በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ዴር ሡልጣን ገዳም ችግር ጉዳይ ጉባኤው በስፋት ከተነጋገረ በኋላ ችግሩን አስመልክቶ መፍትሔ ማግኘት እንዲቻል ለኢፊድሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ለእስራኤል ኢምባሲ እና በእስራኤል ለኢትዮጵያ ኢምባሲ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ተወስኗል፡፡
፭. ሚያዝያ ፲ ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳርና በፍትሕ መንፈሳዊ መጽሐፍ ላይ ‹‹ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሊቃውንት ጳጳሳትን አይሹሙ›› የሚለው በ፯ተኛው መቶ ዓመት ግብጻውያን አባቶች በሥርዋጽ ያስገቡት ሕገ ወጥ ጽሑፍ ስለ ኾነ ምልዓተ ጉባኤው ተነጋግሮ ጽሑፉ የአገራችንና የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚነካ ኾኖ በመገኘቱ ከአሁን በኋላ ጽሑፉ እንዳይነበብ፤ ከመጻሕፍቱም ውስጥ እንዲወጣ፤ ወደፊትም በሚታተሙ መጻሕፍት እንዳይገባ ተወስኗል፡፡
፮. ሥርዓተ ምንኵስና እና ሥልጣነ ክህነት አሰጣጥን አስመልክቶ ቀደም ባሉት ዓመታት የተወሰኑ ውሳኔዎች በአብዛኛው አፈጻጸም ላይ ችግሮች እንዳሉ ስለሚታይ ወደፊት የሚወሰነው ተጠብቆ እንዲሠራበት ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
፯. ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንና አጥማቂዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አገልግሎት እንዳይሰጡ የተወሰነ ቢኾንም ውሳኔው መከበር ስላልቻለ፤ ችግሮችም በስፋት የሚታዩ ስለ ኾነ አሁንም በውሳኔው መሠረት የቁጥጥሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተስማምቷል፡፡
፰. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም በአዲስ አበባም ኾነ በየአህጉረ ስብከቱ በማኅበር ተደራጅተው ገዳማትን በማስጐብኘትም ኾነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በልዩ ልዩ አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራትን መቆጣጠር የሚቻልበት የማኅበራት ማደራጃ ደንብ እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
፱. የቤተ ክርስቲያኒቱ ዅለንተናዊው ችግር በባለሙያ ተጠንቶ እንዲቀርብ ቀደም ሲል በተወሰነው መሠረት ጥናቱ ተጠናቆ ከቀረበ በኋላ ጉባኤው ተመልክቶ የሕግ ባለሙያዎችና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ባሉበት ተመርምሮና ተስተካክሎ ለጥቅምቱ ፳፻፲ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
፲. የስብከተ ወንጌል መስፋፋት፤ የሰንበት ት/ቤትና የመንፈሳውያን ኮሌጆች መጠናከር፤ የአብነት ት/ቤቶች መደራጀትና በበጀት እንዲደገፉ ማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓይነተኛ ተግባር መኾኑን ምልዓተ ጉባኤው ተነጋግሮ፣ በስብከተ ወንጌል ትምህርት አሰጣጥና በመንፈሳውያን ኮሌጆች ደቀ መዛሙርት አያያዝ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፡፡
፲፩. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የኾነውን ሀብትና ቅርስ በባለቤትነት መጠበቅና ማስጠበቅ እንዲቻል ተዘጋጅቶ የቀረበውን ጥናት ቅዱስ ሲኖዶስ ካዳመጠና ከተወያየበት በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በቅድሚያ በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እንዲቀርብ ወስኗል፡፡
፲፪. ብፁዓን አበው በሌሉባቸው አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ዕጩዎች ቆሞሳት ምርጫን በተመለከተ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ ቆሞሳትን በማወዳደር ፲፮ ቆሞሳት ለኤጲስ ቆጶስነት ተመርጠዋል፤ በዓለ ሢመታቸውም ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም እንዲፈጸም ተወስኗል፡፡
፲፫. ኤጲስ ቆጶሳት የሌሉባቸውን የውጭ አህጉረ ስብከት በተመለከተም በጥቅምቱ ፳፻፲ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እየታየና እየተጠና ብፁዓን አበው እንዲመደቡባቸው ለማድረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡
፲፬. በኦሮምያ ክልል በሰባት ዞኖች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ‹‹መንፈሳዊውን ትምህርት በቋንቋችን እንዳንማር ማኅበረ ቅዱሳን በደል አድርሶብናል›› በሚል ባቀረቡት አቤቱታ ዩንቨርሲቲዎቹ ያሉበት አህጉረ ስብከት ጉዳዩን ግራና ቀኝ አጣርተውና ተመልክተው መፍትሔ እንዲሰጡና ውጤቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተገለጹት የውሳኔ ነጥቦችና በሌሎችም ዐበይት ጉዳዮች ላይ ለ፲፬ ቀናት ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና
ሕዝቦቿን ይባርክ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤
አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም