ነቢዩ ሚክያስ/‹‹እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?››/
ነሐሴ ፳፪፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ከነገደ ብንያም የተወለደው ነቢዩ ሚክያስ የስሙ ትርጓሜ ‹‹እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?›› ነው። እንደ ስሙ ትርጕምም የእግዚአብሔር ቸርነት ከየትኛውም ኃጢአትና ከየትኞቹም በቊጥር የበዙ ኃጢአተኞች ይልቅ ታላቅ መሆኑን፣ ይልቁንም እግዚአብሔር ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኞችን የማይጸየፍ እንደሆነ አስተምሯል። በሰባት ምዕራፎች በተጠቃለለ ነገረ ድኅነትንና ንስሐን ማዕከል ያደረገ ትምህርቱና ትንቢቱ መሲሑ የሚወለደበትን ስፍራ ሳይቀር ‘ደረቅ ትንቢት’ በግልጽ እንዲህ ሲል “አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል” ተናግሯል።
ከነቢዩ ሆሴዕና ኢሳይያስ ጋር ነበር፤ ከ ፯፻፵፱-፮፻፺፯ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በነበሩት በሦስቱ የይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥታት የነበረ ነቢይ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ እናገኘዋለን። ነቢዩ ኢሳይያስ በኢየሩሳሌም በሚያስተምርበት ጊዜ እርሱ በምዕራባዊው ይሁዳ ያስተምርና ትንቢት ይናገር ነበር። አብዛኛው ስለ መሲሕ ያስተማሩት ትምህርትም ሆነ የተናገሩት ትንቢት ይመሳሰላል።
የነቢዩ ሚክያስ የትንቢት መጽሐፍ በሐዲስ ኪዳን በአራቱም ወንጌላውያን መጠቀሱ በጥንት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አስተምህሮ ልዩ ቦታ እንዲኖረው ምክንያት ሆኗል። አጻጻፉም በኅብረ አምሳል የተመላና በእስራኤልና ይሁዳ ሊመጣ የነበረውን መፈራረስ የሚያትት ነው፤ አያይዞም በመሲሑ የሚመጣውን መነሣትና ክብር ተንብዮ አስፍሯል።
የትንቢቱም ወራት እንደተፈጸመ ወደ በጎ ሽምግልና ደርሶ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ሄደ፡፡ ማርታ በምትባል ቦታም ተቀበረ፡፡
የነቢዩ ሚክያስ ጸሎቱ፣ አማላጅነቱና ተረዳኢነቱ አይለየን፤ አሜን!