‹‹ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ›› (መዝ.፹፰፥፫)
ዲያቆን ዮሐንስ ተመስገን
ጥቅምት ፪፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ነቢዩ ዳዊት ‹‹ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ፤ ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ›› ብሎ እንደነገረን እግዚአብሔር ባዘጋጀላቸው ማረፊያ ሊያኖራቸው ቃል ኪዳን የሰጣቸው ንዑዳን አሉ።(መዝ.፹፰፥፫) የአምላካችን ቃል ኪዳን ፍጻሜው በመንግሥቱ ማኖር ነው። እያንዳንዱ እንደተጠራበት ጊዜና ሁኔታ በተለያየ አኳኋን ጌታውን ቢያገኝም የአምላካችን ስጦታ ግን ለመረጣቸው ሁሉ አንዷ መንግሥተ ሰማያት ናት፡፡ (ማቴ.፳፥፱)
ቅዱሳን በተለያየ መንገድ ይጠራሉ፤ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው›› ማለቱም ስለዚህ ነው። (፩ኛ ቆሮ.፲፪፥፬) ለአንዱ የሰማዕትነት፣ ለአንዱ የመምህርነት፣ ለአንዱ የሰባኪነት ለሌላው ደግሞ ጸሎት ጸጋቸው ሊሆን ይችላል።
በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ግብጽ ተወልደው ኢትዮጵያ በተጋድሎ የኖሩት አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ተአምራቸው ብዙ፣ ተጋድሏቸው ጽኑዕ ነው። የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ በብሕትውና ጸንቶ በጸሎት መትጋት ነው። ገድላቸው በተመስጦ በጸሎት ባሉበት ጊዜ ሰይጣን እንደ ሁልጊዜው ሊፈትናቸው በቁራ አምሳል መጥቶ ዐይናቸውን እስኪያወጣው ድረስ ጸሎታቸውን እንዳያቃርጡ ይነግረናል። ለጸሎት ያላቸው ልዩ ቦታ በዚህ ይታወቃል። ምን ይደንቅ፣ ምን ይረቅ!? ‹‹ጸሎት ብሂል ተናግሮተ ሰብእ ምስለ እግዚአብሔር፤ ጸሎት በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ያለ ግንኙነት ነው›› የሚለውን የአረጋዊ መንፈሳዊ ትምህርት በተመስጦ ሁነው እየተነጋገሩ ተርጉመው አሳይተውናል።
ለአገራችን ኢትዮጵያና ለዓለም ሁሉ ምሕረት እንዲመጣ አንድ ጊዜ በአፍቸው ድንጋይ ነክሰው፣ ሌላ ጊዜ በፍጹም ተመስጦ ባሕር ውስጥ ገብተው ጸልየዋል። ‹‹ሕዝቡን ካልማርክልኝ ከዚህ አልወጣም›› እስከማለት ደርሰው ፻ ዓመት በባሕር ቆይተዋል። በዚህ ሁሉ ተጋድሎ ድል አደረጉት እንጂ የሰይጣን ፍላጻ አልተለያቸውም። በዚህ ጸሎታቸውም የኢትዮጵያ ሰዎችን አስተምሮ ከባዕድ አምልኮ የሚመልስ ደገኛ አባት አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አስገኝተዋል። እሳቸው በዝቋላ ባሕር ውስጥ በጸሎት፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በረድኤተ እግዚአብሔር እየተመሩ በትምህርት ጸላኤ ሠናያት ዲያብሎስን ድል እየነሡ በርካታ ምእመናንን አጥምቀዋል። ፻ ዓመቱ እንዲሀ አልፏል፡፡
ለወትሮው የሰው ልጅ ሲያያቸው ከግርማቸው የተነሣ የሚደነግጥላቸው አናብስትና አናምርት (ነብሮች ለማለት) ፷;፷ ሁነው በሄዱበት እየሄዱ ባደሩበት እያደሩ ተከትለዋቸዋል። ‹‹ብፁዕ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል›› እንዲል (ምሳ.፲፪፥፲) ሲራክ ለሰው ብቻ ያይደለ ለእንስሳት ነፍስ የሚጨነቁት አባታችንም ‹‹ምን አበላቸዋለሁ? ግዳይ አልጥልላቸው?›› ብለው ፈጣሪያቸውን ጠይቀውት ነበር። ሁሉ ማድረግ የሚቻለው ጌታም ‹‹ጸበለ እገሪከ ይልህሱ በእንተዝ ይጸግቡ፤ የእግርህን ትቢያ ልሰው በዚያ ጠግበው ይኖራሉ›› አላቸው፤ እንዲህ ሁነው ትቢያቸውን እየላሱ አብረዋቸው ኑረዋል።
ምግባቸው ቃለ እግዚአብሔር፣ ልብሳቸው ጸጋ እግዚአብሔር የሆነላቸው እኒህ አባት የሚሰማ ቢገኝ ለዚህ ትውልድ አማናዊ መምህር ነበሩ። ሩትና ኑኃሜን ባደረጉት ንግግር ላይ ‹‹አገርሽ አገሬ ሕዝብሽ ሕዝቤ ነው›› የሚል ኃይለ ቃል አለ። አባታችንም ከንሂሣ ተነሥተው ኢትዮጵያ ሲመጡ ‹‹አገሪቷ አገሬ ሕዝቧም ሕዝቤ ነው›› ብለው ነበር፤ እንዳሉትም ሆነ፤ ሕዝቡ ተቀበላቸው፤ እርሳቸውም ያለመታከት በጽኑዕ ተጋድሎ እግዚአብሔር እንዲምርላቸው ጸለዩ፤ ማረላቸውም።
ይህ ትውልድ አባቱን አላወቀም፤ ቢያውቅማ “ይህ የእኔ እንጂ ያንተ ቀየ አይደለም” ማለትን ከወዴት ያመጣው ነበር። ማን አስተማረው? ንጹሕ ስንዴ ዘርተው እንክርዳድ አብሮ እንደበቀለ ወንጌል ይነግረናል። እንክርዳዱን ማን እንደዘራው ቢጠይቁ መልሱ “ጠላት ይህን አደረገ” የሚል ነበር። በውኑ “የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ልጅ ነኝ” የሚል ሁሉ “ሕዝቡ ሕዝቤ” በማለት ፋንታ ያንተ ቀየ አይደለም ይላልን? ክርስትና ላልደረሳቸው በመትጋት ፋንታ “እኔ ልዩ ዘር ነኝ” በማለት ይኩራራልን? ክርስቶስን ባለማወቅ መዳን ስለቀረባት አንዲት ነፍስ በማዘንና በመጨነቅ ፋንታ ወትሮም ከእናንተ ዘንድ ሃይማኖት የለም በማለት ይታበያልን? አስተውሉ፦ ‹‹በሰማይ በሕይወት ካሉት ከ፺፱ በጎች ይልቅ ጠፍታ በተገኘች አንዲት ነፍስ ደስታ ይሆናል፡፡›› (ሉቃ.፲፭፥፬)። ከአባታችን ሕይወት ለሚማር ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ የሰውን ዘር መጥላትና ማሳደድ ይቅርና ለእንስሳው እያዘነ ከአንበሳው ጋራ መኖርን ገንዘቡ ያደርጋል።
የመቃርስና የእንጦንስን ቆብ በክብር የተቀበሉት አባታችን ዘመናቸውን ሙሉ በመክሊታቸው እያተረፉ ከጌታችን ‹‹ጸጋ በዲበ ጸጋ፤ በጸጋ ላይ ጸጋ›› ተሰጥቷቸዋል። በወንጌል አምስት መክሊት ተሰጥቶት ላተረፈው “ላለው ይጨመርለታል” ብሎ እንደጨመረለት ያለ፡፡ (ማቴ.፳፭)
ከልጅነታቸው ጀምሮ ልብስ አለበሱም፤ ጸጋ እግዚአብሔርን ለብሰዋል፤ ምግብ አይበሉም፤ ‹‹ወኅብስተ መላእክቲሁ በልዑ እጓለ እመሕያው፤የመላእክትን እንጀራ የሰው ልጆች በሉ›› እንዳለ ዳዊት (መዝ.፸፯፥፳፭) እንደ መላእክት ምስጋና ምግብ ሁኗቸው ረጅም ዘመናት ኑረዋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍቅሩ የተነሣ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምን አሳይቷቸው ባርካቸዋለች፤ መላእክት እንዲታዘዙላቸው አድርጎላቸዋል፤ በደመናትና በመባርቅት ላይ ሹማቸዋል፤ በምድር ሁነው የሰማይን ምሥጢር አይተዋል፤ ሩጫቸውን ሲጨርሱም ‹‹የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል›› እንዳለ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ የድል አክሊል አቀዳጅቷቸዋል። (፪ኛጢሞ.፬፥፰)
እንዲህ ላሉት ዓለም አልተገባንም እያሉ የበግና የፍየል ሌጦ እየለበሱ በዱር በገደል ለኖሩት ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይልላቸዋል፤ ‹‹እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና፡፡›› (ዕብ.፲፩፥፲፮) ይህ ከሕጉ የወጡትን እንደሚያፍርባቸውና እንደሚፈርድባቸው ሲያሳየን ሕጉን ጠብቀው ለተጓዙት ደግሞ ባዘጋጀላቸው ከተማ እንዲኖሩ ወደ ጌታህ ደስታህ ግባ እያለ ይፈርድላቸዋል። (ማቴ.፳፭፥፳፩) ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርባቸውምና።
ዘወትር ለምሕረት ከጌታችን ፊት በጸሎት የተጉት፣ በሐዋርያት እግር ተተክተው አምልኮተ ጣዖት የበዛባቸውን አካባቢዎች በጸሎት ኃይል እና በትምህርት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የመለሱት ታላቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ጥቅምት አምስት ነው። ታኅሣሥ ፳፱ ተወልደው ፭፻፷፪ (አምስት መቶ ስድሳ ሁለት) ዘመናት በትሕርምት እየተጋደሉ ኑረው መጋቢት አምስት ዕረፍታቸው ቢሆንም ክርስቲያኖች የጌታችንን ጾምና መከራውን እያሰቡ ፍጽምት በምትሆን ጾምና ጸሎት የሚያሳልፉበት የዐቢይ ጾም ወቅት በመሆኑ አባቶቻችን የዕረፍታቸውን መታሰቢያ ወደ ጥቅምት አምስት አምጥተውታል። በዚህም ምክያት ጥቅምት አምስት የዕረፍታቸውን መታሰቢያ እናከብራለን።
ማስታወሻ፦ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ተአምራትና ተጋድሎ እጅግ በጣም አጭር ነገር ጻፍን እንጂ የአባታችን ተአምርና ተጋድሎ እንዲህ በሽራፊ ጽሑፍ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። ይልቁንም ገድሉንና ተአምሩን ማንበብ ይገባል እያልን በዚሁ እንሰናበታለን።
ምንጭ፡- ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ