‹‹…እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ…›› (፩ኛ ቆሮ.፲፫፥፲፫)
ክፍል ሁለት
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ጥር ፳፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? የዓመቱ አጋማሽ ፈተናስ እንዴት ነበር? መቼም በርትቶ ሲማርና ሲያጠና ለነበረ ተማሪ ፈተናው እንደሚቀለው ተስፋ አለን፤ ጎበዝ ተማሪ የሚያጠናው ፈተና ሲደርስ ብቻ አይደለምና! መምህራን ሲያስተምሩ ተግቶ በአግባቡ የሚከታተል ያልገባውን የሚጠይቅ፣ መጻሕፍትን የሚያነብ የበለጠ ዕውቀት ለማግኘት ተግቶ የሚያጠና ነው!
ታዲያ እንደዚህ አድርጎ ትምህርቱን የሚከታተል ጥሩ ውጤትን ያመጣል! እንግዲህ በተለያየ ምክንያት በግማሽ ዓመቱ ፈተና በደንብ ያልሠራችሁ በቀሪው የትምህርት ዘመን በርትታችሁ በማጥናት ዕውቀትን እንድታገኙና ጥሩ ውጤት እንድታመጡ አደራ እንላለን!
ልጆች! ሌላው ደግሞ በመንፈሳዊ ሕይወታችሁም ጎበዞች መሆን አለባችሁ! ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ተማሩ! መልካም! ባለፈው ትምህርታችን ‹‹ተስፋ›› በሚል ርእስ ስለ ተስፋ ተምረናል፤ ዛሬ ደግሞ ስለ ፍቅር እንማራለን!
‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው›› (፩ኛ ዮሐ.፫፥፱)
ፍቅር የክርስትና ሃይማኖት መሠረት ነው፤ ፍቅር ደሃ፣ ሀብታም፣ ኃጥእ፣ ጻድቅ ሳይሉ ሁሉን እኩል መውደድ ነው፤ ፍጹም ፍቅር ያለው ጻድቅ ነው ብሎ አይወድም፤ ኃጥእ ብሎ አይጠላም፤ እኩል ይወዳል፡፡ ሰው ወንድሙን ከወደደው ክፉ አያደርግበትም፤ በድክመቱ በውድቀቱ አይሳለቅም፤ ገበናውን ይሸፍናል፤ ሲያጠፋ ቢያየው እንኳን ይመክረዋል፤ ገበናውን ይሸፍንለታል፤ አሳልፎ አይሰጠውም፤ ለራሱ ብቻ ጥፋቱን ይነግረዋል፡፡ ቢበደል ይቅርታን ያደርጋል፤ ለበደል የተሰነዘረበትን በትር ሳይሆን ያንን በትር የመከተለትን የእግዚአብሔርን የምሕረት እጅ ያስተውላል፤ ከመበቀል ይልቅ ለይቅርታ ልቡን ይከፍታል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ያለ ፍቅር የሚፈጸም ሥርዓት ምግባር የለም፤ ፍቅር ሙት ከማንሣት፣ ድውይ ከመፈወስ፣ ምሥጢር ከማወቅ፣ ተራረ ከማፍለስ፣ ባሕር ከመክፈል ይበልጣል፤ ፍቅር ያለው ጥልቅ ሥራ በጥላቻ ከተሞላ ብዙ ተግባር ይበልጣል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፩-፲፫) ያለ ፍቅር የሚፈጸም በጎ ምግባር ዋጋ እንደ ሌለው ቅዱስ ጳውሎስ ነግሮናል፡፡
በመጽሐፈ ሳሙኤል ለፍቅር ምሳሌ የሚሆነን ታሪክ እንመልከት፤ አንዴ እንዲህ ሆነ ፍልስጤኤማውያንና እስራኤላውያን ጦርነት ሊያደርጉ በነበረበት ጊዜ ንጉሥ ዳዊት በፍልስጤኤማውያን እጅ ወድቃ ከነበረችው (ተይዛ ከነበረች) ከቤተ ልሔም ከምትባል ከተማ ካለች ምንጭ ውኃ መጠጣት አማረው፤ ይህም ታሞ ስለነበረ ነው፤ የታመመ ሰው ያደገበት አካባቢ ትዝ ይለዋልና ካደገበት ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ መጠጣት ፈለገ፡፡
አንድም እንደ ማየ ሕይወት (እንደ መድኃኒት) ትቆጠር ስለነበረ ነው፡፡ ንጉሥ ዳዊት ‹‹ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን አምጥቶልኝ ባጠጣኝ›› ሲል ተመኘ፤ በዚህ ጊዜ የጭፍሮቹ አለቆች አዲኖን፣ ኢያቡስቴ እና ኤልያና የሚባሉ ባለ ሟሎቹ ለዳዊት ካላቸው ፍቅር የተነሣ ‹‹የማን ጌታ ውኃ፣ ውኃ እያለ ይሞታል›› ብለው ብቻቸውን ወደ ጠላቶቻቸው ጦር ሄዱ፡፡ ፍልስጤኤማውያንም የውጭ በር ከፈቱላቸውና ጦሩን ሰንጥቀው አልፈው ውኃውን ቀድተው ለንጉሣቸው አመጡለት፤ ንጉሥ ዳዊትም ቆራጥነታቸውን አደነቀ፤ ለእርሱ ፍቅር ብለው ደማቸውን ለማፍሰስ መድፈራቸውን ተገነዘበ፤ “የወንድሞቼን ደም እንደመጠጣት ነው” ብሎ በዚህ ጊዜ ያመጡለትን ውኃ “አልጠጣም” አለ፤ ውኃውንም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ብሎ አፈሰሰ፡፡ የንጉሥ ዳዊትና የጦር አለቆቹ ፍቅር ለእኛ ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ (፪ኛ ሳሙ. ፳፫፥፲፬-፲፯)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ወታደሮቹ ንጉሣቸውን በጣም ስለ ወደዱት ስለ እርሱ ፍቅር ሲሉ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለው ውኃውን አመጡለት፤ እርሱ ደግሞ የእነርሱን ፍቅር አይቶ ምንም ቢያምረውም፣ ውኃው ቢያስፈልገውም አልጠጣውም አለ፤ እርስ በእርሳቸው ይዋደዱ ነበር፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹…እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንት ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ …›› በማለት እርስ በእርሳችን እንዋደድ ዘንድ አስተምሮናል፡፡ (ዮሐ.፲፫፥፴፬)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ፍቅር በቃላት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤ በተግባር እንጂ፡፡ ፍቅር በንጽሐ ነፍስ ላይ የሚገኝ የቅድስና ማዕረግ ነው (ሁሉን እኩል መውደድ)፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹…ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ…›› በማለት እንድንዋደድ ይመክረናል፡፡ ( ፩ኛ ጴጥ. ፬፥፰) ፍቅር ያለው ሰው የሰዎችን ገበና (ድክመት) ይሸፍናል፡፡ በሰው ላይ ቶሎ አይፈርድም፤ ይታገሣል፤ ቢበደልም ይቅርታን ያደርጋል፡፡ ፍቅር የጥሩ ማኅበራዊ ግንኙነት መንገድ የእውነተኛ ሕይወት ውበት ነው፡፡ ፍቅር ካለን ከሁሉ ጋር ተግባብተን ተስማምተን እንኖራለን፤ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌላውም እናስባለን፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እውነተኛ ፍቅር እንዲህ በማለት ጽፏል፤ ‹‹ፍቅር ይታገሣል፤ ቸርነትም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፤ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፤ የራሱንም አይፈልግም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቆጥርም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዐመፅ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፤ ሁሉን ያምናል፤ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፡፡›› ( ፩ኛ ቆሮ.፲፫፥፬-፯)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለግንዛቤ ያህል ስለ ፍቅር በጥቂቱ ተማርን፤ ፍቅር ከተማርነውም በላይ ጥልቅ ምሥጢር አለው፤ እንግዲህ እኛም ሰዎችን በመውደድ የፍቅር ሰዎች በመሆን ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጸልን መልካም የምናደርግ ትዕግሥተኞች፣ እውነትን የምንከተል፣ ይቅር ባዮች እንሁን!
ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ ዘመናዊ ትምህርታችሁን በርትታችሁ ተማሩ! ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡
ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!