ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
ለ ሕጋዊ የሚድያ ተቋማት በሙሉ፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያካበተቻቸውን መንፈሳዊ፣ ቁሳዊ፣ ታሪካዊ እና ኪናዊ ሀብቶቿን በተለያዩ የብዙኅን መገናኛ ተቋማት የሚዲያ ሽፋን በመስጠት ጉልህ አስተዋጽኦ ስታበረክቱ መቆየታችሁ ይታወቃል።
ስለሆነም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከብዙኅን መገናኛ ድርጅቶች ጋር ተቀራርባ የምትሠራባቸው የተሻለ አሠራር መዘርጋት ትችል ዘንድ የብዙኋን መገናኛ ድርጅቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና ተሰጥቷቸውና ሕግና ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ ከቤተ ክርስቲያናችን የሚወጡ መረጃዎችን በኃላፊነት እና መርሕን ባከበረ መንገድ፤ ለተዛባ ትርጉም ሳይጋለጡ እንዲዘገቡ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሚዲያዎች መረጃዎችን በትክክል እንዲያደርሱ የግንኙነት መዋቅር መዘርጋት ይቻል ዘንድ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
ስለሆነም ይህ ማሳሰቢያ ከወጣበት ጊዜ አንሥቶ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ የግል እና የመንግሥት ብዙኅን መገናኛ ተቋማት ምዝገባ እንዲያካሂዱ ጥሪ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።
በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዐውደ ምሕረት እና የዐደባባይ በዓላትን ለመዘገብ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየጊዜው የምትሰጣቸውን መግለጫዋች የሚዲያ ሽፋን ለመስጠት፣ በየአብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ቅርሶችን፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን እና በርካታ ሀብቶችን መሠረት ያደረገ የሚዲያ ሽፋን በመስጠትና ልዩ ልዩ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለመሥራት ወዘተ… የሚፈልግ ማንኛውም የመንግሥትም ይኹን የግል ሚዲያዎች ከዛሬ የካቲት ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም እስከ የካቲት ፲፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ድረስ ብቻ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በመገኘትና የተዘጋጀውን ቅጽ በመሙላት ምዝገባ እንድታካሂዱ እያሳሰብን አዲስ የሚመሠረት የሚዲያ ተቋምና ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ካልሆኑት በስተቀር ማንኛውም የሚዲያ ተቋም በእነዚህ ቀናት ተገኝቶ ምዝገባ በማከናወን ቤተ ክርስቲያናችን በምታዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ካልተካፈለ በምንም ዓይነት መንገድ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ አገልግሎት ጥያቄ ቢያቀርብ የማይስተናገድ መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ
ግንኙነት መምሪያ
የካቲት ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም