“እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጣ” (ዮሐ.፫፥፩)
በቃሉ እሱባለው
መጋቢት ፳፮፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
የዓለምን ኃጢአት አስወግዶ፣ ኃጢአተኞችን በፍቅሩ መረብ አጥምዶ፣ በቃሉ ትምህርት ልቡናቸውን ማርኮ፣ በተአምራቱ ኅሊናቸውን ገዝቶ የፈጠራቸውን ሰዎች ወደ ሕይወት መንገድ ሊጠራ የመጣው መሲሕ በአይሁድ ቤት እንደ ባላጋራ ይታይ ነበር። ከዚያም አልፎ የአይሁድ አለቆች የሥልጣናቸውን በትር ተጠቅመው፣ ቀጥቅጠው፣ ከእግራቸው በታች አድርገው ሊገዙት ይሹ ነበር። ተግሣፁን እና የተአምራቱን ኃይል በአዩ ጊዜም በቅንዓት ተነሳሥተው ሊወግሩት ምክንያት ይፈልጉ ነበር። የባሕርይ አምላክነቱን ገንዘቡ እንደሆነ ሲነግራቸው፣ ራሱንም የእግዚአብሔር ልጅ እያለ ሲጠራ ሲሰሙ የቅን ተቆርቋሪ መሳይ ጠባያቸው እስከ መግደል ድረስ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል።
የኦሪትን ሕግ በቃላቸው መናገር፣ ትእዛዟንም በአንደበታቸው ማሳመር፣ በአደባባይም እየተቀቡ መውጣት፣ ለሙሴ ሕግ እና ለነቢያት ትንቢት ተቆርቋሪ መምሰልና ራሳቸውን እንደ ጠቢብ ከፍ ማድረግ የአይሁድ ጠባይ ነው። የፍዳውን ዘመን ማብቂያ ሊያደርግ የብሥራት ዘመን መጀመሪያ ሆኖ ሰውን ከወደቀበት ሊያነሣ የመጣውን የእግዚአብሔርን ልጅ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንዲጠላው ከእርሱ ጋርም አብሮ መታየትን፣ አብሮ መብላትንም ከኃጢአተኞች ጋር እንደመቆጠር አድርገው እስከማየት ድረስ አድርሷቸውም ነበር።
አንዳንዶቹ የልባቸውን በር ከመክፈት በጥላቻ ዘግተው፣ አንዳንዶቹ በትዕቢት ልባቸውን አጠንክረው የመዳን ዕድላቸውን የገፉ ነበሩ። አንዳንዶቹ የምኵራብ አለቆችን እና መምህራንን ፈርተው፣ ሌሎቹ ደግሞ የክብራቸው ሐሳብ አስጨንቋቸው የጌታችን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት እያደነቁ ግን በርቀት ሆነው ምቹ ጊዜ ይጠብቁ የነበረ ነበሩ። ከእነዚህ ወገን የአይሁድ አለቃ የሚሆን የኦሪትም መምህር የሆነ “ኒቆዲሞስ “የሚባል ፈሪሳዊ ነበር። (ዮሐ.፫፥፩)
ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ፣ የኦሪትና የነቢያትን ትምህርት ያወቀ፣ በሥልጣንም ከአይሁድ ሸንጎ አባል የነበረ፣ በሀብትም ቢሆን ትልቅ ሀብት ካላቸው ወገን የሚመደብ ሰው ነው፡፡ (Commentary on Gospel of Saint John by Father Tadros Yacoub Malaty page 169)። በኢየሱስ ትምህርት ልቡ አምኖ፣ እንደ ሐዋርያትም ከእግሩ ሥር ተቀምጦ፣ ልቡ እና አእምሮው ሊጠይቅ የተመኘውን ጠይቆ ነፍሱ የምታርፍበትን ጊዜ እየጠበቀ ምቹ ጊዜ እየፈለገ የነበረ ሰው ነው። ይህ ጉዳይ በወንጌሉ ክፍል ላይ በድንቅ አነጋግሩ እንዲታወቅ ሆኖ ተቀምጧል። “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው” እንዲል:: (ዮሐ.፫፥፪)
ኒቆዲሞስ ከአይሁድ ማኅበር ተለይቶ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ። በመምህርነቱ እንደ ፈሪሳዊነቱ ሳይታበይ በትሕትና ያልገባውን ሊረዳ (ረ ጠብቆ ይነበብ)፣ እንደ ባላ ሥልጣንነቱ በክብሩ ሳይመጻደቅ ይልቁንም ሁሉን ረስቶ የጌታችን ኢየሱስን ከእግዚአብሔር መላክ፣ የሚያደርገውንም በማድነቅ ልቡናውን አቅንቶ በሌሊት ከወገኖቹ ተለይቶ ከብርሃን ጌታችን ዘንድ ሊማር ወድዶ እንደ ተማሪ ሆኖ ተገኘ። መምህርነቱም ሆነ በዘመኑ የነበረው ልምድ ወደ አዲሱ የእግዚአብሔር መንግሥት ሊያደርሰው አልተቻለውም። ይልቁንም በኢየሱስ በኩል አዲስ ማንነትን ፍለጋ በሌሊት መጣ እንጂ።
ያቺ በጨለማ ያደረጋት የእውነት ፍለጋ ወደ ብርሃን መራችው፤ በአዲስ ልደትም ዳግም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እንዲሆን ረዳችው። ለመዳን ሁሉም የተጠራ ነበር፤ ነገር ግን ከአይሁድ ምኩራብ፣ ከመምህሮቻቸውም፣ ከፈሪሳውያንም መጠራቱን የመረመረ ለመጠራቱም ተገቢውን ምላሽ የሰጠ ከአንድ እጅ ጣቶች ያነሰ ያህል ቁጥር ነበራቸው። (Commentary on Gospel of Saint John by Tadros Yacoub Malaty. page 169)
በቤተ ክርስቲያናችን ትርጓሜ ወንጌል እንዲሁም በሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናት በዚሁ የወንጌል ክፍል ላይ የተቀመጠውን ኃይለ ቃል በተብራራበት ክፍል ላይ ኒቆዲሞስ ለምን ከቀን ይልቅ ሌሊትን መረጠ የሚለውን ሲተነትን ጠቃሚ ነገሮች ተካተውበት እናገኛለን።
፩.በቀን ጌታችን ኢየሱስ ሕዝቡን ሰብስቦ ሲያስተምር ይውላል። በዚህ ያልረካው ኒቆዲሞስ ሌሊት ብቻውን በጽሙና ሊያገኘው፣ በእርጋታም ሊጠይቀው ፈልጎ ከቀን ይልቅ በሌሊት መጣ። ሌሊቱን ሙሉ ከእርሱ ጋር ሊያድር ፈልጎ ከቀን ይልቅ ሌሊትን መረጠ።
፪. ሌሊትን የመረጠበት ምክንያት በጥበብ ነበር። ቀኑን ሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ሕዝቡን ሲያገለግል ይውል ነበርና። ኒቆዲሞስም ሕዝቡን አሰናብቶ እስኪጨርስ ይጠብቀውና በሌሊት ወደ እርሱ መጥቶ የድኅነት መንገድ ሊጠይቀው ይፈልግ ስለነበረ ነው። በማስተዋል ሆኖ ከልቡ ይማር ዘንድ ወድዷልና።
፫. ሌላው በቀን መሄዱን አይተው ለካህናት እንዳይናገሩ ፈርቶ ነው። ይህም አይሁድ በክርስቶስ ላይ ቅናታቸው በርትቶ በእርሱም ላይ እንዳይነሳሡ ስለፈራ ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ ራሱ ኒቆዲሞስ ለራሱም ፈርቶ ነው። ይህን አስመልክቶ በክርስቶስ ላይ ተቃውሞ ሲያነሡ ጠበቃ ሆኖ ሲከራከርለት የመለሱትን ልብ ይሏል። (ዮሐ.፯፥፵፰-፶፪) በዚህ ምክንያት በመፍራት ሌሊት መሄድን መርጧል።
፬. ውዳሴ ከንቱ ሽቶ “በአይሁድ ፊት መምህር መባል ይቀርብኛል” ብሎ አይሁድ እንዳያዩት፣ እንዳይሳለቁበትም ፈርቶ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጣ።
፭. ሌሊት ጨለማ ነው፤ ብርሃን የለም፤ ይህም የኃጢአት ምሳሌ ነው። ኒቆዲሞስም “ኃጢአት አለብኝ” ሲል ንስሓ ያገኝ ዘንድ በጨለማ ወደ ብርሃን ጌታችን ኢየሱስ መጣ።
፮. ጨለማ የብሉይ ኪዳን የቀደመው ዘመን ምሳሌ ነው። “ኦሪት በወንጌል ተተክታለችና መምህረ ኦሪት የምሆን እኔ መምህረ ወንጌል ከምትሆን ከብርሃን አባት እማር ዘንድ መጣሁ” ሲል ነው። ኦሪትን ዐውቆ ወንጌልን ባይዙ ለድኅነት አያበቃም። ወንጌልን በትምህርት፣ በሕይወትም ከብሉይ ጋር አስማምቶ የያዙት እንደሆን ከድኅነት ያደርሳል፤ ሰምና ወርቁን አስማምቶ ቢተረጒሙት የሕይወት ትምህርት ያስገኛል። ለዚህ ምሳሌ ይሆን ዘንድ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጣ። (ምንጭ ትርጓሜ ወንጌል ዘቅዱስ ዮሐንስ ምዕራፍ ፫፣ Commentary on Gospel of Saint John by Tadros Yacoub Malaty. Page 170)
መጽሐፍ ጠቅሰን፣ ኃይለ ቃል አብራርተን የዚህን መምህር ትሕትና እንጽፈው ዘንድ አይቻለንም። ያገኘውን ክብርም ተናግረን ልንጨርሰው አንደፍርም። በሌሊት መጥቶ በቀን አበራ። ላይረሳም ከመቅደሱ አናቅጽ ዐምድ ሆኖ ተተክሎ ዘወትር እናስበዋለን። ከአርማትያሱ ሰው ከዮሴፍ ጋርም መጥቶ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ከመስቀል አውርዶ ለመቅበር ታደለ። “ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ” እንዲል፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፴፱)
በፍርሃት መጥቶ ፍቅሩን በአደባባይ ገለጠ። ማንም በሌለበት ሰዓት ተምሮ፣ ማንም በሌለበት ሰዓት ተገኝቶ፣ መቃብሩን በሽቱ አክብሮ፣ ገንዞ ቀበረው። ምን ዓይነት መታደል ነው! የአይሁድን ሸንጎ ሰብሮ አይሁድ ፈርደው በሐሰት የሰቀሉትን መምህር አውርዶ ገንዞ መቅበር እንዴት ያለ ድፍረት ነው?! ያኔ ሲመጣ የአይሁድ ሐሳብ ያስጨንቀው ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የፍቅሩ ብዛት ያስጨንቀዋል። በሌሊት ሳይመጣ በድንግዝግዝ ይጓዝ ነበር፤ ዛሬ በብርሃን መንገድ ይረማመዳል። የፈሪሳውያንን የዓይን ጦር ሰብሮ በድፍረት ለመቆም በቅቷል።
አባቶቻችን በቅኔ ጣት ከጣት እንዲበልጥ መምህርም ከመምህር ይበልጣልና ኒቆዲሞስ በጨለማ ኅሊናውን በሰቂል አድርጎ ይማር ዘንድ ረቢ ሆይ (መምህር ሆይ) እያለ በተማሪነት በትሕትና መጣ፤ ለመምህሩም ሰገደ። “ረቢ ሰገደ በመንፈቀ ሌሊት ለረቢ አኮኑ አጽባዕት እምነ አጽባዕት የዓቢ፤ጣትም ከጣት እንዲበልጥ በመንፈቀ ሌሊት መምህሩ (ኒቆዲሞስ) ለመምህሩ (ለኢየሱስ) ሰገደ” ያሉት ይህንን ነው።
ቅዱስ ያሬድም በጾመ ድጓው “ኒቆዲሞስ” ብሎ በሰየመው ክፍል መምህረ አይሁድ ኒቆዲሞስ ክርስቶስን ፍለጋ ሊቅ ሆይ እያለ እንደሄደ እንዲህ ብሎ አስቀምጦልናል። “ኒቆዲሞስ ስሙ ዘሖረ ኀቤሁ ቀዲሙ ሌሊተ ወይቤሎ በጽሚት ረቢ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ ወበምጽአትከ አብራህከ ለነ ወሰላመ ጸጎከነ አንሥእ ኃይለከ ወነዓ አድኅነነ፤ አስቀድሞ በሌሊት ወደርሱ ይሔድ የነበረ ስሙ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው በቀስታ “ሊቅ ሆይ ከአብ ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን፤ ኒቆዲሞስም ወደ እርሱ ሔደ፤ ረቢ ኢየሱስንም ሊቅ (አዋቂ) እንደሆንክ ለማስተማር ከአብ ዘንድም እንደመጣህ እኛ እናውቃለን፤ በምጽአትህም አበራህልን፤ ሰላምንም ሰጠኸን፤ ኃይልህን አንሳ፤ መጥተህም አድነን አለው” ይለናል። (ጾመ ድጓ) ከእርሱ የሚበልጥ ሁሉን የሚያውቅ መምህር፣ ከሣቴ ምሥጢር ነውና ኒቆዲሞስ ረቢ ሆይ እያለ ሊማር እግሮቹን ወደ ኢየሱስ አነሳ።”
ጠቢቡ ሰሎሞን “ሌሊት በምንጣፌ ላይ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግሁት” እንዳለ የመዳኗን ተስፋ ያደረገች የኒቆዲሞስ ነፍስ የሚያድናትን መድኃኒት ፍለጋ ሌሊት በጨለማ ጸብአ አጋንቱን፣ ግርማ ሌሊቱን ሳትፈራ ፍለጋዋን ገሰገሰች። (መኃ.፫፥፩) አባቶቻችንም ዛሬ ጉባኤ ቤት ተክለው፣ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ትምህርትን በሌሊት የሚያስተምሩት ይህን ሊቅ አብነት አድርገው ነው፤ በሌሊት ኅሊና ይሰበሰባል፤ በቀላሉም የመጻሕፍትን ምሥጢር ለመረዳት ሐሳብ መሰብሰብ ያስፈልጋል።
ሊቅ ሆይ ምናለ ከነፍስ ፍቅር የተነሣ የመፈለግን ትምህርት ምሥጢር ብታስተምረን! እኛ ራሳችንን መምህር አድርገን የሕይወትን መምህር ረስተናል። ትንሽ የቃረምናት ንባብ በሕይወታችን ሥር ሰዳ የዕውቀት ትዕቢት ሆናብናለች። አንተን ዓይተን፣ የትሕትናህን ከፍታ ተረድተን፣ ከእግረ መምህሮራን ዘንድ “ነፍሴ የወደደቻችሁ መምህራን ሆይ ወዴት አላችሁ?” እያለች በጥሪ የምትፈልግ ኅሊና ይኖረን ዘንድ ከወዴት ባገኘን! እኛ ራሳችንን መምህር አድርገን በመሾም ራሳችንን ከመልካም የሕይወት መምህር አርቀናል።
ክርስቲያኖች ሆይ ኑ፥ የትሕትና ቃላትን ከኒቆዲሞስ እንማር! እርሱ ብዙ እያለው ብዙ የሌለው መምህር ሆኖ ሲማር ዓይተነዋልና። ብሉያትን ዐዋቂ፣ በአይሁድ ሸንጎ ዘንድ የተከበረ፣ በገንዘብም ከፍ ያለ ባዕለ ጸጋ የነበረው ሰው ራሱን እንኳን ማስጠጊያ ወደ ሌለው መምህር በጨለማ ሲሄድ አይደንቅምን? በቀን በብርሃን መሄዱ ባላስደነቀን ነበር። ሰዎችም ባሉበት ጊዜ በሆነ ሰዓት ቢሆን አንክሮ ባልሰጠነው ነበር። ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ የሆነ ነገር አደረገ። እርሱ በጨለማ የሕይወት መብራት ፈልጎ ሄደ። “ተምሬአለሁ” ብሎ ለመታበይ ያይደለ ነፍሱን አርነት ያወጣ ዘንድ፣ አዲሱን ሰው ይለብሰው፣ ከጨለማው መንገድ ወደ ብርሃን አገር ያወጣው ዘንድ እንጂ። ተወዳጆች ሆይ! የመከራው ቀን ደራሾች ሆነን እንገኝ ዘንድ ኑ እንውጣ! ከሳሾቻችንን በደጅ ጥለናቸው የሰላምን መንገድ ለመፈለግ እንውጣ!
ብዙ የፈሪሳዊነት ጠባያቶቻችን ከመዳን መንገድ እንቅፋት ሆነውብናል። “መምህር ሆይ ከሰማያት የወረድክ የሕይወት እንጀራ ስትሆን አንተን ተመግበን፣ የአባትነትህን ፍቅር እያየን በሕይወት እንኖር ዘንድ አትተወን” እያልን በተማጽኖ ቃል እንለምነው ዘንድ ኑ! በስውር ወደ ጌታ እንቅረብ። “በአደባባይ የቃላት ድርድር እያመጣን እንሰብክሃለን” ከምንለው በሥውር ሄደን በመከራ ቀናቶች የምንቆምበትን ምሥጢር ለመቀበል “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን” እያልን አንተ የሕይወትን ምልክቶች ስጠን እንበለው። (ዮሐ.፫፥፪)
የሁላችንም አባት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! በቤትህ ልናድር እንሻለንና አንተ በልባችን ያለውን የፈሪሳዊነት ምልክት ሳታይ በአባትነትህ ፍቅር ብቻ ተቀበለን፤ አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን!