‹‹እግዚአብሔርን መፍራት›› (መዝ. ፴፫፥፲፩)
ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
ነቢዩ ዳዊት ‹‹ልጆቼ ሆይ ኑ፥ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራቹሁ ዘንድ›› ያለን ሰው አምላኩ እግዚአብሔርን በመፍራት ሊኖር እንደሚገባ ሲገልጽ ነው፡፡ በዚሁ መዝሙር ላይ ‹‹ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው?? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ። ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን ሻት፥ ተከተላትም። የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃኑ፥ ጆሮዎቹም ወደ ልመናቸው ናቸውና›› ብሏል፤ ይህም እኛ ከፈጣሪያችን ጋር እንኖር ዘንድ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ እንድንፈጽም ነው። (መዝ. ፴፫፥፲፩-፲፭)
በዚህም የሰው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ የእግዚአብሔርን ሕግ በማክበርና ትእዛዛቱን በመፈጸም ዘወትር እግዚአብሔርን በመፍራት እና በመታዘዝ እንዲኖር ተፈጥሯል። ምክንያቱም እኛም ጠቢቡ ሰለሞን በምሳሌ ፩፥፯ ላይ እና ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር ፻፲፥፲ ላይ ሁለቱም የጥበብ መጀመሪያ አምላካችን እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ ነግረውናል።
ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸው ሰዎች
ሰዎች ፈሪሀ እግዚአብሔር ከሌላቸው ክርስቲያናዊ ተግባራትንና ግዴታዎችን አይወጡም፤ አንድ ክርስቲያን ሊፈጽማቸው ከሚገቡ ተግባራቶች መካከል በመጸለይ፣ በመጾም፣ በመስገድ፣ለድኆች በመመጽወት እግዚአብሔር አምላክን ዘወትር በማሰብ መኖር ናቸው፡፡ እነዚህን ክርስቲያናዊ ግዴታዎች ስንፈጽም ከኃጢአት ስለምንርቅ እግዚአብሔር አምላካችንን በመፍራት እንኖራለን፡፡ (ማቴ. ፳፭፥ ፴፭-፴፮)
ሆኖም በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ የማይኖሩና ለቃሉ የማይታመኑም ሰዎች በዓለማችን በዝተዋል፡፡ ይህም ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ ‹‹ቃሉን ሰምቶ የማያደርገው ቢኖር፥ የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ይመስላል›› እንዳለ። እነዚህ ሰዎች ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸው፣ መንፈሳዊነት የራቃቸውና አስመሳዮች እንዲሁም ለምድራዊ ኑሮና ለግል ዝና የሚለፉ ናቸው፡፡
ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ ሆነው ለጊዜያዊ ደስታ እና ለታይታ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። (ያዕ.፩፥፳፫)
ሰውን አሳዝነው ለሰው ጻድቅ መስለው ለመታየት የሚጥሩ፣ የሰውን ነፍስ በከንቱ የሚያጠፉ፣ ለሰው ልጅ ግድ የሌላቸው ብዙዎች ናቸው። እነዚህን ሰዎች ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ላይ ‹‹የሰላምን መንገድ አያውቋትም፡፡ በዐይኖቻቸውም ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለምና›› ብሎናል። (ሮሜ ፫፥፲፯-፲፰)
ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች
‹‹እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው›› እንደተባለው በጥበብ የሚኖሩ ሰዎች የሚያከናውኑት ነገር ሁሉ ጥበብን የተመረኮዘ ነው። በምድር ላይም ዕድሜአቸው ይረዝማል፤ ‹‹እግዚአብሔርን መፍራት ዘመንን ያረዝማል፤ የኃጥአን ዕድሜ ግን ያጥራል›› እንዲል። (ኢዮ. ፳፰፥፳፰፤ ምሳ. ፲፥፳፯)
ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች ትእዛዛቱን የሚፈጽሙ ናቸው፤ እነዚህን ሰዎች የዮሐንስ ራእይ ‹‹የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጠብቁ፥ ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው ይህ ነው።›› ሕጉን በተግባር የሚፈጽሙ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚጎናጸፉ ናቸው፤ በምድር ላይ በሚኖሩበት ጊዜ ዘወትር ልዑል እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነው፤ የእግዚአብሔር መልአክም ይጠብቃቸዋል ይለናል። (ራእ. ፲፬፥፲፪)
ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች ለሌሎች ያስባሉ፤ በሰዎች ላይ ክፋት አይሠሩም፤ አይበድሉምም። በጎ በማሰብም በሰዎች መካከል ፍቅርን የሚሹ እና ለሰው ደስታም ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው።
እነዚህ ሰዎች ክፉውን ሰው ወደ በጎ ለመለወጥ ቅድሚያ የሚሰጡት መጀመሪያ የራሳቸውን ክፉት በማስወገድ፣ ቀጥሎም ክፋትን በመጸየፍ ነው፣ ክፉ ተግባራቸውን ይናዘዛሉ፣ መልካም ማድረግ ይለማመዳሉ፤ የያዙትን በጎ ህልውና አጽንተው ይይዛሉ፤ ሁል ጊዜ ስጦታቸውን በመመልከት፣ ዘወትር ጽድቅን እያሰቡ ወደፊት የሚደርሱበትን ይናፍቃሉ። በሌሎች የመበለጥ ፍራቻን መተውና ሰውን በዚያ ሳቢያ ክፉ ነው ብለው ማሰብን ያቆማሉ፤ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው ‹‹አንተ ሰው እገሌ ክፉ ነው ብትል ምን ትጠቀማለህ።››
ልዑል እግዚአብሔርን በመፍራት እንኑር!
ሠለስቱ ምእትም በፍትሐ ነገሥት ‹‹የክርስቲያን የመጀመሪያ ጥበብ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ ማወቅ ነው፤ ያለ ጥበብ አትኑር›› ብለዋል። ይህ ማለት የልዑል እግዚአብሔርን ሕግ መተላፍን በመፍራት ቃሉን መፈጸም፤ ጥበብ ሥጋዊን ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር በማዋሐድ መማር፣ ማስተማር እርሱንም በመፍራት መኖር ያስፈልጋል።
እግዚአብሔርን በመፍራት ውስጥ ካልኖርን፣ ልንገዛው የተፈጠረልን ዓለም እየገዛን፣ ልንመራው የተፈጠረልን ዓለም እየመራን፣ ተከታዮች ብቻ እንሆናለን።
ልዑል እግዚአብሔርን ለመፍራት ትምህርተ ሃይማኖትን መማር፣ መጻሕፍትን ማንበብ፣ የተጣላነውን ሁሉ መታረቅ ያስፈልጋል። ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ›› እንዳለን ለእኛ ካለው ፍቀሩ የተነሳ ለሰው ዘር ድኅነት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ በመስቀሉ እንዳዳነን እኛም መስቀሉን ተሸክመን ልንጓዝ ያስፈልጋል፤ነፍሳችንን ከኃጢአት ጽድታ ፍቅርን ትመገብ ዘንድ እግዚአብሔርን በመፍራት እንኑር። (፩ቆሮ ፲፩፥፩)