«እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም» (ማቴ.፲፩፥፲፩)
በዘመነ ሥጋዌ ንጉሥ ሄሮድስ ሲሞት ሦስቱ ልጆቹ ሄሮድስ ፍሊጶስ ዳግማዊ፣ አርኬላዎስ እና ሄሮድሰ አንቲጳስ መንግሥቱን ለሦስት ተካፈሉት፡፡ ሄሮድስ ፍሊጶስ ቀዳማዊ ሄሮድያዳ የምትባል ሚስትና ሰሎሜ የምትባል ልጅ ነበሩት፡፡ ይህች ሄሮድስን ባሏን ትታ መጥታ የገሊላ ገዥ የነበረውን የባሏን ወንድም ሔሮድስ አንቲጳስን አገባች፡፡
በዚህን ጊዜ መጥምቁ ዮሐንስ «የወንድምህን የፍልጶስን ሚስት ማግባት አይገባህም» እያለ በድፍረት ይገስጸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት አሲዞ ወደ እስር ቤት አስገባው፤ ሊገድለው ቢፈልግም ሕዝቡ እንደ ነቢይ ይመለከተው ነበርና ተቃውሞ እንዳይነሳበት ፈርቶ ተወው፡፡ (ማቴ.፲፬÷፬)
ቅዱስ ዮሐንስ በእስር ቤት ሳለ ጌታ በእርሱ እጅ ከተጠመቀና ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ በማድረግ ላይ ያለውን ነገር /ትምህርቱን፣ ተአምራቱን/ በሰማ ጊዜ በደቀመዛሙርቱ አማካኝነት ወደ ጌታችን መልእክት ላከ፤ እንዲህ ሲል፡- «የሚመጣው አንተ ነህ? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ?» ጌታችንም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልሶ እንዲህ በማለት በምሥጢራዊ ዘይቤ የአዎንታ መልስ ላከለት፡ «ሂዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፡፡ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶችም ይሄዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፡፡ በእኔም የማይሰናከል ብፁዕ ነው፡፡» (ማቴ.፲፩፥፭)
መልእክተኞቹ ከሄዱ በኋላም ጌታ አብረውት ለነበሩት ሕዝቦች ቅዱስ ዮሐንስን «እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም» እያለ አመስግኖታል፡፡ (ማቴ.፲፩፥፲፩)
ቅዱስ ዮሐንስ ታሥሮ ከጳጉሜን ፪ ቀን እስከ መስከረም ፪ ቀን በእስር ቤት ቆየ፡፡ ያሳሰረው ሔሮድስ አንቲጳስ መስከረም ሁለት ቀን የልደት በዓሉን ያከብር ነበር፡፡ በዚህ ዕለት የሆነውን ነገር ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ በምዕራፍ ፲፬ እንደሚከተለው አስፍሮታል፡፡
«የሄሮድስም የልደቱ ቀን በሆነ ጊዜ የሄሮድያዳን ልጅ /ሰሎሜ/ በመካከለቸው ዘፈነችለት፤ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፡፡ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ ሊሰጣት ማለላት፡፡ እርሷ ግን አስቀድማ በእናቷ ዘንድ አውቃ ነበርና የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በወጪት ስጠኝ» አለችው፡፡ (ወጭት እንደ ጎድጓዳ ሳህን ያለ ዕቃ ነው) ንጉሡም አዘነ፤ ነገር ግን ስለ መሐላው፣ አብረውት በማዕድ ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች የዮሐንስን ራስ ቆርጠው ይሰጧት ዘንድ አዘዘ፡፡ ልኮም በግዞት በእስር ቤት ሳለ የዮሐንስን ራስ አስቆረጠው፡፡ ራሱንም በወጭት አምጥተው ለዚያች ብላቴና ሰጧት፤ እርስዋም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች፡፡ ደቀመዛሙርቱም መጡ፤ በድኑንም ወስደው ቀበሩት መጥተውም ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ነገሩት፡፡» /ማቴ.፲፬፥፭-፲፪/
የመጀመሪያ ባሏን ሄሮድስ ፊሊጶስን ትታ የባሏን ወንድም ያገባችው ሄሮድያዳ «የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም» በሚለው በቅዱስ ዮሐንስ ግሣጼ ትበሳጭ ስለነበር የምታጠቃበትን መንገድ ሁልጊዜ ትፈልግ ስለነበር ለልጇ ለሰሎሜ እንዲህ ያለ ምክር መክራ የቅዱስ ዮሐንስ አንገት እንዲቆረጥ አደረገች፡፡
ሄሮድስ አንድ ጊዜ በሰዎች ፊት ቃል ስለ ገባ እንጂ በውሳኔው ደስተኛ አልነበረም፤ አዝኗል፡፡ ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው አስቀድመን እንደጠቀስ ነው፤ ሕዝቡ ቅዱስ ዮሐንስን ይወዱትና ይቀበሉት ስለነበር እንዳይቃወሙት ፈርቶ ነው፡፡ ሁለተኛው የቅዱስ ዮሐንስን ሕይወትና ትምህርት እያስተዋለ ሲሔድ ቅዱስ ዮሐንስ በእውነትም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ መሆኑን ስላወቀ ነው፡፡ ይህም ቅዱስ ዮሐንስን አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ ጌታችን ያደርጋቸው የነበሩትን ተአምራት በሰማ ጊዜ «ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶአል፤ ስለዚህ በእርሱ ተአምራት ይደረጋል» በማለቱ ይታወቃል፡፡ (ማቴ.፲፬፥፪)
የመስከረም ሁለት ስንክሳር በዚህ ላይ ተጨማሪ አስደናቂ ነገር ይነግረናል፡፡ «በዚያችም ቀን የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ከሄሮድያዳ ከእጆቿ ላይ ወደ አየር ስለ በረረች ታላቅ ድንጋጼ ሆነ፡፡ ደግሞም ሄሮድስ ሆይ የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም እያለች በመጮህ ዘልፋዋለችና» (ስንክሳር ዘወርኃ መስከረም)
ነቢዩ ሚልክያስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መምጣትና መንገድ ጠራጊነት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ «እነሆ ታላቁና የምታስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እልክላችኋለሁ፡፡ … እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል፡፡» (ሚል.፬፥፭-፮)
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም የቅዱስ ዮሐንስን መወለድ ለአባቱ ለዘካርያስ በቤተ መቅደስ ሲያበሥረው እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ «… እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከሓድያንንም ዐሳብ ወደ ጻድቃን ዕውቀት ይመልስ ዘንድ፥ ሕዝብንም ለእግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል፡፡» (ሉቃ.፩፥፲፯)
በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ከመሲህ መምጣት በፊት የኤልያስን መምጣት ይጠብቁ ነበር፡፡ ለምሳሌ ጌታችንን ደቀመዛሙርቱ «ጻፎች ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣ ዘንድ አለው ለምን ይላሉ?» ብለው ጠይቀውት ነበር፡፡ (ማቴ.፲፯፥፲፣ ማር.፱፥፲፩)
ጌታችንም ኤልያስ ይመጣል ተብሎ የተነገረው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን እንዳስረዳቸው እነርሱም እንደተረዱ ቅዱስ ማቴዎስ ይነግረናል፤ «ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለችው «አዎን፥ ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣል፥ ሁሉንም ያቀናል፡፡ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ፈጽሞ መጥቶአል፤ የወደዱትንም ሁሉ በእርሱ ላይ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ …» ከዚህም በኋላ ደቀመዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደነገራቸው አወቁ፡፡» (ማቴ.፲፯፥፲፩-፲፫)
ከአንድ ታላቅ እና ታዋቂ ሰው በኋላ የሚነሱ ደጋግ ሰዎችን በእዚያ በታላቁ ሰው ስም መጥራት በትንቢቶች ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ዳዊት እሥራኤላውያን የሚወዱትና ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ንጉሣቸው ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ካለፈ በኋላ እግዚአብሔር ደጋግ ነገሥታትን እንደሚያስነሳላቸው ለእሥራኤል ተስፋ ሲሰጥ ዳዊትን አስነሳላችኋለሁ ይላቸው ነበር፡፡ «ባርያዬም ዳዊት በላያቸው ላይ ንጉሥ ይሆናል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል» እና «ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም፥ ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ» እንደተባለው አሁንም የተደረገው ይኸው ነው፡፡ አይሁድ ኤልያስን በጣም ይወዱትና ያከብሩት ነበር፡፡ አሁንም ድረስ ያሉ አይሁዳውያን የፋሲካን በዓል በሚያከብሩበት ዕለት ለማዕድ ሲቀመጡ «ለኤልያስ» ብለው አንድ ቦታ ይተዋሉ፤ የወይን ጠጅ የተሞላ ብርጭቆም ያስቀምጣሉ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ መምጣት «ኤልያስ ይመጣል» ተብሎ የተነገረው ለዚህ ነው፡፡ «እንደ ኤልያስ ያለ የኤልያስን ዓይነት ሥራ የሚሠራ ነቢይ ይወጣል» ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ለካህኑ ለዘካርያስ የተናገረው ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ «…በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል…» (ሕዝ.፴፯፥፳፬፣ኤር.፴፥፱፣ ሉቃ.፩፥፲፯)
ቅዱስ ዮሐንስ ዛሬ እኛን እግዚአብሔር ለወዳጆቹ በሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት በጸሎቱ ከእግዚአብሔር ያማልደናል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ዘወትር «ሰአል ለነ ዮሐንስ» «ዮሐንስ ሆይ ለምንልን» ትለዋለች፤ «በአንተ ዮሐንስ መጥምቅ መሐረነ» «ስለ ዮሐንስ ስትል ማረን» እያለችም ትጸልያለች፡፡ እኛም ገድሉንና፣ መልኩን በመጸለይ፣ መታሰቢያው በሚደረግበት ጊዜም በስሙ ዝክር በመዘከር፣ ቸርነት በማድረግ በረከትን ለማግኘት ልንተጋ ይገባናል፡፡ «ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ በደቀ መዝሙሬ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ የሚጠጣ፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም» /ማቴ.፲፥፵፪/
የቅዱስ ዮሐንስ ጸሎቱና በረከቱ ይደርብን! አማላጅነቱ ይደረግልን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር