‹‹እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው›› (ዕብ. ፲፩፥፩)
መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ
እምነት የግሪኩን ፔስቲስ የሚለውን የሚተካ የግእዝ ቃል ነው፡፡ እውነትን መቀበልና ልባችንን ለእውነት መስጠትን ያመለክታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው›› ሲል ስለ እምነት አስተምሯል፤ እምነት ተስፋ የሚሰጥና ነውና፡፡ (ዕብ. ፲፩፥፩)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ›› እንዲሁም ‹‹ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል›› በማለት አስተምሯል፡፡ ስለዚህ ጸሎታችን በእምነት ሊሆን ይገባል፤ በእምነት ስንጸልይ እግዚአብሔር አምላክ ይሰማናል:: (ማቴ. ፳፩፥፳፪፤ማቴ. ፲፯፥፳)
ሰው ተስፋ ካለው የማይታየውን እንዳየ ሆኖ ይረዳል፡፡ እምነት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት፣ እርሱን ደስ የምናሰኝበት ጥበብ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እምነት እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኝበት ጥበብ መሆኑን ሲያስረዳ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይ ቻልም ብሏል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፮)
የእምነት ፍሬ በእምነት እንድንኖር ይረዳናል:: ‹‹በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፡፡›› እምነት የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልናጠፉ የምትችልበት ጋሻ ነው::(ኤፌ.፮፥፲፮)
ከላይ እንዳየነው እምነት ከመንፈስ ቅዱስ የሚመነጭ የመንፈስ ፍሬ ነው:: ይህም ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘው ፍሬ ነው:: እንዲሁም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም:: ‹‹ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና›› አንደተባለው እምነት መልካም ምስክርነትን ያመጣል:: (ዕብ. ፲፩፥፪)
በእምነት ጥንካሬአቸው የተመሰከረላቸው ቅዱሳን በእግዚአብሔር በመታመናቸው በሚያቃጥል የእሳት ነበልባል ውስጥ በመጣል፣ ወደ አንበሳ ጉድጓድ በመወርወር፣ በሰይፍ በመተርተር እምነታቸውን ገልጠዋል፡፡ ንጉሡ ናቡከደነጾር ለጣዖት አንሰግድም ብለው እምነታቸውን የገለጡትን ሠለስቱ ደቂቅን ርዝማኔው አስራ ስድስት ክንድ ከሚደርስ የእሳት ነበልባል ውስጥ በሰንሰለት አስሮ ቢወርወራቸውም ከሰውነታቸው አንዳች ሳይቃጠል በመዳናቸው፤ ‹‹በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ ሲል እግዚአበሔርን አክብሯል፡፡›› (ዳን. ፫፥፳፭)
በዘመነ ሐዲስ በሰው ፍቅር ተስቦ ወደዚህ ዓለም የመጣው ቸሩ አምላክ ለአገልግሎት ከመረጣቸው ሰዎች አንዳንዶቹ ምንም ዓይነት መሠረታዊ የሃይማኖት ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን አላዋቂዎችን የመረጠው በዘመኑ በዕውቀታቸው የሚታበዩ ሰዎችን ዕውቀት ከንቱ ለማድረግ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታችን የዓለምን ጥበብ ከንቱ ለማድረግ እነዚያን ሰዎች እንደመረጠ ሲያስረዳ፤ ‹‹እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔር የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም መረጠ›› ብሏል፡፡ (፩ኛቆሮ.፩፥፳፮-፳፱)
እግዚአብሔር ለእምነት አገልግሎት ሰዎችን ሲመርጥ ሞኞች ጠቢባን ይሆናሉ፤ አላዋቂዎች ሀብተ እውቀት ያገኛሉ፤ ደካማዎች ብርቱዎች ይሆናሉ፡፡ አላዋቂ የነበሩት ተከታዮቹ ጠቢባን፤ ደካማ የነበሩት ብርቱዎች እስከሚሆኑ ድረስ ለቀጣይ የእምነት ሕይወታቸው ብርታት እንዲሆናቸው የተለያዩ ጥያቄዎችን ለጌታችን ያቀርቡ ነበር፡፡
ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይከተሉ ከነበሩ ሰዎች ካቀረቡለት ጥያቄ አንዱ ‹‹አለማመኔን እርዳው›› የሚል ነው፡፡ ጌታችን የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው የተከተሉትን በሕይወት ሰጪ ትምህርቱ በነፍስ የታመሙትን፣ ተስፋ የቆረጡትን፣ ባዶነት የሚሰማቸውን እና መንፈሳዊ ዝለት የገጠማቸውን ሲፈውስ፤ በተአምራቱ ደግሞ በሕማመ ሥጋ የታመሙትን ፈውሷል፡፡ የጌታችንን ሕይወት ሰጪ ትምህርት ፈልገው የተከተሉ አብዛኛዎች በተከፈለ ልብ ነበር፡፡ መድኃኒታችን የእነርሱን ልብ ማረጋጋት እና ያዘኑትን ማጽናናት ባሕርዩ በመሆኑ ድክመታቸውን ሳይሸሸጉ የሚቀርቡትን ፈጣን ምላሽ ይሰጣል፡፡ (ማር.፱፥፳፬)
የጌታችን ደቀ መዛሙርት ልጁን እንዲፈውሱለት የወሰደው ሰው፤ ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ የእምነት ማነስ የተነሣ መፍትሔ ቢያጣም ከጌታችን ዘንድ መጥቶ የእምነቱ ጉድለት በጌታችን እንዲስተካክልለት የልጁን በሽታ ከዘረዘረ በኋላ፤ ‹‹ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳን›› የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ቢቻልህ የሚለውን የጥርጣሬ ቃል ‹‹ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሰው ሁሉ ይቻላል›› በሚል ቃል ሲያርመው የተቸገረው ሰው አለማመኑ በእርሱ እንዲጠገንለት በታላቅ ድምፅ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው ብሎታል፡፡ ይህ ሰው ‹‹አምናለሁ አለማመኔን እርዳው›› በማለት በእምነት ሕይወት ውስጥ ያለበትን ችግር ሳይሸሸግ መናገሩን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡፡፡ (ማር.፱፥፳፪-፳፬)
እናምናለን እያልን የማናምን፣ ንስሓ እየገባን የማንፀፀት፣ እየቆረብን ለሥጋ ወደሙ ክብር የማንሰጥ፣ እየቀደስን ያልተቀደስን ብዙዎች ነን፡፡ እኛም ‹‹እናምናለን፤ ነገር ግን እምነታችን በአንተ ይታገዝ፤ እርዳን›› ማለት አለብን፡፡ ሰዎች ክርስቶስ መወለዱን፣ መጠመቁን፣ ከሙታን መነሣቱን (ትንሣኤውን መግለጡን) ሊያምኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እና ተስፋ ግን ይጠራጠራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር እያመንን በእምነት ሕይወት ውስጥ አንኖርም፤ ለዚህ ማለዘቢያ ግን እምነታችን፣ አለማወቃችንና ድካማችን በጌታችን እንዲደገፍ መማጸን ነው፡፡
በማቴዎስ ወንጌል ቅዱሳን ሐዋርያት የታመመውን ልጅ ለመፈወስ አቅም ያጡበትን ምክንያት ለመረዳት፤ ‹‹እኛ ጋኔኑን ልናወጣው ያልቻልነው ስለምንድነው?›› ሲሉ ጌታችንን ጠይቀውታል፡፡ ይህ ጥያቄ የእኛም ጥያቄ ነው፡፡ እኔ የተሰጠኝን ሓላፊነት ያልተወጣሁት ስለምንድነው? ያልቆረብኩት ስለምንድነው? ከልቤ ውስጥ የሚጉላላውን ቂም ያላወጣሁት ስለምንድነው? የበደልኩትን ያልካስኩት ስለምንድነው? የሚፈታተነኝን የሰይጣን ፈተና ማለፍ ያልቻልኩት ስለምንድነው? መንፈሳዊ ሕይወቴ ማደግ ያልቻለው፣ ራሴን ማወቅ መረዳት ያልቻልኩት ስለምንድነው? ብለን እንድንጠይቅ የቅዱሳን ሐዋርያት ጥያቄ ይጋብዘናል፡፡ (ማቴ.፲፯፥፲፱)
ቅዱሳን ሐዋርያት እግዚአብሔር ከጎናቸው እያለ የእምነት ጉድለት ስለታየባቸው ማድረግ የሚገባቸውን ለመፈጸም አልቻሉም፤ ነገር ግን አእምሮአቸው ውስጥ የነበረውን ጥያቄ መጠየቃቸው መልካም ነበር፡፡ በእምነት ሊያደርጉት የሚቻላቸውን ነገር ማድረግ የተሣናቸው ስለእምነታቸው ጉድለት መሆኑን ጌታችን አስረግጦ እንዲህ በማለት ነግሯቸዋል፡፡ ‹‹እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ሾላ ተነቅለህ በሌላ ቦታ ተተከል ብትሉት ይታዘዝላችኋል›› ብሏቸዋል፡፡ (ሉቃ.፲፯፥፮)
ስለእምነት፣ በእምነት ሕይወት ስለመኖር፣ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ የቅዱሳንን ገድልና ትሩፋት በመግለጥ ብዙ ነገር ተምረናል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛዎቻችን ቃሉ በጭንጫ ላይ የተዘራ ዘር ሆኖብናል፤ ጌታችን በጭንጫ ላይ ዘር ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ደረቀ ያለውን ሲፈታ ‹‹በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል ነው፡፡ ነገር ግን፥ ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ላይ ሥር የለውም፤ በቃሉም ምክንያት መከራ፥ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይክዳል›› ብሏል፡፡ (ማቴ. ፲፫፥፳)
በእምነት መንፈሳዊ ሕይወታቸው አልጸና ብሎአቸው ይቸገሩ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን ያቀረቡት ጥያቄ መሠረታዊ ምላሽ አግኝቶ፤ የሰውነታቸው ለልብሳቸው፤ የልብሳቸው ለጥላቸው አልፎ ሕሙም ከመፈወስ ሙት እስከ ማስነሣት ደርሰዋል፡፡ ይኸውም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ በዚህም አገልግሎታቸው እንደ ሠመረላቸው መረዳት ይቻላል፡፡
እኛም በሃይማኖት ስንኖር ራሳችንን እንድንመረምር እንደተነገረን፤ በቅድሚያ መንፈሳዊ ሕይወቴ ያላደገው ለምንድነው? ብለን ያለንን የእምነት ጥንካሬና ድክመት መመዘን አለብን፡፡ በማስከተል እንደ ታመመው ልጅ አባት ‹‹አለማመኔን እርዳው›› የሚል ጥያቄ አቅርበን፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል ፍጹም እምነት ሲኖረን ጌታችን እንዳለው ተራራ የሆነብን ትዕቢት፣ ከፊታችን የተደቀነው ክፋት፣ ምቀኝነት ከሕይወታችን ይነቀላል፡፡ እየወላወለ የሚያስቸግረን ልቡናችን ክፍት እንዲሆን ወይም እንዲሰበሰብልን መማጸን አለብን፡፡ በእምነት ያልጸናው ሰው ለእግዚአብሔር አምላኩ ‹‹አለማመኔን እርዳው›› ሲል ያቀረበው ጥያቄ የሁላችንንም ሕይወት የሚወክል ነው፡፡ ዛሬ እምነቱ ሥርዓቱ፣ ትውፊቱ እያለን በፍጹም ልብ ያለማመን ችግር አለብን፡፡ ልጁ የታመመበት ሰው አለማመኔን እርዳው ሲል በአንተ ታምኜ የምኖርበትን ኃይል ለአንተ የሚገዛ ልብ እና ሕይወት ስጠኝ ማለቱ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ከአባቶቻችን የተቀበልነው እምነት የፈተና ጎርፍ እና ሳይሸረሽረው ነፋስ ሳያዘመው በዐለት ላይ ተመሥርቶ እንዲጸናልን ዘወትር መጸለይ አለብን፡፡ በመሆኑም ልባሞች ከመብራታቸው ጋር ዘይት ይዘው ሙሽራውን እንደጠበቁ፤ ባለማመን የጠወለገውን ሕይወታችንን በቃሉ ዝናምነት በማለምለም አለማመናችን በእግዚአብሔር ቃል መረዳት አለበት፡፡
ማንኛውም የሕይወት ውጣ ውረድ ቢያጋጥመን በእምነት ከጸናን የማናልፈው ነገር የለም፡፡ የማንዘለው የችግር እና የመከራ ግንብ፣ የማንሻገረው ባሕር እና መሰናክል አይኖርም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹በእምነት ከእግዚአብሔር ጋር ከኖርን የሚያስፈራን አንዳች ነገር አለመኖሩን ሲያስረዳ በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሔድ፤ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል›› ብሏል፡፡ (መዝ. ፳፪፥፬)
ቅዱስ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ብዙ ችግርና ፈተና ያጋጠመው ሰው ቢሆንም በእምነት በመጽናቱ ፍጻሜው ሠምሮ ‹‹ልበ አምላክ›› ለመባል በቅቷል፡፡ በመሆኑም ዛሬ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የተደቀነብንን ፈተና የምናልፈው በእምነት ነው፤ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኘው በእምነት ነው፤ የሚመጣውን ነገር በተስፋ የሚያስረዳንም እምነት በመሆኑ በእምነት ልንጸና ይገባል፡፡
አለማመናችን በእግዚአብሔር ሲረዳ ወይም በእምነት ስንጸና ረድኤተ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ኃያላን የሆኑትን አራዊት ሳይቀር ገራም ያደርግልናል፡፡ በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ዳንኤል ከአናብስት ጉድጓድ ሲወረወር የተራቡት አንበሶች ለነቢዩ ገራም የሆኑት የእምነት ሰው በመሆኑ ነው፡፡ በቅድስናቸው የተመሰከረላቸው ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አናምርት (ነብሮች) እና አናብስት (አንበሶች) የእግራቸውን ትቢያ እየላሱ የታዘዙላቸው በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን በእምነት ነው፡፡ ዛሬ ዲያብሎስ እንደተራበ አንበሳ በፊታችን በሚያደባበት ዘመን የእምነትን ጥሩር መልበስ ያስፈልጋል፡፡ ለቀደሙት አባቶች ሥጋት የነበሩት ነገሮች ቀሊልና ታዛዥ እንደሆኑ ለእኛም ይሆኑልናል፡፡ ብዙ ጊዜ ፈቃደ ሥጋችን ፈቃደ ነፍሳችንን ሲጫነው የምንወደውን ሳይሆን የማንወደውን እናደርጋለን፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም›› ሲል እንደተናገረው፤ የሥጋችን ፈቃድ ብዙ ጊዜ ነፍሴ ብይ፣ ጠጪ ደስ ይበልሽ ወደ ማለት ቢያዘነብልም ቅሉ ወደ ፈቃደ ነፍስም መለስ ብሎ እኔ ማነኝ? ጉዞዬስ ወዴት ነው? ተስፋዬስ ማን ነው? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ፈቃደ ሥጋው እያየለ ሲያስቸግረው፤ በእንባው መኝታውን እያራሰ በእግዚአብሔር ፊት ቢያለቅስ፤ የኃጢአት አሽክላ እየተቆረጠለት በእምነቱ የሚደሰት ሰው ሆኗል፡፡(ሮሜ. ፯፥፲፱)
በእምነት ጉድለት በዲያብሎስ ሽንገላ የእምነት አቅም አጥተን ከቤተክርስቲያን ከቅድስና ሕይወት የራቅን ወገኖች፤ እግዚአብሔር እንዲረዳን ሳንሰለች ጥያቄ ማቅረብ አለብን፡፡ በእምነት ጉድለት ምክንያት ያጣነውን ድኅነት እና ጽናት እናገኛለን፡፡
የሰው ልጅ ወደ እምነት ፍጹምነት ውስጥ ሲገባ ሁሉ ነገር በእግዚአብሔር እጅ እንደሆነ ይረዳል፤ ከጭንቀትም ያርፋል፡፡ በአቅማችንና በፈቃዳችን የተቸገረን መርዳት፣ አምላክን ከልብ መውደድ፣ ማመስገን የእምነት ሰው መገለጫ ናቸው፡፡
በእምነት የጸኑ አባቶችን በአንበሳ ጉድጓድ፣ በእሳት ውስጥ፣ በወህኒ ቤት በተጣሉ ጊዜ የተረዳና የእምነታቸውን ዋጋ የከፈለ እግዚአብሔር ዛሬም አለ፡፡ በመሆኑም መንፈሳዊ ሕይወታችንን በእምነት አሳድገን መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ያብቃን፤ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር