‹‹እኔ ሩፋኤል ነኝ››
ጳጉምን ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
በመላእክት ዓለም በነገድ ተከፍለውና በሊቀ መላእክት ሹመት ቅዱሳን መላእክት ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን እያመሰግኑ ዘወትር ያገለግላሉ፡፡ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክትም ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ሊቀ መላእክት የሆነው ቅዱስ ሩፋኤል የተሾመበትና የከበረበት ዕለት ጳጉሜ ሦስት ታላቅ በዓል ነው፡፡
በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተጻው ሐዋርያት የቅዱስ ሩፋኤልን ክብሩን ያስረዳቸው ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በለመኑበት ጊዜ ከሦስተኛው ዓለም ውስጥ የመላአክት አለቆች ቅዱስ ሚካኤልን ቅዱስ ገብርኤልን እና ቅዱስ ሩፋኤልን እንዲመጡ አዘዛቸው፤ እነርሱም መጥተው በታላቅ ደስታ ለክብር ባለቤት ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰገዱ፡፡ ጌታችንም ቅዱስ ሩፋኤልን እንዲህ አለው፤ ‹‹የክብርህን ገናናት የባልንጀሮችህንም ልዕልናቸውን እንዲያውቁ ለሐዋርያት ንገራቸው፡፡›› ያንጊዜም ለጌታችን ሰገደ፤ እንዲህም አላቸው፤ ‹‹ደገኛው የመላእክት አለቃ ሚካኤል ለሁሉም መላእክት አለቃቸው ነው፤ ስሙም ይቅር ባይ ይባላል፡፡ ሁለተኛም የመላክት አለቃ ገብርኤል ይባላል፤ የስሙም ትርጓሜ አገልጋይም ጌታም የሆነ የዓለሙ ሁሉ እመቤት የሆነች አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምን ያበሠራት ነው፡፡ የእኔም ስሜ ሩፋኤል ነው፡፡ ይህም ደስ የሚያስኝ ቸር መሐሪ ቅን የዋህ ማለት ነው፡፡ እኔም ኃጢአተኞችን በእግዚአብሔር ዘንድ አልከሳቸውም፤ ከኃጢአት በንስሓ እስኪመለሱ ስለ ቅንነቴ በእነርሱ ላይ እታገሣለሁ እንጂ፤››
በሃያ ሦስቱ የመላእክት ነገደ ሠራዊት ላይ እግዚአብሔር የሾመኝ እኔ ሩፋኤል ነኝ፤ እግዚአብሔር አብን ይቅር ባይ ልጁን አጽናኝና አዳኝ የሆነ መንፈስ ቅዱስን እናመሰግነው ዘንድ፤ በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺህ ዓመት ተድላ ደስታ የክብር ጽዋን በሚሰጣቸው ጊዜ ለቅዱሳኖቹ በጎ ነገርን እንድንሰጣቸው ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ፡፡ ደግሞም በዚህች ቀን ከዕፀ ሕይወት ዐጽቅ ወስጄ ለተመረጡ ክርስቲያኖች በእጄ እንድንሰጣቸው እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ፡፡የሰማያት መዛግብትም ከእጄ በታች ተጠብቀው የሚኖሩ እኔ ሩፋኤል ነኝ፡፡ እኔም እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እከፍታቸዋለሁ፤ እዘጋቸዋለሁም፡፡
በምድር ሰው ባልንጀራው ስለ ስሜ በጎ ነገር ቢያደርግ እኔ ከመከራው በችግሩ ረዳዋለሁ፤ ወይም የሹመቴን ነገር የሚጽፍ ወይም ከቅዱሳን ጋራ ስሜን የሚያስብ ወይም በስሜ ለቊርባን የሚሆነውን የሚሰጥ ወይም በበዓሌ ቀን ምጽዋትን የሚሰጥ ይኸውም እግዚአብሔር በሊቃነ መላእክት ክብር የሾመኝ ያከበረኝ ጳጉሜን ሦስት ቀን ነው፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማየዊት እስከማስጋበው በብርሃን ሠረገላ እኔ እሸከመዋለሁ፡፡ በምድር ላይ ከቶ እንደርሱ ያለ የማይገኝ መዐዛው እጀግ ጣፋጭ በሆነ ሽቱ ነፍሶቻቸው እርሱን በማሽተት ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ፡፡ ሐዋርያት ሆይ በእግዚአብሔር ፊት እስክትቆሙ እጠብቃችሁ ዘንድ ከእኔ ርዳታ ሹ፡፡››
የዚህ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሩፋኤል ተአማራቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ በተከበረች በጳጉሜን ሦስት የጦቢትን ዓይን ያበራና የራጉኤልን ልጅ ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቃት ይህ መላእክ ነው፤ በመጽሐፈ ጦቢት ታሪኩ እንደተጻፈው በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጦቢት የተበላ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ የሾመና ለወገኖቹ ምጽዋት የሚሰጠት በጎ ሰው ነበር፡፡ ሐና ከምትባል ሚስቱም አንድ ልጅ ነበረው፡፡ ንጉሥ ስልምናሶር ከሞተ በኋላ ግን በሰናክሬም ዘመነ መንግሥት ከሹመቱ ስለሻረው ወደ ምድያም ምድር መሄድ አልቻለም፡፡
በዚያን ጊዜ ሣራ የምትባል ራጉኤል ልጅ አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት፤ ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት፤ እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡ የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ አጥብቆ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጁ የኑሮ ጓደኛህን እንዲፈልግ ከአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ወገን የሆነችውን እንዲያገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጠው ገንዘብ ስለነበር እርሱ በሕይወት እያለ ቢያመጣው እንደሚሻል ነገረው፡፡ ጦብያም ያባቱን ምክር ሁሉ በጽሞና ካዳመጠ በኋላ የነገርከውን ነገር ሁሉ እንደሚፈጽም ቃል ገባለት፤ ሆኖም ግን ከገባኤል ጋር ስላለው ገንዘብ ማምጣት ስለማይቻለው ሀገሩን አያውቀውና የአባቱን ርድታ ጠየቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢት ልጁ ጦብያን አብሮት የሚሄድ ሰው እንዲልግ እና ደመወዝ አንደሚሰጠው ቢሆን ከእርሱ ጋር የሚሄድ አንድ ሰው ግድ እንደሚያሰፈልገውና ሄደው ሰው እንዲፈልግ ነገረው፡፡
ጦብያም አብሮት የሚሄደው ሰው ለመፈለግም በሄደ ጊዜ አንድ መልከ መልካም ጐበዝ ሰው አገኘ፤ ይኸውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ነበር፡፡ ነገር ግን መልአኩ መሆኑን ፈጽሞ አላወቀም ነበር፡፡ ጦብያም መልአኩን ሰው መስሎ እንዳገኘው ‹‹ሀገሩን ታውቅ እንደሆነ ወደ ሜዶን ክፍል ወደ ራጌስ ከእኔ ጋር መሄድ ትችላለህን?›› በማለት ጠየቀው፤ ቅዱስ ሩፋኤልም ‹‹ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ መንገዱንም ዐውቀዋለሁ፤ በገባኤል ቤት ነበርሁ›› አለው፡፡ጦብያም መልሶ ከአባቱ ጋር ወስዶ ካስተዋወቀው በኋላ ጦቢትም ከወዴት እንደ መጣ ማን ተብሎ እንደሚጠራ ጠየቀው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም ‹‹እኔስ የወንድምህ ታላቁ አናንያ ዘመድ አዛርያ ነኝ›› አለው፡፡ ጦቢትም የወንድሙ ዘመድ መሆኑን ከሰማ በኋላ ‹‹አንተስ ወንድሜ ደህና ነህን፤ ብሎ ሰለምታ ከሰጠው በኋላ የልጁን የጦብያን ነገር አደራ ሰጥቶ ስንቃቸውን አስይዞ ሸኛቸው፡፡
ከዚህም በኋላ አዛርያስ (ቅዱስ ሩፋኤል) በመንገድ ይመራው ነበር፤ በዚህም መላኩ ‹መራኄ ፍኖት› (መንገድ መሪ ) ይባላል፡፡ እነርሱም ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያ ለማደር ተቀመጡ፡፡ ከዚያም ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ዓሣውንም እንዳይዘው ነገረው፤ ጦቢያም ዓሣውን ይዞ ወደ የብስ አወጣው፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ ‹‹ዓሣውን እረደው፤ ልቡንና ጉበቱን፣ ሐሞቱን ያዝ፤ አጥብቀህ ጠብቅ›› አለው፡፡
ጦብያም መልአኩ እንዳዘዘው ዓሣውን አርዶ ሐሞቱንና ጉበቱን ያዘ፤ ሌላውን ሥጋውን ግን ጠብሰው ራታቸውን በሉት፡፡ ጦብያም ያንን የዓሣውን ጉበትና ሐሞት ለምን እንዲጠነቀቅለት ለመረዳት ‹‹አንተ ወንድሜ አዛሪያ! የዚህ ዓሣ ልቡ፥ ጉበቱና ሐሞቱ ለምንድን ነው?›› በማለት ጠየቀው፤ ቅዱስ ሩፋኤልም ‹‹ልቡና ጉበቱ የሚያሳምም ክፉ ጋኔን ያደረበት ቢኖር ወይም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ቢኖር ያን ጊዜ ለዚያ በፊቱ ቢያጤሱለታል፤ ሴትም ብትሆን ያጤሱባታል፤ ከዚያም በኋላ አይታመሙም፡፡ ሐሞቱን ግን በዐይኑ ላይ ብልዝ ያለበትን ሰው ይሉኩታል፤ እርሱም ይድናል›› ብሎ መለሰለት፡፡ እንደዚህም እያሉ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ‹‹አንተ ወንድሜ! ዛሬ ከራጉኤል ቤት እናድራለን፤ እርሱም ዘመድህ ነው፤ አንዲት ልጅ አለችው፤ ስሟም ሣራ ይባላል፡፡ ሚስት ትሆንህ ዘንድ ስለ እርሷ እናገራለሁ›› አለው፡፡ ጦብያም ‹‹ያች ልጅ ከዚህ በፊት ሰባት ሰዎች እንዳገቧትና ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ሞተው እንደሚያድሩ ስለሰማ ለእርሱ ለአላባቱና ለእናቱ አንድ በመሆኑ እርስዋን አግብቶ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች የሞተ እንደሆነ አባቱንና እናቱን የሚረዳቸው የለም፤ ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እንደሚፈራ ነገረው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን ‹‹ከዘመዶችህ ሚስት ታገባ ዘንድ አባትህ ያዘዘህን ቃል አታስብምን? አሁንም አንተ ወንድሜ ስማኝ፤ የጋኔኑን ነገርስ አያሳዝንህ፤ በዚህች ሌሊት ከዘመዶችህ ወገን እርሷ ሚስት ሆና ትሰጥሃለችና፤ ወደ ጫጉላ ቤትም በገባህ ጊዜ የዕጣን ዕራሪ ወሰድ፤ ከዚህም ዓሣ ሐሞትና ከጉበቱና ከልቡ ጨምረህ አጢስበት፡፡ ጋኔኑም በሸተተው ጊዜ ይሸሻል፤ ለዘለዓለሙም አይመለስም፡፡ ወደ እርሷም በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ፤ እርሱም ያድናችኋል፡፡ ይቅርም ይላችኋል፤ እንግዲህ አትፍራ፤ ከጥንት ጀምሮ እርሷን አዛጅግቶልሃልና፤ አንተም ታድናታለህ፤ እርሷም ጃንተ ጋር ትሄዳለች›› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡
ከራጉኤል ቤት እንደ ደረሱም ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው፤ የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳየው ሚስቱ አድናን ‹‹ይህ ልጅ ድንቅ ነው፤ ከዘመዶች ወገን የሆነ ጦቢትን ይመስለዋል››አላት፤ ከዚያም ‹‹ወንድሞቻችን! እናንተ ከወዴት ናችሁ?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ወደ ነነዌ ከተማረኩት ከንፍታሌም ልጆች ሀገር ነን›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹ወንድሜ ጦቢትን ታውቅታላችሁን?›› በማለት ጠየቃቸው፡፡ ጦቢያም የአባቱ ስም ሲጠራ ‹‹እናውቀዋለን››፡፡ እርሱም ‹‹በሕይወት አለ?›› እነርሱም ‹‹አዎ፤ ደኅና ነው›› አሉት፤ ጦብያም ‹‹አባቴ ነው›› አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል ተነሥቶ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው ተላቀሱ፡፡ ራጉኤልም በግ አርዶ አበላቸው፡፡
ራት ከበሉ በኋላም ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን ዐስቦ ቅዱስ ሩፋኤልን በመንገድ የነገርከውን እንዲፈጽምለት ሲለምነው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹‹አንድ ጊዜ ብላ፤ ጠጣ፤ ደስም ይበልህ፤ ልጄ ለአንተ ትገባለችና፥ አንተም ታገባታለህ›› አለው፡፡ ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን ኑሮዋቸው እንዲቃናና ጋብቻቸው እንዲባረክ አስቀድመው ወደ ፈጣሪያቸው ጸሎት እንዲያደርጉ አሳሰባት፤ አብረውም ጸሎት ካደረጉ በኋላም ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡ የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ ‹‹መልአከ ከብካብ›› ይባላል፡፡
ከዚያ በኋላ የሰርጉ ቀን የሚሆን የ፲፬ ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሩ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው አማሎ ካቆየው በኋላ የሰርጉ በዓል ተፈጽሞ ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ላከው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና በመዘግየቱ ልጃቸው ክፋት አግኝቶት እንዳይሆን ስግተው ነበር፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ወደ እነርሱ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ተብሎ ሲነገረው ዓይነ ሥውር በመሆኑ እርሱን ለመቀበል በሚሄድበት ጊዜ ወደቀ፤ ጦብያም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር ወዲያው የአባቱን ዓይን ቀባው፤ የአባቱ ዓይኖቹም ተከፈቱ፡፡
ጦብያም ከዚህ በኋላ አብሮት ለነበረው ለመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል የድካሙን ዋጋ ሊከፍለው ሽቶ ገንዘብ ለመስጠት በጠሩት ጊዜ ጦቢትንና ጦብያን እንዲህ አላቸው፤ ‹‹ፈጣሪያችሁን አመስግኑ፤ እናንተ እስከ ዛሬ ድረስ ከየት እንደመጣሁ ማን እንደ ሆንኩ አላወቃችሁኝም፡፡ የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፤ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፤ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ›› በማለት ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡
ዳግምም በጳጉሜ ሦስትም ቅዱስ ሩፋኤልም በግብጽ ሀገር የምትገኘውን በአንድ ዓሣ አንበሬ ላይ የታነጸችውን ቤተ ክርስቲያኑን ዓሣ አንበሬው እንዳይገለብጣት ያጸናበትም የተአምር ዕለት ነው። በዚህ ዕለት ቀላያተ ምድር ሁሉ በመልአኩ በበትረ መስቀሉ ይባረካሉ። ስለዚህም ስለ እኛ ይማለድልን ዘንድ የበዓሉን መታሰቢያ ልናደርግ ይገባል፡፡
ምንጭ፤ መጽሐፈ ጦቢት፣ ድርሳነ ሩፋኤል፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ጳጉሜ