‹‹ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል›› (ሐዋ.፭፥፳፱)
መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራሁ
ሰኔ ፲፯፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ይህንን ቃል የተናገሩት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዓለም ለይቶ የጠራቸው፣ የመረጣቸው በመሆናቸው ነው። በዓለም እየተዘዋወሩ ቅዱስ ቃሉን በሚያስተምሩበት በስሙ ተአምራት በሚያደርጉበት ጊዜ ፈተና ነበረባቸው፤ እንቅፋት ያጋጥማቸው ነበረ። ብዙዎች በምቀኝነትና በቅናት እየተነሣሡ እንዳያስተምሩ ይከለክሏቸው ነበረ፤ ይናገሯቸውም ነበረ። በዚህ ሰዓት ነበር ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል›› በማለት ያስተማሩት፤ እግዚአብሔር እንዲያስተምሩ አዟቸው ነበርና። (ሐዋ.፭፥፳፱)
የእግዚአብሔር የሆነች ሰውነት የምትታዘዘውና የምትገዛው ለእግዚአብሔር ነው፤ የእግዚአብሔር መሣሪያ ስለሆነችም ይገለገልባታል፤ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አሳልፈው ያልሰጡ ሰዎች ትእዛዙን ሊጠብቁ፣ ሕጉን ሊፈጽሙም ሆነ ሊያገለግሉት አይችሉም። በዓለም ዛሬ ለሰው የሚታዘዙ አገልጋዮች ብዙዎች ናቸው። የሰውን ትእዛዝ ለመፈጸም ሞትን እንኳን የማይፈሩ አሉ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለመፈጸም የተዘጋጁና የሚፈጽሙ ግን ጥቂት ናቸው። ታዲያ ዛሬ ማነው የእግዚአብሔር ሰው? እግዚአብሔር የወደደውን፣ እግዚአብሔር የፈቀደውን ለመፈጸም የሚተጋ?
ለእግዚአብሔር የሚታዘዝ በጠፋበት ዘመን ለእግዚአብሔር የምንታዘዝ እውነተኞች ልጆች ሆነን መገኘት አለብን። እግዚአብሔር የጠራን ለዚህ ነው። እርሱን በማገልገል ክብር እንድናገኝ፣ የማታልፍ መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ በመሆኑ ትእዛዙን መጠበቅ ይገባል፡፡ ሰውነታቸውን ሰጥተው ለእግዚአብሔር በማስገዛት፣ ትእዛዙን ለመፈጸም የሚተጉትን ሰዎች ብዙ ፈተና ያጋጥማቸዋል፤ብዙ ችግር ይደርስባቸዋል። በፈተናው ግን አይሸነፉም። ችግሩ ሕይወታቸውን፣ እምነታቸውን፣ በጎ ምግባራቸውን አይለውጠውም፤ ያጸናቸዋል፤ ያበረታቸዋል እንጅ። ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል፤የሰውን ፈቃድ ከመፈጸም ይልቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ይገባል›› በማለት መልስ የሰጡት ለዚህ ነው።
ለምሳሌ እግዚአብሔር ከቀድሞ ጀምሮ ከመረጣቸው ሰዎች አንዱ ነቢዩ ዳንኤል ነው። እርሱም የእግዚብሔርን ትእዛዝ ለመፈጸም የሚደክም ነበረ። የሰውን ትእዛዝ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ አያስበልጥም ነበረ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ከመጠበቅ የሚያስተው፣ ከእግዚአብሔር ፈቃድ የሚያርቀው ማናቸውንም ዓይነት ትእዛዝ “እሽ” ብሎ አይፈጽምም፤ አይቀበልም ነበረ። በዘመኑ የነበረውን ንጉሥ ነቢዩ ዳንኤልን የማይወዱ ሰዎች አሳሳቱት። (ዳን.፮፥፵፬)
ነቢዩ ላይ የሚቀኑበት ምቀኞቹ ብዙዎች ነበሩ። በምክንያት ዳንኤልን ለማጥቃት ብለው የዳንኤል ጠላቶች ንጉሡን ዐዋጅ አስነግሮ ከሕዝብህ መካከል፣ ከመኳንንቶቹ መካከል ቃሉን የሚፈጽመውንና የማይፈጽመውን መለየት እንደሚችል ነገሩት። (መዝገበ ታሪክ ገጽ ፻፯-፻፰፣ዳን. ፫፥፩-፪) እውነት መስሎት ጠላቶች፣ ክፉዎች፣ ምቀኞች፣ ቅናተኞች እንደ መከሩት እርሱ ለሠራው ምስል እንዲሰግዱ ዐዋጅ አስነገረ። ነቢዩ ዳንኤል ግን ዕለት ዕለት ለእግዚአብሔር ይንበረከካል፤ ዕለት ዕለት በጸሎቱ ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገራል። ‹‹ጸሎትሰ ተናግሮተ ሰብእ ምስለ እግዚአብሔር ልዑል፤ ጸሎት ማለት ሰው ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ነገር ናት›› እንዲል፡፡ (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፬) ነቢዩ ዳንኤል የምድራዊውን ንጉሥ ዐዋጅ ፈርቶ ለእግዚአብሔር መስገድ እና ወደ እግዚአብሔር መጸለይ አልተወም። ከምድራዊው ንጉሥ ትእዛዝ ይልቅ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም እንደሚገባው ያውቅና ያምን ነበርና፤ ማወቅ ብቻውን ግን አይጠቅምም። ባወቁት ነገር ማመንና መጽናትም ያስፈልጋል።
ትንቢተ ዳንኤል ፮፥፱ ላይ ዐዋጁ ከታወጀ በኋላ ይህን ዐዋጅ ያፈረሰ፣ የጣሰ፣ የተላልፈ ብርቱ ቅጣት እንደሚደርስበትም አብሮ ተነግሯል። ዳንኤል ግን ወደ ቤቱ ገባ፤ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበረ። ቀድሞም ያደርግ እንደነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ፤ አመሰገነ።
ወገኖቼ እናንተ የእግዚአብሔር ናችሁ፤ የምትከተሉት እግዚአብሔርን ነው፤ የምትገዙት ለእግዚአብሔር ነው፤ የምታመሰግኑት እግዚአብሔርን ነው፤ የምትመኩት በእግዚአብሔር ነው። ይህንን ተው የሚላችሁ ቢመጣ ትተዋላችሁ? ምን ታደርጋላችሁ? እስኪ ራሳችሁን ጠይቁ። ማንነታችሁን በእግዚአብሔር ቃል መንዝሩ፤ ማንነታችሁን በእግዚአብሔር ቃል መርምሩ፤ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ በዕብራውያን መልእክቱ ምዕራፍ አራት ላይ የእግዚአብሔር ቃል የልብን ሐሳብና ስሜት ይመረምራል። “ምንድን ነው ሐሳቤ? ምንድን ነው ስሜቴ? ምንድን ነው ፍላጎቴ? ምንድን ነው አምሮቴ?” ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፤
ዛሬ እንደ ዳንኤል ያለ ሰው እግዚአብሔር ይፈልጋል። “መንፈሳዊ ጉዞዬን አላቆምም፤ መንፈሳዊ አገልግሎቴን አላቆምም፤ መከራ ፈርቼ ከእግዚአብሔር አልርቅም” የሚል ሰው ዛሬም እግዚአብሔር ይፈልጋል። ዳንኤል ወደ ኢየሩሳሌም ዞሮ ይሰግድ ነበረ፤ ዳንኤል ወደ ኢየሩሳሌም ዞሮ ይጸልይ ነበረ፤ እኛም ወደ ኢየሩሳሌም ዞረን እንስገድ። ኢየሩሳሌማችን በክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን ናት። ወደ እርሷ ዞረን እንስገድ፤ ወደ እርሷ ዞረን እንንበርከክ፤ የምንሰግደው የምንንበረከከው ለእግዚአብሔር ነው። ነቢዩ ዳዊት ”በቅድስናው ሥፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ” እንዳለ። (መዝ.፻፴፪፥፯)
ዳንኤል ወደ ኢየሩሳሌም ዞሮ እንደጸለየ ፊታችንን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አዙረን እንጸልይ፤ በጸሎታችን ከእግዚአብሔር ጋራ እንነጋገር። በኅብረት እንጸልይ፤ እንደፈቃዱ እንጸልይ፤ የምንጸልየውን እንወቅ፤ በጸሎታችን ጊዜ ኃጢአታችንን እንናዘዝ እንጅ ፍርሃትን ወደ ውስጣችን በማስገባት ልንረበሽ፣ ልንሸበር፣ ልንጨነቅ አይገባም። ዓላማ ያስፈልገናል። ወደ ግራም ወደ ቀኝም ልንል ልንንገዳገድ አይገባንም፤ ጸንተን ልንቆም እንጅ። ዳንኤል በእምነት ጸንቶ በመቆሙ እነዚያ ምቀኞቹ፣ ቀናተኞቹ፣ አድመኞቹና ተንኮለኞቹ ከሰሱት። ዳንኤል የንጉሡን ዐዋጅ ንቆ መስኮቱን በኢየሩሳሌም አንጻር ከፍቶ፣ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ እየተንበረከከ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ እንዳገኙት መሰከሩበት ። (ዳን.፮፥፲፪)
ንጉሡ ዳንኤልን ይወደው ነበር። ቢሆንም “የተናገረውን እንዴት ያስቀራል? ንጉሥ አይደለምን?” ብለው እነዚያ ከሳሾቹ እርሱን እንዳያሙት ዳንኤልን ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲጥሉት አዘዛቸው። (ዳን.፮፥፲፮) የተራቡ አንበሶች ከጉድጓድ ውስጥ ሆነው ሲያገሱ እጅግ ያስፈራ ነበር። ዳንኤል ግን አልፈራም። ለምንድን ነው ያልፈራው ብንል እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደሆነ ያውቅ ስለነበረ ነው። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋራ የሆነ ምንም ምንም የሚያስፈራው፣ የሚያሸንፈውምና የሚቃወመውም አይኖርም። ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ ‹‹እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?›› ብሎ ተናግሯል። (ሮሜ ፰፥፴፩)
ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥም እግዚአብሔር እንደሚጠብቀው ያውቅ ነበር። ነቢዩ ዳዊት አንድ የተናገረው ቃል አለ። ‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ እግዚአብሔር ጠባቂዬ ነው፤ የሚያሳጣኝም የለም፤ በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃም ዘንድ ይመራኛል፡፡ በሞት ጥላ መካከል እንኳን ቢሄድ እግዚአብሔር እንደሚያድነው በመታመን አልፈራም። በፊቴ ገበታን አዘጋጀልኝ፤ የምበላውን እንጀራ። ጽዋዬም የተረፈ ነው አለ። የምጠጣው ጽዋ ጎደሎ አይደለም፤ የትትረፈረፈ ነው፡፡›› (መዝ.፳፫፥፩-፭) እንዲህ ነው የእግዚአብሔር ሰዎች በእግዚአብሔር የሚመኩት። ዳንኤል ወደ አንበሶች ጉድጓድ ተጣለ። የጉድጓዱ አፍ ተገጠመ። ከዳንኤል ጋር ግን እግዚአብሔር ነበረ።በማለዳ መጥቶ በኀዘን ቃል ንጉሡ ጠራው፤ ‹‹የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን?›› አለው፡፡ ለእግዚአብሔር የማይቻለው አለ እንደ ወገኖቼ? ለእግዚአብሔር የማይቻለውና የሚሳነው ነገር የለም። ዳንኤል ምን አለ? ‹‹በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፥ ንጉሥ ሆይ፥ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም›› አለው። እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ። እንዲያ ሲያገሱ የነበሩትን የአንበሶቹን አፍ ዘጋ። ዳንኤል ከአንበሳ ጉድጓድ ወጣ። ለምንድን ነው ዳንኤል ከአንበሶቹ የዳነው? ሰውነቱ የምትታዘዘው ለማን ስለሆነ ነው? ለእግዚአብሔር! ለእግዚአብሔር የምትታዘዝ ሰውነት ከመከራ ትሰወራለች። (ዳን.፮፥፲፱፥፳፫)
ወገኖቼ! እኛም አናብስት እንዳይበሉንና እንዳያጠፉን ለእግዚአብሔር የምትታዘዝ ሰውነት ትኑረን። እኔንና እናንተን ለማጥፋት የተዘጋጁ አናብስትና አጋንንት ናቸው። እንቅልፍም ሆነ ዕረፍት የላቸውም። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው ‹‹በጊዜው ከፍ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃያሉ ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ። የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት፤ እርሱ ስለእናንተ ያስባልና። ጠላታችሁ ዲያብሎስ ግን የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙሪያችሁ ይዞራል።›› (፩ኛጴጥ.፭፥፮) አዎ እርሱ በዙሪያችን ይዞራል። እኛ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ስንተው ሰብሮ እና በኃጢአት ጦር ወግቶ ይጥለናል። ወገኖቼ! እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ። ዛሬም ቅዱስ ሚካኤልን ልኮ የአጋንንትን አፍ እንዲዘጋልን፣ የአጋንንትን ኃይል እንዲያደክምልን እግዚአብሔርን እንለምነው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን እንዲልክልን፣ ሰይጣንን ድል እንዲያደርግልን፣ የሰይጣንን ኃይል እንዲያደክምልን፣ ወጥመዱን እንዲሰብርልን፣ መረቡን እንድበጣጥስልን እግዚአብሔርን እንለምነው። እግዚአብሔር ለለመኑት ቅርብ ነው፤ እርሱ ይሰማል፤ ያያልም።
ዳንኤል ለእግዚአብሔር በመታዘዙ ድኗል። ሠለስቱ ደቂቅ አናንያ፣ አዛርያ፣ ሚሳኤል በወጣትነት ዘመናቸው፣ በእሳትነት ዘመናቸው ለሰውነታቸው ፈቃድ ሳይገዙ ሳይታዘዙ የዓይን አምሮት ሳያሸንፋቸው ለእግዚአሔር የታዘዙ ናቸው። ለእግዚአብሔር የተገዙ መብል መጠጥ እንኳን ያላሸነፋቸው እነዚህ ወጣቶች ተማርከው ወደ ባቢሎን ሲደርሱ በቤተ መንግሥት ጮማ እንዲቆርጡ፣ ጠጅ እንዲጠጡ እንዲበሉ ሲጋበዙ አንበላም፤ አንጠጣም፤ የምንቆረጥመው ሽምብራ ከቀዝቃዛ ውኃ ጋር ብቻ ይሰጠን በማለት ጠይቀዋል፡፡ ከነቢዩ ከዳንኤል ጋራ በጾም በጸሎት ተወስነው የተገኙ ሦስቱ ወጣቶች ናቸው።
በዚያን ጊዜ ንጉሡ ጣዖት አቆመ፤ አሁንም እነዚህ ሦስቱ ወጣቶች እግዚአብሔር አዋቂዎች ያደረጋቸው ጥበበኞች ስለነበሩ ምቀኞች ተነሡባቸው። ንጉሡንም ዐዋጅ እንዲያውጅና እርሱ ላቆመው ምስል የሚሰግደውንና የማይሰግደውን መለየት እንደሚችል ነገሩት። ሠለስቱ ደቂቅ እንደማይሰግዱ ስለሚያውቁ ይህን መከሩት። በንጉሥ ዘንድ ባለሟሎች ስለሆኑ በዚህ ተመቅኝተዋቸው ነው። (ዳን. ፫፥፬-፮) ንጉሡም ዐዋጅ አሳወጀ። ሁሉም በግዛቱ ሥር ያሉ እርሱን ፈርተው ለጣዖት ሲንበረከኩ ሦስቱ ወጣቶች ግን አልሰገዱም። በዚህም ጊዜ አይሁድ ንጉሡን እንዲህ በባቢሎን ሀገሮች ለሚሠራ ሥራ የሾማቸው፥ ለአይሁድ ወገን የሚሆኑ ትእዛዙን እምቢ ያሉ፥ አምላኩን ያላመለኩ፥ ለሠራውም ለወርቁ ምስል ያልሰገዱ አዛርያ፣ አናንያ እና ሚሳኤል የተባሉት ሰዎች እንዳሉ ነገሩት፡፡ (ዳን. ፫፥፱-፲፪) ንጉሡም ሠለስቱ ደቂቅን አስጠርቶ ‹‹ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን የመሰንቆውንና የክራሩን የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፡፡ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?›› ብሎ ተናገራቸው።
ሠለስቱ ደቂቅም መልሰው ‹‹ናቡከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም፡፡ ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፥ ከሚነድደው ከእሳት እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ፥ ላቆምከውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ›› አሉት፡፡ (ዳን.፫፥፲፬-፲፰) የሚነደው እሳት አላስፈራቸውም። ለምን ይፈራሉ? ከእግዚአብሔር ጋር የሆች ሰውነት ትፈራለች? አትፈራም።
እግዚአብሔር ፍርሃትን ያርቃል። ለእግዚአብሔር የሆነች ሰውነት ደካማ አይደለችም፤ ብርቱ ናትና። ለእግዚአብሔር የሆነች ሰውነት ፈሪ አይደለችም፤ ጀግና ናትና። ይህን ማወቅ ያስፈልጋል። እጅ እግራቸውን አስረው “ለጣዖት ትሰግዳላችሁ ወይስ ወደዚህ እሳት ብትጣሉ ይሻላችኋል?” ምረጡ ተባሉ። አቤት እኛ ምን እንል ይሆን? ሦስቱ ወጣቶች ግን ምንድን ነው ያሉት? ‹‹እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፥ ከሚነድደው ከእሳት እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል።›› ምን ዓይነት እምነት ነው? ዛሬ የጠፋው ይህ እኮ ነው! ከሁሉ አስቀድሞ ጽኑ እምነት ያስፈልጋል። እምነትን ደግሞ ከበጎ ምግባር ማዋሐድ ያስፈልጋል።
እግዚአብሔር ሊያድነን ይችላል። ይህንን አንጠራጠርም። ነገር ግን ፈቃዱ ሳይሆን ቀርቶ እንኳን ባያድናቸው እርሱ ላቆመው ጣዖት እንደማይሰግዱ ሠለስቱ ደቂቅ ነግረውታል። ወደ እሳት ጣሏቸው፤ እነርሱን የጣሉ ወታደሮች የእሳቱ ወላፈን በላቸው፤ ሞቱ። ሦስቱ ወጣቶች ግን እጅ እግራቸው ተፈቶ ከአራተኛው ሰው ጋር በእሳቱ ተመላለሱ። እምነት እንዲህ ነው! በእሳት ውስጥ የሚያመላልስ፣ የእሳትን ኃይል በረዶ የሚያደርግ እምነት ነው። ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ የታሠሩ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ፈታ፤ በእሳት ውስጥ ይመላለሱም ጀመር። ለእግዚአብሔር የምትታዘዝ ሰውነት እንዲህ ናት። እሳት አይበላትም፤ እሳት አያቃጥላትም።
ወገኖቼ! ለእግዚአብሔር የምትታዘዝ ሰውነት ካለች፣ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር እንታዘዛለን ብለን የምንወስን ከሆነ እንኳን ምድራዊ እሳት ገሃነመ እሳት አያቃጥለንም። ከዳግመ እሳት የምንሠወረው ከሥጋችን ይልቅ ለነፍሳችን ስንኖር ነው። እኛ ግን የምንወጣው የምንወርደው፣ የምንጨነቀው፣ የምንደክመው፣ ለሥጋችን ነው። የሥጋ ፍላጎታችንን፣ የዓይን አምሮታችንን ለማሟላት ነው። የሥጋ ፍላጎታችን የዓይን አምሮታችን ከተሟላ እውነቱን ሐሰት ብለን ከመለወጥ አንመለስም። ያየነውን አላየንም፤ የምናውቀውን አናውቅም ነው የምንለው። ይህን ያህል ደፋሮች ነን።
ወገኖቼ! የእውነት ምስክሮች እንሁን። እውነትን ይዘን እንሙት። ይህ ነው ከእኛ የሚጠበቀው። ቅዱሳን ሐዋርያት የተናገሩት ቃል አለ፤ (ሐዋ.፫፥፳)። እነርሱ በነበሩበት ዘመን የነበሩ ባለሥልጣናት ወደ ሸንጎ ጠርተው “ዝም በሉ” አሏቸው። ፈጣሪያቸው ግን “ተናገሩ” ብሎ ነው የላካቸው። እንግዲህ የማንን ትእዛዝ ይቀበሉ? የመረጣቸው አምላክ ተናገሩ፤ ዝም አትበሉ፤ ጩኹ፤ አስተምሩ አላቸው። የሰማይ የምድር ጌታ፣ በመንግሥቱ ሽረት በባሕርይው ሞት የሌለበት ባለ ሥልጣን፣ ለዘመኑ ጥንትና ፍጻሜ የሌለው “አስተምሩ፡ ተናገሩ” ብሎ አዘዛቸው። ሰዎች ደግሞ ተነሥተው በቅናት በምቀኝነት “ዝም በሉ” አሏቸው። ሐዋርያት የማንን ትአዛዝ ይፈጽሙ? ለማን ይታዘዙ? እስኪ እናንተ ፍረዱ! ለእግዚአብሔር! እምቢ ሲሉ እንደሚገረፉ ቢያውቁም አምላካቸውን ታዝዘዋል።
እንዲያው እኛስ ማንን ነው የምንታዘዘው? ምን ዓይነት ሕይወትስ ነው ያሳለፍነው? የርኩሰት? የቅድስና? ራሳችንን እንመርመር። በኃጢአት ከሆነ ወደ ጽድቅ እንመለስ። እግዚአብሔር ዕድሜ ለንስሓ ሰጥቶናልና። በጨለማ ያለን ወደ ብርሃን እንምጣ። በሞት ያለን ወደ ሕይወት እንሻገር። ዛሬ እኮ ሐሰት የነገሠበት፣ የተስፋፋበት ዘመን ነው። በዚህ ዘመን እውነተኛ ሰው ይስፈልጋል፤ የእውነት ባለቤት እግዚአብሔርን አምኖ እውነቱ ይህ ነው የሚል፣ የማይፈራ፣ እንደ ነቢዩ ዳንኤል፣ እንደ ሠለስቱ ደቂቅ፣ እንደ ሐዋርያት እውነቱን የሚናገር ይፈለጋል። እውነት ስትናገሩ “አበጃችሁ” የሚላችኹ ላይኖር ይችላል። ሆኖም ግን ከሰው ምንም አትጠብቁ። ከማን ነው መጠበቅ ያለባችኹ? ከእግዚአብሔር ብቻ ነው!የሐሰት አጋፋሪዎች ብዙዎች ናቸው። ከእውነት ጋር ግን የቆሙ አልተገኙም። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ላይ እንዲህ አለ፤ ‹‹ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን፡ የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፤ ዓይተንማል፤ እንመሰክራለንም።›› (፩ኛ ዮሐ.፩፥፩)
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ የሕይወት ቃል ያለው ማንን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በወንጌሉ ላይ ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበር፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።…….ያ ቃል ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛም አደረ›› (ዮሐ.፩፥፩) ያለለት የሕይወት ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።“እንመሰክርማለን” በማለት ተናገረ። እንዲህ ያስፈልጋል ወገኖቼ! የእውነት ምስክር! ሰው የእውነት ምስክር መሆን የሚችለው መቼ ነው? እንዲህ በሥጋ ፈቃድ ብቻ አይደለም።
ሰውነቱን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ያደረገ፣መንፈስ ቅዱስ አፉን ከፍቶ፣ ፊቱ ጸፍቶ የሚያናግረው ሰው ስለእውነት ይመሰክራል።ለእግዚአብሔር ይታዘዛል።የሐዋርያት ሥራ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕርገቱ አስቀድሞ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር።‹‹ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤እውነትን ለመመስከር ኃይል ታገኛላችሁ። በኢየሩሳሌም፣በይሁዳ ሁሉ፣በሰማርያ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮች ትሆናላችሁ፡፡›› (ሐዋ.፩፥፰)ይህ ነው የሚያስፈልገው።
ሰውነታቸው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆኑን ያወቁ ሰዎች ግን ከኃጢአት ተመልሰው ከበደል ርቀው ሰውነታቸውን ሠርተው፣ ቀጥተው ለእግዚአብሔር በመታዘዝ፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ በመሆን ዘወትር እውነትን ይናገራሉ፤ ስለ እውነት ይመሰክራሉ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ እንዲህ ብሏቸው ነበረ፤ ‹‹ዛሬ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱ ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል።›› (ዮሐ.፲፭፥፳፯) ጌታችን በደቀመዛሙርቱ ላይ አድሮ እውነት እንዲመሰክሩ፣ እውነት እንዲናገሩ ያደርጋቸዋል። ይህንን ነው የነገራቸው። ‹‹እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ እኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክርላችሁ›› ብሏቸዋል። እኛ በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት መንፈስ ቅዱስ ሠረጸ የምንለው ከአብ ነው! አንዳንዶች ግን ከአብና ከወልድ ነው የሠረጸው ብለው ምሥጢረ ሥላሴን የሚያፋልሱ መናፍቃን አሉ። መድኃኒታችን ግን ከአብ የሚወጣ መንፈስ ቅዱስ አለ። ከአብ ሠረጸ የምንለውም ለዚህ ነው። ሰው የመጻሕፍትን ቃል ጥሬውን ደረቁን መናገር ብቻ ሳይሆን ማስተዋልም ይገባዋልና፤ ትርጓሜውን መረዳት ይገባዋልና። “ንባብ ይገድላል፤ ትርጓሜም ያድናልና” አበው እንደተናገሩ።
በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ላይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ አለ፤ ‹‹ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግ በነቢያት በመዝሙራትም ስለእኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። በዚያን ጊዜ መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሯቸውን ከፈተላቸው። እንዲህም አላቸው ክርስቶስ መከራ ይቀበላል፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ በስሙም ንስሓና የኃጢአት ሥርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል። ተብሎ እንዲሁ ተጽፏል። እናንተም ለዚህ ምስክሮቼ ናችሁ።›› (ሉቃ.፳፬፥፵፬) ምስክሮቼ ናችሁ ያላቸው ደቀ መዛሙርቱን ነው። ስለ ዓለም የሚመሰክር ብዙ ነው። ስለ እግዚአብሔር የሚመሰክር ግን ማን ነው? እርሱ የመረጣቸው ነቢያትም ይሁኑ ሐዋርያት ከሐዋርያትም በኋላ ብዙ ቅዱሳን የእውነት ምስክሮች ሆነው ቆመዋል። ስለ እውነት ብለው በመጋዝ ተተርትረዋል፤ በሰይፍ ተመትረዋል፤ በእሳት ተቃጥለዋል፤ ለአናብስት ተሰጥተዋል፤ እጅ እግራቸው ተቆራርጧል። የእውነት ምስክሮች በመሆን።
ዛሬ ግን እንኳን መከራ መጥቶ ሥጋዊ ፍላጎታችን፣ የዓይን አምሮታችን ስላሸነፍን ከእውነት እየራቅን ነው፤ ከእውነት እየሸሸን ነው። ከላይ ሲያዩን እውነተኞች እንመስላለን በውስጣችን ያለው ግን ሐሰት ነው፣ ከላይ ሲያዩን ቅዱሳን እንመስላለን፤ በውስጣችን ግን ርኩሰት ያለብን፣ የተለሰንን መቃብሮች ነን፤ ከላይ ሲያዩን ንጹሐን እንመስላለን፤ ውስጣችን ግን በኃጢአትና በበደል የቆሸሸ ነው። ለዚህ ነው የእውነት ምስክሮች ልንሆን ያልቻልነው። እነዚያን ግን የመረጣቸውን እንዲህ አላቸው፤ ‹‹እናንተ ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።፤ እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፡፡›› (ሉቃ.፳፬፥፵፱) ኢየሩሳሌም ቅድስት፣ የሰላም እና መንፈሳዊ ከተማ ናት፤ በዚያ እንዲቆዩ፣ ከእርሷ ሳይወጡ፣ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳይሉ የቆዩ እንደሆነ ከላይ ኃይል እንደሚያገኙ እና መንፈስ ቅዱስ እንሚወርድላቸው ነገራቸው። ቅዱሳን ሐዋርያትም ቃሉን ጠበቁ፤ ቃሉን ፈጸሙ፤ በኢየሩሳሌም ቆዩ፤ ደካሞች የነበሩ በረቱ፤ የእውነት ምስክሮች ሆኑ።
እኛ ግን ዓለም እያጓጓችን ከዓለም ያለውን ስንቀላውጥ ጠፍተን ቀርተናል። ትአዛዙ ግን “በኢየሩሳሌም ቆዩ” ነው። እኛ በየት እንቆይ? ኢየሩሳሌማችን ማን ናት? ቤተ ክርስቲያናችን ናት። እምነቷን ሥርዓቷን ጠብቀን በእርሷ ጸንተን እንኑር! የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እናገኛለን። ከዚያ በኋላ ጠላታችንን ዲያብሎስን እናሸንፋለን እንጂ አንሸነፍም። ከዚያ በኋላ ሰውነታችን ለእግዚአብሔር የምትታዘዝ ትሆናለች፤ ለእግዚአብሔር የምትገዛ ትሆናለች።
ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ቃል አለ፤ ‹‹መታዘዛችሁም ለሁሉ ዘንድ ተሰምቷል። …የሰላም አምላክም ፈጥኖ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይቀጥቅጠው።›› (ሮሜ ፲፮፥፲፱) እኛ እንታዘዝ እንጂ እርሱ ጠላታችንን ያሸንፍልናል፤ ድል ያደርግናል። ሁላችንም ከኃጢአት ተመልሰን፣ ከበደል ርቀን፣ ኃጢአታችንን ለካህን ተናዘን፣ ንስሓ ገብተን፣ አማናዊ ሥጋውን አማናዊ ደሙን ተቀብለን፣ በቤተ ክርስቲያን ጸንተን እንድንኖር፣ ለእግዚአብሔር የምትታዘዝ ሰውነት እንድትኖረን፣ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት አይለየን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!