‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ›› (ዘሌ.፲፱፥፪)
መምህር ኃይለሚካኤል ብርሀኑ
የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት (ሰንበት) ቅድስት ይባላል፡፡ ስያሜው የቅዱስ ያሬድ ሲሆን የመዝሙሩ ርዕስ የጾመ ድጓው መክፈያ ሆኖ የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ከቅድስት ሰኞ ጀምሮ ጾመ ኢየሱስ ይባላል፡፡ በዚህ ሳምንትም ስለ እግዚአብሔር ቅድስና የሚያነሱ መዝሙራት ይቀርባሉ፤ እኛም እግዚአብሔርን መቀደስ (ማመስገን) እንዳለብን የሚገልጹ ምንባባት ይነበባሉ፣ትምህርት ይሰጣል፡፡
እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፤ ቅድስናውም ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስ ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት፣ቅዱሳን ጻድቃን፣ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ሰማዕታት፣ ቅዱሳን አበው፤ ቅዱሳት አንስት፤ ቅዱሳን ሊቃውንት፣ቅዱሳን ጳጳሳት፣ ቅዱሳን መነኮሳት፣ ቅድስናን ያገኙት በባሕርዩ ቅዱስ ከሆነው ከአምላካችን ከቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡
ቅዱስ የሚለውን ቃል ስንመለከት ምስጉን፣ክቡር፣ንጹሕ፣ የተለየ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው ስንልም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ የሚመሰገን፤ የቅድስና ምንጭ በቅድስናው የተቀደሰ፤ ቅዱሳንን የሚቀድስ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው፤ኢሳ (፮፥፩)፡፡
ፍጡራንስ ቅዱስ ተብለው መጠራታቸው እንዴት ነው? ብለን ብንጠይቅ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ሁሉ የተለየ ቅዱስ ስለሆነ ወደ እርሱ የተጠሩና የመጡ ለእርሱ ክብር የተለዩ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ይህም ማለት ቅድስናን በጸጋ አግኝተው እንዲያጌጡበት የተጠሩት ሰውና መላእክት ሲሆኑ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የዋሉ የመቅደሱ ዕቃዎች አልባሳቶች በአጠቃላይ ንዋያተ ቅዱሳቱ ቅዱስ ተብለው ይጠራሉ፡፡ እኛም እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ መንግሥቱ ሲጠራንና ልጅነትን ሲሰጠን ለእግዚአብሔር ተለይተን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች እንሆናለንና፤ቅዱሳን ተብለን እንጠራለን፡፡
እግዚአብሔር ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ›› ብሎ እንደተናገረው ንጽሕናን ቅድስናን በጸጋ እግዚአብሔር ገንዘብ ያደረጉ ሰዎች ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ እንዲሁም ሰውና መላእክት የሚገናኙባት፣ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምታስገኝ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ስንል ለእግዚአብሔር አምልኮ የተለየች ክብርትና ንጽሕት ናት ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ለራሱ ትሆን ዘንድ የለያት ነፍሱን ስለ እርስዋ አሳልፎ እስከ መስጠት የወደዳት ፣ በደሙ የዋጃትና በቃሉ ያነጻት የክርስቶስ አካሉ ቤተ ክርስቲያን ንጽሕት ናትና ክርስቶስ ክቡር እንደሆነ ክብርት፣ ንጹሐ ባሕርይ እንደሆነ ንጽሕት፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ የኖረች የክርስቶስ ሙሽራ ናት ማለታችን ነው፡፡
ፍጡራን የቅድስናቸው ምንጭ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፤ ከላይ እንዳየነው እርሱ የቅዱሳን ቅዱስ ነውና፡፡ በሙሴ መጽሐፍ እንደ ተጠቀሰው እስራኤልን እግዚአብሔር ከግብጻውያን እጅ እንዳዳናቸውና ግብጻውያንም እንደሞቱ በባሕር ዳር አዩ፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፡፡ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርም አመኑ፤ ባሪያውንም ሙሴን አከበሩ፡፡ በአንድነትም በዝማሬ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ በዝማሬያቸውም የእግዚአብሔርን ቅድስና እንዲህ ሲሉ ገለጹ ‹‹አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማን ነው? በምስጋና የተደነቅህ ነህ፤ ድንቅንም የምታደርግ ነህ፤ ቀኝህን ዘረጋህ ምድርም ዋጠቻቸው›› (ዘፀ ፲፭፥፲፩) በማለት መስክረዋል፡፡
አምላከ አማልክት፤ እግዚአ አጋዕዝት ጌታ በቅድስና የከበረ ነው፡፡ ምስጋናውም ቅዱስ እንደሆነ ያየውና የሰማው ኢሳይያስ ስሙን ቅዱስ ብሎ ጠርቶታል፡፡ ‹‹እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ?›› (ኢሳ ፵፥፳፭) ይላል ቅዱሱ እግዚአብሔር፡፡
ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ እንደተናገው ‹‹አንተ ብቻ ቅዱስ ነህ›› ብለው መላእክት በሰማይ በባሪያው በሙሴ መዝሙር እንደሚያመሰግኑት ጽፎልናል፡፡ ‹‹ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ መንገድህ ጻድቅና እውነት ነው፤ ጌታ ሆይ አንተን የማይፈራና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፡፡ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለህ አንተ ነህ፤ አቤቱ ፍጥረትህ ሁሉ በፊትህ ይሰግዳሉ፤ ፍርድህ ተገልጦአልና››፤ (ራእ.፲፭፥፫) ይላል፡፡
በአፈ መላእክት ቅዱስ ተብሎ የሚጠራውና የሚቀደሰው በልሳነ ሰብእም ይትቀደስ ስምከ (ስምህ ይቀደስ) እየተባለ የሚጠራ ስሙ ቅዱስ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ስሙን እየጠሩ እንደሚያመሰግኑት ሲመሰክር “አንዱም ለአንዱ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” ሲል ገልጾታል(ኢሳ.፮፥፫)፡፡
ቅዱሱን የወለደች እመ አምላክ ድንግል ማርያምም “ወቅዱስ ስሙ፤ስሙ ቅዱስ ነው ብላ መስክራለች” (ሉቃ.፩፥፶)፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለ ራሱ ቅድስና ሲናገርም “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌ.፲፱፥፪) ብሏል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ በእርሱ ቅድስና እንድንቀደስ እንደሆነ ሲገልጽ “የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” ይላል (፩፥፲፭)፡፡
የጠራን እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ በቅድስና መኖር ያስፈልጋል፡፡ ከእግዚአብሔር የተወለድንበት ምሥጢረ ጥምቀት የቅድስናችን መጀመሪያ ስለ ሆነ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ለመሆን ተሠራን፡፡ ነገር ግን ከቅድስና የሚያጎድሉንን ክፉ ተግባራት ስንፈጽም እንበድላለንና በጸጋ ያገኘነውን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እናጣለን፡፡ ስለዚህ እንዳንበድልና ቅድስናን እንዳናጣ ተግተን በእውነት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር ያስፈልጋል፡፡