‹‹…እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ…›› (፩ኛ ቆሮ.፲፫፥፲፫)
ተስፋ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ጥር ፲፭፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲሁም በዓለ ጥምቀቱን እንዴት አክብራችሁ አሰለፋችሁ? እነዚህ በዓላት ከጌታችን ዐበይት በዓላት መካከል የደስታ በዓላችን ናቸው፡፡ ዘመናዊ ትምህርትስ እንዴት ነው? እየበረታችሁ እንደሆነ ተስፋችን ነው!

የግማሽ ዓመት ትምህርት ተጠናቆ ፈተና እየተፈተናችሁ ያላችሁ እንዲሁም ደግሞ ለፈተና ዝግጁ የሆናችሁ ተማሪዎቸ አላችሁ፤ ትምህርት ከተጀመረ ጊዜ አንሥቶ መምህራን ሲያስተምሩ በደንብ የተከታተለ፣ የተሰጠውን የቤት ሥራ የሠራ እንዲሁም ያልገባውን እየጠየቀ የተረዳ፣ ያጠና ተማሪ ፈተናውን በቀላል ይሠራዋል! እናንተም እንደዚህ እንደምትሆኑ ተስፋችን እሙን (የታመነ) ነው፡፡ በርቱና ተማሩ! ፈተናውንም በተረጋጋ ሁኔታ ሆናችሁ ሥሩ፡፡ መልካም! ለዛሬ “ተስፋ” በሚል ርእስ እንማራለን፡፡

ተስፋ ማለት ከጨለማው ባሻገር ብርሃን፣ ከአቀበቱ ጀርባ ለምለም ሜዳ፣ ከኀዘን ባሻገር ደስታ፣ ከወጀብና ከአውሎ ነፋስ በኋላ ጸጥታ መረጋጋት፣ ከትንሣኤ በኋላ ሕይወት እንዳለ ማመን ነው፡፡ ለክርስቲያኖች ተስፋ ማለት እንደማይጨበጥ ደመና (ጉም) አልያም ርቆ እንደተሰቀለ ዳቦ ሳይሆን፣ የሚፈጸም እውነት የሆነ ነው፡፡ ተስፋ ምኞትና ናፍቆት ብቻ ሳይሆን አለኝታና መተማመን የሚገኝበት ነው።
ተስፋ የእምነታችን ምንጭ ነው፤ የተስፋ ምንጭ ወይም መገኛው የሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹…የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ…›› በማለት ገልጾልናል፡፡ (ሮሜ ፲፭፥፲፫)

ተስፋ ሕያው ነው፤ ግኡዝ አይደለም፤ ወይም ቁስ አይደለም፤ ‹‹…በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፣ ትዕግሥትም ፈተናን፣ ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍረንም፡፡›› (ሮሜ ፭፥፲-፪)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሰው ምግብ ሳይመገብ፣ ውኃም ሳይጠጣ ለተወሰነ ጊዜ መቆየት ይችላል! ልጆች! ሰው ተስፋ ከቆረጠ ግን መኖር አይችልም! በዚህ ምድር ላይ እየተቸገርን፣ በፈተና ወጀብ ታጅበንም፣ እየተሰደድንም እየኖርን ያለነው ነገን ከዛሬ የተሻለ ሆኖ እናገኘዋለን በሚል ተስፋ ነው፤ ተስፋ ባይኖረን ከትናንት አልፈን ዛሬን ባላየናት፣ ዛሬ ላይ ቆመን ነገን ባልናፈቅናት፡፡

ተማሪ ጠዋት ተነሥቶ መጽሐፉን ደብተሩን፣ ምሳ ዕቃውን ይዞ ትምህርት ቤት ሄዶ የሚማረው ከመምህራን ዕውቀትን ቀስሞ ያላወቀውን በማወቅ በርትቶ በማጥናት የሚሰጠውን ፈተና በማለፍ ከክፍል ክፍል ተሸጋግሮ ከዚያም ዩንቨርሲቲ በመግባት ተመርቆ ራሱን፣ ቤተሰቡን ከዚያም አገሩን ለማገልገል ተስፋ አድርጎ ነው፡፡

ወላጆቻችን ለትምህርታችን የሚያስፈልገውን አሟልተው፣ ጥያቄያችንን መልሰው፣ የምንለብሰውን ልብስ የምንመገበውን ምግብ፣ የምንማርበት የትምህርት መሣሪያ፣ አሟልተው ትምህርት ቤት የሚልኩን እኛ ልጆቻቸው ጎበዝ ተማሪ በመሆን ተምረን ትልቅ ሰው እንድንሆን ተስፋ አድርገው ነው፡፡ (ጳጳስ፣ ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ካፒቴን፣ የአገር መሪ፣…) እንደምንሆንና ሕዝብን እንደምናገለግል፣ አገራችንን የምንወድ እንድንሆን ተስፋ አድርገው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም በ፩ኛ ቆሮ. ፱፥፲ ላይ ‹‹..የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ..›› ይላል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በትምህርታችን አልረዳ ያለንን፣ ትምህርት ተስፋ ቆርጠን ትምህርቱን መጥላት ወይም ይህ ትምህርት አይገባኝም ማለት ሳይሆን ደጋግመን መሞከር፣ ማጥናት፣ መጠየቅ፣ መሥራት እንዲረዳን ማድረግ እንጂ አልወደውም፤ አይገባኝም ብለን ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡ እችለዋለው፣ እለምደዋለው፣ ብከታተለው፣ ትኩረት ብሰጠው አውቀዋለሁ፤ ይረዳኛል ብለን ተስፋ ማድረግ አለብን፡፡

ተስፋ ለክርስቲያኖች ትልቅ ትርጉም አለው፤ ከምድራዊ የእንግድነት ኑሮ ባሻገር፣ ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት እግዚአብሔር ለወዳጆቹ የአዘጋጃትን መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን የሚል ታላቅ፣ የሚሆን፣ የሚፈጸም፣ የሚገኝ ተስፋን በልባችን ሰሌዳ ጽፈናል በሕሊናችን ጓዳ አሳድረናል፡፡ ታዲያ ይህን የመሰለውን ታላቁን ዘለዓለማዊውን ሕይወት በደስታ፣ በተድላ፣ በክብር እንደምንወርስ እያመንን በምድር ላይ ጊዜያዊ በሆነ በእንግድነት ኑሮአችን ጊዜ ባመጣው አልያም ሰዎች ባደረጉት ለእኛ ፈተና በሆነብን ነገር ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም!
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹…በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም…›› ይላል፡፡ (፪ኛ ቆሮ.፬፥፰) አባቶቻችን ‹‹ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥም›› በማለት የሚናገሩት ለዚህም ነው ፡፡ ‹‹…ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፣ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራ ሥር ቢጎድል፣ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፣ በጎችም ከበረት ቢጠፉ፣ ላሞችም በጋጥ ውስጥ ባይገኙ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለው›› እንዲል፡፡ ( ዕን.፫፥፲፯)

ተስፋ አለማድረግ ወይም ተስፋ መቁረጥ ጭንቀትን ያመጣል፡፡ ሕመም ይሆናል፤ ሞትንም ሊያስከትል ይችላል፡፡ በሽተኛ እንደሚድን ተስፋ ካላደረገ የሚታየው መከራ ነው፤ ሕመሙ አይጸናበት፤ ምን ሰማዕታትስ የክብር አክሊልን ተስፋ ካላደረጉ መከራውን እንዴት መታገስ ይችላሉ፤ የምንፈልገውን ለማግኘት በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ አለብን፡፡ ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት ‹‹የሁሉ ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህ›› ብሏል፡፡ (መዝ.፻፵፬፥፲፭)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሕይወታችን ተስፋ ስናደርግ ከእኛ የሚጠበቀውንም እያደረግን መሆን አለበት፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ መልካም ሥራን መሥራት አለብን፤ በዘመናዊ ትምህርታችን የምንፈልገውን ለመሆን ተስፋ ስናደርግ በርትተን መማር፣ማጥናት፣ ያልተረዳንን መጠየቅ አለብን፤ ያኔ ተስፋ ያደረግነውን ነገር እናገኛለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እኛ ተስፋችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ለሚገጥመን ፈተና ሁሉ መውጪያውን የሚያዘጋጅልን እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱን ተስፋ ባደረግን ቁጥር ነገሮች ይከናወኑልናል፡፡ ንጉሥ ዳዊት ‹‹አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም፤ በከንቱ የሚገበዙ ያፍራሉ›› ይላል፡፡ (መዝ.፳፬፥፫)

ልጆች! ስለ ተስፋ ከብዙ በጣም በጥቂቱ ተምረናል፤ ያወቅነውን ነገር በተግባር እንተርጉም፡፡ ቸር ይግጠመን!

ይቆየን!