እነሆ ክረምት አለፈ
ጥቅምት 1 ቀን 2005 ዓ.ም.
በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ
“እነሆ ክረምት አለፈ ዝናሙም አልፎ ሄደ አበባው በምድር ላይ ታየ የመከር ጊዜ ደረሰ የቁርዬውም ድምጽ ተሰማ በለሱ ጎመራ ወይኖቹም አበቡ” መኀ.2፥11-13
ከዚህ ቀድሞ እንደተመለከትነው ክረምት ወርኀ ማይ/ውኃ/ ወርኀ ልምላሜ ወንዞች የሚሞሉበት ደመናና ጉም የሚሳብበት ሰማይ በደመና ተሸፍኖ የእግዚአብሔርን ጥበብ የሚያስተምርበት በመብረቅ በነጎድጓድ ድምጽ ታጅቦ ኀይለ እግዚአብሔርን የሚያስረዳበት መሆኑን ተመልክተን ነበር፡፡ አሁን ግን መግቦቱን ጨርሶ እነሆ ክረምት አለፈ ጊዜውንም በክረምት ከሚታየው ልምላሜ ቀጥሎ ለሚመጡ ለአበባና ለፍሬ አስረክቦ ከልምላሜ ቀጥለው የምናያቸው አበባና ፍሬ የሚያስተምሩት ቁም ነገር አለና፡፡
ከአበቦች ምን እንማራለን?
አበቦች ውብና ማራኪ አስደሳች ከመሆናቸው የተነሣ የሰው ልጅ በሙሉ አበቦችን ይፈልጋል ምድርም በአበቦች አጊጣ ተሸልማ ስትታይ ክረምት ከለበሰችው ልምላሜ ይበልጥ ታስደስታለች፡፡ “አሰርገዎ ለሰማይ በከዋክብት ወለምድርኒ አሰርገዋ በሥነ ጽጌያት” ሰማይን በከዋክብት አስጌጠው ምድርንም በአበቦች ደምግባት ሸለማት” ብሎ ቅዱስ ያሬድ ዘምሯል፡፡ ከዚህ የምንረዳው አምላካችን የሁሉ ጌጥ መሆኑን ነው፡፡ መጽሐፈ ኪዳን “ሠርጎ ዓለም ሣራሪሃ ለምድር ወኩሎ ተከለ ለሠርጎ ዓለም፡፡” የዓለም ጌጥ ምድርን የፈጠራት ሁሉንም ለዓለም ጌጥ ፈጠረ” ተብሎ ተጽፏል፡፡ በሜትር የማይለካ ሰማይን በከዋክብት፣ በፀሐይ፣ በጨረቃ ስፋቷ በዐይነ ገመድ የማይመጠን ምድር በአበባ ማስጌጥ ከቻለ ለሦስት ክንድ ከስንዝር የሆነ የሰውን ልጅ ማልበስ ማስጌጥ መሸለም ለምን አይችልም? ይችላል እንጂ፡፡ ታዲያ ከላይ የተመለከትናቸው ሁሉ የሚናገሩት የእግዚአብሔርን ከሓሊነት ነው፡፡ አፍ ሳይኖራቸው ይናገራሉ፤ አንደበትም ሳይኖራቸው ይመሰክራሉ፡፡
ከዚህ የተነሣ ጌታችን ሲያስተምር እንዲህ አለ “ወበእንተ አራዝኒ ምንተኑ ትሄልዩ ርዕዩ ጽጌያተ ገዳም ዘከመ ይልህቁ ኢይፈትሉ ወኢይጸምው ወባህቱ እብለክሙ ከመ ሰሎሞን ጥቀ ኢለብሰ በኩሉ ክብሩ ከመ አሐዱ እምዕሉ” ማቴ.6፥28፡፡
ስለ ልብስስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ! እንዴት እንደሚያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ! አይደክሙም አይፈትሉም ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞን ስንኳን በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም” ብሎ አበቦች ከእግዚአብሔር አግኝተው ነው ጌጥን ውበትን ተጎናጽፈው የሚኖሩት ለእነዚህ አበቦች ውበትን መውደድን የሰጠ እግዚአብሔር ለእኛም ይሰጠናል ብሎ ማመን የሚገባ መሆኑን በመግለጽ ሰው ምን እለብሳለሁ በምን አጌጣለሁ ብሎ ከመጨነቅ ይልቅ እግዚአብሔር በተፈጥሮ ውብ አድርጎ የፈጠረው እንደሆነ በማሰብ የጎደለው ሁሉ ከእግዚአብሔር የሚገኝ እንጂ በጭንቀት በመወጠርና በማማረር እንደማይገኝ ይልቁንም አበቦችን እንዲህ ያስጌጠ አምላክ ለእያንዳንዳችን የሚያስፈልገንን ሁሉ መስጠት የሚችል መሆኑን ማወቅ የተሻለ ነው፡፡ የእኛ ድርሻ መቀበል እንጂ መጨነቅ ሊሆን እንደማይገባም ያስተምረናል አበቦች ይህን ውበት ያገኙት በመጨነቅ አይደለም ሰውስ ከአበባ እንዴት ያንሳል?
በትክክል ሰው አበባን ይመስላል አበባ ያብባል በመልካም መዓዛው ከሰው ጀምሮ እስከ ጥቃቅን ፍጥረታት ድረስ ይማርካል ከአበባ ላይ መስፈር የሚፈልጉት ንቦች ብቻ አይደሉም ትንኞችና ዝንቦችም ጭምር እንጂ፡፡ ንቦች ማር ይሠሩበታል ዝንቦችና ትንኞች ደግሞ ቆሻሻቸውን ያራግፉበታል፡፡ ከዚህ በኋላ አበባው ይጠወልጋል ይረግፋል የሚከቡት ንቦችም ሆኑ ትንኞችና ዝንቦች አይፈልጉትም፡፡ አበባ በጊዜ ማራኪና አስደሳች ቢሆን ሲደርቅ ግን የሚፈልገው የለም የሚረግጠው እንጂ፡፡ አበባ ሲደርቅ አበባ መሆኑ እንኳን ይዘነጋል፡፡ በዚያን ጊዜ ወዳጁ ሁሉ ይርቀዋል ያን ጊዜ ወዳጅ የሚሆነው መደፋት አሊያም እሳት ብቻ ነው፡፡
ሰውም በእውነቱ ይህን ይመስላል ሲወለድ እናት አባት ዘመድ አዝማድ ወዳጅ በመወለዱ ይደሰታል፡፡ ሲያድግ አንተ ልጅ የማነህ አቡሽዬ የሚለው የሚስመው የሚከበው ይበዛል ሁሉም ምነው እንደዚህ ልጅ በሆንኩኝ አይ ልጅነት እያለ ይመኛል፡፡ ልጁ ካደገ በኋላ ግን እንደ አበባው ደረቅ እያለ የሚያስከፋ የሚያሳዝን፣ የሚያሰቃይም ሕይወቱ አላዋቂ አጫጅ እንደ አጨደው የፈረስ ሳር ምስቅልቅል ያለ ሀዘንና መከራ የከበቡት ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን አበባውን ዝንቦች ትንኞች እንዲሁም ማር መሥራት የሚችሉ ንቦች እንደሚከቡት ሰውንም እንደመአር የሚጣፍጥ መልካም ሥራ እንዲሠራ የሚረዱት መላእክት ይከቡታል ይረዱታል፤ ይላላኩታል በአንጻሩ ደግሞ እንደ ቆሻሻ የኀጢአትን ክምር የሚጭኑበት አጋንንት እንደ ትንኝና ዝንብ ከበው ኅሊናውን በክፉ ሐሳብ ያቆሽሹታል፡፡ በመላእክት ተከቦና ታጅቦ መልካም ሥራ ሲሠራ እግዚአብሔርንም ሰውንም ራሱንም መላእክትንም ያስደስታል፡፡ በፍቅሩም አሕዛብን ይማርካል፡፡ በሌላ መልኩ አጋንንት እንደዝንቦችና ትንኞች በላዩ ላይ ሰፍረው የኀጢአት ቆሻሻቸው መጣያ አድርገውት ክፉ እየሠራ ሲታይ እግዚአብሔርንም መላእክትንም ሰውንም ያሳዝናል አበባው ደርቆ ሲወድቅ እንደሚያስጠላ እርሱም ያንን ይመስላል፡፡
ከዚህ የተነሣ ነው ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ያስተማረው “ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው፡፡ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው፡፡ ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል” ኢሳ.40፥6-8 የሰው ልጅ ሕይወቱ እንዲህ እንደ ሣር ጠፊ እንደ አበባም ረጋፊ ከሆነ በዚህ ጊዜው ንስሐ መግባት ሥጋውን በልቶ ደሙን መጠጣት፤ ስርቆትን፣ ዝሙትን፣ ሐሰትን፣ ትዕቢትን፣ ተንኮልን፣ ክፋትን፣ ቂምን፣ በቀልን፣ ሥጋዊና ሰይጣናዊ ቅናትን አስወግዶ ወደ ፈጣሪው መቅረብ ይገባዋል፡፡ አበባ ዕድሜው አጭር ነው፡፡ ሰውም እንደዚያው ስለሆነ ሰው ሞትን መቅደም አለበት እንጂ ንስሐ ሳይገባ በሞት መቀደም የለበትም፡፡ ሰው በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው ሞትን ማሰብ መቻል ይገባዋል፡፡ “አብድ ውእቱ ዘይሄሊ ካልአ ዘእንበለ መቃብሩ ወርስቱ” እርስቱ ከሆነው ከሞትና ከመቃብር ሌላ የሚያስብ ሰነፍ ነው” እንዲል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ
በሌላ መልኩ አበባን ስንመለከተው የሚወድቀው፣ የሚረግፈው ፍሬ ለማስገኘት ነው፡፡ አበባ ሲኖር በመአዛው ሰውን ያስደስታል፡፡ ሲረግፍም በፍሬው ይጠቅማል፡፡ ሰው ሲኖርም ሲሞትም ፈጣሪውን የሚያስደስት መሆን አለበት እንጂ ያለፍሬ ንስሐ መሞት የለበትም፡፡ “ግብሩኬ እንከ ፍሬ ሰናየ ዘይደልወክሙ ለንስሐ” ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ማቴ.3፥8
“እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ይቆረጣል፡፡ ወደ እሳትም ይጣላል ማቴ.3፥10 ተብሏልና፡፡ ሰውም መልካም ፍሬን አፍርቶ፣ ንስሐ ገብቶ፣ ተዘጋጅቶ፣ የሰማይ ቤቱን ሠርቶ፣ መንግሥተ ሰማያትን ሽቶ፣ ራሱን በንስሐ የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ፣ ሰውቶ፣ ከእግዚአብሔር ተጠግቶ፣ መኖር አለበት፡፡ በጭፈራ በስካር የተሰጠውን ጊዜ ማቃጠል ራስንና እግዚአብሔርን መበደል ከቃለ እግዚአብሔር መኮብለል በኀጢአት ገደል መውደቅ በዚህም እንደታላቅ ሰው መመጻደቅ አይገባም፡፡ ጊዜ መሣሪያ እንጂ መቀለጃ አይደለም፡፡ መጽደቂያ እንጂ መኮነኛ፣ መነሻ እንጂ መውደቂያ፣ መሣሪያ እንጂ መክሰሪያ፣ ሊሆን አልተሰጠም፡፡ ታዲያ በዚህ እንደ አበባ በተሰጠን ጊዜ መጠቀም ድርሻችን ነው፡፡ ስለ አበባ ይህን ያክል በጥቂቱ ካልን፡-
ከፍሬስ የምንማረው ምንድር ነው?
አበባው ሲያልፍ ፍሬው ይተካል፡፡ ስለፍሬው ለመነጋገር ከዛፎች መነሣቱ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ የአበቦችም የፍሬዎችም ተሸካሚ ወይም አስገኝ ዛፎች ስለሆኑ ያለ ዛፍ ፍሬን ማሰብ ከባል በፊት ልጅ እንደማለት ነውና፡፡ ዕፅዋት፣ አዝርዕት አትክልት ሲያፈሩ በአንድ መንገድ ብቻ አያፈሩም በራሳቸው የሚያፈሩ አሉ፡፡ በጎናቸው የሚያፈሩ አሉ፤ በሥራቸው የሚያፈሩ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ምሳሌነት ያላቸው አስተማሪዎች ናቸው በራሳቸው የሚያፈሩት በራሳቸው ጥረው ግረው የሚኖሩ ሰዎች አምሳል ናቸው፡፡ በጎናቸው የሚያፈሩት ሚስት አግብተው፣ ልጅ ወልደው፣ በሐብታቸው ነግደው፣ በንብረታቸው ተጠቅመው የሚኖሩ ሰዎች አምሳል ናቸው፡፡
በሥራቸው የሚያፈሩት ሎሌዎቻቸውን ሠራተኞቻቸውን አዝዘው ልከው የሚኖሩ ሰዎች አምሳል ናቸው ይህ ሰሙ ነው ወርቁ ግን “አንዱ መቶ አንዱ ስልሣ አንዱ ሠላሳ ፍሬ ሰጠ” ማቴ.13፥8-10፡፡
በራሳቸው የሚያፈሩት የባለመቶ ክብር አምሳል ናቸው፡፡ በጎናቸው የሚያፈሩት የባለ ሥልሳ ክብር በሥራቸው የሚያፈሩት የባለ ሠላሳ ክብር አምሳል ናቸው፡፡
ከነዚህም አዝርዕት፣ ዕፅዋት፣ አትክልት ወገን በራሳቸው በጎናቸው በጫፋቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ወፍ ጠርጥሮት፣ ጠላት ለቅሞት የሚቀሩ አሉ፡፡ በሥራቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ከወፍ ከጠላት ሰውረው የሚያስቀሩ አሉ እነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
በራሳቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ወፍ ጠርጥሮት፣ ጠላት ለቅሞት የሚቀሩ በዚህ ዓለም ብዙ ትሩፋት፣ ብዙ ምግባር ሠርተው ይዩልን፣ ይሰሙልን፣ ይወቁልን ብለው በከንቱ ውዳሴ ተጎድተው በወዲያኛው ዓለም ሳይጠቀሙ የሚቀሩ ሰዎች አምሳል ናቸው፡፡
በሥራቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ከወፍ ከጠላት ሰውረው የሚያስቀሩ በዚህ ዓለም ሲኖሩ ብዙ ትሩፋት ምግባር ሰርተው አብልተው አላበላንም፣ አጠጥተው አላጠጣንም፣ አልብሰው አላለበስንም እያሉ ክብራቸውን ሸሽገው በወዲያኛው ዓለም የሚጠቀሙት አምሳል ናቸው፡፡
ዳግመኛም ከአንድ መሬት በቅለው የሚበሉ የማይበሉ፣ የሚጣፍጡ የማይጣፍጡ፣ ሬትና መርዝ፣ ወይንና ትርንጎ ይገኛሉ፡፡ ሬትና መርዝ የኀጥአን፣ ወይንና ትረንጎ የጻድቃን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ከአንድ መሬት በቅለው በመጣፈጥና በመምረር እንዲለዩ ጻድቃንና ኀጥአንም ከአንድ ከአዳም ከአራቱ ባሕርያት ተፈጥረው በምግባርና በሃይማኖት፣ በክህደትና በኀጢአት፣ በክፋትና በበጎነት ተለይተው ሲኖሩ ጻድቃን ወደ ጎተራው መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ፡፡ ኀጥአን ግን አይገቡም፡፡ ወደ ገሃነመ እሳት ይወርዳሉ እንጂ፡፡ “ፍሬያቸው ሐሞት ነው፡፡ ዘለዓለም መራራ ነው” እንዲል ዘዳ.32፥33፡፡
እነዚህ አዝርዕት፣ አትክልት፣ ዕፅዋት በየዘራቸው ይበቅላሉ እንጂ ያለ ዘራቸው አይበቅሉም፡፡ ፍሬም አይሰጡም፡፡ እንደዚሁም ጻድቃንና ኀጥአንም ያለ ዘራቸው ያለ ቤታቸው አይበቅሉም፡፡
“ወእምፍሬሆሙ ተአምርዎሙ እስመ ዕፅ ሠናይ ፍሬ ሰናየ ይፈሪ ወዕኩይሰ ዕፅ ፍሬ እኩየ ይፈሪ” ማቴ.7፥16-18
“ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያደርጋል”
ከአዝርዕት ከአትክልት ክረምት ለምልመው በጋ የሚደርቁ ክረምት ደርቀው በበጋ የሚለመልሙ አሉ፡፡ በክረምት ለምልመው በበጋ የሚደርቁት በዚህ ዓለም ሳሉ በልተው፣ ጠጥተው፣ ለብሰው፣ ሞግሰው በዚያኛው ዓለም የማይጠቀሙት ናቸው፡፡ እንደነዌ ያሉ ሉቃ.16፥25
ክረምት ደርቀው በጋ የሚለመለሙት በዚህ ዓለም ሲኖሩ ተርበው ታርዘው ጎስቁለው በወዲያኛው ዓለም የሚጠቀሙ ሰዎች አምሳል ናቸው፡፡ እንደ አልዓዛር እንደ ኢዮብ ያሉ ናቸው፡፡ ኢዮ.2፥1፣ ሉቃ.16፥19 ስለዚህ እኛም የሰው ልጆች መራራ ሳይሆን ጣፋጭ፣ ጠላት የሚለቅመው ሳይሆን፣ ከጠላት የሚሰውረውን ፍሬ፣ ክረምት ለምለሞ በጋ የሚደርውን ሳይሆን ክረምት ደርቀው በጋ የሚለመልሙትን መሆን አለብን፡፡
እግዚአብሔር በቸርነቱ በምሕረቱ ይርዳን፡፡
ይቆየን