እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል፣ በሰላም አደረሰን/አደረሳችሁ

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

                                                  በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፡-
ከሁሉ በማስቀደም፣ የዘመናት ባለቤት ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር አምላክ፣ በረከት የምናገኝበትን ፆም በሰላም አስጀምሮ በሰላም በማስፈፀም፣እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል፣ በሰላም አደረሰን/አደረሳችሁ! በማለት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር ተዋቅሮ፣ የቅድስት ቤተክርስቲያንን አገልግሎት ለማገዝ፣ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው ማኀበራችሁ፣ ማኀበረ ቅዱሳን፣ መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

ውድ ምእመናን! የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፡- የድኀነታችን ተሰፋ ቃል የተፈጸመበት፤ ዓመተ ኩነኔ ተደምስሶ፣ ዓመተ ምሕረት የታወጀበት ዕለት በመሆኑ፤ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን በዓል በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ ደስታና ድምቀት ታከብረዋለች፡፡

እግዚአብሔር ጊዜን ለእኛ የፈጠረ እንጂ፣ለእርሱ ዘመን የማይቆጠርለትና ቦታ የማይወሰንለት አምላክ ሆኖ እያለ፤ እኛን ለማዳን ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍፁም አምላክ፣ ፍፁም ሰው ሆኖ የተወለደበትን ይህን ዕለት በየዓመቱ እየቆጠርን የምናከብረው፡- የቸርነቱን ስራ እያደነቅን፣ በልደቱ ብርሃንነት ከተገኘው በረከት ተካፋይ በመሆን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የበረታን እንሆን ዘንድ ነው፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ፡-ሰብአ ሰገል ልዩ ልዩ ገጸ በረከቶችን ይዘው፣ በቤተልሔም እንደተገኙ ሁሉ፣ እኛም ክርስቲያኖች በአንድ ልብና በጋራ በመሆን፣ በተሰጠን ጸጋ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ልናግዝና ልንጠብቅ ይገባል፡፡እኛ ክርስቲያኖች በዓሉን፡- ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለሰው ልጆች ድኀነትና ፍጹም ሰላም ሲል ወደ ምድር የመጣበትን በማሰብ የምናከብረው ስለሆነ፤ እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር በተሰጠን ሰላም እየተጠቀምንና እርስ በእርሳችን እየተዋደድን፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ብሎም ለሀገራችን ፍሬ ያለዉ ተግባር እንድንፈጽም እግዚአብሔር ይጠብቅብናል፡፡

ውድ ምእመናን! የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን፣ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ትእዛዛቱን አክብረን በቤቱ ውስጥ መኖር የሚጠበቅብን ስለሆን፣ መዳናችን ዘለዓለማዊነት ያለው ይሆን ዘንድ፣ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም የተመሰለችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ስለመሠረተልን፣ በእርሷ መገልገልና ማገልገል፣ የመንፈሳዊ ሕይወታችን ብቸኛዉ መንገድ ስለሆነ፤ በፍጹም ትጋት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ማኀበረ ቅዱሳንም፡-የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጅ በመሆን አገልግሎቷን እየፈፀመ ያለው፣ሁላችንም ያገኘነውን የእግዚአብሔር ልጅነት በማጽናት የሰማያዊው መንግሥት ወራሾች እንሆን ዘንድ ነውና፤ ማኀበሩ፡- ኃይለ እግዚአብሔርን፣ የአባቶችን ጸሎትና ብራኬ አጋዥ በማድረግ እንዲሁም የአባላቱንና የምእመናንን ዐቅምና ድጋፍ በማስተባበር እየፈጸመ ያለው አገልግሎት፣ እግዚአብሔር እንደፈቀደ፣ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የምናፈራበትና በሥነ ምግባር ተኮትኩተው በማደግ ሀገራቸዉን በሥርዓት ማገልገል የሚችሉ ዜጋዎችን ማግኘት የምንችልበት ነው፡፡

በአጠቃላይም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየተፈጸመ ያለው አገልግሎት፡-
 በዘመኑ ከሚፈለገዉ የቅድስት ቤተክርስቲያን ዘመኑን የዋጀ የአገልግሎት ተደራሽነት፣
 መጠናከር ካለበት አሠራር እንዲሁም
 መፈታት ካሉባቸዉ ፈተናዎችና ችግሮች አኳያ ሲታይ፣ በጣም ትንሽና ከሁላችንም ገና ብዙ የሚጠበቅ ነገር ያለ መሆኑን የሚያሳይ ነዉ፡፡

ስለሆነም ኀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ነው፤ ለኀምሣ ሰው ግን ጌጡ ነው! እንደሚባለው፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሆነውን የማኀበሩን አገልግሎት፡ቀርበን በጉልበታችን፣ በጊዜአችንና በገንዘባችን እናግዝ፡፡ እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ እንደ እየአቅማችንና ተሰጥዎአችን በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ዉስጥ በቃለ ዐዋዲዉ መሠረት እየገባን፣ ድጋፍና ተሳትፎ እናድርግ፣ በማለት ማኀበሩ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

በመጨረሻም፡-በቅዱስ ወንጌሉ፣ «በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን» ተብሎ እንደተጻፈ፣ በዓሉን ስናከብር፡- እግዚአብሔር ሰላምን በሃገራችን እንዲያጸናልን በመለመን፣ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ እና በፍፁም መንፈሳዊ ሕይወት በመመላለስ፣በረከት የምናገኝበት ይሁንልን በማለት ማኀበሩ ምኞቱን ይገልጻል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡