ከሁለት ሺሕ በላይ አዳዲስ አማንያን የሥላሴን ልጅነት አገኙ
ጥቅምት ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በዐርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት በዝጊቲ ደብረ ሰላም አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ከሁለት ሺሕ በላይ አዳዲስ አማንያን ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አገኙ፡፡
‹‹ይህን ያህል አዳዲስ ምእመናንን ማግኘታችን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ድል ነው›› ያሉት የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ገሪማ ጌታነህ የጥምቀት መርሐ ግብሩ ቤተ ክርስቲያናችን መሥራት የሚገባትን ያህል ብትሠራ ከዚህ የበለጠ ድል አድራጊ እንደምትኾን ያመላከተ እንደ ነበረና ሀገረ ስብከቱ በቀጣይ ለሚሠራው ሥራ ከፍተኛ መነሣሣትን እንደ ፈጠረ አስረድተዋል፡፡
ተጠማቂዎቹ በሃይማኖታቸው ጸንተው እንዲኖሩ፣ ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳይለዩ ለማትጋት ሰባክያነ ወንጌልን መመደብ እና የንስሐ አባት እንዲኖራቸው ማድረግ በቀጣይ ሊሠራ የሚገባው ተግባር መኾኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እንደ ተናገሩት እነዚህ አዳዲስ አማንያን ወንጌልን ተምረው የክርስትና ጥምቀትን እንዲጠመቁና የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ልዩ ልዩ ድጋፍ ካደረጉ ምእመናን መካከል ወለተ ማርያም እና ባለቤታቸው ኃይለ ኢየሱስ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
በ፳፻፱ ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ በደራሼና ኮንሶ አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ አዳዲስ አማንያን የክርስትና ጥምቀትን መጠመቃቸውን ያስታወሱት ሊቀ ኅሩያን ገሪማ ጌታነህ አሁንም እናት ቤተ ክርስቲያንን ተቀበይን በማለት የሚጣሩ ነፍሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ መብዛታቸውን ተከትሎ በሀገረ ስብከቱ በሚገኙ ዐሥራ ዘጠኝ ወረዳ ቤተ ክህነቶች የጥምቀት መርሐ ግብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የጥምቀት መርሐ ግብሩን በስፋት ለማስቀጠልና ተጨማሪ ምእመናንን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማምጣት ይቻል ዘንድም በመላው ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በተቻላቸው አቅም ዂሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሊቀ ኅሩያን ገሪማ ጌታነህ መንፈሳዊ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት የዐርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም አበባው ጌታኹን እንደ ገለጹት በአካባቢው ከፊሉ ኅብረተሰብ ሕይወቱን በአሕዛብነት የሚመራ ቢኾንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገረ ስብከቱ፣ በወረዳ ቤተ ክህነቶችና በማኅበረ ቅዱሳን የጋራ ጥረት ከፍተኛ ቊጥር ያላቸውን ወገኖች የቤተ ክርስቲያን አባላት ለማድረግ ተችሏል፡፡
በወረዳው የሚገኙ ኢ አማንያንን በማስጠመቅ የቤተ ክርስያናችን አባል ለማድረግ አንዱ መሰናክል በአማንያኑ ቋንቋ ወንጌልን ማስተማር የሚችሉ ሰባክያነ ወንጌል እጥረት መኾኑን የጠቆሙት መልአከ ሰላም አበባው ወረዳ ቤተ ክህነቱ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በጋራ በመኾን ከሃያ በላይ ጋሞኛ ቋንቋ መናገር የሚችሉ ሰባክያነ ወንልን ማሠልጠኑንና በዚህም ፍሬያማ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ማስተማር የሚችሉ ሰባክያነ ወንጌልን አሠልጥኖ በመመደብ በወረዳው የሚገኙ ያልተጠመቁ ወገኖች በየቋንቋቸው ተምረው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት እንዲኾኑ የማድረጉ ተልእኮ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ያገኙ ከሁለት ሺሕ በላይ አዳዲስ አማንያን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ ለማበረታታትም ጋሞኛ ቋንቋን መናገር የሚችሉ ወጣቶችን በመመደብ የክትትልና የማስተማር ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ መልአከ ሰላም አበባው ጌታኹን አስረድተዋል፡፡
‹‹የጠፉትን በጎች ለመፈለግ ከታቀደ ቆይቷል፡፡ በአካባቢው የክረምቱ ወራት በመግባቱ መርሐ ግብሩ ለተወሰነ ጊዜ ቢጓተትም በእግዚአብሔር ተራዳኢነት፣ በበጎ አድራጊ ምእመናን ጥረት ዕቅዳችን በዛሬው ዕለት እውን ኾኖ በርካታ የጠፉ በጎችን ፈልገን ለማግኘት ችለናል›› ያሉት ደግሞ የዝጊቲ ደብረ ሰላም አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አስተዳዳሪ መምህር ቀለመ ወርቅ በላይ ናቸው፡፡
መምህር ቀለመ ወርቅ አያይዘውም ‹‹እነዚህ ጠፍተው የተገኙ፣ ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ያገኙ በጎች ተመልሰው በተኵላ እንዳይነጠቁ በአካባቢያቸው በርካታ የስብከት ኬላዎችን በማዘጋጀት ምእመናኑ አምልኮተ እግዚአብሔርን እንዲፈጽሙ፣ በእምነታቸው እንዲጸኑና አቅማቸውን አጎልብተው የራሳቸውን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እንዲገነቡ የማስቻል ሥራ ሊሠራ ይገባል›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ከተጠማቂዎቹ መካከል አንዱ የኾኑት በዝጊቲ ባቆሌ ቀበሌ ነዋሪና የሌላ እምነት ተከታይ የነበሩት አቶ ዘሪኹን ቱሎ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አምላክነት የሚሰበክባት፣ በጠበልና በእምነት ከሕመም መዳን የሚቻልባት እውነተኛ ሃይማኖት እንደኾነች በእኛ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ይነግሩኝ ነበር፡፡ ይህ ነገር ምን ያህል እውነት ነው እያልኹ ከራሴ ጋር ስሟገት ዓመታት ቢያልፉም ባለቤቴ ‹ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመለሱ› የሚል መልእክት በራእይ በመስማቷ ማንም ወደ ጥምቀቱ ሳያመጣን አምነን ተጠምቀን በዛሬዋ ዕለት የሥላሴን ልጅነት አግኝተናል›› በማለት የቤተ ክርስቲያን አባል የኾኑበትን ምሥጢር አስረድተዋል፡፡
አቶ ዘሪኹን የቤተ ክርስቲያን አባል ከመኾናቸው በፊት በገጠማቸው የጤና እክል ከዐሥር ዓመታት በላይ ሲሰቃዩ ኖረው በዝጊቲ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጠበል ተጠምቀው ከያዛቸው ደዌ እንደ ተፈወሱ፤ ከዚያም የተዋሕዶ ሃይማኖት አባል እንዲኾኑ ከተገለጠላቸው ራእይ ባሻገር መሠረት በጻድቁ አማላጅነት በተደረገላቸው ድንቅ ሥራ በመማረካቸው ከባለቤታቸው ጋር በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው፣ ንስሐ ገብተው የክርስትና ጥምቀትን ተጠምቀው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባል ለመኾን መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዝጊቲ ባቆሌ ማላላ መንደር የተገኘችው ወጣት ስመኝሽ አዦ በበኩሏ ‹‹እኔ በዛሬው ዕለት ለመጠመቅ የመጣሁት ማንም ሰው ቀስቅሶኝ ወይም ሒጂ ብሎኝ አልነበረም፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ አባል እንድኾንባት ስመኛት የኖርኋት ሃይማኖት በመኾኗና የዛሬውን የጥምቀት መርሐ ግብርም ዳግመኛ የማገኘው ስላልመሰለኝ ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከመላ ቤተሰቦቼ ጋር ተጠምቀን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባል ኾነናል›› በማለት ወደ ክርስትና የመጣችበትን መንገድ ተናግራለች፡፡
ወጣት ስመኝሽ አዦ አይይዛም ‹‹ወደፊትም በሃይማኖቴ ጸንቼ እኖራለሁ፤ ቃለ እግዚአብሔር በመማርም በአካባቢዬ የሚኖሩ መናፍቃንና አሕዛብ ለሚጠይቁኝ ጥያቄ ምላሽ የሚኾን ስንቅን እቋጥራለሁ፤ እንደዚሁም በዝጊቲ አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በየቋንቋቸው እየተዟዟርኹ በማስተማር ቀጥተኛውንና እውነተኛውን መንገድ አሳያቸዋለሁ›› በማለት መንፈሳዊ ዕቅዷን ገልጻለች፡፡
በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በዝጊቲ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በተከናወነው የጥምቀት መርሐ ግብር የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊና የትምህርት ክፍሉ ሓላፊ፤ የየወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች፤ በጎ አድራጊ ምእመናን፤ ከአዲስ አበባና ከዐርባ ምንጭ የመጡ መምህራንና ዘማርያን፤ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና የዐርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች፤ የዝጊቲና የአካባቢው ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ምእመናን በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፍ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
መረጃውን ያደረሰን የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ሪፖርተር ካሣኹን ለምለሙ ነው፡፡