እንጦንዮስ አበ መነኰሳት

ጥር  22 ቀን 2005 ዓ.ም.

  • ምንጭ፡- የበረሃው ኮከብ ቅዱስ እንጦንዮስ መጽሐፍ

 

ጨለማ በዋጠው በግብፅ በረሃ ውስጥ ለብዙዎች አርዓያ በሆነ የእምነት ገድል የቅድስናን ብርሃን በማብራቱ የበረሃው ኮከብ ብለው ብዙዎች ይጠሩታል፡፡

 

kiduse entonseብፁዐዊ ቅዱስ እንጦንስ በምንኩስና ሕይወት ለመኖር ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተማረው አብነታዊ ትምህርት (ማቴ.4፥1-10) ከዚህ ዓለም ተድላና ደስታ በመራቅ ከሰዎች ሁሉ ተለይቶ  ፍጹም መንፈሳዊ ተጋድሎን በመጋደል በተወለደ በ106 ዓመቱ ጥር 22 ቀን በ356 ዓ.ም. ከዚች ዓለም በሥጋ ተለይቷል፡፡ “ክቡር ሞቱ ለፃድቅ በቅድመ እግዚአብሔር” “የፃድቅ ሰው ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው” በማለት ክቡር ዳዊት እንደተናገረው፣ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን የልደታቸውን ጊዜ፣ የተጋድሏቸውን ሁናቴ፣ ቃል ኪዳን የተቀበሉባቸውንና ያረፉባቸውን ዕለታት በክብር ታስባለች፡፡ ይህም በቅዱስ መጽሐፋችን “የፃድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው”(ምሳ.10÷7)፡፡ በመሆኑም “ስለ ፅድቅ የሚሰደዱ ብጹአን ናቸው ÷ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” (ማቴ.5÷8) በሚለው በጌታችን ትምህርት የዚችን ዓለም ጣዕም ንቆ በምናኔ በመኖር ለመነኮሳት አብነት የሚሆናቸውን የቅዱስ እንጦንስን ዜና ሕይወት አቅርበናል፡፡ለመሆኑ ቅዱስ እንጦንስ ማን ነው? አስተዳደጉና የፈጸማቸው አገልግሎቶቹ ምን ይመስላሉ?

 

ልጅነት

እንጦንዮስ/እንጦንስ/ ትውልዱ ግብጻዊ ሲሆን ቤተሰቦቹም መልካሞችና ባለጸጎች ነበሩ፡፡ እነርሱም በሕፃንነት ኑሮው ከቤቱና ከወላጆቹ በስተቀር ምንም አላወቀም፡፡ እያደገና ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ ትምህርት ቤት አልገባም ነበር፡፡ ይህም ከሌሎች ልጆች ጋር ጓደኝነት ባለመፈለጉ ነበር፡፡ የእርሱ ፍላጎት በቅዱስ መጽሐፍ ተጠቅሶ እንደሚገኘው እንደ ያዕቆብ በብቸኝነትና በጭምትነት በቤቱ በመቀመጥ ቀላል ሕይወትን መምራት ነበር፡፡ ዘፍ.25፥27 በእርግጥ ከወላጆቹ ጋር ቤተ ክርስቲያን እየሄደ ያስቀድስ ነበር፡፡ በዚህም ከአንድ ልጅ ወይም ከአንድ ወጣት የሚታየው የመሰልቸትና የጥላቻ መንፈስ በጭራሽ አልታየበትም፡፡ ለወላጆቹ በመታዘዝ የሚሰጡትን ትምህርቶችና የሚነበቡትን ቅዱሳት መጻሕፍት በጥሞና ይከታተል ነበር፡፡ ከነዚህም የሚቀስመውን ጥቅም በልቡ በማስተዋል አኖረ፡፡ በሌላም በኩል በልጅነቱ ወራት ምንም እንኳ ያለ አንዳች ችግር ቢኖርም ወላጆቹን ለቅንጦትና ለድሎት ለምግብም ሲል አያስጨንቃቸውም ነበር፡፡ ይህን በመሰሉት ሁሉ አይደሰትም ነበር፡፡ በፊቱ በሚቀርብለት ብቻ ይረካ ነበር፡፡ ተጨማሪም አይጠይቅም፡፡

 

መጠራት

ወላጆቹ ከሞቱ በኂላ እንጦንዮስ ገና ልጅ ከነበረች አንዲት እኅቱ ጋር ብቻኛ ሆነ፡፡ በዚህ ወቅት ዕድሜው ከ18 እስከ 20 ዓመት ገደማ ነበር፡፡ ቤቱንና እኅቱንም ይጠብቅ ጀመር፡፡ እነርሱን ካጣ ከስድስት ወር በኋላ እንደ ልማዱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ በመንገድ በኅሊናው ያስብ ጀመር፡፡

 

ሐዋርያት ሁሉን ትተው ጌታን እንደተከተሉት (ማቴ.10፣ 20፣19፣ 27)፤ በግብረ ሐዋርያት ሕዝቡ ያላችውን ሁሉ ሸጠው ለድሆች ይከፋፈል ዘንድ በሐዋርያት እግር ሥር ስለማኖራቸው (ሐዋ.4፡35)፤ ይህን ለመሳሰሉ ሥራዎች በሰማያት እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ እንዳላቸው (ኤፌ.1፡18 ቆላ.1፡15) እኒህን አሳቦች በኅሊናው እያወጣና እያወረደ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ፡፡ በዚያም ወቅት ወንጌል ይነበብ ነበር፤ ሲያዳምጥ ጌታ በሀብታሙ ሰው የተናገረውን የሚጠቅሰው ምዕራፍ ተነበበ፡፡

 

“ልትጸድቅ ብትወድድ ሂደህ ያለህን ሁሉ ሽጥና ለድሆች ስጥ፡፡ መጥተህም ተከተለኝ፡፡ በሰማያት መዝገብ ታከማቻለህ፡፡” ማቴ.19፡21 ፡፡ እግዚአብሔር ቀድሞ ስለ ቅዱሳን እንዲያስብ እንዳደረገውና እዚህም የተነበበው በቀጥታ ለእርሱ እንደተነገረ ስለተሰማው እንጦንዮስ በቀጥታ ከቤተ ክርስቲያኑ በመውጣት ከዘመዶቹ የወረሰውን 300 ሄክታር ወይም 12 ጋሻ መሬት ለድሆች አከፋፈለ፡፡ መሬቱ ለምና ለዐይንም ያማረ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለእርሱም ሆነ ለእኅቱ እንቅፋት እንዲሆንባቸው አልፈለገም፡፡ የተረፈውን ሁሉን ተንቀሳቃሽ ሀብቱን ሸጠ፡፡ አብዛኛውን ለድሃ ሰጥቶ ጥቂቱን ለእኅቱ አስቀመጠው፡፡

 

እንጦንዮስ በሌላ ቀን እንደገና ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ሳለ ጌታ በወንጌል የተናገረውን ሲነበብ አደመጠ፡፡ “ለነገ አትጨነቁ” ይል ነበር ጥቅሱ ማቴ.6፡34፡፡ ይህንንም ሰምቶ ሳይዘገይ ወደ ቤቱ በመመለስ የተረፈውን ሁሉ ለድሆች ያከፋፍል ጀመር፡፡ እኅቱን ግን የታወቁና የታመኑ ወደሆኑ ደናግል ማኅበር ወሰዳት፡፡ በዚያም ታድግ ዘንድ ለደናግል ትቷት ተመለሰ፡፡ ከዚያ በኋላ ብቻውን በመሆኑ ንቁ ሆኖ ራሱን በመካድ በመኖሪያ ቤቱ አጠገብ ጊዜውን ለብሕትውና ሕይወት ሰጠው፡፡

 

ትሕትና

እንጦንዮስ ራሱን ዝቅ በማድረግና በነፍስ ትሕትና የጸና ነበር፡፡ ምንም እንኳ ታላቅና ዝነኛ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያንን ልዑካንና ጸሐፍትን ከእርሱ ይልቅ እንዲከበሩ ይሻ ነበር፡፡ በጳጳሳትና በካህናት ፊት እራሱን ዝቅ አድርጎ እጅ ሲነሣ አሳፋሪ አያደርገውም፡፡ ዲያቆን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ጠቃሚ ነጥብን ካገኘም ላገኘው ዕውቀት ሳያመሰግን አያልፍም፡፡

 

በገጽታው ሊገለጽ የማይቻልና ታላቅ የሆነ ብሩህ ገጽ ይነበብበታል፡፡ በመነኮሳት ጉባኤ ተቀምጦ ሳለ ቀድሞ የማይተዋወቀውን ሰው ሊያነጋግረው ከፈለገ ማንም ሳያመለክተው በዓይኖቹ እንደተሳበ ሁሉ ሌሎቹን አልፎ በቀጥታ ወደ እንጦንዮስ ይሄዳል፡፡ ከሌሎቹ ልዩ አድርጎ የሚያሳውቀው ቁመናው ምስሉ ሳይሆን የረጋ ባሕርይውና የነፍሱ ንጽሕና ነበር፡፡ ነፍሱ የማትነዋወጽ በመሆንዋ አፍአዊ ገጽታውም የረጋ ነበር፡፡ በመጽሐፍ  “ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል፡፡ በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች፡፡”ተብሎ እንደተነገረው (ምሳ.15፥13)፡፡ ለምሳሌ ያዕቆብ አጎቱ ደባ ተንኮል እንዳሰበበት ባወቀ ጊዜ ለሚስቶቹ እንዲህ ብሏቸው ነበር የአባታችሁ ፊት ከእኔ ጋር እንደዱሮ እንዳልሆነ አያለሁ፡፡ ዘፍ.31፥5፡፡ ነቢዩ ሳሙኤል ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ ይቀባው ዘንድ በተላከ ጊዜ ደስታን የሚያንጸባርቁ ዓይኖቹንና እንደ ወተት የነጡ ጥርሶቹን አይቶ አወቀው፡፡ 1ሳሙ.16፥10፡፡ እንጦንዮስም እንዲሁ ይታወቅ ነበር፡፡ አይነዋወጽም፡፡ ነፍሱ እርጋታ ነበራትና፡፡ አያዝንም፡፡ አዕምሮው ደስታን የተሞላ ነበር፡፡

 

ቅዱስ እንጦንዮስ ፍቅረ ነዋይ ላለቀቀው መነኩሴ ያስተማረው ትምህርት

ዓለመን ንቆ ገንዘብ ስለመውደድ ከመነኮሰ በኋላ ለድሆች ካከፋፈለ በኋላ ለራሱ ጥቂት ያስቀረ አንድ ወንድም ወደ ባሕታዊው ወደ እንጦንዮስ መጣ፡፡ እንጦንዮስም ይህን ካወቀ በኋላ እንዲህ አለው፡፡ “ መነኩሴ ለመሆን ከፈለግህ ወደ መንደር ሂድና ጥቂት ሥጋ ገዝተህ ራቁትህን በሰውነትህ ላይ ተሸክመህ ተመለስና ወደእኔ ና” አለው፡፡ያም ወንድም ይህን ባደረገ ጊዜ ወፎችና ውሾች በሰውነቱ እያንዣበቡ ይታገሉት ጀመር፡፡ በደረሰም ጊዜ እንጦንዮስ እንዳዘዘው ማድረጉን ጠየቀው፡፡ እርሱም የቆሰለውን ሰውነቱን ባሳየው ጊዜ እንጦንዮስ እንዲህ አለው፡-“ዓለምን ከናቁ በኋላ ገንዘብ የሚመኙትም እንደዚሁ በአጋንንት ይገደላሉ፡፡” አለው፡፡

 

ቅዱስ እንጦንስ ስለ ዕረፍቱ በቀደ መዛሙርቱ ፊት የተናገረው የመጨረሻ ንግግር

የአባቶቼን መንገድ እሄዳለሁ

እንደልማዱ መነኮሳትን ይጎበኝ ዘንድ በተራራው ውጭ ሳለ በጌታ ቸርነት አስቀድሞ ስለ ሞቱ ስላወቀ ለወንድሞች እንዲህ ሲል ተናገራቸው፡፡ “ይህ ከናንተ ጋር የማደርገው የመጨረሻው ግንኙነት ነው፡፡ በዚህም ሕይወት ዳግመኛ እንተያይ እንደሆነ እንጃ እጠራጠራለሁ፡፡ ዕድሜዬ አንድ መቶ አምስት ዓመት ገደማ ሆኗልና አሁን እኔ የምሞትበት ጊዜ ነው፡፡” ይህን በሰሙ ጊዜ ሽማግሌውን ሰው አቅፈው እየሳሙ ያለቅሱ ጀመር፡፡ እርሱ ግን ከውጭ ከተማ እንደሚለይ ሁሉ በደስታ ያወጋቸው ነበር፡፡ በጥብቅም መከራቸው፡፡ “ከጥረታችሁ ግዴለሽ አትሁኑ፡፡ በብሕትውና ሕይወት ፍጹም ተስፋ አትቁረጡ፡፡ ዕለት ዕለት እንደምትሞቱ ሆናችሁ ኑሩ፡፡ አስቀድሜ እንደተናገርኩት ነፍስን ከርኩስ አሳቦች ለመጠበቅ በሥራ ትጉ፡፡ ቅዱሳንን ምሰሉ፡፡ ቅድስና የሌለውን የስንፍና ትምህርታቸውን ታውቃላችሁና ወደ መለጣውያን (መናፍቃን) አትቅረቡ ኑፋቄያቸው ለማንም ግልጽ ነውና፡፡

 

በመጽሐፈ መነኮሳት (ፊልክስዮስ) መቅድም ላይ ስለ ቅዱስ እንጦንስ ከተፃፈው የሚከተለው ይገኛል፡-እንጦንዮስ (እንጦንስ) አባቱ ባለጸጋ ነበር፡፡ አገሩም ጽኢድ ዘአምፈለገ አቅብጣ ናት፡፡ …በሕጻንነቱ ከትምህርት ቤት ሄደ፡፡ ተምሮ ሲመለስ አባቱ “ሕግ ግባ” አለው፡፡ እርሱ ግን “አይሆንም” አለ፡፡ምነው ቢሉ ፈቃዱ እንደ ቀደሙ ሰዎች እንደ ኤልያስ፤ እንደ ኋላ ሰዎች እንደ ዮሐንስ ንጽሕ ጠብቆ፣ ከሴት ርቆ በድንግልና መኖር ነውና፤ ግድ አለው፡፡ “ግድማ ካልከኝ …ፍቀድልኝና ለእግዚአብሔር አመልክቼ ልምጣ እንጂ” አለ፡፡ “ደግ አመልክተህ ና” አለው፡፡ሄዶ ባቅራቢያው ካለ ዋሻ ገባ፡፡ ወዲያው አባትህ ታመመ አሉት፡፡ ቢሄድ አርፎ አገኘው፡፡ ገንዘቡን ሦስት ነገር አስቦ አስቀድሞ ይመጸውታል፡፡ መጀመሪያ ያባቴ በድኑ ከመቃብር ሳይከተት መብሉ በከርሰ ርሁባን፤ መጠጡ በጉርኤ ጽሙአን፤ ልብሱ በዘባነ ዕሩቃን ይከተት ብሎ፡፡ ሁለተኛው ወኢይወርድ ምስሌሁ ኩሉ ክብረ ቤቱ /ሀብቱ ንብረቱም ሁሉ አብሮ መቃብር አይወርድም/ ያለውን የነቢዩን ቃል ያውቃልና፤ ሦስተኛ የሚመንን ነውና ልብ እንዳይቀረው፡፡ ሲመጸውትም አየቴ ኀይልከ፤ አይቴ አእምሮትከ አይቴ ፍጥነትከ /ኀይልህ የት አለ እውቀትህስ የት አለ ፍጥነትህስ የት አለ/ እያለ መጽውቶታል፡፡ መጽውቶ አባቱን አስቀብሮ ሲያበቃ ቅዳሴ ለመስማት ከቤተክርስቲያን ገብቶ ቆመ፡፡ ቄሱ ወንጌል ብሎ ወጥቶ ሲያነብ እመሰ ፈቀድከ ትኩን ፍጹመ ሲጥ ኩሉ ንዋይከ ወሀብ ለነዳያነ ወነዓ ትልወኒ ያለውን ቃል ሰማ፡፡ ይህ አዋጅ የተነገረ ለኔ አይደለምን? ብሎ እኅት ነበረችው ከደብረ ደናግል አስጠግቶ ሂዶ ፊት ከነበረባት ዋሻ ገብቶ ተቀመጠ፡፡

 

ከዕለታት አንድ ቀን ወለተ አረሚ ሠናይተ ላህይ ይላታል ከደንገጡሮቿ ጋር በቀትር ጊዜ መጥታ ከዛፉ እግር ከውኃው ዳር አረፈች፡፡ ፊት እሷን አስጠጓት፤ ኋላ እርስበሳቸው ይተጣጠቡ ጀመር፡፡ እሱም እርቃናቸውን እንዳያይ ዓይነ ሥጋውን ወደ ምድር ዓይነ ነፍሱን ወደ ሰማይ አድርጎ ሲጸልይ ቆየ፡፡ ያበቃሉ ቢል የማያበቁለት ሆነ፡፡ ኋላ ደግሞ ቆይተው ነገረ ኀፊር እያነሱ ይጨዋወቱ ጀመር፡፡ ምነው እንግዲህማ አይበቃችሁም? አትሄዱም? አላቸው፡፡ ኦ እንጦኒ! ኦ እንጦኒ!፤ ለእመ ኮንከ መነኮሰ ሑር ኀበ ገዳም እንጦኒ ሆይ መነኩሴ እንደሆንክ ከዚህ ምን አስቀመጠህ ከበረሃ አትሄድም ነበርን?/ አለችው፡፡ ከዚያ አስቀድሞ መነኩሴ አልነበረ መነኮስ ማለት ከምን አምጥታ ተናገረች? ቢሉ ጌት ለአበው ትምህርት የሚሆነውን ነገር በማናቸውም ባልበቃ ሰው አድሮ መናገር ልማዱ ነው፡፡ አንድም እሱ ከመነኩሴ ፊት እንዲህ ያለ ኀፊር ትናገሪያለችን? አላት፡፡ ከሱ ሰምታ ኦ እንጦኒ ኦ እንጦኑ እመሰ ኮንከ መነኮሰ ሑር ሐበ ገዳም አለችው፡፡

 

እንጦኒ ኦ እንጦኒ እመሰ ኮንከ መነኮሰ ሑር ሐበ ገዳም እያለ ራሱን እየገሰጸ ፊቱን እየሰፋ ጽሕሙን እየነጨ ከዚያ ተነሥቶ አናብስት፤ አናምርት፤ አካይስት፤ አቃርብት ካሉበት ነቅዐ ማይ፤ ልምላሜ ዕፅ ከሌለበት ድሩክ ለተአቅቦ ይላል ዘር ተክል ከማይገኝበት ገዳመ አትፊር ሄደ፡፡ የዚህ መንገዱ ፍለጋ የለውም፡፡ አሸዋ ላሸዋ ነው፡፡ ነጋድያን ሲጓዙ የወደቀውን ያህያና የግመል ፋንድያ እያዩ በዚያ ምልክት ይሄዳሉ፡፡ በረሃነቱም ጽኑ ነው፡፡ ከሐሩሩ ጽናት የተነሣ በቀትር ጊዜ ከደንጊያ ላይ ተልባ ቢያሰጡ ይቆላል፡፡ እሱም ከዚያ ሄዶ ሲጋደል አጋንንት ጾር አነሱበት፡፡ ኦ ሕጹጸ መዋዕል እፎ ደፈርከ ዝየ፡፡ /በእድሜ ሕፃን የሆንክ ከዚህ እንደምን ደፍረህ መጣህ?/ አዳም ከወጣበት ገነት እንጂ እገባ ብሎ ነው፡፡ ብለው ዘበቱበት፤ እሱም በትሕትና ይዋጋቸዋል፡፡ መሆንማ ይሆን ብላችሁ ነውን? እናንተ ብዙ አኔ አንድ ብቻዬን፤ እናንተ ረቂቃን እኔ ግዙፍ፡፡ እናንተ ኀያላን እኔ ደካማ በኀይለ ክርስቶስ ብችላችሁ ነው እንጂ ያለዚያስ አልችላችሁም እያለ በትሕትና ሲዋጋቸው ኖረ፡፡

 

ከዕለታት ባንድ ቀን ይኸን ፆር አልቻልሁትም ልሂድ እንጂ ብሎ ሲያስብ አደረ፡፡ ማለዳ በትረ ሆሣዕና ነበረችው ያችን ይዞ ከደጃፉ ላይ ቆመ፡፡ እንዳይቀርም ፆሩ ትዝ እያለው እንዳይሄድም በዓቱ እየናፈቀው አንድ እግሩን ከውስጥ፤ አንድ እግሩን ከአፍአ አድርጎ ሲያወጣ ሲያወርድ መልአኩ የሰሌን ቆብ ደፍቶ፤ የሰሌን መቋረፊያ ለብሶ፤ የሰሌን መታጠቂያ ታጥቆ ብትን ሰሌን ይዞ መጣ፡፡ ምን ሊያደርግ ይሆን? ሲል ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ቆመ፡፡ ወዲያው ጸሎተ ወንጌልን፤ ነአኩቶን፤ ተሠሀለኒን፤ ደግሞ መጀመሪያ ለሥላሴ እጅ ነሳ፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ አቡነ ዘበሰማያት ሠላሳ ስድስት ሰጊድ አድርሶ በመጨረሻ አንድ ጊዜ እጅ ነሥቶ ተቀመጠ፡፡ ወዲያው ያን ብትን ሰሌን አቅርቦ ይታታ ጀመር፡፡ እንጦንዮስም እንግዲህማ የዚህን ፍጻሜ ሳላይ እሄዳለሁን? ብሎ ተቀምጦ ይመለከተው ጀመር፡፡ ሠለስት ሲሆን ደግሞ ተነሥቶ አቡነ ዘበሰማያቱንም ሰጊዱንም ያንኑ ያህል አደረሰው፡፡ የቀሩትንም የሰዓቱንም የሠርኩንም እንደዚሁ አድርጎ አሳየው፡፡ በሠርክ ኦ እንጦኒ ከመ ከመዝ ግበር ወለእመገበርከ ዘንቱ ትድኀን እምጸብአ አጋንንት አለው /እንጦኒ ሆይ እንደዚህ እንደዚህ ሥራ፤ ይህንን ከሠራህ ከአጋንንት ጠብ ትድናለህ/፡፡ ማለት ነው፡፡ የንዋሙን የመንፈቀ ሌሊቱን ግን እርሱ ጨምሮታል፡፡ ንዋም ጌታ የጸለየበት፤ ቀትር የተሰቀለበት፤ ሰዓት ነፍሱን ከሥጋው የለየበት፤ ሰርክ መቃብር የወረደበት ነውና ይህን ሁሉ አንድ አድርጎ ዳዊት ሰብአ ለዕለትየ እሴብሐከ ብሏል፡፡ /መዝ.118፥164/

 

ሠላሳ ዓመት ሲሞላው ጌታ በዕለተ ዓርብ የለበሰውን ልብስ አልብሶታል፡፡ ማየት ከመልአክ፤ መቀበል ከአምላክ እንዲሉ ይህም ምሳሌ ነው፡፡ ቆብ የአክሊለ ሦክ፤ ቀሚሱ የከለሜዳ፤ ቅናቱ የሀብል፤ ሥጋ ማርያም የሥጋ ማርያም፤ አስኬማ የሰውነት ወተመሰለነ በአስኬማሁ እንዲል፤እርሱም ይህን ተቀብሎ በዚህ ዓለም እኔ ብቻ ነኝን ሌላም አለ? ብሎ ወደ እግዚአብሔር አመለከተ፡፡ ጌታም አለ እንጂ አንድ ጊዜ ተራምዶ ሁለተኛውን ሳይደግም የሚሠራውን ሥራ ዓለሙ ሁሉ ቢሰበሰብ የማይሠራው፡፡ በጸሎቱ ዝናም የሚያዘንም ፀሐይ የሚያወጣ፤ እንደዚህ ያለ ወዳጅ አለኝ አለው፡፡ ይኸን ሰው ለማየት ልሂድን ልቅር? ቢለው ሂድ አለው፡፡ መልአኩ እየመራ አደረሰው፡፡ ጳውሎስ /ጳውሊ/ ከበዓቱ ወጥቶ ፀሐይ ሲሞቅ ነበር፡፡ ሲመጣ አይቶ ከበዓቱ ገብቶ ወወደየ ማእጾ ውስተ አፈ በዓቱ /ከበዓቱ አፍ ውስጥ መዝጊያ ጨመረ/ ይላል ዘጋበት፡፡ ከደጃፉ ቆሞ አውሎግሶን አውሎግሶን አለ፡፡ ስለ እግዚአብሔር ብለህ ክፈትልኝ ማለት ነው፡፡ ሰው እንደሆንክ ግባ ብሎ ከፈተለት፡፡ ገብቶ ማን ይሉሃል? አለው ስሜን ሳታውቅ እንደምንም መጣህ? አለው፡፡ እንጦንዮስም ፍጹም ነውና ቢጸልይ ወዲያው ተገልጾለት፤ ጎድጎድኩ ወተርህወ ሊተ ሀሰስኩ ወረከብኩ ጳውሎስ ገዳማዊ አለው፡፡

 

ጳውሎስ/ጳውሊ/ ትባላለህ ቢለው አደነቀ፡፡ ተጨዋውተው ሲያበቁ ባጠገቡ ለብቻው በዓት ሰጠው፡፡ እንጦንዮስም ከዚያ ሆኖ ጸሎቱን ሲያደርግ ዋለ፡፡ ወትሮ ለጳውሊ መንፈቀ /ግማሽ/ ኅብስት ይወርድለት የነበረ ማታ ምሉዕ ኅብስት ወረደለት፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር መምጣቱን ያን ጊዜ አወቀው፡፡ ወዲያው ያን ኅብስት ከሁለት ገምሶ እኩሌተውን ለራሱ አስቀርቶ እኩሌታውን ሰጠው፡፡ ያን ተመግበው ሌት ሁሉም በየሥራቸው ክብራቸው ተገልጾ ሲተያዩ አድረዋል፡፡ ጳውሎስ አሥር ጣቶቹን እንደ ፋና ሆነው እያበሩለት አራቱን ወንጌል ሲያደርስ እንጦንዮስም እንደ አምደ ብርሃን ተተክሎ ሲያበራ ተያይተዋል፡፡

 

በዚያች ሌሊት ከዚያ ቦታ ጨለማ ጠፍቶ አድሯል፡፡ በነጋው ሠለስት እላፊ ሲሆን ጸሎታቸውን አድርሰው ሲያበቁ ተገናኝተው ሲጨዋወቱ፤ እንጦንዮስ ያረገውን ቆብ አይቶ፤ ይህማ ከማን አገኘኸው? አለው፡፡ እርሱ ባለቤቱ ስጠኝ አለ፡፡ እርሱም የጌታን ቸርነት ያደንቅ ጀመር፡፡ እንጦንዮስም እስኪ በኔ ብቻ የሚቀር እንደሆነ ለሌላም የሚያልፍ እንደሆነ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ፡፡ ወዲያው ተገለጸለት፡፡ ወአክሞሰሰ ይላል፡፡ ደስ አለው፡፡ ምን አየህ? ቢለው ጽዕድዋን አርጋብ /ነጫጭ ርግቦች/ በጠፈር መልተው አንተ እየመራሀቸው ተከትለውህ ሲሄዱ አየሁ አለው፡፡ ምንኑው ቢለው? እሊህማ በዚህ በቆቡ የምትወልዳቸው ንጹሐን ጻድቃን ልጆችህ ናቸው አለው፡፡  ሁለተኛ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ ወደመነገጹ ይላል፡፡ አዘነ ምነው ቢሉ በክንፋቸው ጥቁር ተቀላቅሎባቸው አየሁ አለው፡፡ ምንድንናቸው ቢለው ጽድቅና ኀጢአት እየቀላቀሉ የሚሠሩ ልጆችህ ናቸው አለው፡፡ ሦስተኛ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ ገአረ ወበከየ ይላል፡፡ ቃሉን ከፍ አድርጎ ጮኸ፡፡ ምነው አለው አርጋብስ አርጋብ ናቸው አለው፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ዘመን የሚነሡቱ እንደ ቁራ ጠቁረው አየሁዋቸው አለ፡፡ ምንድናቸው? ቢለው ሀሳሲያነ ሢመት /ሹመት ፈላጊዎች/፤ መፍቀሪያነ ንዋይ /ገንዘብ የሚወዱ/ እለ ይሠርኡ በነግህ ማዕደ ምስለ መኳንንት /ከመኳንንት ጋር በጥዋት ማዕድ የሚቀመጡ/ ይላቸዋል፡፡ በፍጻሜ ዘመን የሚነሡ ኀጥአን ልጆችህ ናቸው፡፡ አለው፡፡ ያለ ንስሓ ባይጠራቸው እስኪ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ፡፡ የዚህ ምላሽ አልመጣለትም ይላሉ፡፡

 

ከዚህ በኋላ ጳውሊ እንግዲህ ይህን ከራስህ ያደረግኸውን ለኔ ስጠኝ ላንተ ሌላ ሠርተህ አድርግ አለው፡፡ ይህንንስ እንዳልሰጥህ ከባለቤቱ ተቀብዬዋለሁ፡፡ ነገር ግን ሥራውን ለምጄዋለሁ ሌላ ሠርቼ ላምጣልህ አለው፡፡ እንዲያስ አትዘግይ ቶሎ ሠርተህ አምጣልኝ አለው፡፡ ጊዜው እንደደረሰ አውቆታልና ይላሉ፡፡ እንጦንስም ሠርቶ ይዞ ሲመጣ ጳውሊ አርፎ ነፍሱን መላእክተ ብርሃን ይዘዋት ሲያርጉ አየ፡፡ ማነው ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ያ ሰው አርፏልና ሂደህ ቅበረው አሉት ይህንሳ የያዝኩትን ቆብ ልተወውን? አላቸው፡፡ አትተው አድርግለት ብለውታል፡፡ ከምንኩስና አስቀድሞ የሠሩትን ሥራ ከንቱ እንዳይደለ ለማጠየቅ ነው፡፡

 

ቢሄድ መጽሐፉን ታቅፎ፤ አጽፉን ተጎናጽፎ፤ ከበዓቱ አርፎ፤ አገኘው፡፡ ከራስጌው ቆሞ ሲያለቅስ ሁለት አናብስት መጡ፡፡ የመቃብሩን ነገር እንደምን ላድርግ ነኝ አያለ ሲጨነቅ በእጃቸው እንደመጥቀስ አድርገው አሳዩት፡፡ ልኩን ለክቶ ሰጣቸው፡፡ ቆፈሩለት እሱን ቀብሮ እንግዲህ ከዚህ እኖራለሁ ብሎ አሰበ፡፡ ጌታ ግን ዛሬ በሱ ቦታ ላይ ሌላ ሰው አላየበትምና አይሆንልህም ሂድ አለው፡፡ አጽፉንና መጽሐፉን ይዞ ሂዶ እስክንደርያ ሲደርስ ሊቀ ጳጳሱ አትናቴዎስ ወዴት ሄደህ ነበር? አለው፡፡ እንዲህ ያለ ሰው ልጠይቅ ሄጄ ነበር፡፡ አርፎ አግኝቼ ቀብሬው መጣሁ፡፡ አለ፡፡ ልሄድና ከዚያ ልኑር? አለው አይሆንልህም አትሂድ እኔም አስቤ ነበር፡፡ የማይሆንልኝ ሆኖ መጣሁ እንጂ አለው፡፡ ባይሆን ለበረከት ያህል አጽፊቱን ጥለህልኝ ሂድ ብሎ ትቶለት ሄደ፡፡ መዓርግ ሲሰጥ ሥጋውን ደሙን ሲለውጥ በውስጥ ያቺን ይለብስ ነበር፡፡

 

ከዚያ በኋላ በዚህ ቆብ እንጦንዮስ መቃርስን፤ መቃርስ ጳኩሚስን፤ ጳኩሚስ ጳላሞንን፤ ጳላሞን ቴዎድሮስ ሮማዊውን ቴዎድሮስ ሮማዊ አቡነ አረጋዊንና አባ ዳንኤልን ይወልዳል፡፡ አባ ዳንኤል አቡነ አውስጣቴዎስ፤ አቡነ አረጋዊ እስከ አቡነ ተክለሃይማኖት ያሉትን ወልደዋል፡፡ ከዚህ በኋላ መነኮሳቱ እንደ ሳር እንደ ቅጠል በዝተው ተነሥተዋል፡፡ ይሩማሊስ፤ ጳላድዮስ የሚባሉ ሁለት ሊቃውንት መነኮሳት ከግብፅ ተነሥተው አገር ላገር እየዞሩ የአበውን ዜና በሕይወት ያሉትን ከቃላቸው የሞቱትን ከአርድአቶቻቸው እየጠየቁ ቃለ አበው፣ ዜና አበው እያሉ ጽፈዋል፡፡

አምላካችን ከቅዱስ እንጦንስ በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡