‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› (ማር. ፭፥፴፮)
ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
የደኅነታችን መሠረት እምነት በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ ችግርና መከራ በበዛብን ጊዜ ጸንተን እንድናለፍ ይረዳናል፡፡ የሰው ዘር በኃጢአቱ የተነሣ በምድር እንዲኖር ከተፈረደበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ችግርና መከራ ተይዞ ሲሠቃይ ፈጣሪውን ያስባል፤ ይማጸናልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፈውስን ሲያገኝ በሌላ ጊዜ ግን ወደማይመለስበት ዓለም በሞት ይለያል፤ ሆኖም ድኅነተ ሥጋንም ሆነ ድኅነተ ነፍስን ከአምላካችን እናገኝ ዘንድ እምነት ያስፈልጋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እምነት ሲገልጽ ‹‹እምነት ተስፋ ለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ እና የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው›› ብሏል፡፡ በእምነት የማናየውን ነገር እንድናይ አድርገን መቀበል መታመን ወይም መታዘዝ ጭምር መሆኑንም አስተምሮናል። (ዕብ. ፲፩፥፩-፻)
በማርቆስ ወንጌል እንደተጻፈውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰዎች ከምኵራቡ ሹም ቤት መጥተው፥ ‹‹ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህርን አታድክመው›› ሲሉት ጌታችን ለምኵራብ ሹም፥ ‹‹እመን እንጂ አትፍራ፤›› አለው፡፡ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስም በቀር የሚከተለው ማንም እንዳይኖር ከከለከለ በኋላ ወደ ምኩራብም ሹም ቤት ገባ፤ በዚያን ጊዜም ሲታወኩና፥ ሲያለቅሱ፥ እጅጉም ሲጮኹ አገኛቸው፡፡ ገብቶም፥ ‹‹ለምን ትጮኸላችሁ? ለምንስ ታለቅሳላችሁ? ልጅቱስ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም›› አላቸው፡፡ በጣምም ሳቁበት፤ እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናት፥ ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞአቸው ብላቴናይቱ ወደ አለችበት ገባ፡፡ የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ፥ ‹‹ጣሊታ ቁሚ፤ አንቺ ብላቴና ተነሺ›› አላት፡፡ ያን ጊዜም ያቺ ብላቴና ተነሥታ ወዲያና ወዲህ አለች፤ ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ እነርሱም እጅግ ተደነቁ፡፡ ይህን ድንቅ ተአምር ያደረገ አምላክ ከበሽታና ክፉ ደዌ ማዳን እንደሚችል ማመን የእኛ ፈንታ ነው፡፡ (ማር.፭፥፴፭-፵፪)
የክርስትና ኑሮ የተጋድሎ ሕይወት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ለፊሊጲዎስ ሰዎች ‹‹ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም፡፡ እንግዲህ እኔን እንዳያችሁኝ፥ የእኔንም ነገር እንደ ሰማችሁ ምንጊዜም ተጋደሉ›› በማለት አስረድቷቸዋል፡፡ (ፊሊ. ፩፥፳፱-፴)
ለዚህ ምሳሌ እንዲሆነን የጻድቁ አባታችን የኢዮብ ታሪክ እናውሳ፤ ‹‹አውስጢድ በሚባል ሀገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ ያም ሰው ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ከክፋ ሥራም የራቀ ነበር::›› (ኢዮብ ፩፥፩)
ለዚህም ጻድቅ ሰው በዘመኑ እንደርሱ ያለ ዕውነተኛ ደግ ሰው እንዳልነበረ እግዚአብሔር መሰከረለት:: ሰይጣንም ቀንቶበት በገንዘቡና በልጆቹ ላይ ያሠለጥነው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጠየቀ:: የጻድቅ ኢዮብን ትዕግሥት እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ሰይጣንን በኢዮብ ላይ አሰለጠነው፡፡
ከዚህ በኋላም በአንዲት ቀን የኢዮብ ገንዘብ ሁሉ ጠፋ፤ ሥጋው በደዌ ሥጋ ከራሱ ጠጉሩ እስከ እግሩ ጥፍሩ ድረስ ተመታ:: በዚህም በአስጨናቂ ደዌ ውስጥ ኖረ፤ ደግሞ እግዚአብሔርን አመሰገነ:: አንዲት ቃልን እንኳ በፈጠረው እግዚአብሔር ላይ አላጕረመረመም፤ ነገር ግን ‹‹ረገማ ለዕለት ዘተወልደ ባቲ፤ ……የተወለደበትን ቀን ረገመ::›› (ኢዮብ ፫፥፩)
የነበሩት ከብቶቹ፣ ገንዘቡ፣ ሀብትና ንብረቱ ሁሉ በጠፋ ጊዜ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ፈቀደ ሆነ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን አለ:: (ኢዮብ ፩፥፳፩)
ያ የከበረና የተመሰገነ ኢዮብ በዚህ መከራ በነበረበት ዘመናት በተራራ ላይ ተጥሎ ሳለ የወዳጆቹና የሚስቱ ዘለፋ በዝቶበት ነበር:: ሚስቱም ልታበረታው፣ ልትረዳው፣ ልታፅናናው ሲገባ ከወዳጆቹ ብሳ እንዲህ ብላ መከረችው:- ‹‹እስከ መቼ ድረስ በሞኝነት ትኖራለህ፤ እንግዲህስ ስደበውና ሙት፤ ዳግመኛ እግዚአብሔርን ደጅ እጠናዋለሁ፤ መከራውንም እታገሣለሁ፤ የቀድሞ ኑሮዬን ተስፋ አድርጋለሁ ትላለህ›› አለችው::
ዳግመኛም አለችው:: ‹‹እንዲህስ እንዳትል ከዚህ ዓለም እንሆ ስም አጠራርህ ጠፋ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼ ሞቱ:: እኔም ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ላይረቡኝ ላይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምኩ:: አንተም በመግል ተውጠህ፣ በትል ተከበህ ትኖራለህ፤ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ፤ እኔም እየዞርኩ፣ እቀላውጣለሁ፤ ከአንዱ ሀገር ወዳንዱ ሀገር ካንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ:: ከድካሜ በእኔ ላይ ከመጣው ከችግሬም ዐርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኽው ሙት›› አለችው::
ኢዮብም ሚስቱን እየተመለከተ በትዕግሥት ሰማት:: እንዲህም አላት፦ ‹‹ይህን ሁሉ እግዚአብሔር ለመልካም አደረገ፤ ሥርዓት እንዳልተሠራባቸው አሕዛብ ሴቶች እንዳንዲቱ ተናገርሽ፤ ከዚህ ቀድሞ በጎውን ነገር ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበልን፤ ከዚህ በኋላ መከራውን እንታገሥም ዘንድ›› አላት::
ኢዮብ በዚህ ባገኘው መከራ ሀብቱ÷ ንብረቱ÷ ልጆቹ÷ መላ አካሉ በበሽታ ሲመታ፤ ጤናው ሁሉ ሲታወክ አምላኩን አመሰገነ እንጂ አንድም የስንፍና ቃል በአምላኩ ላይ አልተናገረም::
‹‹ወተፈተነ ወተነጥፈ ከመ ወርቅ በእሳት፤ ወርቅ በእሳት እንዲፈተን ፈጽሞ ተፈተነ›› ብሎም መሰከረ:: ያለ መከራ ዋጋ ያለፈተና ጸጋ አይገኝምና፤ እግዚአብሔርም በደመና ውስጥ ኢዮብን ተናገረው:: ከዚያ በኋላ ከደዌ ሁሉ ፈወሰው፤ ሀብቱንም ሁሉ ባርኮ ከቀድሞ እጥፍ አደረገለት የተባረኩ ልጆችም ሌሎች ወንዶችና ሴቶችም ሰጠው::
ጻድቁ ኢዮብ ከደዌ ከተፈወሰ በኋላ ለመቶ ሰባ ዘመን በምድር ኖረ፤ በጠቅላላውም ሁለት መት አርባ ስምንት ዓመት በበጎ ሽምግልና ኖሮ እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም ዐረፈ፤ መንግሥተ ሰማያትንም ወረሰ፡፡ (ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት)
የጻድቁ ኢዮብ ታሪክ በእምነት መጽናት፣ በተስፋ መኖርና መታገሥን ያስተምረናል፡፡ የትኛውንም ዓይነት መከራም ሆነ ችግር ለማለፍ እና ጠላትን ለማሸነፍ የሚረዳን ኃይል እምነት መሆኑንም ከእርሱ የተጋድሎ ሕይወት እንረዳለን፡፡ እምነት ሲኖር ተስፋ እናገኛለን፤ ተስፋም ወደ አምላካችን ያቀርበናል፡፡
ሆኖም ሰው ከአምላኩ ርቆ በኃጢአት ባርነት በሚኖረበት በዚህ ወቅት ፍቅር፣ ሰላምንና ጤና አጥቷል፤ በአስከፊ ሁኔታም መከራ እየተቀበለ ይገኛል። በማናውቀውም ሆነ ባወቅነው ኃጢአት እና በእምነታችን መጉደል ምክንያት የተለያዩ መከራዎችን መቋቋም በማንችልበት መልኩ ግፍ እየደረሰብን ነው፤ የሰዎች ሕይወት እንደ ቅጠል እየረገፈ መሆኑን ስናስብና ስናይ አስከፊ መሆኑን አንክድም፡፡ በተለይም ለኮሮና በሽታ ወረረሽኝ መድኃኒት አለመገኘት ፍራቻ ሊፈጥርብን ይችላል፤ የወደፊቱን ለማሰብም ያዳግተናል፤ የእኛም ዕለተ ሞት መቼ እንደሆነ ባለማወቃችን በስጋት እንድንኖር ያደርገናል፡፡ ነገር ግን የነገን የሚያውቅ እግዚአብሔር በመሆኑ በእርሱ ሥራ ከመግባት ይልቅ የዛሬን በጽድቅ በመኖር ለዘለዓለማዊ ሕይወታችን መጨነቅ ይሻላል፤ እግዚአብሔር አምላክ ከፈቀደው ነገር አንዲት የሚቀየር የለምና፡፡ በመሆኑም በእምነትና በጽናት፤ ያለ ፍራቻ ልንኖር ይገባል፡፡
ነገን በማሰብ ምድራዊ ችግርና መከራን ተቋቁመን ተስፋ የምናደርገውን ርስት እንድንወርስ እግዚአብሔር ይርዳን፤ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዐሥራት ሀገሯን ኢትዮጵያን ትጠብቅልን፤ አሜን።
ምንጭ፤ መጽሐፈ ኢዮብ እና ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት ፪