ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን፤ ስደተኛው ኢየሱስ የስደተኞች ተስፋቸው ነህ (ሰቆቃወ ድንግል)
በመጋቤ ሐዲስ በርሄ ተስፋ መስቀል
መጽሐፍም ታሪክም እንደሚነግረን በዓለም ብዙ ዓይነት ስደት አለ። ሁሉም ስደቶች ግን የአዳምንና የሔዋንን ስደት ተከትለው የመጡ ናቸው። ቀደምት ወላጆቻችን ሕገ እግዚአብሔርን ባፈረሱ ጊዜ ከገነት ተሰደው ምድረ ፋይድ ወርደዋል (ዘፍ. ፫፥፩፥፲፩)፡፡ ከዚህ በኋላ ከቦታ ወደ ቦታ መሰደድና መንከራተት የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ ሆኗል። በዘመነ ብሉይ የነበሩት ስደተኞችና በምርኮ የተያዙ ሁሉ ስደታቸውን በሚጠት የሚፈፅም፣ ኀዘናቸውን በደስታ የሚለውጥ አንድ መሢሕ እንደሚመጣ በተስፋ ይጠባበቁ ነበር (መዝ. ፹፬፥፬፣ ሰቆቃወ ኤርምያስ. ፭፥፳፩)፡፡
ሊቁ አባ ሕርያቆስ “አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት፤ አዳም አባታችን ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነሽ” በማለት መናገሩ የአዳምና የሔዋን ሚጠት ማለት ወደ ቀደመው ክብር – ወደ ገነት መመለስ ድንግል ማርያም በወለደችው በክርስቶስ እንደሚሆንና ድንግል ማርያምም ምክንያተ ድኅነት መሆኗን ለመግለጥ ነው።
በዘመነ ሐዲስም ቢሆን ጽድቅን ፍለጋ የሚሰደዱ እንዳሉ ሁሉ እንጀራን ፍለጋ ሀገር ጥለው ከወገን ርቀው የሚሰደዱ መከራና ግፍ የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች አሉ። የእነዚህም ተስፋቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለዚህም ነው ስድተኞቹ በየሔዱበት ዓለም እየተሰባሰቡ የአምልኮ ሥርዓታቸውን የሚያካሔዱት። ይህን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተገነዘቡት አባ ጽጌ ድንግል “ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን ፥ ኢየሱስ ግፉእ ተስፋሆሙ ለግፉአን” በማለት የተናገሩት።
ወደ ዋናው አሳባችን እንመለስና የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል ኮከብ እየመራቸው “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው” እያሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ (ማቴ. ፪፥፪)፡፡ ሰብአ ሰገል /የጥበብ ሰዎች ለምን ክርስቶስን የአይሁድ ንጉሥ ብለው ጠሩት? የሚል ይኖራል፦ ስም ላዕላዊ፣ ስም ማዕከላዊ፣ ስም ታሕታዊ የሚባል አለ። ስለዚህ
- በስም ላዕላዊ – “አይቴ ሃሎ አምላክ /ፈጣሪ ዘተወልደ” ቢሏቸው ምን ሞኞች ናቸው ሰማይና ምድር የማይችሉትን እንዴት ተወለደ ይላሉ ባሏቸው ነበር።
- በስም ታህታዊ – “አይቴ ሃሎ ሕፃን ዘተወልደ” ቢሏቸው ምን ሞኞች ናቸው በእስራኤል የተወለደው ስንት ሕፃን አለ ስንቱን እናውቃለን? ባሏቸው ነበርና፣
- ስም ማእከላዊን ወስደው – “አይቴ ሃሎ ንጉሠ እስራኤል ዘተወልደ፤ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” – ቢሏቸው ሄሮድስ ምድራዊ ንጉሥ መስሎት ንጉሥማ ንጉሥን ሳይሽር ይነግሣልን ብሎ ደንግጧል (ማቴ. ፪፥፫)፡፡
ወንጌላዊው ማቴዎስ እንደ ጻፈልን ሰብአ ሰገል ጌታን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ባገኙት ጊዜ ወድቀው ሰገዱለት ፥ እጅ መንሻውንም አቀረቡለት (ማቴ. ፪፥፪-፲፩) ዓይነቱም ወርቅ ፥ ዕጣን፣ ከርቤ ነው። የቀረበው እጅ መንሻ እንዲህ መሆኑም ያጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን ምሥጢር አለው።
- ወርቅ አመጡለት፦ ወርቅ ስንገብርላቸው የነበሩ ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፍያን ናቸው ፥ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርክ ፥ በኋላም የማታልፍ ዘለዓለማዊ አምላክ ነህ ሲሉ ወርቅ አመጡለት። በተጨማሪም ወርቅ ጽሩይ እንደሆነ አንተም ጽሩየ ባሕርይ ነህ ለማለት ወርቅ አመጡለት።
- ዕጣን አመጡለት፦ ይህን ስናጥናቸው የነበሩት ጣዖታት ጥንቱም ፍጡራን ፥ ኋላም ኃላፍያን ናቸው ፥ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርክ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ ዕጣን አመጡለት። በሌላ አገላለጽ ዕጣን ምዑዝ ነው አንተም ምዑዘ ባሕርይ ነህ ሲሉ ነው።
- ከርቤ አመጡለት፦ ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርክ በኋላም የማታልፍ ብትሆን ለሰው ስትል ፈቅደህ በተዋሐድከው ሥጋ የፈቃድ ሞትን መቀበል አለብህ ሲሉ ከርቤ አመጡለት።
በተጨማሪም ከርቤ የተሰበረውን እንዲጠግን ፥ የተለያየውን አንድ እንዲያደርግ አንተም ከማኅበረ መላእክት የተለየውን አዳምን ጽንዐ ነፍስን ሰጥተህ ወደ ቀደመ ቦታው ትመልሰዋለህ ሲሉ ከርቤ አመጡለት – በማለት ሊቃውንት ተርጉመዋል (ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ. ፪፥፲፩)፡፡ አዳምን ወደ ቦታው ለመመለስ ከተደረጉ የማዳን ሥራዎች መካከል የጌታ ስደት አንዱ ነው።
ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ መጽሐፈ ምሥጢር በተባለው ድርሰታቸው፦ “በዚያ በጽርሐ አርያም የሚደነቅ ከማይታይ አብ የመወለድ ምስጋና አለው ፥ በዚህም በቤተ ልሔም ከድንግል መወለድ ምስጋና አለው። በዚያ ከሰማያውያን ካህናት በወርቅ ማዕጠንት የዕጣኑን መዐዛ ይቀበላል ፥ በዚህም ወርቅንና ከርቤን ዕጣንንም ከሰብአ ሰገል ተቀበለ” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል (ሉቃ. ፪÷፩-፲፯፣ ራእይ. ፰÷፰-፬፣ ማቴ. ፪÷፲፩፣ መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ. ፷፰-፸)፡፡
የጥበብ ሰዎች የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ባሉት ጊዜ ሄሮድስ በጉዳዩ ሰግቶ ሰብአ ሰገልን “ሒዱ ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ” ብሏቸው እንደ ነበር እናስታውሳለን (ማቴ. ፪፥፰)፡፡ ምንም እንኳ ኢየሱስ ክርስቶስ ነገሥታት የሚሰግዱለት የባሕርይ ንጉሥ መሆኑ እውነት ቢሆንም ነገር ግን ሄሮድስ መጥቼ እንድሰግድለት ማለቱ በተንኮል ነበር። ስለዚህም የጥበብ ሰዎች ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸው ሔዱ (ማቴ. ፪፥፲፪)፡፡
ከዚያ በኋላ ነው መልአኩ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጾ – “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሸሽ ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” በማለት የተናገረውና ጻድቁ ዮሴፍ ሕፃኑንና እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ በሌሊት ወደ ግብፅ የተሰደደው (ማቴ. ፪፥፲፫) ሄሮድስም ሰብአ ሰገል እንደ ተሳለቁበት ባወቀ ጊዜ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን ያገኘ መስሎት እጅግ ብዙ ሕፃናትን ፈጅቷል (ማቴ. ፪፥፲፮)፡፡ ጌታችን ግን ጊዜው ሳይደርስ ደሙን ሊያፈስ ፥ ሊሞትም አይገባምና ከሄሮድስ ፊት ያመልጥ ዘንድ ከእናቱ ጋር ተሰዷል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሰደደ፤ ለምንስ ስደቱን ወደ ግብፅ አደረገው?
ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ምክንያት እንዳለው ሁሉ የተሰደደበት እና ስደቱን ወደ ምድረ ግብፅ ያደረገበት ምክንያትም አለው። ይኸውም፡-
- ትንቢተ ነቢያትን ለመፈጸም ነው፣
የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ አስቀድሞ በልብ የመከረውን ፥ ኋላም በነቢያት ያናገረውን ለመፈፀም እንጂ በአጋጣሚ የተከናወኑ አይደሉም። ወደ ግብፅ እንደሚሰደድም ትንቢት ተነግሮለት ነበር። “ከጌታ ዘንድ በነቢይ፦ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሔደ ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ” (ማቴ. ፪፥፲፬-፲፭) እንዲል፡፡ ነቢያት ትንቢታቸውን ሲናገሩ የጌታችንን መሰደድ ብቻ ሳይሆን ከማን ጋር ፥ ወዴት እንደሚሰደድ፣ በስደቱ ጊዜ ምን ምን እንደሚሠራ በግልፅ አስቀምጠውታል። የክርስትናን አስተምህሮ እርግጠኛ የሚያደርገውም ይህ ነው።
ከነቢያቱ መካከል ነቢዩ ኢሳይያስ መንፈሰ እግዚአብሔር መርቶት ቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ ወደ ምድረ ግብፅ እንደምትሰደድ “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብፅ ይመጣል” (ኢሳ. ፲፱፥፩) በማለት ተናግሯል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ድንግል ማርያምን “አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ ምንዳቤ ወአጸባ ለዓይን እምቀራንባ፤ በኀዘንና በችግር ጊዜ ሰውን ለመርዳት ከዓይን ጥቅሻ ይልቅ ድንግል ማርያም ፈጣን ናት” እያለች የምታመሰግነው ለዚህ ነው። ይህን የኢሳይያስን ትንቢት ሁለት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እንደሚከተለው አመስጥረው ተርጉመውታል፡፡
- ቅዱስ ያሬድ
መዓዛ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ “… ኢሳይያስ ነቢይ ፥ ልዑለ ቃል እም ነቢያት ከልሐ ወይቤ እግዚአብሔር ጸባኦት ይወርድ ብሔረ ግብፅ፤ ከነቢያት ይልቅ ድምፁ ከፍ ያለው ነቢዩ ኢሳይያስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ግብፅ ምድር ይወርዳል ብሎ አሰምቶ ተናገረ። – ደመና ቀሊል ዘይቤ ኢሳይያስ ይእቲኬ ማርያም ድንግል እንተ ጾረቶ በከርሣ ለወልደ እግዚአብሔር፤ ኢሳይያስ ፈጣን ደመና ብሎ የተናገረላትም የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁን በማሕፀኗ የተሸከመችው ድንግል ማርያም ናት” (መዋሥዕት) በማለት አብራርቶታል፡፡
- አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ
ዐምደ ሃይማኖት የተሰኘው ቅዱስ አባ ጊዮርጊስም “ሄሮድስ ኃሠሠ ዘኢይትረክብ ወእግዚእ ተግሕሠ ውስተ ምድረ ግብፅ ፥ ተጽዒኖ ዲበ ደመና ቀሊል ፥ በከመ ይቤ ኢሳይያስ – ናሁ እግዚአብሔር ይወርድ ውስተ ምድረ ግብፅ ተጽዒኖ ዲበ ደመና ቀሊል ፥ ደመናሰ ቀሊል አንቲ ክመ ኦ ቅድስት ድንግል፤ ሄሮድስ የማያገኘውን ፈለገ ጌታም በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብፅ ምድር ሔደ ፥ ነቢዩ ኢሳይያስ እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብፅ ምድር ይወርዳል ብሎ እንደ ተናገረ፥ ቅድስት ድንግል ሆይ ፈጣን ደመና መቼም መች ቢሆን አንቺ ነሸ። … እግዚአብሔር ተአንገደ ውስተ ምድረ ግብፅ ተሐዚሎ በዘባን፤ … እግዚአብሔር በጀርባሽ ታዝሎ በግብፅ ምድር እንግዳ ሆነ” (አርጋኖን ዘሰኑይ) እንዲል፡፡
የተከበራችሁ አንባብያን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔርን የምታገለግልባቸው፥ ምእመናንን የምታስተምርባቸው ድርሳናት እንዳሏት እሙን ነው። እነዚህ ሁሉ መሠረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑንም ከሁለቱም ሊቃውንት ልናስተውል ይገባል። ከዚህ የተነሣ የማኅሌቱ፣ የቅዳሴውና የሰዓታቱ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ነው ብለን መናገር እንችላለን። በሌላ አገላለጽ ድርሳናት ገድላት መደበኛ ሥራቸው ረቂቅ ምሥጢር የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ማመሥጠር፥ ማብራራት ፥ መተርጎም መሆኑን ከሊቃውንቱ ድርሰት ተምረናል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ትምህርቷ ምሉእ ፥ እምነቷ ርቱዕ የሆነውም በዚህ ምክንያት ነው።
አምልኮ ጣዖትን ለማጥፋት ነው
ጌታችን ወደ ግብፅ የተሰደደበት ምክንያት አለው ያልነው እዚህ ላይ ይገለጻል። ይኸውም በዚያ ጊዜ ግብፃውያን ክሕደት ወይም አምልኮ ጣዖት ጸንቶባቸው ነበርና ይህን ክፉ አምልኮ ጣዖት ለማጥፋት፣ ለመደምሰስ ክርስቶስ ስደቱን ወደ ግብፅ አድርጎታል። ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብፅ ይመጣል።” ካለ በኋላ ዓላማውን ሲገልጽ “የግብፅም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ” ብሏል (ኢሳ. ፲፱÷፩)፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ጌታችን ወደ ግብፅ የተሰደደበትን ምክንያት ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፡- ይፈጽም ትንቢተ የሐድስ ብሊተ፤ ይክሥት መንክራተ ፥ ዘሀሎ መልዕልተ፤ ለቢሶ ስብሐተ ፥ ብሔረ ግብጽ ቦአ ይሥዐር ጣዖተ፤ ወይንሥት ኵሎ ግልፍዋተ፤ ትንቢትን ይፈጽም ዘንድ፣ አሮጌውንም ያድስ ዘንድ፣ በላይ ያለውን ድንቅ ነገር ይገልጥ ዘንድ፣ ምስጋናን ተጎናጽፎ ጣኦታትን ሊሽር፣ ምስሎችንም ሁሉ ሊያፈርስ ወደ ግብፅ ምድር ገባ /ድጓ ዘበአተ ግብፅ/ ሌላው ኢትዮጵያዊው ሊቅም ሰቆቃወ ድንግል በተሰኘው ድርሳኑ ድንግል ማርያምን ከታቦተ ጽዮን ጋር በማነጻጸር እንዲህ ብሏል፡-
ታቦተ አምላክ እስራኤል ጽዮን ዘነገደት ምድረ ኢሎፍሊ፤ ወቀጥቀጠቶ ለዳጎን ነፍሳተ ብዙኅን ማህጎሊ፤ አመ ነገደት ቍስቋመ በኅይለ ወልደ ከሃሊ፤ ወድቁ አማልክተ ግብጽ መናብተ ሰይጣን ሐባሊ፤ ወተኅፍሩ ኵሎሙ ዘቦሙ አስጋሊ። ወደ ኢሎፍሊ ምድር ተማርካ የሄደች የእስራኤል አምላክ የቃል ኪዳኑ ታቦት ታቦተ ጽዮን፥ የብዙዎችን ነፍሳት ያጠፋ ዳጎንን ሰባበረችው። ድንግል ማርያምም ሁሉን ማድረግ በሚችል ልጇ ግብፅ ወደሚባል ሀገር በሔደች ጊዜ የሐተሰኛ ሰይጣን ዙፋኖች የሆኑ የግብፅ ጣዖታት ፈረሱ ፥ ጠንቋይ አስጠንቋይ ያላቸው ሁሉ ዐፈሩ (ሰቆቃወ ድንግል)፡፡
ከዚህ የምንረዳው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስደት ተራ ስደት ሳይሆን ሰዎችን ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮቱ ማለትም ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ለማምጣት የተደረገ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ስለዚህ ጌታ በስደቱ ሰዎችን ከክህደት አድኗል ማለት ነው።
- ስደትን ለሰማዕታት – ለቅዱሳን ሁሉ ባርኮ ለመስጠት
መልካም እረኛ በበጎቹ ፊት ይሔዳል። “የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሔዳል ፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤” (ዮሐ. ፲፥፬) እንዲል፡፡ መልካሙ እረኛ ክርስቶስ ሲሆን በጎች የተባሉትም ደጋጎቹ ምእመናን ናቸው። በፊታቸው ይሔዳል ሲል፡- ኢየሱስ ክርስቶስ መምህር፥ መሪ እንደ መሆኑ መጠን ምእመናንን ይመራቸዋል እንጂ በኋላ ሆኖ አይነዳቸውም። ይህ ማለት እኛ ክርስቲያኖች ልናደርጋቸው የሚገቡ ነገሮችን በሙሉ እርሱ አስቀድሞ በተግባር ፈጽሞ አሳይቶናል። ስለዚህ የክርስቲያኖች ትክክለኛው አርአያ አብነት ክርስቶስ ነው። መጠመቁን አብነት አድርገን ተጠምቀናል (ማቴ. ፫፥፲፮-፲፯)፣ መጾሙን አብነት አድርገን እንጾማለን (ማቴ. ፬፥፩-፲)፣ የምንጸልየው መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ ስለ ጸለየ ነው (ማቴ. ፳፮-፵፩)፣ ጠላታችንን ይቅር ማለት ያለብን ክርስቶስን አብነት አድርገን ነው። (ቆላ. ፫፥፲፫)፤በፊት መሔድ ማለት ለመልካም ነገር ሁሉ አብነት አርአያ መሆን ማለት ነው።
እንደዚሁ ሁሉ በመሰደዱ ምክንያት ስለ ጽድቅ ብለው ለሚሰደዱ ቅዱሳን፣ መናንያን ባሕታውያን ሁሉ አብነት ሆኗል። ጥምቀታችንን፣ ጾም ጸሎታችንን እንደ ባረከ ሁሉ፥ ስደቱንም ባረኮ ጀምሮ ሰጥቶናል። ለዚህም ነው “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው ፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።” (ማቴ. ፭፥፲) በማለት የተናገረው፡፡
ጻድቃን ፥ ሰማዕታት በአጠቃላይ ቅዱሳን ሁሉ ክርስቶስን ተስፋ አድርገው ሀብትን ንብረትን ትተው ፥ ዓለምን ንቀው ተሰደዋል። ክርስቶስ በስደቱ ጊዜ ብዙ መከራዎችን እንደ ተቀበለ ቅዱሳንም በዓላውያን ነገሥታት፣ ክፋት በጸናባቸው ሰዎች እጅግ ብዙ መከራን ተቀብለው ተሰደዋል። በዚህም ዋጋቸውን አግኝተዋል። ስለዚህ እራሱ ባርኮ ባይሰጠን ኖሮ ስደትን ማንም አይችለውም ነበር።
ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው ክርስቶስ አብነት ያልሆነበት የጽድቅ፣ የበረከት ሥራ እንደሌለ ነው። ይህ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቲያኖች ሊያደርጓቸው የሚገቡ መልካም ነገሮችን ሁሉ አስቀድሞ አድርጓቸዋል። በመሆኑም ክርስቲያኖች ሁሉ እረኛችንን ክርስቶስን አውቀን፣ ድምፁንም ለይተን በመረዳት በመልካም ነገር ሁሉ እረኛችንን ክርስቶስን እንመስል ዘንድ ይገባናል ማለት ነው።
- ወደ ቀደመው ርስታችን ሊመልሰን ተሰዷል
ከላይ እንደ ተገለጠው የመጀመሪያው ስደተኛ አዳም ነው። በመቀጠልም ልጆቹ ሁሉ ስደተኞች ሆነዋል። ስለዚህ ዳግማይ አዳም ክርስቶስ የተሰደደው አዳምንና ልጆቹን ፍለጋ ነው (ሉቃ. ፲፭፥፩-፱)፡፡ ከዚህ በመነሣት ነው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ “…ዘሐሰሶ ለበግዕ ግዱፍ ወሶበ ረከቦ ፆሮ ዲበ መትከፍቱ፤ የጠፋው በግ አዳምን የፈለገው ፥ ባገኘውም ጊዜ በትክሻው የተሸከመው እውነተኛ እረኛ” /ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ/ በማለት የተናገረው። ከዚህ አኳያ የቀዳሚት ሔዋን ስደትም በዳግማዊት ሔዋን ድንግል ማርያም ስደት ተክሷል፡፡
መልአከ እግዚአብሔር ዮሴፍ ድንግል ማርያምን ይዞ እንዲሰደድ እንደ ነገረው ሁሉ ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ከሆናቸው በኋላ መልአኩ እንደገና “የሕፃኑን ነፍስ የፈልጉት ሞተዋልና ተነሣ ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሒድ” (ማቴ. ፪፥፳) በማለት ነግሮታል፡፡ ልብ በሉ ገዳዩ ሞተ ፥ ሊገደል የታሰበው ሕያው ሆነ። ዮሴፍም ሕፃኑን ክርስቶስን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር እንደ ተሰደደ ይዟቸው ወደ እስራኤል ተመልሶ ገባ (ማቴ. ፪፥፳፩) መንግሥተ ሰማያት የሚገቡት እነማን ናቸው ቢሉ ጌታን ከእናቱ ጋር የያዙት ናቸው።
ማጠቃለያ
የጌታችን ስደት ጠላታችን ዲያብሎስ ከሰዎች ልብ ወጥቶ እንዲሰደድ ያደረገ በመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሚገባ ታከብረዋለች፡፡ ለዚህም ነው ሊቃውንቱ “ጕየተ ሕፃን አጕየዮ ለዲያብሎስ፤ የሕፃኑ ስደት ዲያብሎስን እንዲሸሽ አድርጎታል” በማለት የሚገልጡት።የተከበራችሁ የልዑል እግዚአብሔር ወዳጆች! ድንግል ማርያም ልጇን ወዳጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ፣ ዮሴፍንና ሰሎሜን አስከትላ ከእስራኤል እስከ ግብፅ፥ ከዚያም እስከ ኢትዮጵያ በመሰደድ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር እጅግ ብዙ መከራን ተቀብላለች (ራእ. ፲፪፥፩-፮፤ ፲፬-፲፰)፡፡
አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “እወ አማን እምውሉደ ሰብእ አልቦ ፥ ምንዳቤ ወግፍእ ዘከማኪ በውስተ ዓለም ዘረከቦ፤ ድንግል ሆይ! አዎን በእውነት ከሰው ልጆች መካከል በዚህ ዓለም እንደ አንቺ ችግርና መከራ የደረሰበት የለም” በማለት እንደመሰከሩት መከራዋም ልዩና እጅግ ብዙ ነው። በዚህም ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ የማይተካ ሚና ያላት መሆኑን መረዳት ይገባል። በተጨማሪም እናቶች ለልጆቻቸው ምን ያህል መሥዋዕትነት መክፈል እንዳለባቸው ያስተማረች የሕይወት መምህር መሆኗን መገንዘብ ብልህነት ነው። የጌታ ስደት ስደታችንን፣ ሚጠቱ ሚጠታችንን የሚያመለክት ነው። በሌላ አገላለጥ የድንግል ማርያም ስደት የሔዋንን ስደት፣ ሚጠቷም እናታችን ሔዋን በዳግማዊት ሔዋን በድንግል ማርያም መመለሷን ያሳያል። የዮሴፍና የሰሎሜ ስደት የደቂቀ አዳም ሁሉ ስደትን የሚያሳይ ሲሆን ሚጠታቸውም የአዳም ዘር ሁሉ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ወደ ቀደመው ክብራችን፣ ወደ ገነት መመለሳችንን ያመለክታል። እንዲህም ስለሆነ ግብፅ የሲኦል ምሳሌ ፥ ኢየሩሳሌምም የገነት ምሳሌ ናት፡፡ በዚህ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእስራኤል ወደ ግብፅ ተሰዶ እንደገና ወደ እስራኤል መመለሱ፥ ከገነት የተሰደደው አዳም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስደትና አጠቃላይ የማዳን ሥራ ወደ ጥንተ ክብሩ መመለሱን የሚያጠይቅ ነው። እግዚአብሔር ከተሰደድንበት የጽድቅ ሥራ በንስሓ ይመልሰን፥ የድንግል እናቱን በረከትና ረድኤት ያድለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ኛዓመት ቁ፪/ቅጽ ፳፮ ቁጥር ፫፻፺፭ ከጥቅምት፩-፲፭ ቀን፳፻፲ወ፩ ዓ.ም