‹‹እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም›› (ዘዳ. ፴፫፥፳፮)
ዲያቆን ዮሐንስ አባተ
ጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ከጠፈር በላይ ርቀቱ፣ ከባሕር በታች ጥልቀቱ፣ ከአድማስ እስከ ናጌብ ስፋቱ የማይታወቅ፣ ነፋሳት ሳይነፍሱ፣ አፍላጋት ሳይፈሱ፣ ብርሃናት ሳይመላለሱ፣ የመባርቅት ብልጭታ ሳይታይ፣ የነጎድጓድ ድምጽ ሳይሰማ፣ መላእክት ለቅዳሴ ከመፈጠራቸው አስቀድሞ፣ በአንድነቱ ሁለትነት፣ በሦስትነቱ አራትነት ሳይኖርበት፣ ለቀዳማዊነቱ ጥንት፣ ለማዕከላዊነቱ ዛሬ፣ ለደኃራዊነቱ ተፍጻሜት የሌለበት፣ በባሕርዩ ሞት፣ በሥልጣኑ ሽረት፣ በስጦታው ንፍገት የማይስማማው፣ የማይሾሙት ንጉሥ፣ የማይጨበጥ እሳት፣ የማይነጥፍ የፍቅር ጅረት፣ የነበረ ያለና የሚኖር፣ እንደ አምላካችን እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም፡፡
ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ስለ እግዚአብሔር ክብርና ስለማይመረመር ባሕርዩ በአስተማረው ትምህርት የእግዚአብሔርን ክብር ተናግሮ መጨረስ ባይቻልም የልጅነታችንን ያህል ስለ ቅዱስ ስሙና ስለ ግብረ ባሕርዩ በቅዱሳት መጻሕፍትና በሥነ ፍጥረት የተገለጠልንን ያህል ማወቅና መናገር እንደምንችል እንዲህ ሲል በምሳሌ ያስረዳናል፤ ‹‹የባሕርን ውኃ ጠጥቼ የማልጨርስ ከሆነ ጥሜን የሚያረካልኝን መጠን ያህል መጠጣት አይገባኝምን? ዓይኖቼስ ፀሐይን በመላዋ ወስነው ማየት ስለማይችሉ የሚያስፈልገኝን ያህል ማየት አይገባኝምን? ወይስ ወደ አትክልት ሥፍራ ገብቼ በዚያ ያሉትን ፍራፍሬ ሁሉ መመገብ ስለማልችል ከነረኃቤ ከዐጸዱ መውጣት ይኖርብኛልን?›› በማለት ምንም እንኳ ስለ እግዚአብሔር የማይመረመር ባሕርይ በብዛት መናገር ባንችልም ስለ ማንነቱ ተናግረን ባንጨርስም የልጅነታችንን ያህል በጥቂቱ የምናውቅና የምንናገር መሆኑን በትምህርቱ ያስረዳል። (የሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም ካቴኬቲክ ትምህርቶች ገጽ ፻፶)
የእግዚአብሔር ስም ሥነ ፍጥረትና በእግዚአብሔር ፈቃድ የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር ከሚነግሩን የተገለጸውን ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም የእግዚአብሔርን ስም ዓይነትና የትርጒሙን ምንነት ስንመረምር በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በብዛት የምናገኘው የእግዚአብሔርን ግብረ ባሕርያዊ መገለጫ የሚያስረዳን ነው።
በሰው ልጆች የሕይወት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስመ እግዚአብሔርን መጥራትና በስሙም መማል የተጀመረው የሴት ልጅ በሆነው በሄኖስ ዘመን መሆኑንና ቅዱስ ሄኖስም ይህን በማድረጉ እግዚአብሔር በጸፍጸፈ ሰማይ (በሰማይ ሰሌዳ) ላይ ሃያ ሁለቱን አሌፋት (ፊደላት ) ጽፎ እንዳሳየው የብሉይ ኪዳን መተርጉማን ይናገራሉ። ነቢየ እግዚአብሔር ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ በሃያ ሁለቱ አሌፋት(ፊደላት) ልክ ፈጠሪውን አመስግኗል፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ ፊደል የእግዚአብሔርን የስም ትርጒም ማወቅ በምንችለው መጠን ልክ የሚያስረዳን ስለሆነ ነው። (ዘፍ. ፬፥፳፮ አንድምታ፣መዝ. ፻፲፰)
ለምሳሌ ፦
፩) ‹አሌፍ› የሚለው ፊደል በዕብራይስጥ የመጀመሪያው ፊደል ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹አብ ፈጣሬ ኵሉ ዓለም፤ አብ (እግዚአብሔር) የዓለም ሁሉ ፈጣሪ ነው›› የሚል ትርጓሜ አለው፤ በዚህም ስመ ፊደል እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረ መሆኑን እንረዳበታለን። ሠለስቱ ምዕት በሃይማኖተ አበው ‹‹ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን›› ብለው ገልጸውታል። ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መጀመሪያውና መጨረሻው እርሱ መሆኑን ሲገልጥልን ‹‹አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ›› በማለት ነበር። ‹አልፋ› የመጀመሪያው የግሪክኛ ፊደል ሲሆን ‹ዖሜጋ› ደግሞ የመጨረሻው ፊደል በመሆኑ ቀዳማዊነቱንና ደኃራዊነቱን በነዚህ ፊደላት ሊገልጥልን ችሏል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አልፋና ዖሜጋ እየተባለ ይጠራል። (ራእ. ፩፥፰፣ ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምዕት ም. ፲፯፥፫ ገጽ ፵፮)
፪) ‹ቤት› ብሂል ባዕል እግዚአብሔር፤ ቤት ሁለተኛው የዕብራይስጥ ፊደል ሲሆን ትርጒሙም ‹‹እግዚአብሔር ባለጸጋ ነው›› ማለት ነው። ከእርሱ ሳይጎድልበት ለሌላው የሚሰጥ ‹‹ብዕለ ጸጋ ጥበቡ ዘኢይትዓወቅ፤ በጥበቡ እየሰፈረ የሚሰጠው የጸጋው ብዛት የማይታወቅ›› የሚባል ከእርሱ ውጭ ማን አለ?
፫) ‹‹ጋሜል ብሂል ግሩም እግዚአብሔር፤ ጋሜል ማለት እግዚአብሔር ድንቅ ነው›› ማለት ነው። ዓለምን ፈጥሮ በውስጥም በውጭም የሚኖር ከእርሱ በቀር ማንም የለምና ግሩም እግዚአብሔር ይባላል፡፡ ‹‹ግሩም በውስተ ደመናት ወልዑል እምሰማያት….፤ በደመናት ግሩም ነው፤ ከሰማያትም ይልቅ ከፍ ያለ ነው…›› ሠለስቱ ምዕት በቅዳሴያቸው እንደተናገሩት ማለት ነው፡፡
፬) ‹‹ዳሌጥ ብሂል ድልው እግዚአብሔር፤ ዳሌጥ ማለት እግዚአብሔር ዝግጁ ነው፤ በጌትነቱ ዙፋን ይኖራል›› ማለት ነው፡፡
፭) ‹‹ሄ ብሂል ህልው እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር በአንድነቱ በሦስትነቱ አለ›› ማለት ነው፡፡
፮) ‹‹ዋው ብሂል ዋሕድ እግዚአብሔር፤ ዋው ማለት እግዚአብሔር አንድ ነው›› ማለት ነው፡፡
፯) ‹‹ዛይ ብሂል ዝኩር እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ እየታሰበ ሲመሰገን ይኖራል›› ማለት ነው፡፡
፰) ‹‹ሔት ብሂል ሕያው እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ሕያው ዘለዓለማዊ ነው›› ማለት ነው፡፡
፱) ‹‹ጤት ብሂል ጠቢብ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ጥበበኛ ነው›› ማለት ነው፡፡
፲) ‹‹ዮድ ብሂል የማነ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች›› ማለት ነው፡፡
፲፩) ‹‹ካፍ ብሂል ከሃሊ እግዚአብሔር- እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ አምላክ ነው›› ማለት ነው፡፡
፲፪) ‹‹ላሜድ ብሂል ልዑል እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ታላቅና ገናና ነው›› ማለት ነው፡፡
፲፫) ‹‹ሜም ብሂል ምዑዝ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ምዑዘ ባሕርይ ነው›› ማለት ነው፡፡
፲፬) ‹‹ኖን ብሂል ንጉሥ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ንጉሥ ነው›› ማለት ነው፡፡
፲፭) ‹‹ሳምኬት ብሂል ሰፋኒ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር በባሕርዩ ሁሉን ገዢ ነው›› ማለት ነው፡፡
፲፮) ‹‹ዔ ብሂል ዐቢይ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነው›› ማለት ነው፡፡
፲፯) ‹‹ፌ ብሂል ፍቁር እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ተወዳጅ የፍቅር አምላክ ነው›› ማለት ነው፡፡
፲፰) ‹‹ጻዴ ብሂል ጻድቅ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ሐሰት የሌለበት እውነተኛ ነው›› ማለት ነው፡፡
፲፱) ‹‹ቆፍ ብሂል ቅሩብ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ለሚወዱት ቅርብ ነው›› ማለት ነው፡፡
፳) ‹‹ሬስ ብሂል ርኡስ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር የሁሉም ነገር መገኛ ራስ ነው›› ማለት ነው፡፡
፳፩) ‹‹ሳን ብሂል ስቡሕ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር በባሕርዩ ምስጉን ነው›› ማለት ነው፡፡
፳፪) ‹‹ታው ብሂል ትጉህ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር በባሕርዩ ድካም እንቅልፍ የሌለበት ትጉህ ነው›› የሚል ትርጒም አላቸው፤ እኒህም ስመ ፊደላት እግዚአብሔር ለፍጥረታቱ በሚያደርጋቸው አምላካዊ መግቦቶችና የማዳን ሥራዎች ምክንያት ጥቂት ስለእርሱ የሚያሳውቁን የእግዚአብሔር ስሞች ናቸው።
ሁሉም የእግዚአብሔር ግብረ ባሕርያዊ የመገለጫ ስሞች በምሳሌ ነገር እግዚአብሔርን በቅርበት እንድናውቅ፣ ፈቃዱንም እንድንከተልና በሕይወት ከእርሱ ጋር እንድንኖር እንድንሆን ወደ እርሱ የሚያደርሱን ስሞች ናቸው፡፡ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን የተለያየ ዓይነት ምክንያታዊ ግንኙነቶች የሚያጠነክሩ ናቸው። ለምሳሌ ‹ኤልሻዳይ› የሚለው ስም ትርጓሜ ‹‹ሁሉን ቻይ›› ማለት ሲሆን የሰው ልጆች ሁሉን በሚችለው በእግዚአብሔር እንዲመኩና እርሱን እንዲደገፉ የሚጋብዝ ስም ነው። ያለእሳት የሚያነድ፣ ያለ ውኃ የሚያበርድ፣ ከእርሱ ውጪ የማይቻለውን የሚችል ማን አለ? ልዑል እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ መሆኑን ለመግለጥ ሠለስቱ ምዕት በቅዳሴያቸው ‹‹ዘእንበለ እሳት አንደደ ወዘእንበለ ማይ አብረደ፤ ያለእሳት አነደደ፤ ያለውኃ አቀዘቀዘ›› በማለት ከሃሊነቱን የመሰከሩለትና እኛም በዚሁ አምላክ በመመካት እንድንኖር የሚጋብዙን ለዚህ ነው፡፡ (ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት)
በተጨማሪም ‹ኤል› የሚለው ስም ዕብራስጥኛ ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ኃያል አምላክ›› ማለት ነው። በዚህ ዓለም የአንዱ ኃይል ከሌላው ኃይል ይበልጣል፤ የሁሉም ኃይል በመጠን ይለካል። የእግዚአብሔር ግን ኃይሉ የማይመጠን፣ የኃይለኞች ኃያል፣ የብርቱዎች ብርቱ፣ በተናቁት ወዳጆቹ አድሮ ኃይል በመስጠት ታላቅ ሥራን የሚሠራ ኃያል አምላክ ነው።
ሌሎችም ክብሩንና ሁሉን አድራጊነቱን የሚገልጹ ስሞች አሉ። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን ባሕርይና ከሃሊነት ሙሉ በሙሉ በሰው ቃላት መግለጽም ሆነ ማስረዳት አይቻልም፤ ምክንያቱም ፍጹም የሆነውን የአምላክ ባሕርይ የሰዎች ውሱን አእምሮ ሊደርስበትና ሊመረምረው አይችልምና። ነገር ግን በእርሱ አምነን የዘለዓለምን ሕይወት እናገኝ ዘንድ እኛ ሰዎች በምንረዳው አቅም ራሱን ገለጠልን እንጂ ባሕርዩን በባሕርዩ ሰውሮ የሚኖር የእርሱን ገናንነት ማን ይናገረዋል፤ ‹‹ክዱን ብከ ዕበይከ ወስውር ብከ ኃይልከ ለሊከ ብከ አንጦላዕከ ኪያከ ወአንተ ብከ ለሊከ ተከደንከ፤ ገናንነትህ በአንተ የተሠወረ ነው፤ ኃይልህም በአንተ የተሠወረ ነው፤ አንተ ቅሉ ራስህን በራስህ ጋረድህ አንተ ራስህን በራስህ ሠወርህ›› እንዲል፤ (ቅዳሴ ዘዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ)
ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና የእርሱን የባሕርዩን ገናንነት ለዓይን ሩቅ ለአእምሮ ረቂቅ የሆነውን የስሙን ትርጓሜ ለመረዳት የሞከሩ አበው በተመስጦ ተነጥቀው የባሕርዩን ጥልቀት ከነቢዩ ዳዊት ጋር እንዲህ ሲሉ በትሕትና ያደንቃሉ፤ ‹‹ዕውቀትህ ከእኔ ይልቅ ተደነቀች፤ በረታች፥ ወደ እርስዋም ለመድረስ አልችልም።›› (መዝ. ፻፴፰፥፮)
እኛም በቅዱሳት መጻሕፍት ከተጻፉልን በሥነ ፍጥረት ከተረዱልን አስማተ እግዚአብሔር በመነሣት የእርሱን ገናንነት ‹‹አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና›› ከማለት ውጪ ምን እንላለን፤ (መዝ.፹፭፥፲)
እግዚአብሔር አምላካችን የተመሰገነ ይሁን፤ አሜን!